ከ200 በላይ የዓለም ምግብ ፕሮግራም መኪኖች ወደ ትግራይ ለመጓዝ ሰመራ ላይ እየተጠባበቁ ነው ተባለ

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታን የጫኑ ተሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, WFP

የምስሉ መግለጫ,

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታን የጫኑ ተሽከርካሪዎች [ከፋይል]

በዓለም ምግብ ፕሮግራም የሚመሩ ከ200 በላይ የጭነት መኪኖች ሰመራ ሆነው ወደ ትግራይ ለማለፍ እየተጠባበቁ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ። መኪኖቹ ወደ ትግራይ የሚጓጓዝ ምግብ እና ሌሎች የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶች የጫኑ ናቸው።

ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ለመጓዝ ደህንነታቸው ሲረጋገጥ የጉዞ ፍቃድ እንደሚሰጣቸው ተጠቁሟል።

ድርጅቱ ከዚህ በተጨማሪ ከተለያዩ የረድኤት ድርጅቶች የተውጣጡ ከ30 በላይ ሠራተኞችን ወደ ትግራይ በአውሮፕላን መላኩን አስታውቋል።

ከዚህ በኋላ በሳምንት ሁለት ጊዜ ወደ ትግራይ በረራ እንደሚደረግና በዘላቂነት እርዳታ ሰጪዎች በክልሉ እንደሚንቀሳቀሱ ተገልጿል።

ሰኔ 24 ማንኛውም ወደ ትግራይ የሚደረግ የንግድ በረራ ከተቋረጠ ወዲህ የአሁኑ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በረራ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

የዓለም ምግብ ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ማይክል ደንፎርድ "የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ በረራ (UNHAS) መቀለ ሲያርፍ ሠራተኞቻችን እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሰጪ አጋሮቻችን ተደስተዋል" ብለዋል።

ድርጅቱ እርዳታውን ለ2.1 ሚሊየን የትግራይ ነዋሪዎች የማዳረስ እቅድ አለው። በትግራይ ክልል የረሃብ አደጋ እንዳንዣበበ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎችም የረድኤት ተቋሞች በተደጋጋሚ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም።

በቂ ምግብ አለመኖሩ፣ የሰብዓዊ እርዳታ መስጫ እጥረት፣ ስልክና ኢንተርኔትን የመሰሉ የመገናኛ ዘዴዎች መቋረጥ እርዳታውን ፈታኝ እንዳደረገው የዓለም ምግብ ፕሮግራም በድረ ገጹ አስታውቋል።

ጦርነቱ ከትግራይ አልፎ ወደ አፋርና ሌሎችም አካባቢዎች እየተስፋፋ መምጣቱን በመጥቀስ፤ ይህም የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ ሌሎችም ድርጅቶች እርዳታ የሚያጓጉዙበት መንገድ ሊያሳጣ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ከቀናት በፊት የዓለም ምግብ ፕሮግራም መኪኖች ወደ ትግራይ እርዳታ ሲያጓጉዙ ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው አይዘነጋም።

የዓለም ምግብ ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ማይክል ደንፎርድ "ሁሉም አካል ከተረባረበ ረሃብን መግታት ይቻላል። ሁሉም አካላት ተኩስ አቁመው ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ እንዲቻል የዓለም ምግብ ፕሮግራም ይጠይቃል" ብለዋል።

እርዳታ ለማድረስ የሚሆኑ መንገዶች በአጠቃላይ በአፋጣኝ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተኩስ አቁም እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፈው ወር በትግራይ ክልል ደቡባዊ እና ምዕራባዊ አካባቢዎች ከ730,000 በላይ ለሆኑ ሰዎች ምግብ ማድረስ መቻሉን ገልጿል።

ይህም ዛና በሚባል አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ የምግብ እርዳታ የተደረገላቸውን 40,000 ዜጎችን ያካትታል።

ድርጅቱ በቀጣይ ቀናት በደቡብ ምዕራብ አካባቢ ለ80,000 ሰዎች ምግብ የማዳረስ እቅድ እንዳለው ተናግሯል። በተጨማሪም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የተመጣጠነ ምግብ የሚያስፈልጋቸውን ቤተሰቦች ለመድረስ ወጥኗል።

አሁን ላይ ትግራይ ውስጥ በመቀለ እና በሽረ በሚገኙ የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘኖች 7,500 ሜትሪክ ቶን ምግብ እንደተከማቸ በድርጅቱ ድረ ገጽ ተጽፏል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተጨማሪ 13 የጭነት መኪናዎች ማዘጋጀቱንም አክሏል። የይለፍ ፍቃድ ሲያገኝ ተጨማሪ 30 መኪናዎችን እንደሚያሰማራም አስታውቋል።

ሰኔ ላይ በድርጅቱ አማካይነት የተሠራ የዳሰሳ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ በሐምሌ መጨረሻ 400,000 ሰዎች ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል።

ከትግራይ ሕዝብ 4 ሚሊዮን ያህሉ (ማለትም 70 በመቶው) ከፍተኛ የምግብ እጥረት ስጋት ያለባቸው ሲሆን አስቸኳይ እርዳታም ያሻቸዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በትግራይ አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረግ 176 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ገልጿል።