መዳን እየቻለ ለአካል ጉዳት የሚዳርገው የእግር መቆልመም

የእግር መቆልመም መምጫው መንስዔው አይታወቅም

የፎቶው ባለመብት, Hope Walks-Ethiopia

የምስሉ መግለጫ,

የእግር መቆልመም መምጫው መንስዔው አይታወቅም

የሔለን (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሟ ተቀይሯል) የእርግዝና ጊዜዋ ቀደም ካለው የተለየ አልነበሩም።

መደበኛ የህክምና ክትትሏን በሚገባ ተከታትላለች።

ሆስፒታል ደርሳም በሠላም ወንድ ልጅ ተገላግላገለች።

እኛ የልጁን ስም አቤል እያልን እንቀጥላለን።

ከወለደች በኋላም አሰፈላጊውን ሁሉን ነገር አጠናቃ ወደ ቤቷ ተመለሰች።

“የወለድኩት ሐኪም ቤት ነው። ማንም ምንም አላለኝም” ስትል ታሪኳን ትጀምራለች።

ቤት ስትደርስ ቤተሰብ ጎረቤት በዕልልታ ጠበቃት።

አዲስ የቤተሰብ አባል ስለመጣ ቤቱ በደስታ አየር ተሞልቷል።

እሷ መኝታ ክፍል ውስጥ ጨቅላውን ለማጠብ እየተሰናዳች ነው።

አቤልን በደንብ ያየችው ስታጥበው ነው።

“እግሩን አየሁት። ከዚያ በፊት እንደዚህ አይነት ነገር ፈጽሞ አይቼ አላውቅም ነበር” ትላለች።

‘ብዙ ነገር አይቻለሁ’ ለምትለው ሔለን የአቤል እግር የተቆለመመ መሆን ግራ ሆኖባታል።

“በጣም ነው የደነገጥኩት። ደጋግሜ እግሩን ልዘረጋው ሞከርኩ” ለውጥ የለም።

የእግር መቆልመም በእንግሊዘኛ ስሙ 'ክሌፍት ፉት' ይባላል። የአጥንት፣ የጅማት እና ተያያዥ ችግር ነው።

ችግሩ የሚታየው በወሊድ ወቅት ነው።

“በተፈጥሮ የሚመጣ ሲሆን እግርን ወደ ውስጥ እና ወደ ታች የሚቆለምም እና የሚያዞር ነው” ይላሉ በሙያ ፊዚዮቴራፒስት እና በሆፕ ዎክስ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ እንዳሻው አበራ።

የእግር መቆልመም በጨቅላ ህጻናት ላይ የሚከሰትበት ምክንያት አይታወቅም።

“ምናልባትም አንዳንዶች ከእርግዝና ጋር ያያይዙታል። ሌሎች ደግሞ እናትየው በእርግዝና ወቅት ወድቃ ሊሆን ይችላል ሲሉ ከምግብ ወይንም እንክብል ካለመወሰድም ጋር የሚያያዙትም አሉ” ቢሉም “ይህ ሃሰት ነው። መንስኤው አይታወቅም” ይላሉ አቶ እንዳሻው አበራ።

በዘር እንዳይባል ከትውልድ ትውልድ አይከሰትም። በመኖሪያ አካባቢ እንዳይባል በአንድ አካባቢ ብዙ ሰዎች ችግሩ አይገጥማቸውም።

ለዚህም ነው ምንክያቱ የማይታወቅ በተፈጥሮ የሚከሰት ነው የሚሉት አቶ እንዳሻው።

የእግር መቆልመም በአንደኛው እግር ላይ ብቻ ሊከሰት ይችላል። በብዛት ግን በሁለቱም እግር ላይ ያጋጥማል።

አቤል ግራ እግሩ ነው የተቆለመመው።

“አንደኛው እግሩ ደህና ነው። ሌላኛው ትክክል አይደለም” ትላለች ሔለን።

የተቆለመመው እግር፣ ልጁ እያደገ ሲሄድ መራመድ እስካለመቻል ያደርሰዋል።

አንዳንዶችም እየዳኹ ለመሄድ ይገደዳሉ።

እንቅስቃሴን ይገድባል። በኋላም ዘላቂ ከሆነ ችግር ጋር መኖር ይመጣል።

ያልተፈለጉ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ችግሮች ደግሞ ይከተላሉ።

“በትክክለኛው መንገድ እግራቸው ካደገ ልጆች ይለያል። መራመድም ሆነ መሮጥ ከባድ ይሆናል” ይላሉ አቶ እንዳሻው።

ይህም እንደማንኛውም የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች በእንቅስቃሴያቸው ላይ እንቅፋትን ማስከተሉ አይቀርም።

የጨቅላ ህጻናትን የእግር መቆልመም ምንም ዓይነት ጥንቃቄ በማድረግ መከላከል አይቻልም። ምክንያቱም የአፈጣጠር ችግር ነው።

ነገር ግን ችግሩ በእርግዛና ወቅት መታወቅ ይችላል።

በተለይም ‘በሁለተኛው ሩብ ዓመት የወሊድ ክትትል በአልትራሳውንድ የጽንሱ እግር’ ይታያል።

በዚህ ወቅት ችግሩን በመለየት ወላጆች ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ ይደረጋል።

በሥነ ልቦና እንዲዘጋጁ እንጂ ምንም የሚሰጥ ህክምና የለም።

በኢትዮጵያ ግን እዚህ ደረጃ ላይ አለመደረሱን አቶ እንዳሻው ይገልጻሉ።

የእግር መቆልመምን እንዳይፈጠር መከላከል አይቻልም። ከተወለዱ በኋላ በሚሰጥ ህክምና ግን ፍቱን መፍትሔ መስጠት ይቻላል።

ህክምናው ሙሉ ለመሉ ችግሩን የሚቀርፍ ነው።

ሔለን ጉዳዩን ለምታውቀው የህክምና ባለሙያ በፍጥነት አስታወቀች።

“በጣም ቀላል ነገር ነው። መዳን የሚችል ነው። አትደንግጪ አለኝ” ትላለች።

ሐኪም ቤት ስትደረስ ያየችውን አላመነችም።

“የእኔ ልጅ ችግር ብቻ ይመስለኝ ነበር” ስትል ታስታውሳለች።

“ከእኔም ልጅ በባሰ የተጎዱ በጣም ብዙ ልጆች አየሁኝ። ከእኔ በላይ ያዘኑ ሰዎች አየሁ። እንደዉም ለ’ነሱ አዘንኩኝ። እኔ ተጽናናሁ።“

“ሁለት እግራቸው ላይ ጉዳት ያለባቻው ልጆች ብዙ ነበሩ” ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Hope Walks- Ethiopia

የምስሉ መግለጫ,

በኢትዮጵያ በየአመቱ አምስት ሺህ የሚጠጉ ህጻናት ከእግር መቆልመም ጋር ይወለዳሉ

ለተቆለመመ እግር የሚሰጠው ህክምና

ህክምና ተጀመረ።

ሔለን ልጇ እንደሚድን ተነገራት። ከተመሳሳይ ችግር የዳኑ ልጆችንም ማየቷ ተስፋ ሰጣት።

አቤል ህክምና ሳይጀመር ተስፋውን አየች።

“ፖንሴቲ የህክምና ዘዴ ነው። ኮንሰርቫቲቭ የሚባል አይነት የህክምና ዘዴ ነው። ህክምናው ያለምንም ቀዶ ህክምና የሚከናወን እንደማለት ነው። ከወጪ አንጻርም ለሁሉም ተደራሽ በሆነ መልኩ የሚቀርብ ነው”  ይላሉ አቶ እንዳሻው።

ህክምናው በጄሶ እና በጫማ የሚደረግ ባለሁለት ደረጃ የማስተካከል ድጋፍ ነው።

በጄሶ ይጀመራል።

የተቆለመመውን እግር ቀጥ በማድረግ በጄሶ ያያዛል። ቀጥሎም ጅማት ማስተካከል ይከናወናል።

ህክምናው ከ5 እስከ 8 ሳምንታት ይሰጣል። ጄሶው በየሳምንቱ ይቀየራል።

በመጨረሻም አነስተኛ የቋንጃ ህክምና በመስጠት ይጠናቀቃል።

ቀጥሎ ወደ የአካል ድጋፍ ወይንም የጫማ ህክምና ያመራል።

የጫማ ህክምናው በጄሶ የተስተካከለውን እግር ‘ለመከላከል እና ለማስጠበቅ የሚሰጥ ነው።’

በጄሶ ብቻ የተሰጠው ህክምና አስተማማኝ አይደለም።

“ተመልሶ ችግሩ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ ነው” ይላሉ አቶ እንዳሻው።

ለዚሁ ሲባል የተሠራው ጫማ የዳነውን ‘ለማስጠበቅ እና ለመከላከል’ ይሠጣል።

አቤልም በዚህ መልኩ ህክምናውን አጠናቋል።

አቤል “እየዳኸ ቆይቶ ወንበር ይዞ መራመድ ጀመረ” ትላለች ሔለን።

ህክምናው በፍጥነት መጀመር አለበት። በመጀመሪያዎቹ 15 ቀናት ውስጥ መጀመር እንዳለበት ይመከራል። በፍጥነት እንዲድን በፍጥነት ህክምና ማግኘት።

ቀናት በረዘሙ ቁጥር ግን ውጤታማነቱ እየቀነሰ ይሄዳል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት የወሊድ ምጣኔ ከፍተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች የእግር መቆልመም ይጨምራል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ200 ሺህ በላይ ልጆች ከእግር መቆልመም ጋር ይወለዳሉ።

80 በመቶው ህጻናት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚወለዱ ናቸው።

የዚህ ምክንያት ምጣኔ ሃብት አይደለም። በእነዚህ አገራtእ የውልደት ምጣኔ ከፍ ያለ መሆኑ ነው።

ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ደግሞ የውልደት መጠን ከፍ ሲል የእግር መቆልመም የመከሰት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው።

በዓመት በህይወት ከሚወለዱ 800 ህጻናት በአንዱ ላይም ችግሩ ይከሰታል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ አምስት ሺህ የሚጠጉ ህጻናት ከእግር መቆልመም ጋር ይወለዳሉ።

ይህ አሃዝ ከናይጄሪያ ቀጥሎ በአፍሪካ ደረጃ ሁለተኛ የሚባለው ነው።  

ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚዎቹ ናቸው።

የእግር መቆልመም የአፈጣጠር ችግር ነው። ይህን ያለ ምክንያት አይደለም የምንደጋግመው።

የእግር መቆልመም ሲከሰት ለቅሶ፣ ፍርሃት፣ መደንገጥ የሚፈጠርባቸው ብዙ ናቸው።

“ችግሩን ሲከሰት ‘ፈጣሪን ምን አድርጌ ነው? ተረግሜያለሁ እንዴ?’ የሚሉ አሉ። ልጆቹንም የሚደብቁ ጥቂት አይደሉም። ከእምነት ጋር የሚያይዙትም አሉ። በዚህ ምክንያት ወደ ህክምና ተቋማት መውሰድ ይፈራሉ። ‘ወደ ተቋማት ከመጣሁ ይጠቋቆሙብኛል፣ ያወሩብኛል’ የሚል ፍርሃት አለ” ይላሉ አቶ እንዳሻው።

ሔለን መጀመሪያ ደንግጣ እንደነበር ገልጸናል።

ይህ ግን የእሷ ብቻ አይደለም።

“ቤት መጥተው ልጄ ላይ ስለገጠመኝ ችግር የምነግራቸው ሰዎችም በጣም ነው የሚደነግጡት” ትላለች።

“በተለይም ጄሶ ከታሰረለት በኋላ ደንግጠው ያስደነግጣሉ። ወይም ሊያቅፉት ብለው እግሩን ያዩና ‘ምን ሆኖ ነው?’ ይላሉ። ‘ምንም’ እላለሁ። አንዳንዴም ሲያነሱት ስለሚከብዳቸው ‘ስፖርት እየሠራ ነው’ እላቸዋለሁ።”

የፎቶው ባለመብት, Hope Walks-Ethiopia

የምስሉ መግለጫ,

የጫማ ህክምና

“ከህክምናው ጎን ለጎን ማለት ነው። ይህን ለመቅረፍ በሰዎች አስተሳሰብ ላይ እየሠራን ነው” ይላሉ አቶ እንዳሻው።

ሆፕ ዎክስ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ በዋነኝነት በእግር መቆልመም ላይ ይሠራል።

በዋናነት በአፍሪካ እና በእስያ የሚሠራ ሲሆን ችግሩን በፍጥነት በመለየት ህክምናውን ይሰጣል። በዚህም ችግሩን ከቤተሰብ፣ ከልጁ እና ከአገር ጫንቃ ላይ ለማላቀቅ ያለመ ነው።

ድርጅቱ ላለፉት 13 ዓመታት ሠርቷል።

ህክምናው ከ2009 እስከ 2019 በኪዩር ሆስፒታል ሲሰጥ ቆይቷል። ላለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ ፈቃድ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

አሁን ከ48 መንግሥት የህክምና ተቋማት ጋር መሥራት ጀምሯል። በሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮችም ይንቀሳቀሳል።  

የፎቶው ባለመብት, Hope Walks-Ethiopia

የምስሉ መግለጫ,

ከህክምና በፊት እና በኋላ

ለህክምና ተቋማቱ የሥልጠና፣ የህክምና ግብዓት አቅርቦት እና ሌሎችንም ድጋፎች በማድረግ ላይ ይገኛል።

“አንዳንድ ሰዎች ከመጀሪያው ህክምና በኋላ ይጠፋሉ። እኛ ጠንካራ ልጆችን ለማፍራት እንፈልጋለን። የሚማሩ ራሳቸውን የሚችሉ እና ሃገር ተረካቢ ልጆችን ለመፍጠር እንሠራለን” ይላሉ አቶ እንዳሻው።

ህክምናውም እየተስፋፋ ነው። አሁን ህክምናውን በ48 ክሊኒኮች በመስጠት ሽፋኑን 50 በመቶ አድርሷል።

ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ 56 በመቶ የማድረስ ዓላማ ተይዟል።

በ2030 ደግሞ ችግሩን ታሪክ ማድረግ ነው ዓላማው።

ሔለን ልጇ አቤል ቆሞ ይሄዳል የሚል እምነት አልነበራትም።

“ህክምናውን አግኝቶም ጊዜውን ጠብቆ መስተካከል እስኪጀምር ድረስ [በእግሩ ቆሞ መሄድ ይችላል ብዬ] አላመንኩም ነበር።”

“ጫማው እየጎተተው ወደኋላ ስለሚድኽ አስፈርቶኝ ነበር” ትላለች።

ዕድሜ ለህክምናው እና ለሔለን በፍጥነት ወደ ሐኪም ቤት መሄድ ይግባቸውና አቤል ጠንካራ እና ደስተኛ ልጅ ሆኗል።

እንደልቡ ይራመዳል ይሮጣል።