19 የቻይና የጦር አውሮፕላኖች የአየር ክልሌን ጥሰው ገቡ ስትል ታይዋን ከሰሰች

የቻይና ጦር ጄት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታይዋን ብዛት ያላቸው የቻይና ወታደራዊ አውሮፕላኖች እሑድ ዕለት የአየር መከላከያ ቀጠናዋ ጥሰው ገብተው እንደነበረ አስታወቀች።

የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር የቻይና ተዋጊ አውሮፕላኖች እና ኑክሌር ቦምቦችን የመጣል አቅም ያላቸው አውሮፕላኖች የአየር መከላከያ መለያ ቀጠና (አዲዝ) ወደሚባለው አካባቢ መግባታቸውን ገልጿል።

በቻይና አየር ኃይል የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ታይፔ ከአንድ ዓመት በላይ ቅሬታዋን ስታቀርብ ቆይታለች።

ቻይና ታይዋንን እንደ ተገንጣይ ግዛት ስትመለከታት ታይዋን በበኩሏ ራሷን እንደ ሉዓላዊት ግዛት ትቆጥራለች።

እሑድ የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በቻይና አየር ኃይል እንቅስቃሴ ኤች -6 የተባሉ የኑክሌር ቦምብ ጣዮችን እንዲሁም ጸረ ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ያካተቱ ናቸው።

ሚኒስቴሩ ከፕራታስ በስተሰሜን ምስራቅ ከታይዋን የባሕር ዳርቻ ይልቅ በቻይና የባሕር ጠረፍ አቅራቢያ የነበረውን የበረራ ካርታ ይፋ አድርጓል።

የቻይና አውሮፕላኖችን ለማስጠንቀቅ የሚሳይል ስርዓቶች ከመዘርጋታቸው ባለፈ የውጊያ አውሮፕላኖች መላካቸውን ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል።

ቻይና እስካሁን በይፋ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠችም።

ቤይጂንግ በታይዋን በሚሰጡት አስተያየቶች ቅር መሰኘቷን ለመግለጽ ብዙ ጊዜ እንደዚህ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ታደርጋለች።

በሰኔ ወር 18 ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ወደ አዲዝ የላከች ሲሆን ይህም እስከዛሬ በታይዋን የተዘገበው ከፍተኛው ጥሰት ነው።

ቻይና የአሁኑን ተልዕኮዋን እንድትፈጽም ያስገደዳት ምክንያት ግልጽ አይደለም።

ሆኖም የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት የቻይና ጦር ኃይሎች የታይዋንን መከላከያ "ሽባ" ሊያደርጉ እንደሚችሉ እና የቻይና ስጋት እያደገ መምጣቱን አስጠንቅቋል።

ቻይና እና ታይዋን፡ መሠረታዊ ጉዳዮች

ቻይና እና ታይዋን እአአ በ1949 የተካሄደው የቻይና የእርስ በእርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ ራሳቸውን የቻሉ የተለያዩ መንግስታት ሆኑ። ቤጂንግ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የታይዋንን ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ለመገደብ የሞከረች ሲሆን ሁለቱም በፓስፊክ አካባቢ ተጽዕኖዋቸውን ለማሳደር ሞክረዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ውጥረቱ የጨመረ ሲሆን ቤጂንግ ኃይልን ጨምሮ የትኛውንም አማራጭ በመጠቀም ደሴቲቱን ለመመለስ እንደምትሠራ አስታውቃለች።

ታይዋን በይፋ ዕውቅና ያገኘችው በጥቂት ሃገሮች ብቻ ቢሆንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው መንግሥቷ ከብዙ ሃገሮች ጋር ጠንካራ የንግድ እና መደበኛ ያልሆነ ግንኙነት አለው።

ልክ እንደ አብዛኛዎቹ ሃገራት አሜሪካ ከታይዋን ጋር ኦፊሴላዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባይኖራትም የአሜሪካ ሕግ ደሴቲቱ ራሷን ለመከላከል የሚያስችሏትን አማራጮችን እንድትሰጥ ያስገድዳታል።