ጋዜጠኛ ተመስገን ወታደራዊ ምስጢሮችን ይፋ በማድረግና በሌሎች ወንጀሎች ክስ ተመሰረተበት

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

የፎቶው ባለመብት, Tariku Desalegn Facebook

የፍትህ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወታደራዊ ምስጢሮችን ለህዝብ ይፋ በማድረግ የሚለውን ጨምሮ በሦስት ወንጀሎች በዛሬው ዕለት ሰኔ 22፣ 2014 ዓ.ም ክስ እንደተመሰረተበት ጠበቃው ሔኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በዛሬው ዕለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብርና የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፣ አቃቤ ህግ ጋዜጠኛውን የከሰሰበት ሦስት ክሶችንና ማስረጃዎችን አቅርቧል።

ወታደራዊ ምስጢሮችን ለህዝብ ይፋ በማድረግ፣ ሃሰተኛ የሆኑ ወታደራዊ መረጃዎችን በማውጣት፣ ለአመፅ ህዝቡን በማነሳሳት በሚል አቃቤ ህግ ክስ እንደመሰረተበት ቢቢሲ ከጠበቃው መረዳት ችሏል።

በሦስቱም ክሶች ላይ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሚሰራበት ሚዲያ ላይ በመጻፍ እነዚህን የወንጀል ተግባሮች ፈፅሟል የሚልም ወደ ሰባት የሚሆኑ የፍትህ መፅሄቶች በማስረጃነት በዛሬው ችሎት ቀርበዋል።

አቃቤ ህግ ለክሶቹ ካቀረባቸው ፍትህ መፅሄት ላይ የታተሙ ፅሁፎች መካከል በተደጋጋሚ የተጠቀሰው ከጄኔራል ተፈራ ማሞ ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶች እንደሆኑ ጠበቃው አስረድተዋል።

እዚያ ላይ የተጠቀሱ መረጃዎችም በወታደራዊ ምስጢርነት፣ በሃሰተኛ መረጃዎች እንዲሁም ህዝብን ለአመፅ የሚያነሳሱ ናቸው በሚልም ተጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ፍትህ መፅሄት ከንግድ ፈቃድ ጋር በተገናኘ የብሮድካስት ባለስልጣን የጻፋቸው ደብዳቤዎች፣ የፌደራል መከላከያ የጻፋቸው ደብዳቤ በማስረጃነት ተካትተዋል። በአጠቃላይም ለክሶቹ አስራ አንድ ማስረጃዎችን አቃቤ ህግ አቅርቧል።

ፅሁፎቹ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የታተሙ ሲሆን አንዳንዶቹ የቀረቡበት ክሶች ጋዜጠኛው ያልጻፋቸው ፅሁፎች ሲሆኑ እነዚህም በፍትህ መፅሄት አባላት ወይም በሌሎች ተፅፈው በመፅሄቱ ለህትመት የበቁ መሆናቸውንም ጠበቃው ለቢቢሲ ገልጸዋል። እስካሁን ባለው ምንም አይነት የሰው ማስረጃ እንዳልቀረበም ጠበቃ ሄኖክ ተናግረዋል።

ክሶቹ ከቀረቡ በኋላም ጠበቃው በምላሹ ወደ ዝርዝር ጉዳይ እንዳልሄዱና በቀጣዩ ቀጠሮ ወደ ወንጀሎቹ ዝርዝር እንደሚመለሱ ገልጸው፣በዛሬው ችሎት በዋናነት ያነሱት የዋስትና ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጋዜጠኛው የዋስ መብቱ ተከብሮ ጉዳዩን እንዲከታተል ለፍርድ ቤት የጠየቁ ሲሆን አቃቤ ህግ በምላሹ በዋስትና ሊወጡ እንደማይገባ ሦስት ምክንያቶችን በመጥቀስ ተከራክሯል።

በአጠቃላይ ጋዜጠኛው የተከሰሰባቸው ሦስት ወንጀሎች ድምር ከባድ ቅጣት የሚያስቀጣ በመሆኑ፣ ተደራራቢ ክሶች በመቅረቡና እንዲሁም ቢፈታ ሌላ ወንጀል ይፈፅማል የሚል የመከራከሪያ ሃሳቦችን ለችሎቱ ማቅረቡን ጠበቃ ሔኖክ ገልጸዋል።

ጠበቃውም በምላሹ የአቃቤ ህግ መከራከሪያ ሃሳቦች ተገቢነት የሌላቸውና ተመስገን ከዚህ በፊት ተከሶ በነበረበት ወቅት በቀድሞው ስርዓት የፍርድ ቤት ቀጠሮዎችን በማክበር ይቀርብ እንደነበር ማስመስከሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአገሩን ጉዳይ ሳይወጣ እንደሚከታተልና እና አገሩን ለቆ እንዲወጣ በርካታ ጫናዎች ቢበረቱበትም ያንን ተቋቁሞ መቆየቱን ህግን አክብሮ እንደሚመጣ ማሳያ መሆኑንም በመጥቀስ ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

አቃቤ ህግ ዋስትና እንዲከለከል በጠየቀበት ወቅት ተመስገን በጠበቃው በኩል ባስተላለፈው መልዕክት በነበረው መንግሥት ከአገር እንዲወጣ የማባበል፣ በሌሎች መንግሥታትም እንዲወጣ የተለያዩ ምክሮች ቢቀርቡለትም አለመቀበሉን ለችሎቱ አስረድቷል።

ጋዜጠኛው በአገሩ ላይ መልካሙንም፣ ክፉውንም ተቀብሎ የመኖር ፍላጎት እንዳለው እንዲነገርለት በጠየቀው መሰረት ጠበቃው ለችሎቱ እነዚህን ሃሳቦች ማንሳታቸውን ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱም በዋስ መብት ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ ለሰኔ 24፣ 2014 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ድብደባ ተፈፅሞበታል የተባለው ተመስገን፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ታስሮበት የነበረው ውስን በሆነ ክፍል በርካታ ሰዎች ባሉበት ነበር።

ፖሊስ ለዚህም ወንዶች ይታሰሩበት የነበረው እስር ቤት እድሳት ላይ ነው የሚልም ምክንያት አቅርቦም ነበር በአሁኑ ወቅት ተመስገን የታደሰው ክፍል ውስጥ መግባቱንና በተሻለ ጥበቃ ነጻነትና ጤንነታቸውን የሚጠብቁበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠበቃው አስረድተዋል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ  ከ33 ቀናት በፊት ግንቦት 18/2014 ዓ.ም. ከሥራ ቦታው በሁለት መኪና ተጭነው በመጡ የፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መወሰዱ ይታወሳል።