የአፍሪካ ሕብረት ከሱዳን የሰላም ውይይት ራሱን አገለለ

ሱዳናዊያን ወታደራዊው አመራር ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያደርጉ ሰንብተዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአፍሪካ ሕብረት የተባበሩት መንግስታት የሱዳንን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ባመቻቸው ውይይት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ማቋረጡን አስታወቀ።

በውይይቱ የሕብረቱ ተወካይ ሂደቱ ግልፅነት የጎደለው እና ጠቃሚ የፖለቲካ ተዋናዮችን ያገለለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በካርቱም የአፍሪካ ሕብረት ተወካይ ሞሃመድ ቤላይሽ “የአፍሪካ ሕብረት ግልጽነት፣ ታማኝነት እና አካታችነት በሌለው ሂደት ውስጥ መሳተፍ አይችልም" ማለታቸውን የሱዳኑ የዜና ወኪል ዘግቧል።

እንዲሁም “ሁሉንም ተዋናዮች በማያከብር ብሎም በእኩል አይን በማያይ ሂደት ውስጥ ሕብረቱ አይሳተፍም’’ ሲሉም አክለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት እና ክፍለ አህጉራዊው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በያዝነው ወር መጀመሪያ በተባበሩት መንግስታት አስተባባሪነት የተጀመረውን የውይይት ሂደት ደግፈው ነበር።

ይሁንና ውይይቱ መጀመሩ ይፋ በተደረገ በጥቂት ቀናት ውስጥ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይፋ ተደረገ። ለዚህም ምክንያቱ የቀድሞው የነጻነት እና የለውጥ ኃይሎች ጥምረት (ኤፍኤፍሲ) የተሰኘው ጥምረት ውይይቱ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አይደለሁም ማለቱ ነው።

ጥምረቱ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ላይ ያለው ወታደራዊ አመራሩ ስልጣኑን ለቆ ለሲቪል የሽግግር መንግስት እንዲያስረክብ ጥያቄውን እያቀረበ ነው።

ሱዳንን ለአስርተ ዓመታት በበላይነት የመሩት ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ በሱዳን ከአራት አመታት በፊት በአገሪቱ ወታደራዊ ሠራዊት፣ በሲቪሎች እና ተቃውሞውን በመሩት ቡድኖች መካከል የሥልጣን ክፍፍል መደረጉ ይታወሳል።

በዚህም ሲቪሉን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን አብደላ ሐምዶክ ይዘው የቆዩ ሲሆን ከሠራዊቱ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር በመሆን ሜጀር ጄነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሐን ከፍተኛውን ቦታ ይዘው ቆይተዋlእ።

ነገር ግን ባለፈው አመት ወታደራዊው አመራር በሲቪሉ ላይ መፈንቅለ መንግስት በማካሄድ ሃምዶክም ከስልጣን ተወግደዋል። የቀድሞው የአልበሽር መንግስት ባለስልጣናት የመመለስ አዝማሚያ እየታየ መሆኑንንም ተቃዋሚዎች እየገለጹ ይገኛሉ።