የብሪታኒያ ሠራዊት የዩቲዩብና የትዊተር ገጾች መጠለፋቸው ተነገረ

ፊቱ የማይታይ የብሪታኒያ ሠራዊት አባል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የብሪታኒያ ሠራዊት የትዊተርና የዩቲዩብ አካውንቶቹ ባልታወቁ አካላት መጠለፉቸውን ተከትሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑ ተነገረ።

የሠራዊቱ የዩቲዩብ መጠቀሚያ ከተጠለፈ በኋላ የዓለማችን ቢሊየነር ኤሎን መስክን ምስል የያዙ የክሪፕቶከረንሲ ቪዲዮዎች ታይተውበታል።

በተጠለፈው የትዊተር ገጹ ላይ ደግሞ ዲጂታል የጥበብ ሥራዎች መገበያያ የሆነው ኤንኤፍቲ በርካታ የትዊተር መልዕክቶች እንደገና ተጋርተውበታል።

ሠራዊቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ወደ ገጾቹ ባልታወቀ ወገን “ተሰብሮ እንደተገባ” አረጋግጦ፣ በመረጃ ደኅንነቱ ላይ “ጥብቅ ቁጥጥር” እንደሚያደረግ፣ ለተከሰተው ጠለፋ መፍትሔ ለመፈለግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በአሁን ወቅት ሁለቱም የዩቲዩብ እና የትዊተር አካውንቶቸ በሠራዊቱ በቁጥጥሩ ስር መግባታቸው ታውቋል።

የሠራዊቱ ቃል አቀባይ “የተከሰተውን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን ጠለፋ በተመለከተ አስፈላጊው ምርመራ እየተካሄደ በመሆኑ በዚህ ወቅት አስተያየት መስጠት ተገቢ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

እስካሁን የማኅበራዊ ገጾቹ ላይ ጠላፋውን የፈጸመው ወገን ማን እንደሆነ ያልታወቀ ሲሆን፣ የገጾቹ ስምም ተለውጦ ነበር።

የትዊተር ገጹ ‘ባፔስክላን’ በሚል ስም ተቀይሮ የመለያው ምስልም ጦጣ በሚመስል የካርቱን ስዕል ተተክቶ ነበር።

እሁድ ዕለት ማታ የትዊተር አካውንቱ ከጠላፊዎቹ በማስለቀቅ በሠራዊቱ እጅ ስር መግባቱ ተነግሯል።

ይህንንም ተከትሎ ሠራዊቱ "ገጻችን ላይ አጋጥሞ በነበረው ችግር ይቅርታ እንጠይቃለን። ምን እንደተከሰተ ለማወቅ ሙሉ ምርመራ የምናደርግ ሲሆን፣ ስለምትከተሉን እያመሰገንን ሙሉ አገለግሎታችን አሁን መልሶ ተጀምሯል" የሚል መልዕክት ሰፍሯል።

የብሪታኒያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ የፓርላማ አባልና በምክር ቤቱ የመከላከያ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ተቢያስ ኤልዉድ፣ የተከሰተው ነገር “አሳሳቢ ይመስላል” ሲሉ የሠራዊቱ የማኅበራዊ ገጾች መጠለፍ ቀላል ጉዳይ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

"ጠለፋውን በተመለከተ የሚደረገው ምርመራ እና የሚወሰደው እርምጃን በተመለከተ በተገቢው ሁኔታ እንደሚገለጽ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉም የፓርላማ አባሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

በትዊተር ላይ ከፍተኛ እውቅና ያላቸው ገጾች ሲጠለፉ ይህ የብታኒያ ሠራዊት ገጽ የመጀመሪያው አይደለም።

ከሁለት ዓመት በፊት ዋነኛ የሚባሉ የአሜሪካ የትዊተር አካውንቶች በቢትኮይን አማካይነት ከሚደረግ ማጭበርበር ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ተጠልፈው እንደነበር ይታወሳል።

ጠለፋ ከተፈጸመባቸው ገጾች መካከል የታዋቂዎቹ ኤሎን መስክ፣ ጄፍ ቤዞስ፣ ቢል ጌትስ፣ ባራክ ኦባማ፣ ጆ ባይደን እና የካኒዬ ዌስት ይገኙባቸዋል።