ከሕዝባቸው መሬት የወርቅ ማዕድን ማውጣትን በድሮን ‘የገቱት’ ተሟጋቾች

አሌክስ ሉሲታንቴ እና አሌክሳንድራ ናርቫዝ

የፎቶው ባለመብት, Goldman Environmental Prize

በኢኳዶር የቀደምት ሕዝቦች ጥንታዊ ግዛት ላይ የወርቅ ማዕድን የማውጣትን ተግባር የተቃወሙ ሁለት ተሟጋቾች ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ሽልማት አሸንፈዋል።

አሌክስ ሉሲታንቴ እና አሌክሳንድራ ናርቫዝ ይባላሉ ያሸነፉትም ሽልማት ስመ ጥር የሆነውን የጎልድማን ሽልማትን ነው።

ይህም ሽልማት ስር ነቀል የሆነ ለውጥን ለሚያመጡ ዘመቻዎች ወይም እንቅስቃሴዎች ዕውቅናን የሚሰጥ ነው።

በሕዝባቸው መሬት ላይ የሚደረገውን የማዕድን ቁፋሮና የማውጣት ሥራ በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በመጠቀም መረጃዎችን ሰብስበዋል።

ድሮኖችን በመጠቀም ያነሷቸም ምስሎችና ቪዲዮዎች 79 ሺህ ሄክታር የሆነው የደን ስፍራ ከማዕድን የማውጣት ሥራ እንዲጠበቅም ለማድረግ ሕጋዊ መረጃዎች ሆነው ቀርበዋል።

መረጃዎቹም ድላቸውን በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, Goldman Enviromental Prize

የ29 ዓመቱ አሌክስ ሉሲታንቴ እና የ32 ዓመቷ አሌክሳንድራ ናርቫዝ 1 ሺህ 200 አባላት ያሉት የቀደምት ሕዝቦች ከሆነው የኮፋን ማኅበረሰብ ነው ትውልዳቸው።

የኮፋን ማኅበረሰብ በኢኳዶር ደኖች ውስጥ ለዘመናት ኖረዋል። አሌክሳንድሪያ ‘ላ ጋርዲያ’ የተሰኘ አካባቢውን የሚጠብቁ 25 የበጎ ፈቃደኞች ቡድን መስራች እና የጥበቃ ቡድኑንም በመቀላቀል የመጀመሪያዋ ሴት ናት።

በአውሮፓውያኑ 2017 በአጓሪኮ ወንዝ ዳርቻ በመሬታቸው ላይ ማዕድን አውጪ ከባድ ማሽኖች ሲሰማሩም ለመጀመሪያ ጊዜ ያዩት የላ ጋርዲያ አባላት እንደነበሩ አሌክስ ሉሲታንቴ ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ምርመራ ስንጀምር የኢኳዶር መንግሥት ለበርካታ ኩባንያዎች 20 የማዕድን ማውጣት ፍቃድ መስጠቱን እና 32 ተጨማሪ ለማጽደቅ እየጠበቁ መሆናቸውን ደርሰንበታል" ብሏል።

የመብት ተሟጋቹና ጠበቃ መሆን የሚፈልገው ሉሲታንቴ የኮፋን ማኅበረሰብ ቅሬታቸውን ለባለሥልጣናቱ ቢያቀርቡም ምላሽ ባለመግኘታቸው ጉዳዩን በሕግ እልባት ለማግኘት መወሰናቸውንም ይናገራል።

ሉሲታንቴ እንደሚለው ማኅበረሰቡ በሰው አልባ አውሮፕላኖች ታግዞ ያነሳቸው የአየር ላይ ምስሎች እና በግዛታቸው ላይ የተደረገውን ወረራና ጣልቃ ገብነትንም ፎቶዎቹ በዝርዝር ማሳየት በመቻላቸው ለትግላቸው ወሳኝ ሚናን ነበረው።

ለአንድ ዓመት ያህልም ከዘለቀ የፍርድ ቤት ሙግት በኋላም ማኅበረሰቡ አስደናቂ ድል አስመዝግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Goldman Environmental Prize

በግዛታቸው የሚገኘው የሱኩምቢዮስ ፍርድ ቤት የኢኳዶር ባለሥልጣናት የማዕድን ፍቃዶችን በሕጋዊ መንገድ ለመስጠት የኮፋን ማኅበረሰብን አላሳወቁም፣ እንዲሁም ፍቃዳቸውንም አላገኙም ሲል ብይን አስተላልፏል።

ፍርድ ቤቱ በባለሥልጣናቱ የተሰጡ ነባር ፍቃዶችን በመሰረዝ እንዲሁም በመጠባበቅ ላይ ያሉ ፈቃዶችን ውድቅ በማድረግ ማዕድን የማውጣት ሥራው እንዲቆም አዟል።

የኢኳዶር መንግሥት ይግባኝ ማለቱን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ መሬቱ የኮፋን ማኅበረሰብ ቀደምት ግዛት መሆኑን እና በጤናማ አካባቢ መኖር እና ንጹህ ውሃ የማግኘት መብታቸው ተጥሷል በሚል የወሰነ ሲሆን ይህም ለማኅበረሰቡ ተጨማሪ ድልን አስገኝቷል።

አሌክሳንድራ ናርቫዝ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ውሳኔው መሠረታዊና ቁልፍ የሚባል ነው፣ ምክንያቱም “ግዛታችን፣ መሬታችን ሕይወታችን ነው” ትላለች።

“ይህንን ግዛት እናውቀዋለን፤ መሬታችን ነው። የምንተላለፍበት ነው። የተቀደሱ ቦታዎችን እናውቃለን፣ ለአደን የሚሆኑ፣ እንስሳት ለመብላት የሚመጡባቸውን ቦታዎች እናውቃለን። ስፍራው ሕይወት የተሞላ ነው፤ እናም ለእኛ ሁሉ ነገራችን ነው” ትላለች።

“የኮፋን ማኅበረሰብ ያለ መሬቱ፣ ያለ ግዛቱ ኮፋን አይደለም" ስትል የጥንት ግዛታቸው ለማኅበረሰቡ ያለውን ጠቀሜታ” ትናገራለች።

አሌክሳንድራ ናርቫዝ በመንግሥት ላይ ሕጋዊ ትግል ከመጀመሯ በፊት በማኅበረሰቧ ውስጥ ምን ያህል ቁርጠኛ መሆኗንና ለትግሉም የተሰጠች መሆኗን ማስመስከር ነበረባት።

“የጥበቃው አካል ወይም ላ ጋርዲያን ለመቀላቀል የመጀመሪያዋ ሴት መሆን በጣም ከባድ ነበር፤ መጀመሪያ ላይ ከወንዶችም ሆነ ከሴቶች ብዙ ትችቶች ደርሶብኛል” ትላለች።

“በእኛ ማኅበረሰብ በተለምዶ ሴቶች ልጆችን እና ቤትን በመንከባከብ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጋል። እናም

የፎቶው ባለመብት, Goldman Environmental Prize

የላ ጋርዲያን አባል መሆጀን እንደምፈልግ ስናገር ከፍተኛ ውዝግብን ፈጠረ” በማለት ታስረዳለች።

“ነገር ግን በቁርጠኝነት ይህን ማድረግ ያለብኝ ለራሴ ብቻ ሳይሆን ለሁለቱ ሴት ልጆቼ እና በማኅበረሰባችን ላሉ ሴቶች ሁሉ ነው አልኳቸው” ስትል የነበረውን ሁኔታ ትገልጻለች።

እናም በመጨረሻ በማኅበረሰቧ ውስጥ ያሉትን ጥርጣሬዎች እንዲወገዱ በማድረግና ሴቶች በባህሉ ውስጥ ያላቸው ዕውቀት ለላ ጋርዲያ ጠቃሚ መሆኑን ማሳመን ቻለች።

"ውሃ የምንቀዳው እኛ ነን፤ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ዕፅዋትን እና የአንገት ሃብሎችን ለመስራት ዘሮችን የምንሰበስበው ሴቶች ነን።  ስለዚህም ከመሬታችን፣ ከግዛታችን ጋር ጥልቅ ትስስር አለን” ትላለች።

“ዓለም ድምፃችንን ሊሰማ ይገባል። እያልንም ያለነው መሬታችንን በህይወታችን እንጠብቃለን!”

አሌክሳንድራ በቀድምት ሕዝቦች ጥበቃን ውስጥ ሴቶች እንዲሳተፉ ፈር ቀዳጅ በመሆን አምስት ተጨማሪ ሴቶች እንዲቀላቀሉ ምክንያት በመሆኗ ኩራት ይሰማታል።

ለሁለት ሴት ልጆቿ በቂ ጊዜ አልሰጠኋቸውም በሚል ጸጸት የጥበቃውን ሥራ ለማቆም በተቃረበችበት ወቅትም እንድትቀጥልበት ያበረቷቷት ልጆቿ እንደሆኑ ትናገራለች።

“እማዬ፣ ጥበቃ ሂጂ! እኛ ደህና ነን፣ እኛም እንዳንቺ መሆን እንፈልጋለን። ትምህርታችንን እንደጨረስን፣ የለ ጋርዲያ መለያ ለብሰን የአንቺን ፈለግ መከተል እንፈልጋለን አሉኝ። ጥንካሬ የሰጠኝም ይህ ነው” ትላለች።