ሩሲያ ኒዩክሌር የመታጠቅ አቅም ያላቸው ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ለቤላሩስ ለመስጠት ቃል ገባች

ኢስካንደር የተባለው ሚሳኤል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ኢስካንደር የተባለው የሚሳኤል ሥርዓት 500 ኪሎ ሜትር ድረስ መወንጨፍ ይችላል

ሩሲያ በሚቀጥሉት ወራት ኒዩክሌር የመታጠቅ አቅም ያላቸውን አጭር ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ለመተኮስ የሚያስችል ሥርዓት ወደ አጋሯ ቤላሩስ እንደምትልክ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቁ።

ፕሬዚደንቱ እንዳሉት ኢስካንድር- ኤም የተበላው ሥርዓት የባልስቲክ እና የክሩዝ ሚሳኤሎችን መተኮስ የሚያስችል ሲሆን እስከ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ኢላማዎችን መምታት ይችላል።

የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቱን ባለፈው የካቲት ወር ላይ በዩክሬን ላይ ወረራ ማወጃቸውን ተከትሎ በሩሲያና በምዕራባውያኑ መካከል ያለው ውጥረት ጨምሯል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ፑቲን ስለ ኒዩክሌር የጦር መሣሪያዎች ብዙ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ይህንን ንግግራቸውን አንዳንዶች የምዕራብ አገራት ጣልቃ እንዳይገቡ ለማስጠንቀቅ ያለመ ነው ብለውታል።

ፑቲን  የሩሲያ የወደብ ከተማ በሆነችው ሴንት ፒተርስበርግ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ከቤላሩስ ፕሬዚደንት ሉካሽንኮ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ሩሲያ የቤላሩስ ኤስዩ-25 የጦር አውሮፕላኖች የኒዩክሌር የጦር መሣሪያዎችን መያዝ እንዲችሉ ለማድረግ ትረዳለች ብለዋል።  

ፕሬዚደንት ፑቲን ከአቻቸው የቤላሩሱ ፕሬዚደንት አሌክሳንደር ሉካሸንኮ ጋር ባደረጉትና ቅዳሜ ዕለት በቴሌቪዥን በተላለፈው ስብሰባ ላይ “ ወስነናል። በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ለቤላሩስ ኢስካንደር- ኤም የተባለውን የሚሳኤል መተኮሻ ሥርዓት እናስረክባለን” ብለዋል።

መሣሪያዎቹን የማስረከብ ዝርዝር ሂደቱን በተመለከተ የሁለቱ አገራት መከላከያ ሚኒስትሮች እንደሚሰሩም ፕሬዚደንቱ አክለዋል።

ኢስካንደር ሚሳኤሎች የኔቶ አባል በሆኑት ሉትዌንያ እና ፖላንድ መካከል በምትገኘው የሩሲያ ባልቲክ ባህር ዳርቻዋ ካሊኒንግራድ ተሰማርተዋል።

ሁለቱ ፕሬዚደንቶች የሉትዌኒያ አንዳንድ እቃዎች ወደ ካሊኒንግራድ እንዳይጓዙ ለመከለካል ባደረገችው ውሳኔ ላይ የተወያዩ ሲሆን እርምጃው ሞስኮን አስቆጥቷል።

የቤላሩሱ ፕሬዚደንትም የሉትዌንያ እርምጃ “ የጦርነት አዋጅ እና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል።

ሉትዌንያ ግን እርምጃዋ ተፅዕኖ የሚያሳድረው ለወትሮው በወደቡ ከሚተላለፉ የሩሲያ ምርቶች መካከል አንድ በመቶ በሚሆነው ላይ  ነው ስትል ሩሲያ ካሊኒንግራድ እንቅስቃሴውን አግዳለች ስትል ያቀረበችውን ክስ አጣጥላለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እሁድ ዕለት ጠዋት በዩክሬን ኪዬቭ በርካታ ፍንዳታዎች መከሰታቸውን የከተማዋ ከንቲባ ቫይታሊ ክሊሽኮ ተናግረዋል።

“አምቡላንሶችና የነፍስ አድን ሰራተኞች በሥፍራው ይገኛሉ። በሁለት ሕንጻዎች ላይ የነፍስ ማዳንና ሰዎችን የማስወጣት ሥራ እየተከናወነ ነው “ ብለዋል ከንቲባው።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል በከተማ የሚገኘው የመኖሪያ ቤት ሕንጻ መመታቱን ዘግቧል።

ለሳምንታት ከባድ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ ዩክሬን የሩሲያ ኃይሎች ቅዳሜ ዕለት ምሥራቃዊ ከተማዋን ስቨሮዶንስክ “ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን” አስታውቃለች።

ይህ ማለት ሩሲያ የዩክሬንን ሰፊውን የኢንደስትሪ ግዛት፣ዶንባስን የሚፈጥሩትን ሉሃንስክ ክልል ሙሉ በሙሉ በሚቻል ደረጃ እንዲሁም አብዛኛውን ዶንስክ ክልል ተቆጣጥራለች ማለት ነው።  

የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ቅዳሜ ዕለት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፣ በሩሲያ የተያዙ ከተሞቻቸውን ለመመለስ ቃል ገብተዋል።

ሆኖም ከሩሲያ ጋር ያለው ጦርነት በስሜታዊነት አስቸጋሪ ደረጃ ላይ መድረሱንና ምን ያህል ድብደባዎች እና ኪሳራዎች እንደሚኖሩ እንደማያውቁ ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ ተናግረዋል።

አርብ ዕለት ምሽት ሩሲያ ኢላማዋ ወደሆኑት ሰሜንና ምዕራብ ዩክሬን አካባቢዎች የሚሳኤል ጥቃት ከፍታለች።

በዚህ ጥቃት በምዕራብ ኪዬቭ ሳርኒይ በተባለች ከተማ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች በፍርስራሽ ሥር ሳይቀበሩ እንዳልቀረ የአካባቢው ባለሥልጣን ተናግረዋል።

ዩክሬን የተወሰኑት ሮኬቶች የተተኮሱት ከቤላሩስ ነው ብላለች። ቤላሩስ ለሩሲያ የሎጂስቲክስ ድጋፍ እያደረገች ሲሆን ጦሯ ግን በይፋ በጦርነቱ ላይ አልተሳተፈም።

የዩክሬን የደህንነት አገልግሎት የሚሳኤል ጥቃቱ ሩሲያ ቤላሩስን ወደ ጦርነቱ ለማስገባት የምታደርገው ጥረት አካል ነው ብለዋል።

ሩሲያ ሴቬሮዶኔትስክን በቁጥጥር ሥር ማዋሏ የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በኔቶ ንግግር ካደረጉ በኋላ ለጂ7 ስብሰባ ወደ ጀርመን ከማቅናታቸው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ነው።

በቅርብ ወራት ውስጥ የምዕራቡ ዓለም ጥምረት ጭንቀትና ድካም ታይቶበታል።

ይሁን እንጂ ቅዳሜ ዕለት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ዩክሬን ጦርነቱን እንደምታሸንፍ ተናግረዋል።

“ አሁን በዩክሬን ተስፋ የምንቆርጥበት ሰዓት አይደለም” ብለዋል ቦሪስ ጆንሰን።

እሁድ እለት የኢንዶኔዥያ ፕሬዚደንት ጆኮ ዊዶዶ፣ የዩክሬንና የሩሲያ መሪዎች ንግግራቸውን እንደገና እንዲጀምሩ አሳስበዋል።

“ ጦርነት መቆም አለበት፤ የዓለም የምግብ አቅርቦት ሰንሰለትም ማንሰራራት አለበት” ብለዋል ፕሬዚደንት ጆኮ።