አዳማ የግብርና ማሽነሪ ፋብሪካ ከ 10 ቢሊዮን ብር በላይ ማባከኑ ተረጋገጠ

በኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ስር የሚገኘው የአዳማ የግብርና ማሽነሪ ማምረቻ የገጣጠማቸው ትራክተሮች

የፎቶው ባለመብት, ETHIO-ENGINEERING GROUP

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የኦዲት ሪፖርት በኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ስር የሚገኘው የአዳማ የግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ቁጥራቸው 6 ሺህ የሚጠጉ የግብርና ማሽኖችን ቢገዛም አገልግሎት መስጠት ሳይችሉ ተከማችተው መቀመጣቸውን አስታወቀ።

ከዚህ በተጫማሪም ከብድር እና ሽያጭ ገንዘብ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ በአጠቃላይ ከ 10 ቢሊዮን ብር በላይ የሕዝብ ገንዘብ ማባከኑን ኦዲተር ጄነራሏ ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ለምክር ቤቱ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል።

ተቋሙ የመንግሥትን መመሪያ የተከተለ የግዢ ስርዓት መዘርጋት ይገባው የነበረ ቢሆንም ይህንን ሳያደርግ ብሎም የገበያ ፍላጎት ጥናት ሳያደርግ የትራክተሮችን ግዢ ሲያከናውን መቆየቱንም ኦዲተሮች አረጋግጠዋል ብለዋል።

በተጨማሪም የሚገዙት ማሽነሪዎች ከሚፈለጉበት የኢትዮጵያ መልክዓ-ምድር ጋር መስማማታቸው ሳይጠና ያለ ጨረታ እና ያለ እቅድ ከ 14 ሺህ በላይ ትራክተሮችን በአራት አመታት ውስጥ ብቻ መግዛቱን ሪፖርቱ አሳይቷል።

ይህም ከ 2003 እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ባሉት አመታት ውስጥ መሆኑ በሪፖርቱ ውስጥ ተቀምጧል።

ለእነዚህ ግዢዎችም ከመንግሥት ካዝና በውጪ ምንዛሬ ከ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ማውጣቱን የገለጸው ተቆጣጣሪ ተቋሙ ከዚህ ውስጥ ቁጥራቸው ስድስት ሺሕ የሚጠጋው አገልግሎት መሰጠት በማይችሉበት ደረጃ ላይ ተከማችተው እንደሚገኙ ተቆጣጣሪ ተቋሙ አረጋግጧል።

የአዳማ የግብርና ማሽነሪ፣ ማምረቻ ማሽነሪዎችን በሚገዛበት ወቅት ጥራትን የሚያረጋግጥበት ስርዓት የሌለው ሲሆን ይህም በዘልማድ በከፊል የተገጣጠሙ ትራክተሮችን እየገዛ እንዲያስገባ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል።

ከተመሰረተ 40 ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ተቋም እስካሁን በከፊል ትራክተሮችን ከመገጣጠም እና ምርቱን ከውጪ ከማስመጣት ባሻገር አገልግሎቱን ለማሻሻል ሳይችል መቅረቱ ከገንዘብ ጉድለቱ ባሻገር በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ የቀረበበት የአሰራር ጉድለት ነው።

እንዲሁም የሽያጭ ገንዘብ አሰባሰብ ስርአት ባለመኖሩ ከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ፤ እንዲሁም ብድር የሚሰበስብበትን ስርአት ባለማበጀቱ ሌላ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ሳይችል መቅረቱ ተገልጿል።

ታዲያ ከአሰራር ችግሮቹ ባሻገርም በኦሮሚያ፣ በሶማሌ እና አፋር ክልሎች የወሰዳቸውን የመስኖ ፕሮጀት ስራዎች በጊዜው አጠናቆ መስረከብ ባለመቻሉ ብሎም ፕሮጀክቶቹ በጅምር የቀሩ በመሆናቸው 1.ቢሊዮን ብር ማባከኑም ታውቐል።

ዋና ኦዲተሯ ተቋማቸው በ 2014 ዓም የተለያዩ የፌደራል ተቋማትን መመርመራቸውን ብሎም ግኝቶቹን በማስታወቅ እንዲወሰዱ ሲሉ የእርማት ምክረ ሃሳቦቻቸውንም አቅርበዋል።