ታዋቂው ሙዚቀኛ አር ኬሊ ለዓመታት በፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት የ30 ዓመት እስር ተፈረደበት

አርኬሊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታዋቂው አሜሪካዊ ሙዚቀኛ አር ኬሊ ታዋቂነቱን በመጠቀም ታዳጊዎችና ሴቶች ላይ ለዓመታት በፈጸመው ወሲባዊ  ጥቃት የ30 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

አርኤንድ ቢ በተሰኘው የሙዚቃ ስልት ከፍተኛ የዝና ማማ ላይ መውጣት የቻለው የ55 ዓመቱ ሙዚቀኛ መስከረም ወር ላይ ነበር በወሲብ ዝውውር ወንጀልና በማጭበርበር የተከሰሰው።

ለበርካታ ዓመታት ያህል በርካታ ውንጀላዎችን ቢያስተናግድም “ለሰዎች ሰቆቃ ምንም አይነት ሃዘኔታ አላሳየም ግድየለሽም ነበር” ሲሉ ዳኛው ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።

የሮበርስ ሲይልቨስተር ኬሊ ወይም በቅፅል ስሙ አርኬሊ ጠበቆችም በውሳኔው ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።

ብይኑ ከመተላለፉ በፊት በሙዚቀኛው ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በአር ኬሊ ላይ ለመመስከር ፍርድ ቤት ተገኝተው ነበር።

አንጄላ የተሰኘች አንዲት ሴት አር ኬሊን "ፓይድ ፓይፐር" ስትል በመጥራት አዳዲስ ጥቃቶችን በተደጋጋሚ በማድረስ “በክፋት የደረጀ” ስትል ወርፋዋለች። ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሰ ሴቶች ደግሞ መንፈሳቸውን እንደሰበረው መስክረዋል።

“እንዲሰማኝ ባደረግከው ስሜት መሞትን እንድመኝ አድርገኸኛል ብላለች” አንዷ ለፍርድ ቤቱ።

የእስር ቤት ካኪ መለዮ እና ጥቁር መነጽር አጥልቆ ችሎት የተገኘው አርኬሊ ለመናገርም ሆነ ብይኑም ሲተላለፍ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም።

የአሜሪካ ዳኛ አን ዶኔሊ ሙዚቀኛው ወሲብን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ተጠቂዎች ሊናገሩት የማይችሉትን አጸያፊ ነገሮችን እንዲፈፅሙ አስገድዷቸዋል ብለዋል። አንዳንዶቹም ላይ በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች እንዲይዛቸው ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

"ፍቅር ባርነት እና ሁከት መሆኑን አስተምረሃቸዋል" ብለዋል ዳኛዋ።

ፍርድ ቤቱ አር ኬሊ የሚታወቅባቸውን እንደ ‘አይ ቢሊቭ አይ ካን ፍላይ’፣ ‘ኢግኒሽን’ በመሳሰሉ ተወዳጅ ሙዚቃዎቹ ያተረፈውን ተፅእኖ በመጠቀም ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ታዳጊዎችንና ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ለመፈጸም እንደ መስህብ ተጠቅሞበታል ብሏል።

ስድስት ሳምንታት በወሰደው የብሩክሊን የፍርድ ሂደት ሙዚቀኛው በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ሴቶችን እንዴት ያዘዋውር እንደነበር ሰምቷል።

ይህንንም ለማከናወን የሙዚቀኛው ሥራ አስኪያጆች፣ ጠባቂዎችና ሌሎች አጃቢዎች አግዘውታል ተብሏል። በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 1994 አር ኬሊ የ15 ዓመት ታዳጊ የነበረችውን ዘፋኝ አሊያህን ለማግባት በሕገ ወጥ መንገድ ዕድሜዋን የሚያጭበረብር ሰነድ ማውጣቷም ተነግሯል።

ዘፋኟ አር ኬሊን ካገባች ከሰባት ዓመታት በኋላ በአውሮፕላን አደጋ ህይወቷ ማለፉ ይታወሳል።