ተመድ በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ወታደራዊ ምልመላ ይደረግ እንደነበረ መረጃው አለኝ አለ

በመስራቅ ሱዳን ባለ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ምግብ ለመቀበል የተሰለፉ የትግራይ ተወላጆች ታኅሣሥ 3/2013 ዓ.ም.

የፎቶው ባለመብት, AP

የምስሉ መግለጫ,

በምሥራቅ ሱዳን ባለ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ታኅሣሥ 03/2013 ዓ.ም.

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮች በነበሩባቸው የሱዳን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የግዳጅ የውትድርና ምልመላ ይካሄድ እንደነበረ መረጃው ነበረኝ አለ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተቋም እንዳለው ከወራት በፊት ከስደተኞቹ መካከል አንዳንድ ጊዜ በኃይል ጭምር ተዋጊዎችን ለመመልመል የሚደረጉ ጥረቶች እንደነበሩ “ተአማኒ ሪፖርቶች” ደርሰውት እንደነበር ለቢቢሲ ገልጿል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ 2013 ዓ.ም. ላይ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ድንበር ተሻግረው ወደ ምሥራቅ ሱዳን መግባታቸው ይታወሳል።

የስደተኞቹ ከፍተኛ ኮሚሽን ወታደራዊ ምልመላ መኖሩን እንደተገነዘበ ጉዳዩን በተመለከተ ለሱዳን ማዕከላዊ መንግሥት እና ለአካባቢ ባለሥልጣናት ስጋቱን መግለጹን አመልክቷል።

ይህንንም ተከትሎ ሁኔታዎች የተሻሻሉ ይመስሉ እንደነበር የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተቋም ለቢቢሲ በኢሜይል በሰጠው ምላሽ ገልጿል።

ደርጅቱ “ወታደራዊ ምልመላውን ለማካሄድ ከኢትዮጵያ የሚመጡ ሰዎች እንደነበሩ” ከስደተኞች መረዳቱን የገለጸ ቢሆንም፤ የትኛው ወገን ምልመላውን እንዳካሄድ ግን “ማረጋገጥ አልቻልኩም” ብሏል።

ድርጅቱ ይህን ይበል እንጂ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት በተደጋጋሚ በሱዳን በስደተኝነት የተመዘገቡ ሰዎች ድንበር ተሻግረው ከትግራይ ኃይሎች ጋር በመወገን ሲዋጉ ነበር በማለት ሲከስ ቆይቷል።

ሁለት ዓመት ሊደፍን የተቃረበውን የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት መቀስቀስን ትከተሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በአብዛኛው ከምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ወደ ሱዳን መሸሻቸው ይታወሳል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፤ በስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ የሚደረጉ ምልመላን ጨምሮ ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የስደተኞችን እንዲሁም የእርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ ከዓለም አቀፍ የጦርነት ሕጎች እና የስደተኞች መርሆዎች ጋር የሚቃረን ተግባር በመሆኑ በአስቸኳይ ይቁም ሲል ጠይቋል።

ድርጅቱ ጨምሮም ስደተኞችን በመመልመል ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ እና ሰብዓዊ ሕግጋቶችን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርቧል።

የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት

የሰላም አስከባሪ አባላት በጦርነት መሳተፍ

ከጥቂት ቀናት በፊት ብሉምበርግ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት ከትግራይ ኃይሎች ጎን ተሰልፈዋል የሚል ዘገባ አወጥቶ ነበር።

ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ትገባኛለች በሚሏት የአብዬ ግዛት ተሰማርተው ከነበሩት ሰላም አስከባሪዎች መካከል ሚያዚያ አጋማሽ 2014 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ አንመሰለስም ያሉት የትግራይ ተወላጆች ቁጥር ወደ 500 እንደሚጠጋ ከመካከላቸው አንዱ በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

ብሉምበርግ በዘገባው ለደኅንነታችን እንሰጋለን በሚል በሱዳን ቀርተው ጥገኝነት ጠይቀው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት፣ ከሌሎች የትግራይ ተወላጆች ጋር በመሆን በሁመራ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መቃረባቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ነግረውኛል ብሏል።

የብሉምበርግ ዘገባን ተከትሎ ተመድ ለቀድሞ የሰላም አስከባሪ አባላት የስደተኝነት እውቅና ከሰጠ በኋላ ወደ ጦርነት ተሰማርተዋል የሚሉ ክሶች ሲሰሙ በተደጋጋሚ ሲሰሙ ቆይተዋል።

የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ግን የስደተኝነት እውቅናን የሚሰጠው የሱዳን መንግሥት መሆኑን ገልጾ፤ በዚህ ላይ የደርጅቱ ተሳትፎ የቴክኒክ ምክር እና ድጋፍ ማድረግ ብቻ መሆኑን አመልክቷል።

“ቁጥራቸው ወደ 650 የሚጠጋ የቀድሞ ሰላም አስከባሪ አባላት በሱዳን የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበው 247ቱ” የስደተኝነት እውቅና ማግኘታቸውን ከፍተኛ ኮሚሽኑ ገልጿል።

ነገር ግን የስደተኝነት እውቅና የማግኘት ሂደቱን ሳያጠናቅቁ ከሚኖሩበት አካባቢ ጥለው ስለሄዱት ግለሰቦች የሚያውቀው መረጃ እንደሌላው ድርጅቲ ለቢቢሲ በኢሜይለ በሰጠው ምላሽ ገልጿል።

“ዓለም አቀፍ ሕጎች የስደተኝነት እውቅና ከማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጋር አብሮ እንደማይሄድ እና አንድ ወታደር ጥገኝነት ለመጠየቅ ከፈለገ ወታደርነቱን መተው እንዳለበት ይደነግጋሉ” ሲል ከፍተኛ ኮሚሽኑ አክሏል።

ግጭት እንደ አዲስ መቀስቀስ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንደ አዲስ መቀስቀስ “ብዙ በተሰቃዩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ተጨማሪ ሰቆቃን የሚያመጣው ነው” ይላል።

ግጭቱ እንደ አዲስ ማገርሸቱ ተጨማሪ ሰዎች ደኅንነት እና ሰብዓዊ እርዳታን ፍለጋ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ሊያደርግ እንደሚችል ድርጅቱ ተንበያውን ያስቀመጠ ሲሆን፤ በሱዳን እና በመላው ዓለም ተፈናቅለው ለሚገኙ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ያጋጠመው የገንዘብ እጥረት እንዳሳሰበው ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን የእርስ በእርስ ጦርነት በመሸሽ በሱዳን የተጠለሉት አብዛኛዎቹ ሰዎች የሚገኙት ሩካባ እና ቱናያዳባህ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ መሆኑን የጠቀሰው ድርጅቱ፤ እነዚህ መጠለያ ጣቢያዎቹ ከኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር በ500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛሉ ብሏል።

የግጭቱን ማገርሸት ተከትሎ አዲስ ተፈናቃዮች ስለመኖራቸው ክትትል እያደረገ እንደሆነ የገለጸው ኮሚሽኑ፤ እስካሁን ድረስ በተጠቀሱት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያም ሆነ ሃምዲያት ስደተኞች መቀበያ ጣቢያ ግጭት መድረሱን የሚያሳይ ምንም ሪፖርት የለም ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት በሱዳን በሚገኙ የሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም ያለው ድርጅቱ፤ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ግን በቅርበት እንደሚከታተል ገልጿል።