በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ በርካታ ቦታዎች በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸውን መንግሥት አስታወቀ

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የመንግሥት ከሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, Government Communication Service

በቄለም ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ እና በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች የሚገኙ ወረዳዎች በተቀናጀ የፀጥታ ኃይል እርምጃ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ሙሉ በሙሉ መግባታቸውን የመንግሥት ኮሙኑኬሽን አስታወቀ።

ይህ የተገለጸው የአገሪቱን ወቅታዊ ሰላምና ደኅንነት በተመለከተ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በዛሬ ሐሙስ ሰኔ 23/2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ነው።

በአካባቢዎቹ መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚንቀሳቀስባቸው እንደሆነ የሚነገርላቸው ስፍራዎችን የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ተቀናጅተው ባደረጉት ዘመቻ ተቆጣጥረውታል ብለዋል።

በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ጭፍጨፋ አድርሰዋል ባሏቸው "የሽብር ቡድን" ያሏቸው ታጣቂዎች ላይ የተቀናጀው የፀጥታ ኃይል በከፈተው ዘመቻ በርካታ አባላቱ መገደላቸውን በዚሁ ወቅት አስረድተዋል።

ወደ አካባቢዎቹ ጫካ ተበታትነዋል ያሏቸው የቡድኑ አባላትም በፀጥታ ኃይሎችና በኅብረተሰቡ ትብብር በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑንም ነው የገለጹት ሚኒስትሩ።

በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ሰኔ 11/2014 ዓ.ም ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለመፈናቀል መዳረጋቸው ተዘግቧል።

ከጭፍጨፋው የተረፉ ነዋሪዎችና መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመው ‘ሸኔ’ በመባል የሚታወቀው ታጣቂው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንደሆነ ሲገልጹ፣ ቡድኑ ግን ለጥቃቱ የመንግሥት ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጎ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ መጠየቁ ይታወሳል። 

መንግሥት በተለያዩ ክልሎች እያካሄድኩ ነው ባለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የሽብር ቡድኖች በሚል የጠራቸው አካላትና ሕገወጥ ታጣቂዎች ከፍተኛ ቁሳዊና ሰብዓዊ ኪሳራም በመድረሱ እነዚህ አካላት ንጹሃን ዜጎችን ኢላማ እያደረጉ መሆኑም በዚህ ወቅት ተገልጿል።

የምዕራብ ወለጋውን ጨምሮ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች “እጅግ ዘግናኝና ከሰውነት ያፈነገጠ ተግባር ፈፅመዋል” ብለዋል ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)።

በጊምቢ የተፈጸመው ግድያ "የሽብር ድርጊት" መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ “የእነዚህ ኃይሎች ዋነኛ አላማ በኅብረተሰባችን ውስጥ ማኅበረሰባዊ ክፍፍል፣ በጥላቻ ላይ የተመሰረተ የኅብረተሰብ ግጭት በመፍጠር ኢትዮጵያን ለማበልጸግ መንግሥት የያዘውን አጀንዳ ማሰናከል ነው” ብለዋል።

የተፈጠረውን ግድያም ተከትሎ መንግሥት ችግሩ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች አፋጣኝ እርምጃ መውሰዱንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ጉዳት የደረሰባቸውን የቤተሰብ አባላት የማረጋጋት፣ ተደናግጠው ከአካባቢው የለቀቁት ወደቀያቸው እንዲመለሱና ንብረታቸው የወደመባቸው እርዳታ እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።

በጥቃቱም የቆሰሉ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ መደረጉንና የተዘረፉ ንብረቶችም በአካባቢው ማኅበረሰብ አስተባባሪነት እየተመለሱ ናቸው ብለዋል።

በጋምቤላ ጥቃት ሊፈፅሙ ነበር ያሏቸው ቡድኖች ሙሉ በሙሉ መደምሰሳቸውን በዚህ ወቅት የገለጹት ሚኒስትሩ በዚህም መረጋጋትና ሰላም መጥቷል ሲሉ አስረድተዋል።

በጋምቤላ የታቀደው ጥቃት በታሰበው ልክ መሳካት ባለመቻሉ በአዲስ አበባም የተለያዩ የእምነት ተቋማትን በመጠቀም ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም ጥረት እያደረጉ መሆናቸውንም በዚህ ወቅት ተናግረው ኅብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአማራ፣ በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መንግሥት የጀመረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በሰፊው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል። 

በእነዚህ ክልሎች እየተካሄደ ያለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ስኬታማ በሆነ መልኩ በመከናወኑ በመላው አገሪቱ ለሕግ ማስከበርና ሰላምን ለማረጋጋት ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም ጠቅሰዋል።

መንግሥት ወስዶታል ባለው የሕግ ማስከበር እርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ከእስር ቤት ያመለጡ፣ በነፍስ ግድያ የሚፈለጉ፣ በሌሉበት ተፈርዶባቸው ሲፈለጉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም ከልዩ ልዩ የፀጥታ መዋቅሮች ከድተው በሕገወጥ ተግባራት ተሰማርተው ነበሩ ያሏቸው ሚኒስትሩ፣ ተደራጅተው ኅብረተሰቡን መግቢያ መውጫ ያሳጡ ግለሰቦች በአብዛኛው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል።

አብዛኞቹም ጉዳያቸው ተጣርቶ በየደረጃው ባለ ፍርድ ቤት እየታየ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የጦር መሳሪያዎች እንዲሁም ለሽብር አገልግሎት ሊውል ታቅዶ ነበር የተባለ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብርና የውጭ አገር ገንዘቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም ለሽብር ተግባር የሚውሉ የማሰልጠኛ ጣቢያዎችና ቁሳቁሶች እንዲወድሙ ተደርጓል ብለዋል ሚኒስትሩ።

በተወሰደውም እርምጃ ሚኒስትሩ የሽብር ቡድኖች ብለው የጠሯቸው አካላትና ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ቁሳዊና ሰብዓዊ ኪሳራ ደርሶባቸዋል ብለዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በአብዛኛው አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላምና ፖለቲካዊ መረጋጋት እየተፈጠረም መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።