ኬንያዊቷ ‘ሃሰተኛ ፖሊስ’ በቴሌቪዥን ከታየች በኋላ በቁጥጥር ስር ዋለች

ሞኒካ ዋማይታ ጊታ የተባለችው ተጠርጣሪ

የፎቶው ባለመብት, National Police Service

ኬንያዊቷ ግለሰብ በአንድ የቴሌቪዥን መድረክ ላይ ፖሊስ ነኝ በማለት ተወያይ ሆኗ መቅረቧን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ዋለች።

ፖሊስ ሃሰተኛ ፖሊስ ናት ሲል የፈረጃት ግለሰብ በኬንያ በመጪው ነሐሴ በሚደረገውም ምርጫ ለፓርላማ የምትወዳደር እጩ ናት።

 ሞኒካ ዋማይታ ጊታ የተባለችው ተጠርጣሪ በቴሌቪዥን ፕሮግራሙ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ሙሉ የፖሊስ መለዮ ለብሳ ነበር።

በፕሮግራሙ ላይ ተወያይ የነበረችው ሞኒካ ትናገረው የነበረው ሁኔታ አሳማኝነቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ተከትሎም ፖሊስ በአስቸኳይ ወደ ቴሌቪዥን ጣቢያው አቅንቷል።

ተጠርጣሪዋም ሆነ ኢኖሮ የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ፖሊሷ ሃሰተኛ ናት በሚል ከፖሊስ ለቀረበባት ክስ የሰጡት አስተያየት የለም።

“በአሁኑ ወቅት ፖሊስን በማስመሰል ለሰራችው ወንጀል የሚደረጉ ምርመራዎች ላይ በመርዳት ላይ ትገኛለች” በማለት ፖሊስ በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።

ፖሊስ እንደሚለው ግለሰቧ በኬንያ በመጪው ነሃሴ በሚደረገው ምርጫ ናይሮቢን በመወከል ለፓርላማ መቀመጫ እጩ ተወዳዳሪ መሆኗን አሳውቋል።

ፖሊስ በተጨማሪም የሚዲያ አካላት ለቃለ መጠይቅም ከመጋበዛቸው በፊት “ለወደፊቱ ተመሳሳይ ሁኔታዎችን ለማስወገድ” ፖሊስ ብለው የሚጋብዙዋቸው ግለሰቦች ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2013 ጆሹዋ ዋይጋንጆ የተባለ ግለሰብ ለአምስት አመታት ያህል የፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ነኝ በሚል በማስመሰል ተከሷል።

ግለሰቡ በነዚህ አመታት ውስጥ በሪፍት ቫሊ ግዛት የፖሊስ አባላትን ከስራ ማባረር እንዲሁም አዳዲስ ቅጥረኞችን መመልመሉ ተነግሯል።

ግለሰቡ በአውሮፓውያኑ 2020 በከፍተኛው ፍርድ ቤት በነጻ የተለቀቀ ሲሆን አቃቤ ህግ ብይኑን በመቃወም ይግባኝ ብሏል።