በአፋር ማቆያ ውስጥ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ ተነገረ

በማቆያው ውስጥ የሚገኙ ሴት አዛውንቶች

የፎቶው ባለመብት, AM

በኅዳር ወር በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች የትግራይ እና የአፋር የድንበር ከተማ ከሆነችው አብአላ ታፍሰው ወደ ሰመራ መወሰዳቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ያስረዳሉ።

ሮይተርስ በበኩሉ እነዚህ የትግራይ ተወላጆች ከአብአላ ከተወሰዱ በኋላ ሰመራ አቅራብያ በሚገኘው ሶሎዳ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ መቀመጣቸውን ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ በኮሌጁ ውስጥ ቁጥራቸው ከ7000 እስከ 12000 የሚሆኑ ግለሰቦች ይገኛሉ።

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል በበኩሉ ባለፈው ወር በሰመራ ለሚገኙ 9000 ተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረጉን በመግለጽ በይፋዊ የትዊተር ገፁ ላይ አስፍሯል።

ቢቢሲ ከሶሎዳ የተፈናቃዮች ማቆያ የወጣ የትግራይ ተወላጅን አነጋግሮ፣ አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች 15 ኪሎ ስንዴ እና ብርድ ልብስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጿል።

ሮይተርስም ሁለት ተፈናቃዮች እርዳታውን መቀበላቸውን እንዳረጋገጡለት ዘግቧል።

በትግራይ እና በአፋር ድንበር ላይ በምትገኘው አብአላ ለመጀመርያ ጊዜ ውጊያ የተደረገው ታኅሣሥ 09/2014 ዓ.ም ነበር።

በከተማዋ የሚኖሩ ሰዎች አብአላን ሸኸት በማለትም ይጠሯታል።

ታኅሣሥ 09 በትግራይ ኃይሎች እና በአፋር የፀጥታ አካላት መካከል ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ በከተማዋ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን ‘ደህንታችሁ ወደ ሚጠበቅበት ስፍራ እንወስዳችሏለን’ በሚል ወደ ሊላ ቦታ መወሰዳቸውን አብዋሎም ሲሳይ* ለቢቢሲ ተናግሯል።

አብዋሎም እንደሚለው በወቅቱ በእድሜ የገፉ፣ ነፍሰጡር ሴቶች፣ ዐይነ ስውሮችን ጨምሮ በአጠቃላይ 15 ሺህ የሚሆኑ የትግራይ ተወላጆች ተይዘው በፖሊስ ጣቢያ እና በእስር ቤቶች እንዲቆዩ መደረጉን ያስታውሳል።

ከዚህ በኋላም በትላልቅ መኪኖች ተጭነው ወደ ሰመራ ተወሰዱ።

“ከውጊያው በኋላ የአፋር የፀጥታ አካላት ምንም የማያውቁ ነዋሪዎችን ሬዲዮ ነበረክ፣ ከህወሓት ጋር ግንኙነት ስታደርግ ነበር በሚል ውንጀላ ብዙ የምናውቃቸውን ሰዎች ገድለዋል” ይላል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአፋር ክልል ምርመራ እና ክትትል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ኮሚሽኑ ጉዳዩን በሚመለከት ምርመራ ማድረጉን ገልጻለች።

አክላም “እጅግ በጣም የሚያሳስብ እና የሚያሰጋ ሁኔታን የሚያሳየው የምርመራ ውጤትን በኮሚሽነሩ ደረጃ እንዲታይ አድርገናል” ስትል ለቢቢሲ ጥያቄ ምላሽ ሰጥታለች።

ኮሚሽኑ ችግሩ እንዲፈታ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ኮሚሽኑ በአፋር የትግራይ ተወላጆች ያሉበትን ሁኔታ የሚያሳየውን ሪፖርት ገና ይፋ ያላደረገ ሲሆን፣ በማቆያ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ግለሰቦች ለሕይወታቸው አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ግን ኃላፊዋ ለቢቢሲ ገልጻለች።

ቢቢሲ ከአፋር ክልል ኃላፊዎችን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የትግራይ ኃይሎች በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ መቀስቀሱ ይታወሳል።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ከትግራይ ክልል ተሻግሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋ ሲሆን፣ በዚህም ዜጎች ላይ ሞት፣ ርሃብ እና መፈናቀል አስከትሏል።

የህወሓት ኃይሎች አብአላ ላይ ጥቃት ከፈፀሙ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከአፋር ኃይሎች በኩል የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ሲከላከሉ መቆየታቸውን በመግለጽ ሰኞ ጥር 16/2014 “ጠንካራ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ መገደዳቸውን" ገልጸው ነበር።

አብአላ ውስጥ የተከሰተው ምን ነበር?

የትግራይ ኃይሎች ቅዳሜ ታኅሣሥ 09/2014 ዓ.ም. አብአላ ከተማ ገብተው ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ በማግስቱ መውጣታቸውን የሚያስታውሰው አብዋሎም፣ ከዚያ በኋላ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በአፋር የፀጥታ አካላት ከባድ ጥቃት መፈፀሙን ለቢቢሲ ገልጿል።

በዚህም የትግራይ ተወላጆች የሆነ ንብረት፣ ቤት ላይ ተነጥሎ ጥቃት መድረሱን የሚናገረው አብዋሎም፣ “በርካቶች ተገድለዋል፤ ሬሳቸው በየመንገዱ ተጥሎ ሰንብቷል” ይላል።

በሰመራ ማቆያ ስፍራ ውስጥ የሚገኘውና የሁለት ልጆች አባት የሆነው ወልዳይ ገብረጻዲቅ* በበኩሉ አብዛኛዎቹ በመጠለያው የሚገኙ ሰዎች አርሶ አደሮች እና ነጋዴዎች እንዲሁም የቀን ሠራተኞች መሆናቸውን ይናገራል።

ቢቢሲ ወልዳይን ያነጋገረው ወደ መጠለያው በድብቅ በገባ ስልክ ሲሆን፣ ድምፁ እንዳይሰማ በብርድ ልብስ ውስጥ ተደብቆ እንደሆነና በመግለጽ በማንሾካሾክ ነበር የሚያወራው።

እርሱ አንደሚለው ከውጊያው በኋላ ሚሊሻ እና የአፋር ፀጥታ ኃይሎች ሠላማዊ የከተማዋ የትግራይ ተወላጆችን እየለዩ መያዛቸውን “በግምት ከ300 በላይ መገደላቸውን” ይናገራል።

በከተማዋ ብቻ ከ16 ሺህ በላይ የትግራይ ተወላጆች ይኖሩ እንደነበር የሚያስረዳው ወልዳይ፣ በተለይ ጊድሞን እና ወጋርያን የሚባሉ የገጠር ቀበሌዎች በብዛት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ አርሶ አደሮች እንደሚገኙበት ይናገራል።

ወልዳይ የእህቱን ልጅ ጨምሮ ወዳጅ ዘመዶቹ አይኑ እያየ መገደላቸውን ለቢቢሲ ገልጿል።

ቢቢሲ በወቅቱ ተፈፀሙ ስለተባሉ ግድያዎች ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።

የትግራይ ኃይሎችም ሆኑ የአፋር የፀጥታ አካላት በዚህ ተፈጽሟል በተባለ ጥቃት እርስ በእርሳቸው ይካሰሳሉ።

የፌደራል መንግሥትም ሆነ የአፋር ክልል መንግሥት በአብአላ በንፁሃን ላይ ተፈፀመ ስለተባለው ግድያ እስካሁን ድረስ ያሉት ነገር የለም።

ቢቢሲ በስልክ ያነጋገራቸው የጥቃቱ ሰለባዎች ነን የሚሉ ሰዎች እንደሚሉት በከተማው የነበረው አለመረጋጋት፣ ዘረፋ እና ግድያ ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ በኋላ የአፋር የፀጥታ ኃይሎች የትግራይ ተወላጆችን በትልልቅ መኪኖች ጭነው “እንደ ምርኮኛ እያስፈራሩ እና መሳርያ እየተኮሱ” ወደ ሰመራ ወስደዋቸዋል።

በሰመራም ለሦስት ቀናት ያረፉበት መጠለያ ውስጥ ምግብ እና ሕክምና ሳያገኙ መቆየታቸውን አብዋሎም ያስታውሳል።

ሮይተርስ በበኩሉ በመጀመሪያ ከአብአላ የተያዙ ወንዶች በፀጥታ አካላት መደብደባቸውን ከሦስት ግለሰቦች መስማቱን ገልጿል።

ከዚያ በኋላም “ሰው መሞት ሲጀምር ብስኩት እና ውሃ መስጠት ጀመሩ” ይላል አብዋሎም።

ከማቆያው ስፍራ ከወጡ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው አብዋሎም፣ በተለይ የደም ግፊት እና የስኳር ሕመምተኛ የሆኑ ግለሰቦች ከፍተኛ ስቃይ ማሳለፋቸውን ገልጿል።

ቢቢሲ በተለያየ ወቅት ያነጋገራቸው የመጠለያው ነዋሪዎች በማቆያ ስፍራ ከ70 በላይ፣ በአብዛኛው አዛውንቶች የሆኑ መሞታቸውን ይናገራሉ።

በቅርብ ጊዜ በመጠለያው ስለሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ሰፊ ዘገባ ያቀረበው ሮይተርስ የሟቾቹ ቁጥር ከ60 በላይ መሆኑን ይናገራል።

ከእነዚህ ሟቾች መካከልም 11 ሕጻናት መሆናቸውን ጨምሮ ገልጿል።

የትግራይ ተወላጆች የሚገኙበት ይህ ስፍራ ሶሎዳ ኮሌጅ ግቢ የሚባል ሲሆን ወንዶች እና ሴቶች በአጥር በተለዩ ስፍራዎች ይኖራሉ።

ቢቢሲ ለዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል በአፋር ሰመራ ስለሚገኙ እነዚህ ግለሰቦች ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን “ሁኔታቸው ልክ በአገሪቱ ሌሎች አካባቢዎች እንዳሉ ተፈናቃዮች አሳሳቢ” መሆኑን በመግለጽ ተጨማሪ ማብራርያ ከመስጠት ተቆጥቧል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል በአፋር የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን እንደ ተፈናቃይ የሚያይ ቢሆንም፣ እነርሱ ግን በእስር ላይ ነው ያለነው ይላሉ።

ለዚህም እንደማስረጃ የሚያቀርቡት ከመጠለያው ለመውጣት እንደልብ ወጥቶ ለመመለስ መከልከላቸውን ነው።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር በበኩሉ፣ ከኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመተባበርም “ዘጠኝ ሺህ በመቆያው ተጠልለው ለሚገኙ ሰዎች የምግብ ድጋፍ ማድረጉን” ደኅነታቸውን በተመለከተም ከአፋር ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ገልጿል።

የተፈናቃይ መጠለያ ወይስ. . . ?

በማቆያ ስፍራ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በቂ እርዳታ እና ሕክምና አለማግኘታቸውን ገልጸው ሕጻናት እና እስከ 90 ዓመት የሚደርሱ አዛውንቶች በቦታው እንደሚገኙ ይናገራሉ።

ቢቢሲ መጠለያው ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ናቸው የተነባሉ በምግብ እጥረት እና በሽታ የተጎዱ ሕጻናትን ምስል ተመልክቷል።

ወልዳይ ከቢቢሲ ጋር ቃለመጠይቅ ባደረገበት ዕለት ብቻ ሦስት አዛውንቶች ሕይወታቸው ማለፉንና ቀብራቸውም በመጠለያ ግቢ ውስጥ ቆሻሻ በሚጣልበት ስፍራ እንደተፈፀመ ተናግሯል።

በማቆያው ከልጆቹ እና ከባለቤቱ ጋር የሚኖረው ወልዳይ የአካባቢው ሙቀት አንዳንዴ ከ50 ዲግሪ እንደሚያልፍ ያስረዳል።

በዚህ ሀሩር ውስጥ በተጠጋጋ እና ከፍተኛ የውሃ እጥረት ባለበት ሁኔታ በስቃይ ውስጥ እንደሚኖሩም ጨምሮ ተናግሯል።

ከመጠለያ ስፍራው ወደ ውጪ መውጣት እንደማይቻል እንዲሁም የመጸዳጃ ቤት ችግር እንዳለ የሚናገረው ወልዳይ “በተለይ ከአብአላ ታፍሰው ወደ ስፍራው እንደመጣን የመፀዳጃ ስፍራ ስላልተዘጋጀ ሜዳ ላይ ለመጸዳዳት ተገድደን ነበር” ይላል።

በመጠለያው የሚገኙ ሰዎች በቂ ሕክምና እያገኙ አለመሆኑን ገልፀው፣ አንዳንዴ ለጠባቂዎዎች እስከ 500 ብር ድረስ ጉቦ ከፍለው መድኃኒት ለመግዛት እንደሚወጡ ገልፀዋል።

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ የትግራይ ተወላጆች በማቆያ ስፍራ የሚገኙበት ሁኔታ “ለሕይወት እጅግ አደገኛ ነው” ብሎታል።

በማቆያው ስፍራ ስለሞቱት ሰዎች ቁጥር እና በማቆያ ውስጥ ስለሚገኙ ሰዎች ብዛት ለማወቅ ቢቢሲ ጥያቄ አቅርቦ ጥናቱ ስላላቀ አስተያየት ለመስጠት እንደምትቸገር የኮሚሽኑ ባልደረባ ሰላማዊት ገልጻለች።

ሆኖም “በእርግጥ በማቆያው ውስጥ ምንነቱ ያልታወቀ ተላላፊ በሽታ መከሰቱን እና በተለይ ደግሞ ሕጻናትን እያጠቃ መሆኑን” አብራርታ “በዚህ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን” እንደሚያውቁ ተናግራለች።

ከማቆያ ስፍራው የወጣው አውአሎም እዚያ በነበረበት ውቅት የምግብ እና የንጽህና መስጫ ቦታዎች ላይ የተወሰነ መሻሻል ማየቱን ይናገራል።

እነዚህ በሰመራ ሶሎዳ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ የሚገኙት የትግራይ ተወላጆች አያያዝ እንደ ተፈናቃይ ሳይሆን እንደ አስረኛ ማቆያ መሆኑን ሰላማዊት አክላ ተናግራለች።

በመጠለያ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችም በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኙ የተማጽኖ ድምጻቸውን ያሰማሉ።

* ቢቢሲ ያነጋገራቸውን በአፋር ማቆያ የሚኖሩ እና ይኖሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን ስም ለደህንነታቸው ሲል ስማቸውን ቀይሯል።