አሜሪካ እና ዩኬ ታሊባን እውቅና እንዲሰጠው ሰብአዊ መብት ማክበር አለበት አሉ

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን እና የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን እና የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን እና የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን፤ ታሊባን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና ማግኘት ያለበት ሰብአዊ መብት ማክበር ከቻለ ነው አሉ።

መሪዎቹ ባደረጉት ውይይት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለታሊባን እውቅና ሲሰጥ፤ ታሊባን ደግሞ በምላሹ ሰብአዊ መብቶችን ማክበር አለበት ብለዋል።

አፍጋኒስታን ውስጥ ያለው ሁኔታ እንዳይባባስ ሰብአዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መጠቀም የተሻለ አማራጭ እንደሆነ መሪዎቹ ተስማምተዋል።

የሁለቱ ኃያላን አገራት መሪዎች ይህንን ያሉት ታሊባን በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ ንግግር ለማድረግ በጠየቀበት ወቅት ነው።

ሁለቱ መሪዎች ከአፍጋኒስታን ጉዳይ በተጨማሪ ስለ ነጻ የንግድ ትስስር እና የአየር ንብረት ለውጥም ተወያይተዋል።

ነጻ የንግድ ስምምነት

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ነጻ የንግድ ስምምነት የሚኖርበት እድል ጠባብ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ጋር በዋይት ኃውስ ውይይት ካደረጉ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ነጻ የንግድ ስምምነት ላይኖር እንደሚችል ተጠቁሟል።

ከዳውኒንግ ስትሪት የወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው ዩኬ ከአሜሪካ ጋር የተናጠል የንግድ ስምምት መፈራረም ትፈልጋለች።

የዩኬ ሚንስትሮች ከአሜሪካ ጋር የተናጠል የንግድ ውል ካልተፈጸመ የሰሜን አሜሪካ የንግድ ትስስር ውስጥ እንደሚገቡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሁለቱ መሪዎች የ90 ደቂቃ ውይይታቸውን ሲያጠናቅቁ "ለወደፊት ነጻ የንግድ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንሠራለን" ሲል ዳውኒንግ ስትሪት መግለጫ አውጥቷል።

ባይደን "ስለ ንግድ ስምምነት በጥቂቱ ብንወያይም ስምምነት ላይ ለመድረስ ሥራ ይጠይቃል" ብለዋል።

ቦሪስ ጆንሰንም ከቀጣዩ የዩኬ ምርጫ በፊት ከአሜሪካ ጋር የተናጠል የንግድ ስምምነት ላይ መድረስ ፈታኝ መሆኑን "አሜሪካውያን ከባድ ተደራዳሪዎች ናቸው" በማለት ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት የንግድ ስምምነት ላይ ከደረሱ የቀረጥ መጠን ስለሚቀንስ ቁሳቁሶችን በርካሽ ዋጋ መሸመት ይቻላል።

አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ ያሉበት ዩኤስኤምሲኤ የተባለው የንግድ ትስስር ውስጥ ዩናይትድ ኪንግደም ለመግባት ትጠይቃለች ተብሎ ይገመታል።