ሱዳን ከትንኮሳ በዘለለ የያዘችው ተጨማሪ የኢትዮጵያ ግዛት የለም - መንግሥት

ካርታ

ሱዳን እና ኢትዮጵያ በሚወዛገቡበት አልፋሽጋ ድንበር ላይ የደረሰ ጥቃትም ሆነ ተጨማሪ የያዙት ቦታ እንደሌለ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ለቢቢሲ ገለጹ።

የሱዳን ጦር በድንበር ግዛቶች ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ በከባድ መሳሪያና በታገዘና የአየር ጥቃት ከትናንት ጀምሮ ማድረሱ ቢዘገብም አቶ ከበደ ሐሰተኛ መረጃ ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

“በእርግጥ ትንኮሳዎች አሉ፤ ከቀናት በፊትም የተፈጸመው ትንኮሳ በሱዳን ኃይል ነው የተጀመረው። በዚህም የአካባቢው ሚሊሻ እርምጃ ወስዶባቸዋል” የሚሉት ባለሥልጣኑ ለደረሰውም የሕይወት መጥፋት መንግሥት ማዘኑን መግለጹን አስታውሰዋል።

አቶ ከበደ በድንበር አካባቢ ወደሚገኙት መንደሮች ከባድ መሳሪያ መተኮስና አንዳንድ ትንኮሳዎች ከሱዳን በኩል እንዳሉ አመልክተው፣ የጠፋ የሰው ሕይወትም ሆነ የወደመ ንብረት የለም በማለት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በኩል የተሰራጫው ዜና ሐሰት ነው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የሱዳን ጦር በድንበር ስፍራዎች ላይ በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ጥቃት እየፈጸመ እንደሆነም ሮይተርስ አንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣንን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

በዚሁ ዘገባው ላይ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሚያወዛግባት ድንበር አቅራቢያ ይገኛል ያለውን ጃባል ካላ አል ላባን የተሰኘ ቦታን መቆጣጠሯን አሳውቃለች ብሏል።

የሱዳን ጦር በከባድ መሳሪያና በአየር በመታገዝ የተጠቀሰውን ቦታ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ሮይተርስ የሱዳንን ወታደራዊ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

በአልፋሽጋ ግዛት ውስጥ የሚገኘው ጃባል ካላ አል ላባን በኢትዮጵያ ጦር ቁጥጥር ስር የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በሱዳን ጦር ቁጥጥር ስር መሆኑንንም የዐይን እማኞች እንደነገሩት የዜና ወኪሉ ገልጿል።

ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው ይህንን ውድቅ በማድረግ፣ ሱዳኖች ተጨማሪ የተቆጣሩት የኢትዮጵያ መሬት የለም ብለዋል።

ከሱዳን በኩል የሚሰነዘረውን ጥቃትን በተመለከተ ቢቢሲ ያናገራቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን የምዕራብ አርማጨሆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ አያና እንዳሉት፣ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ከሚተኮሰው ከባድ መሳሪያ ውጪ የሱዳን ጦር ባለፉት ቀናት የያዘው ተጨማሪ ቦታ እንደሌለ ገልጸዋል።

ሱዳን ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር የነበሩትን ሰፊ ለም የእርሻ መሬቶችን የያዘውን የአልፋሽጋ አካባቢን መቆጣጠሯ ይታወሳል።

ከአንድ ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ሱዳን ግዛቷን ወርራ ተቆጣጥራለች በማለት አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ከእነዚህ ግዛቶች ሱዳን ጦሯን እንድታስወጣ በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ሱዳን ግን የቀደሙ ግዛቶቼን ነው ያስመለስኩት በሚል እንደማትወጣ አስታውቃለች።

ከቀናት በፊት የሱዳን ጦር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጹት ከሱዳን ግዛት የተወሰዱ ወታደሮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ከተወሰዱ በኋላ ተገድለዋል እንዲሁም አስከሬናቸው በአደባባይ እንዲታይ ተደርጓል ሲል ክስ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሱዳን ምርኮኞችን በአደባባይ ገድሏል በሚል የሱዳን ጦር ያወጣውን መግለጫ መሰረት የሌለው ነው ሲል ውድቅ አድርጎታል።

የመከላከያ ሠራዊት ግጭቱ በተነሳበት ስፍራ እንዳልነበርና የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቆ ገብቷል ያለው የሱዳን ኃይል ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር ተጋጭቷል ሲል ጦሩ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ሚኒስትር ዲኤታው በበኩላቸው ከቀናት በፊት የሱዳን ጦር የህወሓት ታጣቂዎችን ይዞ ለመግባትና በእነሱ ድጋፍም ለመግባት ተሞክሯል ብለዋል። በዚህም የአካባቢው ሚሊሻዎች መከላከላቸውንና ጥቃትም እንደተፈጸመባቸው አክለው ገልጸዋል።

ይህን ክስ አስመልክቶ የትግራይ ክልል ባወጣው መግለጫ “አገዛዙ በአገሪቱ ውሰጥ እየሆነ ካለውን አሳፋሪ ሁኔታ ለመሸፋፈን ትግራይን እንደ መጠቀሚያ አድርጓታል። የሱዳን ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በገቡበት ወቅት የትግራይ ኃይሎች ተቀላቅለዋል የሚለው የሰሞኑ ውንጀላም የአገዛዙን ቅዠት የሚያሳይ ነው” ብሏል።

በሁለቱ አገራት መካከል ከተከሰተው ውጥረት ጋር ተያይዞ የአፍሪካ ኅብረት ፍጥጫው ወደ ወታደራዊ ግጭት እንዳያመራም ጥሪ አቅርቧል።

“ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ባሉ ችግሮች ላይ አፍሪካዊ መፍትሔን ቅድሚያ ትሰጣለች። ለአፍሪካ ኅብረትም ትልቅ ክብር እንዲሁም ታሪካዊ ትስስር አላት። ለአፍሪካውያንና ለአፍሪካ ተቋማት ትልቅ ክብር አለን እንደ አገርም የምንከተለውም መርኅ ነው” ብለዋል አቶ ከበደ።

አክለውም “ከሱዳን ሕዝብ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረንና በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን ለመፍታት ነው ጥረት እያደረግን ያለነው” ሲሉ የሚያስረዱት ሚኒስትር ዲኤታው የመንግሥታቸው አቋም እንዳልተቀየረም ይናገራሉ።

ከሱዳን መንግሥት ጋር ለመነጋገር መንግሥት እያደረገው ያለው ጥረት እንዳለ ከቢቢሲ የተጠየቁት ሚኒስትሩ መንግሥት ችግሮችን በመነጋገር ለመፍታት በተደጋጋሚ ፍላጎቱን መግለጹን አስረድተዋል።

“የኢትዮጵያ መንግሥት ከሱዳን ሕዝብ ጋር ምንም አይነት ግጭት ውስጥ መግባት አይፈልግም። ሰላም የመጀመሪያ አማራጩ አድርጓል። በተለያዩ መንገዶች ግንኙነቶች ነበሩ” ብለዋል።

የድንበር ግጭት ሲነሳ እንዴት መፈታት እንዳለበት ቀደም ብለው ተስማምተውበት የነበረ ጉዳይ መኖሩን አቶ ከበደ ጠቅሰው ከዚያ ያለፈ የተለየ ነገር የለም ብለዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ የሰላም አማራጭን በዋነኝነት ብታስቀምጥም “ሰላም ስለተፈለገ ብቻ አይመጣም። በአንድ ወገን ብቻ አይረጋገጥም። እኛ ከዚያ አልፎ የሚመጣውን ለመመከትና የአገሪቷን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በቂ ቁመናና ዝግጅት አለን” ብለዋል።

አክለውም “ዝም ብሎ ኢትዮጵያን ገብቶ እንደፈለጉ አድርጎ የሚወጣበት አጋጣሚ አይኖርም። የሕዝቦቿን ደኅንነት ለማረጋገጥ ማንኛውንም እርምጃ በመውሰድ ራሳችንን የመከላከል አቅሙ አለን” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ እና በሱዳን ኃይሎች መካከል ግጭቶች ባለፉት አስርት ዓመታት የተለመደ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ግን እየተባባሰ መጥቷል።

በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አገራት በጋራ ድንበራቸው አቅራቢያ ባለው አል ፋሻጋ ለም የእርሻ ቦታ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ውጥረት ነግሷል።

በአውሮፓውያኑ 2008 በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመ ስምምነት ቢኖርም የሁለቱን አገራት ግጭት ማስቆም አልቻለም ።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን በአባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይም ውዝግብ ውስጥ ናቸው።