በአሜሪካ ፅንስ የማቋረጥ መብት በመሻሩ ክሊኒኮች እየተዘጉ ነው

ውሳኔውን ካሳለፈው ከአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውጪ የተሰበሰቡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ውሳኔውን ካሳለፈው ከአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውጪ የተሰበሰቡ ሰዎች

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፅንስ ማቋረጥ የሚፈቅደውን ሕግ መሻሩን ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የፅንስ ማቋረጥ ክሊኒኮች እየተዘጉ ይገኛሉ።

ፍርድ ቤቱ ላለፉት 50 ዓመታት ፅንስ ማቋረጥን የሚፈቅደውን 'ሮው ቪ ዌድ' የተሰኘውን የሕገ መንግሥት አንቀጽ መቀልበሱ ታውቋል።

ይህ ማለት ከአሜሪካ ግዛቶች ግማሹ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትለው ፅንስ ማቋረጥን የሚከለክል ሕግ ያጸድቃሉ ማለት ነው።

13 ግዛቶች አሁን ፅንስ ማቋረጥን ሕገ ወጥ አድርገዋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ውሳኔውን “ቀይ ስህተት” ብለውታል።

በመላው አሜሪካ ውሳኔውን የሚቃወሙ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።

ፅንስ ማቋረጥ ሕጋዊ እንዲሆን በሚጠይቁ የፊኒክስ እና የአሪዞና ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።

በሎስ አንጀለስ ተቃዋሚዎች አውራ ጎዳና ዘግተው ድምጻቸውን አሰምተዋል።

“ይህ መጥፎ ዜና ልባችንን ሰብሮታል”

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማሳወቁን ተከትሎ በአርካንሳስ የሚገኝ የፅንስ ማቋረጥ ክሊኒክ ወዲያውኑ ተዘግቷል።

የክሊኒኩ ሠራተኞች ለሴቶች እየደወሉ የፅንስ ማቋረጥ ቀጠሯቸው መሰረዙን ሲገልጹ ለቅሶ ይሰማም ነበር።

ነርስ አሽሊ ሀንት “ይህ መጥፎ ዜና ልባችንን ሰብሮታል። ሮው ቪ ዌድ ሕገ ደንብ ተሰርዟል ብሎ ለሴት ደንበኞቻችን መንገር ያማል” ብላለች።

አርካንሳስ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሕጉን ሲሽር በቀጥታ የግዛቲቱን ሕግም ከሻሩት መካከል ትጠቀሳለች።

ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጠው ክሊኒክ ሲዘጋ፣ ታካሚዎችን በተቃዋሚዎች መካከል አጅበው ከወጡት ነርሶች አንዷ የሆነችው ሚስ ካረን “ይቺ አገር ስለሰዎች ግድ ይሰጣታል ብዬ አምን ነበር። የሴቶችን መብት እናከብራለን ብዬም ጠብቄ ነበር” ብላለች።

በሌላ በኩል የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ደግፈው ሰልፍ የወጡም በየአካባቢው ታይተዋል።

ከውሳኔው በኋላ ያልተዘጋ አንድ ክሊኒክ አቅራቢያ የነበረ ሰልፈኛ “ይህንን የሐጥያት ስፍራ ለቃችው ሂዱ። ይህ ቦታ እርጉም ነው” እያለ በአካባቢው ያሉ ሰዎችን ሲዘልፍ ነበር።

ኒው ኦርሊንስ እና ሉዊዚያና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎው ወዲያውኑ ፅንስ ማቋረጥን የከለከሉ ግዛቶች ናቸው።

'ዊሜንስ ኸልዝ ኬር ሴንተር' የተባለው እና በግዛቱ ከሦስት የፅንስ ማቋረጥ ክሊኒኮች አንዱ የሆነው ማዕከል ተዘግቶ ሠራተኞቹን በትኗል።

በማዕከሉ ቢቢሲ ያነጋገራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ሊንዳ ኮቸር በሕጋዊ መንገድ ፅንስ ማቋረጥ ከተከለከለ፣ “ሃብታም ሴቶች አሁንም ቢሆን ፅንስ ማቋረጥ ይችላሉ። ድሃ ሴቶች ግን በየጎዳናው ይወድቃሉ” ብላለች።

በተቃራኒው ፅንስ ማቋረጥን የሚነቅፈው ፓስተር ቢል ሻንክስ “ዛሬ የደስታ ቀን ነው” ብሏል።

የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጠው 'ፕላንድ ፓረንትሁድ' እንዳለው፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ወደ 36 ሚሊዮን ገደማ ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሴቶች ፅንስ የማቋረጥ መብታቸውን ያጣሉ።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ የተለያዩ ግዛቶች ፅንስ ማቋረጥን የሚከለክሉ ሕጎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ውሳኔዎችን እያሳለፉ ነው። ከእነዚህም መካከል፦

  • ኬንተኪ፣ ሉዊዚያና፣ አርካንሳስ፣ ሳውዝ ዳኮታ፣ ሚዙሪ፣ ኦክላሆማ እና አላባማ ግዛቶች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትለው ዕገዳውን የሚተገብሩ ግዛቶች ናቸው።
  • ሚሲሲፒ እና ኖርዝ ዳኮታ ውሳኔውን የሚያጸድቁት የዐቃቤ ሕግ ይሁንታ ከተገኘ በኋላ ነው።
  • ዋዮሚንግ በአምስት ቀናት ውስጥ ፅንስ ማቋረጥን ስታገድ፣ የዩታህ ውሳኔ በሕግ አውጪ ምክር ቤት ይታያል።
  • አይዳሆ፣ ቴኒሲ እና ቴክሳስ በ30 ቀናት ውስጥ ዕገዳውን ይተገብራሉ።

ዋሽንግተን በሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅራቢያ የተገኙ የፅንስ ማቋረጥ መታገድ ደጋፊዎች ደስታቸውን ገልጸዋል። ውሳኔውን የሚነቅፉ ደግሞ በመላው አሜሪካ ከ50 በላይ ከተሞች ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ ያካሂዳሉ።

ፒው የተባለ ተቋም በሠራው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ 61 በመቶ አሜሪካውያን ጎልማሶች ፅንስ ማቋረጥ ሁልጊዜ ወይም አብዛኛውን ጊዜ በሕግ መፈቀድ አለበት ብለው ያምናሉ።

37 በመቶ ደግሞ ፅንስ ማቋረጥ ሁልጊዜ ወይም አብዛኛውን ጊዜ መታገድ አለበት የሚል አቋም ያራምዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“ያልተወለደ ልጅም ሰው እንደሆነ ያሳየ ውሳኔ ነው”

በቴክሳሷ ሳን አንቶኒዮ ከተማ ፅንስ ማቋረጥን የምትነቅፈው ተሟጋች ቴር ሀርዲንግ “የሁሉም ሰው ሕይወት ሊጠበቅ ይገባል” ብላለች ለቢቢሲ።

ቴር ሴቶች የሚወልዱበት ማዕከል ያላት ሲሆን፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ “ያልተወለደ ልጅም ሰው እንደሆነ ያሳየ ነው” ብላች።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ “የሴቶችን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ሲሉ ተችተዋል።

“ውሳኔው የአክራሪ አስተሳሰብ ውጤት ነው። በጣም አሳዛኝና የተሳሳተ ውሳኔ ነው” ብለዋል።

ፅንስ ማቋረጥ ወደሚፈቀድባቸው ግዛቶች ተጉዘው ፅንስ የሚያቋርጡ ሴቶች ክልከላ እንዳይጣልባቸው እንደሚሠሩ ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።

እስከ 10 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ፅንስ ለማቋረጥ የሚውል መድኃኒት እንዲሁም እርግዝና መከላከያ መድኃኒት አቅርቦት ዘላቂነት እንደሚኖረውም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትላንቱ ውሳኔ ምን ማለት ነው?

ትላንት ሰኔ 17 የተላለፈው የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ፣ መደበኛውን የፍርድ ቤቱን አካሄድ የለወጠ እንደመሆኑ፣ በአገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

የካሊፎርንያ፣ ዋሽንግተን እና ኦሪገን ግዛቶች ከየትኛውም ግዛት ለሚሄዱ ሴቶች የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

በፔንሲልቬንያ፣ በሚችጋን እና በዊስኮንሰን ግዛቶ ፅንስ ማቋረጥን የሚደግፉም የሚቃወሙም ሰዎች ቁጥር ተቀራራቢ ስለሆነ፣ ውሳኔው የሚለየው በምርጫ ይሆናል።

በሌሎች ግዛቶች ደግሞ የሕግ ክርክሮች ይጠበቃሉ።

አከራካሪ ከሚሆኑ ነጥቦች መካከል ፅንስ ለማቋረጥ ከአንድ ግዛት ወደ ሌላው መሄድ ይፈቀዳል? ፅንስ ማቋረጫ መድኃኒት በፖስታ ማስላክ ይቻላል? የሚሉት ይጠቀሳሉ።

አሁን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ የተነሳው 'ሮው ቪ ዌድ' በመባል የሚታወቀው ሕግ ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት የፅንስ ማቋረጥ መብት እንዲከበር አድረጎ ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሮው ቪ ዌድ ምንድን ነው?

ሮው ቨርሰስ ዌድ (ሮው ቪ ዌድ) እአአ በ1973 በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበ የሕግ ክርክር ነበር።

በሰባት ድምጽ ድጋፍ እና በሁለት ተቃውሞ፣ ፅንስ ማቋረጥ በሕገ መንግሥቱ እንዲፈቀድ የተወሰነበት ነው።

ይህ ሕግ አሜሪካውያን ሴቶች በመጀመሪያዎቹ የእርግዝና ሦስት ወራት ውስጥ ፅንስ ማቋረጥ እንደሚችሉ ይደነግጋል።

በሁለተኛው ዙር የእርግዝና ወቅት (ከሦስተኛው ወር በኋላ) ፅንስ ማቋረጥ ሲገደብ፣ በሦስተኛው ዙር የእርግዝና ወራት ደግሞ ፅንስ ማቋረጥ ተከልክሏል።

ይህ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ፅንስ ማቋረጥን የሚከለክሉ ድንጋጌዎች ቢያንስ በአሥር የአሜሪካ ግዛቶች ተላልፈዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከሰሞኑ ዶብስ ቪ ጃክሰን ውመንስ ኸልስ ኦርጋናይዜሸን ክርክርን ሲመለከት ቆይቷል።

ይህ ክርክር ሚሲሲፒ ከ15 ሳምንታት እርግዝና በኋላ ፅንስ ማስወረድን መከልከሏን በመቃወም ነበር የተካሄደው።

የወግ አጥባቂዎች ቁጥር ከፍ ያለበት ፍርደ ቤቱ ግን የሚሲሲፒን ውሳኔ አጽንቷል።

ውሳኔውን የደገፉት ዳኞች ሳሙኤል አሊቶ፣ ክለራንስ ቶማስ፣ ኒል ጎርሹች፣ በርት ካቫናህ እና ኤሚ ኮኒ ቤሬት ናቸው።

ውሳኔውን የነቀፉት ዳኞች ደግሞ ስቴፈን ብሬየር፣ ሶንያ ሶቶሜር እና ኤለና ካገን ናቸው።

ሦስቱ ዳኞች “ውሳኔውን የነቀፍነው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ሴቶች ፅንስ የማቋረጥ መብታቸው በሕገ መንግሥቱ እንዲከበር ስንል ነው” ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሮው ቪ ዌድን መሻሩ ስለ ሌሎች ውሳኔዎች ዕጣ ፈንታም ጥያቄ አጭሯል።

ከእነዚህ መካከል ‘ጊስዎልድ፣ ሎረንስ እና ኦበርጌፍል’ የተባሉት ይጠቀሳሉ።

ውሳኔዎቹ የእርግዝና መከላከያ እና የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎችን የመጋባት መብት በተመለከተ በፍርድ ቤቱ አወንታዊ ብይን የተሰጠባቸው ናቸው።