በህንድ በሃይማኖት ውዝግብ ምክንያት አንድ ግለሰብ ተቀልቶ መገደሉ ቁጣን ቀሰቀሰ  

በህንድ የተነሳው ውዝግብ

የፎቶው ባለመብት, ANI

በሰሜናዊ ህንድ ራጅስታን ግዛት አንድ የሂንዱ እምነት ተከታይ መገደሉን ተከትሎ በአካባቢው ሃይማኖታዊ ውጥረት ተፈጥሯል።

ሟቹ በልብስ ስፌት ስራ የሚተዳደረው ካንሃያ ላል የሚባል ግለሰብ ሲሆን ገዳዮቹ ሁለት ሙስሊም ግለሰቦች አገዳደሉን ቀርጸው በበይነ መረብ አጋርተውታል።

ድርጊቱ አንድ ፖለቲከኛ በነቢዩ መሃመድ ላይ ለተናገሩት አወዛጋቢ አስተያየት ግለሰቡ ድጋፍ በመስጠቱ የበቀል እርምጃ ነው ብለዋል።

መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሁም ትልልቅ ስብሰባዎች እንዲታገዱ አድርጓል።

በቪዲዮው ላይ ማንነታቸው የገለጹትን ሁለት ገዳዮች ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏል።

በሌላ ቪዲዮ ላይ ግለሰቦቹ ስለ ግድያው በመኩራራት ሲያወሩ እንደነበርና ለጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲም ማስፈራሪያዎች ልከዋል ተብሏል።

አንድ ከፍተኛ የራጃስታን ፖሊስ ባለስልጣን የግድያውን ቪዲዮ “ለመመልከት በጣም አሰቃቂ” በመሆኑ ሚዲያዎች እንዳያሰራጩት ጠይቀዋል።

 የራጃስታን ዋና ሚኒስትር አሾክ ጌህሎት ነዋሪዎች እንዲረጋጉ ተማጽነዋል።

የፌደራል መንግስቱ በበኩሉ  የህንድ ከፍተኛ የፀረ-ሽብር ኤጀንሲ የሆነው የብሄራዊ ምርመራ ኤጀንሲ  ክስተቱን እንዲያጣራ ጠይቋል። 

ገዳዮቹ ወደ ካንሃይያ ላል ሱቅ ለመግባት ራሳቸውን ደንበኛ በማስመሰል ሲሆን እየለካቸውም እያለ ጥቃት አድርሰውበታል ተብሏል።

ሟቹ ባለፈው ወር ስለ ነቢዩ መሐመድ አወዛጋቢ አስተያየቶችን የሰጡትን የቀድሞ ባራቲያ ጃናታ ፓርቲ (ቢጄፒ) ቃል አቀባይ ኑፑር ሻርማን የሚደግፍ የማህበራዊ ሚዲያ ፖስት አጋርቷል።

የፖለቲከኛዋ አስተያየት በበርካታ እስላማዊ አገሮች ጠንካራ ተቃውሞ እንዲሰማ ያደረገ ሲሆን ከህንድ ጋርም ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ምክንያት ሆኗል። ፓርቲያቸው ባራቲያ ጃናታ ፓርቲ (ቢጄፒ) ፖለቲከኛዋን አግዷቸዋል።

ውዝግቡ በህንድ ሃይማኖታዊ ተቃውሞዎችን ያስከተለ ሲሆን ተቃዋሚዎች ድንጋይ በመወርወር እና በህዝብ ንብረት ላይ ጉዳት ካደረሱ በኋላም ሁኔታው በከፍተኛ ሁነታ ተጋግሏል።

ካንሃይያ ላል ከመገደሉ ከሶስት ሳምንታት በፊት ሃይማኖታዊ ስሜቶችን ጎድቷል በሚል በፖሊስ ተይዞ እንደነበር ኢንዲያን ኤክስፕረስ ዘግቧል። ግለሰቡ ከእስር ከተፈታ በኋላ በህይወቱ ላይ ስጋት ፈጥሯል በሚል የፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግለት ጠይቋል።