“ከጥቃቱ ብንተርፍም፣ የረሃብ ጦር እየወጋን ነው” የጊምቢ ነዋሪዎች

ካርታ

በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ በጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ የሚገኙ ነዋሪዎች ከሰኔ 11ዱ ጥቃት የተረፉ ነዋሪዎች አስፈላጊውን የምግብ እርዳታ ስላላገኙ መቸገራቸውን ለቢቢሲ ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ቤት ንብረታቸው ከመውደሙ ባሻገር ንግዳቸው እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻቸው ስለተዘረፉ የምግብ ችግር እንደገጠማቸው እየተናገሩ ነው።

ቢቢሲ ረቡዕ ሰኔ 15 ቀን 2014 ማለዳ ያናገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት፣ በአካባቢው አሁን ላይ የፀጥታ ስጋት ባይኖርም በቂ ምግብ የላቸውም።

ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው ሰዎች ዘመዶቻቸው ጋር ተጠልለው እንደሚውሉና የተወሰኑት ምሽት ላይ በመስጅዶች ውስጥ እንደሚጠለሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በቶሌ ቀበሌ በሚገኙት ጉቱ፣ ጨቆርሳ፣ ስልሳው፣ በገኔ፣ ጫካ ሰፈር እና ሀያው በተባሉ መንደሮች (ጎጦች) ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ. ም. በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ከ300 የሚልቁ ንጹሀን ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ይፋዊ ቁጥር በመንግሥት በኩል ባይነገርም፣ የዐይን እማኞች እንዲሁም የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሟቾችን ቁጥር ከ300 በላይ አድርሰውታል።

በአሜሪካ የአማራ ማኅበር አድቮኬሲ በትዊተር ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ በጥቃቱ ሳቢያ “ቢያንስ 378 የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን ምንጮቻችን አረጋግጠውልናል” በማለት ቁጥሩ ከዚህ በእጅጉ ይበልጣል ብሏል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች እንዲሁም መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመው ‘ሸኔ’ በመባል የሚታወቀው ታጣቂው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንደሆነ ሲገልጹ፣ ቡድኑ ግን ለጥቃቱ የመንግሥት ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባወጣው መግለጫ፣ ታጣቂዎቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙና የጊምቢው ጥቃትም መንግሥት አደራጅቶታል ባለው ኢ-መደበኛ ኃይል እንደተፈጸመ ገልጾ፣ ክስተቱ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል።

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ጠዋት ማካሄድ የጀመረ ሲሆን፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች “በአሸባሪዎች እየተፈጸመ ያለውን ግድያ” እንደሚያወግዝ ገልጿል።

በዚህም ስብሰባው ላይ “የሕግ ማስከበር እርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ" ማስቀመጡንም ፓርቲው አመልክቷል።

“እየራበን እየጠማን ተቀምጠናል”

የሰባት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ፎዚያ* ወንድማቸው ቤት ተጠልለው እንደሚገኙ ይናገራሉ።

የአራት ዓመቱ የመጨረሻ ልጃቸውን ጨምሮ በአንድ ቤት ውስጥ አምስት ቤተሰብ እየኖረ ነው።

በግብርና ይተዳደሩ የነበሩት ወ/ሮ ፎዚያ በጥቃቱ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ ወድሟል።

ስልሳው በሚባለው መንደር ይኖሩ የነበረ ሲሆን፣ ሁለት ጥማድ በሬ፣ ሦስት ላሞች እና አንድ ጎተራ እህል ወድሞባቸዋል።

ዛሬ ለልጆቻቸው ንፍሮ ቢያበሉም፣ ነገ እና ከዚያ ወዲያ ያሉት ቀናት እንደሚያሰጓቸው ገልጸዋል።

“ቤተሰቦቻችን አልቀው ብቻችንን እያለቀስን፣ እየራበን እየጠማን ተቀምጠናል” ብለዋል ወ/ሮ ፎዚያ።

ጥቃቱ ቅዳሜ ጠዋት 3፡00 ጀምሮ እስከ ከሰዓት እንደዘለቀ የዐይን እማኞች ገልጸዋል።

ከእሁድ ጀምሮ እስከ ትላንት ሰኔ 14 ድረስ የሟቾች አስክሬን በጅምላ መቃብሮች ሲቀበር እንደቆየም ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቶሌ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አሕመድ “ወደ 10 ይሁን 20 ኩንታል የሚጠጋ ስንዴ መጥቷል። ስድስት ካርቶን ኮቾሮ ነበር ልጆች በልተውታል። ስኳርም የተወሰነ ከረጢት መጥቷል። ሰው እናክማለን ብለውም ቦታ እየያዙ ነው” ብለዋል።

በግብርና የሚተዳደሩት አቶ አሕመድ እንደሚሉት፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ እርሻቸው ለመመለስ ቸግሯቸዋል።

“. . . ያንን ሁሉ ሬሳ አይተን ልቦናችን ወደ ሥራ አይመራንም። ሰው ዝም ብሎ ሐዘኑን እየተካፈለ ነው። ቅዳሜ ከሞተው ሰው መካከል የተቀበረ፣ አሞራ የጎተተውም አለ” ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት ማሳ ውስጥ ተደብቀው ሕይታቸውን እንዳተረፉ ተናግረዋል።

አሁን መከላከያ ሠራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል በመኖሩ መረጋጋት ቢመለሰም፣ ሙሉ በሙሉ ከስጋት እንዳልተላቀቁ ገልጸዋል።

“ይሄ ማስጠንቀቂያ ነው፣ ከሦስት ቀን በኋላ ወደ አገራችሁ ግቡ፣ እዚህ እንዳትቀመጡ፣ መጨረሻ ላይ ስንመጣ የሚተርፍ ሰው የለም ብለውናል። መንግሥት ከዚህ ያንሳን” ሲሉ ተማጽነዋል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ጥቃቱን “የሽብር ጥቃት” ሲል የፈረጀው ሲሆን፣ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖችና ለደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ “ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት መዋቅራዊ እና ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ በአማራ ሕዝብ ላይ ግድያ፣ መፈናቀል፣ ሃብት እና ንብረቱን ማውደም እንዲሁም መንጠቅ ሲፈጸም ቆይቷል” ብሏል።

ከአብን በተጨማሪ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ እና እናት ፓርቲን ጨምሮ ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች ግድያውን አውግዘዋል።

የአሜሪካ መንግሥት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በኩል ባወጣው መግለጫ “በኦሮሚያ ክልል በአማራ ማኅበረሰብ ላይ የደረሰው ግድያ እጅግ አሳስቦናል። ኢትዮጵያ ነውጥን እንድታወግዝና ወደ ሰላማዊ ውይይት እንድታመራ እንጠይቃለን” ብሏል።

“ሰባት ልጆቼን ምን ላብላቸው?”

በቶሌ ቀበሌ፣ ጨቆርሳ መንደር የሚኖሩት የሰባት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አብዱ* አሁን በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊት እና ልዩ ኃይል በመግባቱ ሰላም ቢመለስም፣ ልጆቻቸውን የሚያበሉት ምግብ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ አቶ አብዱ በጥቃቱ የአጎቶቻቸውን ልጆች አጥተዋል። ቤት ንብረታቸውም ተዘርፏል።

ከመጋዘናቸው 110 ኩንታል በቆሎ እና 15 ኩንታል ሩዝ እንዲሁም አምስት በሬን ጨምሮ በግ እና ፍየል እንደተዘረፉ ተናግረዋል።

“የተፈጸመው አሰቃቂ፣ ዘግናኝ ጥቃት ነው። ትላንትም ሰው ቀብረናል። ሳይቀበር ጫካ የቀረም አለ። አንድ ጉድጓድ ውስጥ 63 ሰው የተቀበረበት ቦታ አለ። ከእነዚህ 40 የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው” ይላሉ።

ጨምረውም “. . . አሁን እኮ አንድ ኪሎ ምግብም የለንም። ልብስም ጫማም የለንም። መንግሥትም አልረዳንም። ከዝርፊያ የተረፈውን እህል ቀቅለን ንፍሮ ነው የምንበላው። ተጨፈጨፍን አሁን ደግሞ የረሃብ ጦር እየወጋን ነው” ብለዋል።

የሰባት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አብዱ፣ ልጆቻቸውን መመገብ እንዳልቻሉና በአካባቢው የተሰማሩት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ለሕጻናት ብስኩት እየሰጧቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“መከላከያዎች የተወሰነ ኮቾሮ እየሰጧቸው ነው እንጂ ሰባት ልጅ እንዴት ይደረጋል? ገና ዓመት ያልሞላት ልጅ አለችኝ. . . ረሃቡ አሳሳቢ ነው።”

ጥቃቱ የተፈጸመ ዕለት እሳቸው ከቀበሌው ወጥተው እንደነበርና ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው ማሳ ተደብቀው እንደተረፉ ተናግረዋል።

አቶ አብዱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሰው ቤት ተጠልለው እንዳሉና እናቷ የተገደለችባት የ15 ቀን ልጅን ጨምሮ በአንድ ቤት ውስጥ በርካቶች እንደሚገኙ ገልጸዋል።

“አሁን እኮ አባ ወራ ብቻውን፣ እማወራ ብቻዋን ቀርተዋል። ምን ተረፍን ይባላል? ከዚያም ብሶ ረሃብ ሊጨርሰን ነው” በማለት እርዳታ እንዲደረግላቸው ተማጽነዋል።

“ለምን እናርሳለን?”

ሌላው ቢቢሲ ያነጋገረው ስልሳው የተባለ መንደር ውስጥ ተወልዶ ያደገው ከማል* በጥቃቱ ወንድሙን አጥቷል።

የሸቀጥ ሱቁ እንደተዘረፈ እና ዘመድ ቤት ተጠልሎ እንደሚገኝ ተናግሯል።

“ዘመድ ቤት፣ ጓደኛ ቤት፣ በየበረንዳው፣ በየመስጆዱ ነው ተጠልለን ያለው” ይላል። 

ከማል ያሳርሰው የነበረው መሬት እንደነበረው፣ ከጥቃቱ ወዲህ ግን ወደ እርሻ የተመለሰ ሰው በመንደራቸው እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ለምን እናርሳለን? ወቅቱ እኮ ታርሶ፣ ነጭ ማዳበሪያ የሚደረግበት ነበር። ግን ስንት ንብረት ቀለጠ! 4 ሄክታር በቆሎ እና አንድ ሄክታር ሩዝ አዘርቼ ነበር። ያው ቀልጦ ቀረ። እና ለምን ብዬ ነው ሁለተኛ ወጪ አውጥቼ ማዳበሪያ የማስረጨው? ለምንስ አስኮተኩታለሁ። ላስኮትኩት ብልስ መቼ ገንዘብ አለን? ገንዘባችን፣ ንብረታችን ተወስዷል። ሰው እንዲሁ እየተንቀዋለለ ነው።”

ከማል እንደሚለው፣ ከየትኛውም የመንግሥት አካል የምግብ እርዳታ እስካሁን አልደረሳቸውም። የመከላከያ ሠራዊት አባላት ለሕጻናት ብስኩት ሲሰጡ መመልከቱን ጠቅሷል።

“የተራረፈ በቆሎ እየቀቀልን ተካፍለን ነው የምበላው። ጨው እንኳን የለንም። መከላከያዎች ከቀለባቸው አዋጥተው ለሕጻናት እና ለእናቶች ጠዋት አንድ፣ ማታ አንድ ብስኩት ሲሰጡ አይቻለሁ። ግን ይሄ እስከ መቼ ያዘልቃል?” ይላል።

የሰኔ ወር ሰብል የሚኮተኮትበት እንደነበረ፣ በጥቃቱ ሳቢያ ሥራ በመስተጓጎሉ ግን አዝመራው በአረም እየተበላ መሆኑን ተናግሯል።

“. . . ሰብል መኮትኮቱ ቀርቶ እኛ ሰው አጥተናል። ስለ በቆሎ አዝመራ ማን ያስባለል? ነፍስ ይቀድማል። የሞተው ሰው ወደ 500 ደርሷል እየተባለ ነው።”

ማኅበረሰቡ አሁን ያለውን ምግብ ተካፍሎ ቢበላም፣ ከጥቂት ቀናት በላይ እንደማያልፍ ይናገራል። እርዳታ በአፋጣኝ እንዲሰጣላቸውም ይጠይቃል።

“መከላከያ ስላለ አሁን ሰላም ነን። መከላከያ ከወጣ ግን ራሱን መከላከል የሚችል ሰው የለም። አሁንም ፈርተን ግማሻችን ስንተኛ፣ ግማሻችን እንጠብቃለን። አንድ ሸንኮራ ‘በሥነ ሥርዓት ተጠቀሙ’ ተብሎ ለሁለት ተካፍለን እንበላለን። በቋፍ ነው ያለነው” ሲልም አክሏል።

ቢቢሲ ከጥቃቱ ተርፈው በችግር ላይ ያሉትን ነዋሪዎች በተመለከተ ከዞን እና ከወረዳው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ በስልክ ቢሞክርም ለጊዜው ምላሽ አልተሳካም።

*በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱት ግለሰቦች ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው ተቀይሯል።