የኢራንን የኑክሊየር ሳይንቲስቶች እያደነ የሚገድላቸው ማን ነው?

ሙሕሲን ፋኽሪዛድ መኪናቸው ውስጥ ሳሉ ነበር የተገደሉት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ባለፈው ሳምንት የእስራኤል ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑት ሰው ድንገት ተነስተው ወደ ቱርክ በረሩ።

አንድ የኢራን ህቡዕ ቡድን የእስራኤል ቱሪስቶችን ለመግደል ተንቀሳቅሷል የሚል መረጃ ስለደረሳቸው ነው ፈጥነው ቱርክ የገቡት።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእስራኤልና ኢራን መካከል የጦፈ ግን ደግሞ ድብቅ ውጊያ እየተደረገ ነው፤ ከመጋረጃ በስተጀርባ።

ይህ ነገር ወደለየለት ጦርነት እንዳያመራ መፈራቱ አልቀረም።

ለበርካታ ዓመታት ሁለቱ አገራት በምሥጢራዊ ጥቃት ተጠምደው ነው የኖሩት።

እስራኤል በምድር ላይ የኢራንን ያህል ጠላት የለኝም ትላለች።

ኢራን በበኩሏ በይፋ እስራኤል ከመካከለኛው ምሥራቅ መጥፋት ያለባት አገር ናት እስከማለት ደፍራ ተናግራለች።

በዋናነት ደግሞ ከአሜሪካ ጋር በማበር በአካባቢው ገናና አገር ሆኜ እንዳልወጣ፣ ዕድገቴን እንዳላፋጥን አንቃ ይዛኛለች በማለት ትከሳታለች።

አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጣት ሲጠቋቆሙ ቆይተው ነገሮች ከፈረንጆች 2020 ወዲህ ጀምሮ መልካቸውን እየቀየሩ መጡ።

ኢራን የእስራኤል ምሥጢራዊ ቡድን ታላቁን የኑክሊየር ሳይንቲስቴን ገደለብኝ ስትል ከሰሰች።

ሳይንቲስቱ ሞህሲን ፋኽሪዛድ ናቸው።

የተገደሉት በቴህራን ጎዳና ላይ መኪናቸውን እያሽከረከሩ ሳለ በርቀት መቆጣጠሪያ በሚታዘዝ መትረየስ ተደብድበው ነበር።

እስራኤል ድርጊቱን ስለመፈጸሟ አላመነችም፣ አላስተባበለችም። ሁልጊዜም እንደምታደርገው ዝምታን መርጣለች።

ሞህሲን ፋኽሪዛድ እንዲህ በህቡዕ ቡድን ሲገደሉ የመጀመሪያው የኢራን ሳይንቲስት አይደሉም።

ከፈረንጆቹ 2007 ወዲህ ብቻ አምስት የኢራን ቁንጮ ሳይንቲስቶች ተገድለዋል።

ኒውዮርክ ታይምስ እኚህ ባለሥልጣን በምን ዝግጅትና ሁኔታ እንደተገደሉ ምንጮቹን ሳይጠቅስ በዝርዝር ዘግቦ ነበር።

የቀድሞው የሞሳድ አለቃ በኋላ ላይ እንደተናገሩት እኚህ የኑክሊየር ሳይንቲስት ለዓመታት የእሰራኤል ራስ ምታት ሆነው ቆይተዋል።

በኑክሊየር ሳይንስ ዘርፍ ያላቸው ዕውቀት እስራኤልን ሲያሳስባት ነው የኖረው።

“በክትትላችን ውስጥ ነው የኖሩት” ብለዋል እኚህ የሞሳድ የቀድሞ ባለሥልጣን።

የምዕራብ አገራት የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች እንደሚሉት ከሆነ ሞህሲን ፋኽሪዛድ ኢራን በምሥጢር ልትገነባው ለምትሞክረው የኒክሊየር ኃይል ዋናው አዛዥ ነበሩ።

ከዚህ ወዲያ ኢራንና እስራኤል ከመጋረጃ ጀርባ በተለያዩ ኦፕሬሽኖች ተጠምደው ነው የቆዩት።

ጆ ባይደን በቀዳሚያቸው ዶናልድ ትራምፕ እንደ መናኛ ተቀዳዶ የተጣለውን ሰላማዊ የኑክሊየር ስምምነት ለመመለስ እየጣሩ ነው።

ስምምነቱን ለመመለስ አንድ ዋና ማነቆ ሆኖ የያዛቸው ጉዳይ በሽብር ቡድን ዝርዝር የገባውን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ስሙ ከሽብርተኞች መዝገብ ይፋቅ የሚለው ሐሳብ አሜሪካንን ስላላስማማት ነው።

እስራኤል በቅርብ ጊዜ በኢራን ተደግሶልኝ ነበር ያለችውን የግድያ ሙከራ ማክሸፏን ተናግራለች።

ኢራን በበኩሏ በእስራኤል ውስጥ የድሮን ጥቃት ኦፕሬሽን ማድረጓን በኩራት ገልጻለች። ሆኖም ዝርዝር ሁኔታው አልተብራራም።

ሁለቱ አገራት አንዱ የሌላውን  የመርከብ ጭነት በማጥቃት ይወነጃጀላሉ።

ኢራን ከምድር በታች ባለት የኑክሊየር ማብሊያ ማዕከል ላይ ለተፈጸመባት አሻጥር እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋለች።

ከቀናት በፊት ኢራን ሦስት ከሞሳድ ጋር ግንኙነት ነበራቸው ያለቻቸውን፣ ሌላ ተጨማሪ የኢራን ኒክሊየር ሳይንቲስት ሊገድሉ እንደሆነ እንደደረሰችባቸው የከሰሰቻቸውን ሰዎች ፍርድ ቤት ልታቀርብ እንደሆነ ተናግራለች።

ኢራን ከዚህ ሌላ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሯ በማይታወቅ ሁኔታ እየሞቱ ያሉ ቁልፍ ሰዎች እያጋጠሟት እንደሆነ አምናለች።

ከእነዚህ መካከልም ሁለት የኤሮስፔስ ኃላፊዎች በሥራ ላይ ሳሉ “ተሰውተዋል” ብላለች። አሟሟታቸው ግን ምሥጢራዊ ነው።

ሌላ በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ይሠራ የነበረ መሐንዲስም እንዲሁ በአሻጥር ተገድሎብኛል ብላለች።

ይሁንና ለእነዚህ ግድያዎች እስራኤልን በቀጥታ ተጠያቂ እስከማድረግ አልሄደችም።

ከመጋረጃው ጀርባ በሁለቱ አገራት መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት እስራኤል እና ኢራን ይበልጥ ወደ መድረክ እየወጡ ይመስላል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

በግንቦት ወር ኮ/ል ሳኢድ ኮዳይ ቤታቸው ደጅ ላይ ነበር የተገደሉት

ይህ ነገር ወደ ሆሊውድም ዘልቆ በአፕል የቴሌቪዥን የቲቪ ትዕይንት ላይ አንድ የሞሳድ ሰላይ የኢራንን አብዮታዊ ጥበቃን በጣጥሶ ሲገባ ያሳያል።

የሆሊውድ ፊልም ግን በመሬት ላይ የማይታይ ነገር አይደለም።

ለምሳሌ ከቅርብ ቀናት በፊት እስራኤል ዜጎቼ ሆይ! እባካችሁ ወደ ቱርክ አትሂዱ፤ በቱርክ አገር ያላችሁም ከሆነ ቶሎ ውጡ ስትል አስታውቃለች።

ይህም አንድ የኢራን ህቡዕ ቡድን በአንዳች ስፍራ የእስራኤል ዜጎችን ኢላማ ለማድረግ እየተሰናዳ መሆኑን ስለደረሰችበት ነው።

መሐመድ ሙራንዲ የቴህራን ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ናቸው። የኢራን የኑክሊየር ድርድር የሚዲያ ጉዳዮች አማካሪም ናቸው።

በምዕራባዊያን ከለላ ሰላማዊ ዜጎችን እያደኑ መግደል ማስገደል ለእስራኤል የተለመደ ተግባር ነው ይላሉ።

“ይሁንና እስራኤል እንደምትለው ያህል በኢራን ውስጥ ኦፕሬሽን አታስፈጽምም። በድንገት የሞቱ የኢራን ዜጎችም የእስራኤል ልዩ ኦፕሬሽን የሥራ ውጤት አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያ አለ” ባይ ናቸው።

ፕሮፌሰሩ ጨምረውም “አትጠራጠሩ፣ ኢራን እያንዳንዱን ጥቃት ትበቀላለች” ብለዋል።

ኢራን ልዩ ኃይሏ 'ቁዱስ' ይባላል።

ቁዱስ የአብዮታዊ ዘብ አንድ ክንፍ ነው። ዓላማና ተግባሩ ደግሞ ከኢራን ውጪ ምሥጢራዊ ግዳጆችን መወጣት ነው።

የቁዱስ ብርጌድ ዋና አለቃ ጄኔራል ኢስማኢል ቃኒ፣ ኢራን ማንኛውንም የአሜሪካና የእስራኤል ጠላት የሆነ ቡድንን መደገፏን ትቀጥልበታለች ብለዋል።

ጄኔራል ኢስማኢል ማናቸው? ከተባለ ቃሲም ሱለይማኒን የተኩ ሰው ናቸው።

ቃሲም ሱለይማኒ ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ፣ በጥር ወር፣ አሜሪካ በድሮን ጥቃት እንደገደለቻቸው ይታወሳል።

ሱለይማኒ አሜሪካ በዐይነ ቁራኛ ስትከታተላቸው የነበሩ ሰው ናቸው።

ዶናልድ ትራምፕ እርምጃ ይወሰደብት እስኪሉ ድረስ በአሜሪካ የስለላ ቡድን መነጽር ሥር ነበር።

ትራምፕ እርምጃው ከተወሰደ በኋላ “ሱለይማኒ የዓለማችን ቁጥር አንድ አሸባሪ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ናፍታሊ ቤኔቲ

ትራምፕ ሱለይማኒ እንዲገደሉ የወሰኑት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ማይክ ፓምፔዎ ግፊት ነው ተብሏል።

ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ የኢራን ሚና እንዲኮሰምን ትልቁን ሚና የተጫወቱ የእስራኤል ባለውለታ ተደርገው ይወስዳሉ።

በተለይ አስራኤል ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል የቀየሰችወን ‘አብረሃም አኮርድ’ የተባለውን ዕቅዷን በማስተዋወቅ እስራኤልን ከአረብ አገራት ጋር አወዳጅተው ነው የሄዱት።

የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና ባህሬይን ከእስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን እንዲያድሱ በማገዝ ‘አብረሃም አኮርድ’ ስምምነትን በማፈጣጠም ይበልጥ ኢራንን የመነጠል ሥራም ሠርተዋል።

“ኢራን የአብረሃም አኮርድ ስምምነቶችን እጅግ ትጸየፋለች” ይላሉ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የአረብ ዲፕሎማት።

አንድ የኢራን የቀድሞ ባለሥልጣን ግን ይህን ያሰተባብላሉ።

“ስምምነቱን ባንወደውም ዘላቂ እንደማይሆን እናውቃለን፤ ጊዜያዊ እፍ እፍ ነው፤ የትም አያደርስም” ብለዋል ለቢቢሲ።

የጆ ባይደን የሰሞኑ የሳዑዲ አረቢያና የእስራኤል ጉብኝት እንዳለ ሆኖ፣ አንድ በባይደን አስተዳደር ውስጥ ያሉ ባለሥልጣን የእስራኤልና ኢራን ፍጥጫ ወደከፋ ደረጃ እንደማይሸጋገር እናውቃለን፤ ቢያንስ በአጭር ጊዜ ያ እንደማይሆን እንረዳለን ይላሉ።

ሪች ጎልድበርግ ደግሞ መቀመጫውን ዋሺንግተን ያደረገ የመከላከያ ጉዳዮች የጥናትና ምርምር ቡድን ባልደረባ ናቸው።

እሳቸው እንደሚያምኑት እስራኤል የምታደርጋቸው ምሥጢራዊ ኦፕሬሽኖች ከመበርከታቸው የተነሳ አሁን አሁን ተራ ዕለታዊ ጉዳዮች እንዲመስሉ እያደረገች ነው።

“...አንድ ቀን ግን ዓለም ከመንቃቱ በፊት እስራኤል በኢራን ኑክሊየር ማበልጸጊያ ማዕከል ላይ ድንገተኛ የአየር ጥቃት ማድረሷ አይቀርም፤ ዓለም ጥቃቱን እናስቁመው ከማለቱ በፊት ጥቃቱ ተገባዶ እናገኘው ይሆናል” ብለዋል።