የአፍሪካ ቀንድን ለማረጋጋት ተነሳሽነት የወሰደችው ቻይና

ቻይና በአፍሪካ ቀንድ የተፈጠረውን አለመረጋጋት፥ የፀጥታ ተግዳሮቶችና ግጭቶችን ለመፍታት ያለመ የአካባቢው ኮንፈረንስ አዲስ አበባ ውስጥ አካሄዳለች።

የፎቶው ባለመብት, FBC

ቻይና በአፍሪካ ቀንድ የተፈጠረውን አለመረጋጋት፣ የፀጥታ ተግዳሮቶችና ግጭቶችን ለመፍታት ያለመ ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ አካሄዳለች።

ከሰኔ 13 እና 14/2014 ዓ.ም. በተካሄደው “የቻይና-አፍሪካ ቀንድየመልካም አስተዳደርና ልማት አንደኛ ኮንፈረንስ” ላይ የቻይና፣ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የኬንያ፣ የኡጋንዳ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የጂቡቲ እና የሶማሊያ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ኤርትራ ግን ኮንፈረንሱ ላይ አልተሳተፈችም።

ለምን እንዳልተሳተፈች በውል የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ከአምስት ወራት በፊት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርትራን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

የኮንፈረንሱ ውጤት ምን ነበር?

በመጀምሪያው ኮንፈረንስ የተሳተፉ አገራት ተወካዮች ምክትል ሚኒስትሮች እና አምባሳደሮች እንደነበሩ በወጣው የጋራ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

በስብሰባው ማለቂያ ይፋ የተደረገው ባለ 12 ነጥቦች ሰነድ "ዘላቂ ሰላም፣ የጦርነት የተወገደበት የአፍሪካ ቀንድን ለመገንባት" ያላቸውን ራዕይ በመግለፅ "በአካባቢው ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ በጋራ ለመስራት" መስማማታቸውን አመልክቷል።

“ተሳታፊ ወገኖች ያላቸውን ፖለቲካዊ መተማመን ለማጠናከር፣ በቀጠናው ያሉ አገራት ያላቸውን ትስስር ለማሻሻልና ከፍ ያለ የጋራ ስምምነት ለማጠናከር ሁሉም ለመወያየት ዝግጁ” እንደሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል።

“ከፍ ያለ የጋራ ስምምነት” መቼና በምን ደረጃ እንደሚካሄድ ግን ተሳታፊዎቹ አላብራሩም።

በዚህ ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የሆኑት አገራት “ደካማ” ነው በሚል ትችት የሚቀርብበት ኢጋድ አባላት ናቸው።

“የአገራት ዲሞክራሲ፣ ሰላም፣ መረጋጋትና ልማት በማምጣት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ሁላችንም እናውቃለን” ያለው መግለጫ “ተሳታፊ ወገኖች ያላቸው የፆታ፣ የዘር እና የፖለቲካ አመለካከት ሳይገድባቸው ሁሉም የቀጠናው አገሮች በዲሞክራሲና በፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማረጋገጥ እንደሚቆሙ ተስማምተዋል” ብሏል።

ቻይና በበኩሏ በጤና፣ ድህነትን በመቀነስ፣ በእርሻ ልማት፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመሠረተ ልማት፣ በአረንጓዴ ልማት እና በፀጥታ በመሳሰሉ ዘርፎች ከአገራቱ ጋር ስታደርገው የነበረውን ትብብር ለማጠናከር ቃል ገብታለች።

ቻይና ጂቡቲ፣ አዲስ አበባ እንዲሁም ሞምባሳ እና ናይሮቢን የሚያካትተው “Two Axes Plus Two Coasts” ተብሎ በሚታወቀው የወደቦች እና የመሠረተ ልማት ግንባታን እንደምታግዝ ገልጻለች።  

  የአፍሪካ ኅብረትና የአሜሪካ ጥረት

በአፍሪካ ቀንድ ያሉትን ግጭቶች ለመፍታትም ሆነ ለማረጋጋት የአፍሪካ ኅብረትና የቀጠናው ተቋም ኢጋድ ሲያካሂዱት የነበረውን ተነሳሽነት እስካሁን ድረስ መሠረታዊ መፍትሔ ማምጣት አልቻለም።

መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያን ወገን እንደሆነ ሲነገርለት የነበረው የአፍሪካ ኅብረት፣ የትግራይን ጦርነት ለመፍታት የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆን ልዩ መልዕክተኛ አድርጎ መሾሙ ይታወሳል።

ልዩ መልዕክተኛውም መቀለና አዲስ አበባ እየተመላሱ ሲያደራድሩ ቆይተው ሂደቱ “ተስፋ” እንዳለው ተናግረው ነበር።

በአሜሪካ የተመራ የምዕራባውያን ሙከራዎችም ቢሆኑ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያም ሆነ በቀጠናው ዘላቂ ሰላምንና ፀጥታን ማረጋገጥ አልቻሉም።

አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ለማረጋጋት እንዲሁም የሱዳን የውሰጥ የፖለቲካ ቀውስን ለመፍታት እስካሁን ሦስት ልዩ መልዕክተኞችን ሾማለች።

ይሁን እንጂ ደም ያፋሰሰውን የትግራይ ጦርነትን በተመለከተ የተኩስ ማቆም ስምምነት ካልሆነ በስተቀር የድጋሚ ጦርነት ስጋት ጠቅልሎ የሚያስወግድ ስምምነት አልተፈረመም።

ሁለቱም ወገኖች የሰላም ውይይት ለማካሄድ ፈቃደኝነታቸውን የገለጹ ቢሆንም ውይይቱ ወዴት እንደሚያመራ ወደ ፊት የሚታይ ነው። 

የሱዳን ሁኔታም ቢሆን፣ የፕሬዝዳንት አል-በሽር ከሥልጣን መወገድ በኋላ ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር የተጀመረው ጉዞ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተቀልብሷል።

በቻይናና በሱዳን ግንኙነት ላይ ጥናት ያካሄደውና የዶክትሬት ትምህርቱን በዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ እየሰራ የሚገኘው አቶ ተስፋዓለም ሃብተ እንደሚለው፤ ምንም እንኳ የቀጠናው ሰላም የሚረጋገጠው በውስጣዊ ምክንያቶች ቢሆንም የውጭ አደራዳሪዎች ታማኝነት አስፈላጊ ነው።

ተስፋዓለም “አሜሪካ ገለልተኛ አደራዳሪ ሆና ለመታየት ያላት ዕድል አነስተኛ ይመስለኛል” ይላል።

በቅርብ ጊዜያት ኤርትራና ኢትዮጵያ ከአመራር ለውጥ ጋር የውጭ ፖሊሲዋ የሚቀያየረውን አሜሪካን በአፍሪካ ቀንድ ባላት ፖሊሲ ምክንያት ሲወቅሷት ቆይተዋል።

ብዙ ተነሳሽነት የምታሳየው አሜሪካ በቀጠናውአለመረጋጋት ራሷ አስተዋፅኦ እንዳላት የአደራዳሪነት ሚናዋን እንደሚያወሳስበው አቶ ተስፋዓለም ይገልፃል።

ጂቡቲ ውስጥ ቀጠናውን የሚከታተል ወታደራዊ ካምፕ ያላት አሜሪካ በቅርቡ መረጋጋትና የፀጥታ ደኅንነትን ልትፈጥር ወዳልቻለችው ሶማሊያ ወታደሮቿን እንደምትልክ አስታውቃ ነበር።

ሶማሊያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ መረጋጋት እየታየ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ በሞቃዲሾ አልሸባብ ተደጋጋሚ ጥቃትን እያደረሰ ይገኛል።

የቻይና ተነሳሽነት እና ጥቅሞቹ

ባለፉት 30 ዓመታት ቻይና ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስርና አጋርነት እየተጠናከረ መጥቷል።

ይህ ትስስር በዋናነት መሠረተ ልማት ግንባታና ብድር ላይ ያተኮረ ነው።

የቻይና አብዛኛዎቹ ብድሮች የባቡር መንገዶችንና ወደቦችን በመገንባት፣ በኢነርጂና በኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት እንዲሁም በርካታ አህጉራትንና አገራትን የሚያስተሳስረው 'ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሸቲቭ’ የቻይና ተሳትፎ ማሳያ ናቸው።

አፍሪካ ለቻይና የመንግሥትና የግል ዘርፎች የግብአት እና የገበያ ምንጭ ናት። በርካታ የቻይና ኩባንያዎችም በማዕድን ሥራ ላይ ተሳትፈዋል። የአፍሪቃ ዋነኛ የንግድ አጋር ደግሞ ቻይና ናት።

ቻይና በጂቡቲ ከአገር ውጭ የገነባችው ብቸኛ ወታደራዊ ካምፕ መገንባቷም የጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቷን ያመለክታል።

“ቻይና የወሰደችው ተነሳሽነት በአውንታ መታየት የሚችል ሆኖ ይሰማኛል። ምን ያህል የተሳካ ይሆናል የሚለውን ለማየት ግን የተያዙት እቅዶች ምን ይመስላሉ? ተዋናዮቹስ እነማን ናቸው? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።  ለምሳሌ የኤርትራ ሚና አፍራሽ ቢሆንም አለመሳተፏ በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ይላል።

ቻይና ቀጠናው ሰላም እንዲያገኝ የጀመረችውን ጥረት የአገርን ሉላዊነት ስለምታከብር፣ በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አለመግባት የሚል ፖሊሲ ስለምትከተል እንዲሁም የምትሰጠውን የልማት ድጋፍና ብድር ወይም የንግድ አጋርነት “ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ” በመሆኑ የተሻለ ሊባል እንደሚችል ተንታኞች ይስማማሉ።

የቀጠናውን እድገት በቅርብ ከሚከታተሉት ውስጥ አንዱ የሆነው ዶ/ር መብራህቱ አተወብርሃን እንደሚሉት ግን ምዕራባውያን አገራት ጥቅማቸውን ለማስከበር ከአምባገነኖች ጎን እንደሚቆሙ በመግለጽ ከቻይና የተሻሉ እንዳልሆኑ ይከራከራሉ።

“ከዚህ አንፃር ሲታይ የቻይናና የምዕራባውያን አካሄድ አይለያይም” የሚሉት መብርህቱ፣ አንድ ለየት የሚያደርገው ቻይና በአገራቱ ያላትን የመሠረተ ልማት ግንባታን በመጠቀም ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ለመወዳደር የምታደርገው እንደሆነ ይገልጻሉ።

ተስፋዓለም በበኩሉ የቻይና ተነሳሽነት ጥቅም “ራሷን የቅኝ ተገዢ እና ዳግም-ቅኝ ተገዢ (colonialism and neo-colonialism) ከሆኑትና በማደግ ላይ ከሚገኙ አገራት ጎን ስለምታደርግ ሁሌም ከፀረ ዳግመ-ቅኝ ገዢነት ጋር በሚደረግ የጋራ ትግል ጎን እንዳለች ተደርጋ ትታሰባለች። ይህም አደራዳሪ ሆና እንድትታይ አስተዋፅኦ አለው” ይላል።