የትግራይ አርሶ አደሮች በዘርና ማዳበሪያ እጥረት የእርሻ ወቅት ሊያልፋቸው እንደሚችል ተገለጸ

የትግራይ አርሶ አደሮች ባለፈው አመት ግንቦት ወር ላይ

የፎቶው ባለመብት, FAO

በትግራይ የሚገኙ አርሶ አደሮች ለክረምቱ መዝራት እንዲችሉ አስፈላጊው ግብዓት በአስቸኳይ እንዲደርሳቸው መደረግ እንዳለበት የዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ገለጸ።

ዘርና ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮቹ በወቅቱ መድረስ ካልቻለ የእርሻ ወቅቱ ሊያልፍ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል። ይህም ሁኔታ በጦርነት ለተጎዳችው የትግራይ ክልል የምግብ ዋስትና በበለጠ የከፋ እንደሚያደርገው ፋኦ በትናንትናው ዕለት ሰኔ 15፣ 2014 ዓ.ም በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

በተያዘው ክረምት የዝናቡ ሁኔታ ጥሩ ሊሆን እንደሚችል እየታየ ሲሆን ይህም በክልሉ የመነመነውን የምግብ አቅርቦት ለማሻሻል ወሳኝ ዕድል እንደሆነም ነው።

እንደ ፋኦ ከሆነ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የትግራይ አርሶ አደሮች የመሬት ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው የዝናብ መምጣቱን እየተጣበበቁ ቢሆንም የግብርና ግብዓቶች በተለይም የማዳበሪያና ዘር አቅርቦት ውስንነት ስጋትን ደቅኗል።

ፋኦ እና አጋሮቹ የኢትዮጵያ መንግሥት ማዳበሪያን ለመግዛት ባቀረበው ጊዜ በአፋጣኝ ለመሸመትም 96 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገናል ብለዋል።

በባለፉት ወራት ፋኦ እና አጋሮቹ 11 ሚሊዮን ዶላር በማሰባሰብ 10 በመቶውን የማዳበሪያ ፍላጎት ለማሟላት ቢችሉም ቀሪውን ግብዓት ለመሸፈን 85 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም አትተዋል።

ተቋሞቹ 60 ሺህ ቶን ማዳበሪያ እና በአገር ውስጥ የሚመረተውን 4 ሺህ ቶን ዘር ከሚያስፈልገው 8 በመቶ ቢሆንም ይህንን ለአርሶ አደሮቹ ለማቅረብ መንገዶችን በመፈለግ ላይ ናቸው።

 ዘር መዘራት ባለበት ወቅት ለማድረስ ያለው ጊዜ አጭር መሆኑ ጋር ተያይዞም ግብዓቶቹ በአስቸኳይ ሁኔታ መቅረብ እንዳለባቸውም ፋኦ አፅንኦት ሰጥቷል።

“በትግራይ ያለውን የምግብ ምርትን የመደገፍ አስፈላጊነትን መግለፅ ከምንችለው በላይ ነው። ክልሉ ተገቢው ዘርና ማዳበሪያ ከሌለው ለህዝቡ በቂ ምግብ ሊያመርት ይችላል ተብሎ የማይታሰብ ነው” በማለት የፋኦ የኢትዮጵያ ተወካይ ዴቪድ ፒሪ ተናግረዋል።

ተወካዩ በተጨማሪም ተቋማቸው በጦርነቱ ለተጎዱት የአማራ አፋር አካባቢዎችም በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በቴክኒክ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማሳደግ እየሞከረ ነው ብለዋል።

 ወደ እነዚህ ክልሎች መድረሱ በጣም ቀላል ቢሆንም ነገር ግን በቂ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዳልነበረም ገልጸዋል።

በመኸር የእርሻ ወቅት ላይ ድጋፍ ከተደረገ አርሶ አደሮች ምርታቸውን መሰብሰብ እና በጥቅምት ወር ላይም ራሳቸውንም መመገብ እንደሚችሉና እስከ መጪው የምርት ወቅት በቂ ምግብ እንዲኖርና  የምግብ ዋስትናቸውን የበለጠ እንደሚያጠናክረው ተገልጿል።

 ሆኖም እነዚህ ግብአቶች ከሌሉ የሚቀጥለው የእርሻ ወቅት ጥቅምት ከመሆኑ ጋር ተያያዞ ረሃቡን ለተጨማሪ አንድ አመት እንደሚያራዝመውና የሰብዓዊ እርዳታውን አስፈላጊነትም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምረዋል።

“በአሁኑ ወቅት እህል መዘራት ያለበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነን። አስከፊ ረሃብን ለመከላከል ትንሽ እድል አለ። ይህም የሚሆነው በክልሉ ውስጥ ያለውን ምርት በመደገፍ ነው ይህም ከረሃቡ በተጨማሪ ሊፈጠር የሚችለውንም ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታን በማስቀረት አስተዋፅኦ አለው” ሲሉ የፋኦ የአደጋ ጊዜ እና የመቋቋም ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ሬይን ፖልሰን ተናግረዋል።   

በባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት የትግራይ አርሶ አደሮች  900, ሺህ  ቶን ዋና ዋና ምግቦች ያመረቱ ሲሆን ይህም 40 በመቶውን መደበኛ ምርት እንደሚይዝም ተገልጿል።

ለረጅም ጊዜ የእርዳታ አቅርቦት ተቋርጠው የቆዩባት ትግራይ ባለፈው መጋቢት ወር የፌደራሉ መንግሥትና የትግራይ ክልል ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺነት የተኩስ አቁም ማወጃቸውን ተከትሎ እርዳታ ወደ ክልሉ በየብስ እየገባ ነው።

ሆኖም መሰረታዊ የሚባሉ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የባንክ አገልግሎቶች አሁንም እንደተቋረጡ ነው።

ከሰሞኑ ትግራይን የጎበኙት የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ጃኔዝ ሌናርቺክ እነዚህን  መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲያስጀምር የኢትዮጵያ መንግሥትን ጠይቀዋል።

በተጨማሪም  ወደ ትግራይ እየገባ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ወደሚፈለገው አካባቢ ለማድረስ በነዳጅ እና በገንዘብ አቅርቦት ላይ የተጣለውን ዕቀባም እንዲነሳ ጠይቀዋል።