በአፍሪካውያን ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰው የቻይናዊው ዘረኛ ቪዲዮ

ቢቢሲ ያደረገው ምርመራ አፍሪካውያን ሕጻናትን በሚያዋርድ ሁኔታ ቪዲዮ በመቅረጽ በቻይና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እያቀረበ የግል ጥቅሙን ሲያሳድድ የነበረን ቻይናዊ የፊልም ባለሙያን አጋልጧል።

በሕጻናቱ ላይ ከሚፈጸመው ብዝበዛ በተጨማሪ የሚቀረጹት ምስሎች ፍጹም ዘረኝነትን የሚያንጸባርቁ እንደሆኑ የምርመራ ዘገባው አረጋግጧል።

በዚህም የቢቢሲ 'አፍሪካ አይ' የምርመራ ዘገባ አንድ ታዋቂ ቻይናዊ የፊልም ባለሙያ ማላዊ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩና ከዘረኝነት ጋር የተያያዙ ቪዲዮዎችን በመቅረጽ ለሽያጭ ማቅረቡን ደርሶበታል።

ይህ የምርመራ ዘገባ ይፋ ከሆነ በኋላ ድርጊቱ አፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን የቻይና መንግሥትን ጭምር አስቆጥቷል።