‘በመጠለያው ከመቆየታችን የተነሳ የተመዘገብንበትን 'ኬዝ' ረስተናል’- ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በካኩማ

የስደተኞች መጠለያ በኬንያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) መረጃ መሰረት እስከ የካቲት 2021 (እአአ) ድረስ በዳደብ ስደተኞች መጠለያ ውስጥ ብቻ 224,642 እንዲሁም በካኩማ ደግሞ 206, 458 ስደተኞች ይገኛሉ።

ይህ አጠቃላይ በኬንያ የተለያዩ ከተሞች ከሚኖሩ ስደተኞች ጋር ሲደመር ከ500 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች አሉ።

እነዚህ ስደተኞች ደግሞ ከኢትዮጵያ፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ከቡሩንዲ፣ ከኤርትራ፣ ከሱዳን፣ ከኡጋንዳ፣ ከሩዋንዳ እና ከሌሎች አገራት የመጡ ናቸው።

ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከሶማሊያ የመጡ ስደተኞች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከ29 ሺህ በላይ መሆናቸውን የድርጅቱ ሰነድ ያስረዳል።

በኬንያ ቱርካና ግዛት የሚገኘው ካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩት አቶ ጀማል አደም እና አቶ አልዩ ኡስማን በየጊዜው በርካታ ስደተኞች ወደ ጣቢያው እንደሚመጡ ይናገራሉ።

ሁለቱ ስደተኞች ኢትዮጵያን ጥለው ከወጡ ሁለት አስርታት ሊቆጠሩ የቀራቸው ጥቂት ጊዜ ነው።

“በልጅነቴ ካኩማ ገብቼ አሁን የስድስት ልጆች አባት ነኝ” የሚሉት አቶ ጀማል የመጡት ከምሥራቅ ሐረርጌ ደደር ከተማ ነው።

በ1997 ዓ.ም ምሥራቅ ሐረርጌ ደደር ከተማ ትምህርታቸውን ከስምንተኛ ክፍል አቋርጠው ወደ ኬንያ የተሰደዱት አቶ ጀማል፣ ካኩማ የስደተኞች መጠለያ የገቡት ገና ታዳጊ እያሉ መሆኑን ያስታውሳሉ።

ከአገር የወጡበትን ምክንያትም ሲያስረዱ ‘ረብሻ አስነስታችኋል’ በሚል በመንግሥት ታጣቂዎች የተለያዩ እንግልቶች ከደረሰባቸው በኋላ፣ ያንን በመሸሽ ወደ ኬንያ መሰደዳቸውን አቶ ጀማል ይናገራሉ።

በ1995 ዓ.ም ከአገራቸው የወጡት አቶ አልዩ ኡስማን በበኩላቸው፣ ረዥም ጊዜ ከመቆየታቸው የተነሳ ለስደተኞች ድርጅት ያስመዘገቡት ጉዳይ ራሱ ምን እንደሆነ መርሳታቸውን ይናገራሉ።

አቶ ጀማል ላለፉት 17 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ሳያገኙ መቆየታቸው ያንገበግባቸዋል።

“ለረዥም ዓመታት ቤተሰቦቼ ያሉበትን ሁኔታ አላወቅም። በቅርቡ ሰዎች እዚያ አካባቢ ያለውን ሁኔታ ፌስቡክ ላይ ስለሚለጥፉ ከእነርሱ ጋር ተጻጽፌ ስለቤተሰቦቼ አንዳንድ ነገር መስማት ጀመርኩ” በማለት የቤተሰቦቻቸው ሁኔታ አሁንም እንደሚያሳስባቸው ይናገራሉ።

አክለውም “እኔ እንኳ በጥቂትም ቢሆን ቤተሰቦቼን አገኛለሁ። ሌሎች ደግሞ በጭራሽ ቤተሰቦቻቸውን ያላገኙ አሉ። እኔ አሁን እዚሁ የልጆች አባት ሆኜ ቀርቻለሁ።”

በስደተኝነት ከተመዘገቡ ከ15 ዓመት በላይ እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ ጀማል እስካሁን ድረስ ግን ምንም ዓይነት ነገር አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።

“እንዲያውም የተመዘገብኩበትን ኬዝ ራሱ ረስቻለሁ። አሁን እርሱን ትቼ የግል ሥራ ጀምሬያለሁ፤ ኑሮዬን ለማስኬድ የንግድ ሥራ ውስጥ ገብቻለሁ። በራሴ ጥረት ልጆቼን እያሳደግኩ እያስተማርኳቸው ነው።”

አቶ አልዩም የተመዘገቡበትን ጉዳያቸውን [ኬዝ] መዘንጋtኣቸውን በመግለጽ፣ “የኬንያ መንግሥት ይህ ካምፕ ይዘጋል እያለ ይዝታል፤ እኛ ከፈጣሪ ውጪ ምንም የለንም፤ ጉዳያችንን የያዙ አካላትም ከእኛ ርቀዋል” ሲሉ በሐዘን ስሜት ስላሉበት የስጋት ኑሮ ይናገራሉ።

አቶ ጀማል በስደት ሕይወታቸው ያፈሯቸው ሦስት ልጆቻቸው አምስተኛ እና ስድስተኛ ክፍል ደርሰዋል “እስከቻልኩ ድረስ እኔን የገጠመኝ ዕድል ልጆቼ እንዲገጥማቸው አልፈልግም። ለዚህ ብዬ ነው ተፍ ተፍ የምለው” ይላሉ።

እርሳቸው ወደ ኬንያ ሲመጡ ባዶ እጃቸው በመሆኑ ትምህርታቸው መቀጠል አለመቻላቸውን በማስታወስ፣ “እኔ ያመለጠኝን ዕድል ልጆቼን በማስተማር ማካካስ አለብኝ” ብለው ልጆቻቸውን በርትተው ማስተማር ላይ ማተኮራቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ሁለቱ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከገቡ 20 እና 30 ዓመታት የሞላቸው እንዳሉ ይነገራል።

በየጊዜው ወደ ሦስተኛ አገር እንሻገራለን የሚል ተስፋ ቢኖራቸውም ይህ ሳይሆን እዚያው ወልደው ቤተሰብ መስርተው ኑሮን ቀጥለዋል።

‘ለሥራ ገንዘብ የለኝም ለመሥራት ግን አቅም አለኝ’

አቶ ጀማል ወደ ካኩማ የስደተኞች መጠለያ ሲገቡ ማንም የሚረዳቸው ከአጠገባቸው እንዳልነበር ያስታውሳሉ።

“በቻልኩት አቅም ጥሬ መማር ወይን ደግሞ መሥራት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። በዩኤንኤችሲአር በሚደረግፍልኝ ድጋፍ ብቻ ትምህርት ከጀመርኩኝ ሰው ላይ ጥገኛ ሆኜ እቀራለሁ። በዚህ ሁኔታ በትምህርትም ስኬታማ አልሆንም ብዬ ነው ወደ ሥራ ዞርኩኝ።”

በወቅቱ ሥራ ለመጀመር የሚሆን ገንዘብ ሳይሆን አቅም እንደነበራቸው የሚያስታውሱት አቶ ጀማል፣ በስደተኞች መጠለያ ውስጥ በወር 50 ሽልንግ እየተከፈላቸው ሆቴል ውስጥ ተቀጥረው መስራት ጀመሩ።

“ያኔ ነው ቁጠባ የጀመርኩት። የሰው ሆቴል ውስጥ እየሰራሁ ደሞዜ ስድስት ሺህ ሺልንግ ገባ። እየቆጠብኩ ብር ሳገኝ የራሴን ሥራ ጀመርኩ” በማለት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ንግድ መግባታቸውን ይናገራሉ።

“አሁን ሱቅ አለኝ፤ ምግብ ቤት አለኝ፤ ከራሴም አልፌ ለተቸገሩ ሰዎች መጠለያ ሆኜ እየረዳሁ ነው። ምንም የሌላቸው ሰዎች እዚህ እኔ ጋር እየሰሩ፣ እየኖሩ ነው። በአሁኑ ወቅት እኔ ጋር እየሰሩ የሚኖሩ ስምንት ስደተኞች አሉ።”

‘የመንግሥት ማስፈራርያ የንግድ ሥራዬን አደናቀፈው’

ኬንያ ውስጥ በሚገኙ ዋነኛ የስደተኞች ማቆያ ካምፖች ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለዓመታት በአሰቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ቆይተዋል።

በቅርቡም የኬንያ መንግሥት የካኩማና የዳደብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን እንደሚዘጋ ካሳወቀ በኋላ ሕይወታቸው ከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ መግባቱን፣ እንዲሁም ሥነ ልቦናቸው መጎዳቱን ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የዳዳብ እና ካኩማ የስደተኛ መጠለያዎች የተሻለ ደኅንነት ፍለጋ በሚል ከአገራቸው የተሰደዱ የበርካታ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን መጠለያዎች ናቸው።

የኬንያ መንግሥት በተደጋጋሚ እነዚህን መጠለያ ጣቢያዎች፣ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ምንጮች በመሆናቸው እዘጋለሁ ሲል ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ተግባራዊ ሳያደርገው ቆይቷል።

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ካምፖቹን የተባበሩት መንግሥታት በ14 ቀናት ውስጥ እንዲዘጋ የኬንያ መንግሥት ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ግን ምንም የተወሰደ ርምጃ የለም።

“መንግሥት ካምፖቹ መዘጋት አለባቸው ብሎ ሲናገር በጣም ነው የምንደነግጠው” የሚሉት አቶ ጀማል “... ሞራሌም ተነካ። በዚህም ምክንያት ለረዥም ጊዜ ሊቆዩ የሚችሉ እቃዎችን ማስገባት አቆምኩኝ። ምክንያቱም ቀጥሎ ምን እንደሚሆን አናውቅም። በሥራዬ ላይ ትልቅ ፈተና ነው የሆነብኝ” በማለት ስጋቱ አሁን ድረስ እንዳለ ያስረዳሉ።

ብዙዎቻችን ንግድ ውስጥ የነበርነው ለማደግ ብዙ ዕድል ነበረን። ግን ይህንን የመንግሥት ውሳኔ ስንሰማ ወደ ኋላ ተመለስን በማለትም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

አቶ አልዩም ይህ የኬንያ መንግሥት ውሳኔ ተረጋግተው ኑሯቸውን እንዳይመሩ እንዳደረጋቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከኬንያ ምርጫ አንዳች ነገር የሚጠብቁት ስደተኞች

ኬንያ በመጪው ነሐሴ ወር ምርጫ ለማካሄድ ሽር ጉዳ እያለች ነው።

ለዚህ ምርጫ የሚፎካከሩ የተለያዩ ዕጩዎች የምርጫ ቅስቃሳ ለማካሄድ ወደ ካኩማ ቢመጡም የስደተኞች ጉዳይ ርዕስ ሆኖ ሲነሳ አለመስማታቸውን አቶ አልዩ እና አቶ ጀማል ይናገራሉ።

አቶ አልዩ ከምርጫው ምን እንደሚጠብቁ ሲያስረዱ፣ የአገሪቱ መንግሥት እዚህ ያለውን የስደተኞች አያያዝ ካላስተካከለ ሁኔታችን በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይደርሳል ይላሉ።

“ሁኔታዎች ካልተስተካከሉና አገራችን ሰላም ከሆነች እኛ ራሱ እዚህ ውለን አናድርም። አሁን ግን አገራችን ያለችበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። ዕድል ካገኘን ደግሞ ወደ ሦስተኛ አገር እንሄዳለን። እኛ እዚህ አርጅተናል ተስፋ ቆርጠናል።”

አቶ ጀማል “ምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ሰዎች ወደዚህ ሲመጡ የእኛን ጉዳይ አያነሱም። ደግሞም መንግሥት ካምፖቹ እንዲዘጉ የያዘው አቋም እስካሁንም ስለመቀየሩ የገለፀው ነገር የለም። ውሳኔው ዓመት ቢሆነውም ምን ሊከሰት አንደሚችል አናውቅም” ይላሉ።

ምርጫ ለመምረጥ መብት ባይኖረንም የሚመጣው አዲስ አስተዳደር ይህንን የአገሪቱን አቋም ይቀይር ይሆን በማለት ተስፋ ያደርጋሉ።