የብራዚል እና አርጀንቲና ጨዋታ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተቋረጠ

የብራዚል እና አርጀንቲና ተጫዋቾች

ትናንት እሁድ ዕለት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ብራዚል እና አርጀንቲና ሲያደርጉት የነበረው ጨዋታ አንዳንድ ተጫዋቾች የኮቪድ-19 መመሪያዎችን ተላልፈዋል በሚል እንዲቋረጥ ተደረገ።

ሶስት የአርጀንቲና ተጫዋቾች የለይቶ ማቆያ መመሪያዎችን ተላልፈዋል በሚል የብራዚል ጤና ኃላፊዎች ጥያቄ መሠረት ዳኞች ጨዋታው በተጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እንዲቋረጥ ወስነዋል።

የዳኞቹ ውሳኔ የተላለፈው ጨዋታው ከመካሄዱ አራት ሰዓታት በፊት የብራዚል የጤና ኃላፊዎች አራት እንግሊዝ ውስጥ የሚጫወቱ የአርጀንቲና ቡድን አባላት ለይቶ ማቆያ መግባት አለባቸው ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

ምንም እንኳን የብራዚል ባለስልጣናት የትኞቹ ተጫዋቾች እንደሆኑ በስም ባይገልጹም በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የሚጫወቱት ኤሚሊያኖ ቡዌንዳ እና ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ ከአስቶን ቪላ እንዲሁም ጂዮቫኒ ሎሴልሶ እና ክርስቲያን ሮሜሮ ከቶተንሀም ናቸው።

ከእነዚህ ተጫዋቾች ደግሞ ማርቲኔዝ፣ ሎ ሴልሶ እና ሮሜሮ ሳኦ ፖሎ በተደረገው ጨዋታ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ መግባት ችለው ነበር።

እስካሁን ድረስ የተቋረጠው ጨዋታ መቼ እንደሚካሄድ ምንም የተባለ ነገር የሌለ ሲሆን የአርጀንቲና ተጫዋቾች የፊታችን አርብ ከቦሊቪያ ለሚያደርጉት ሌላኛው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ጉዟቸውን ያደርጋሉ።

ፊፋ በበኩሉ ጨዋታው መቋረጡን ያረጋገጠ ሲሆን ወደፊት ደግሞ ቀጣይ እርምጃዎችና መረጃዎች ይፋ እንደሚደረጉ አስታውቋል።

የቀድሞው የባርሴሎና የአሁኑ የፒኤስጂ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ጨዋታው ከተቋረጠ በኋላ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን መፍትሄ ለመፈለግ ሲነጋገር ታይቷል።

ጨዋታው ከተቋረጥ ከአንድ ሰዓት በኋላ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል የሆነው 'ኮንሜቦል' ባወጣው መግለጫ የዕለቱ ዳኛ ባስተላለፉት ውሳኔ መሰረት የብራዚል እና የአርጀንቲና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ መቋረጡን ይፋ አድርጓል።

"የዕለቱ ዳኛ እና የጨዋታ ኮሚሽነሩ ለፊፋ የዲሲፕሊን ኦሚቴ ሙሉ ሪፖርት ያቀርባሉ። በዚህም በቀጣይ ምን እንደሚደረግ ይወሰናል። እነዚህ አካሄዶች አሁን ላይ ካለው የኮቪድ መመሪያ ጋር የተጣጣሙ ናቸው'' ብሏል በመግለጫው።

በብራዚል ሕግ መሰረት ወደ አገሪቱ መግባት የሚፈልግ ሰው ባለፉት 14 ቀናት ውስጥ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ቆይታ አድርጎ ከነበረ ብራዚል ከደረሰ በኋላ ለ14 ቀናት እራሱን ለይቶ ማቆየት አለበት።

"አራቱ ተጫዋቾች ብራዚል ከደረሱ በኋላ እራሳቸውን ለ14 ቀናት እንዲያገሉ ተነግሯቸው ነበር። ነገር ግን ይህንን መመሪያ አልተከተሉም። በቀጥታ ወደ ስታዲየም በመሄድ ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር ተቀላቅለዋል። በዚህም በርካታ መመሪያዎችን ነው የጣሱት'' ብለዋል የብራዚል የጤና ጉዳዮች ተቆጣጣሪው አንቶኒዮ ባራ ቶሬስ።

የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ በበኩላቸው ጨዋታው ከመካሄዱ በፊት ቀድሞ መፍትሄ ማግኘት አለመቻሉ በጣም እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

የአርጀንቲና እግር ኳስ ማህበር ደግሞ ቡድኑ ከሶስት ቀናት በፊት ብራዚል መድረሱን እና ሁሉንም የኮቪድ-19 መመሪያዎች ማክበሩን ገልጿል።

የብራዚል እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንም ቢሆን በዚሁ ውሳኔ ደስተኛ አለመሆኑን ገልጿል። በመግለጫውም የጤና ኃላፊዎቹ እርምጃውን የወሰዱበት ሰአት አላስፈላጊ እንደሆነ አስታውቋል።