የምማረው ከገበሬ ነው የሚሉት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይለ

ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይለ

የፎቶው ባለመብት, MU

የምስሉ መግለጫ,

ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይለ

የመቀለ ዩኒቨርሲቲ መስራች እና የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የሆኑት ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይለ፣ ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፍ የግብርና ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።

ዓለም አቀፍ የግብርና እና ላይፍ ሳይንስ ከፍተኛ ተቋማት ማኅበር [GCHERA] ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይለ እና የጌንት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ማርክ ቫን ሞንታጉ የ2021 የዓለም ግብርና ሎሬቶች በማለት ሸልሟቸዋል።

የሽልማቱ ሥነ ሥርዓትም፣ ማክሰኞ ዕለት በቻይና ውስጥ በበይነ መረም የተካሄደ ሲሆን፣ ፕሮፌሰር ምትኩ በአፈር እና ግብርና ልማት፣ በእጽዋት መአዛ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በሰሯቸው ሥራዎች መታጨታቸው ተገልጿል።

መቀለ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የእንኳን ደስ አለዎት ፕሮግራም ላይ፣ ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ “በግብርና፣ የሳይንስ ትምህት እና ሳይንሳዊ ጥናቶች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ” አድረገዋል ብሏል።

የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት በተቋረጠባት የትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙት ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይለ፣ ‘የ2021 የዓለም ግብርና ሎሬት በመሆን አሸንፈሃል፤ ሽልማቱን የምትቀበል እንደሆን አሳውቀን’ የሚለው የኢሜይል መልዕክት እስከደረሳቸው ዕለት ስለ ሽልማቱን እንደማያውቁ ይናገራሉ።

ከሳምንታት በፊት፣ ይሄንን መልዕክት ሲያዩ ‘ማጭበርበር ይሆን?’ ብለው ተጠራጥረው እንደነበር እና መደነቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ኢንተርኔት በማይገኝበት ሁኔታ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ ማወቅ አይቻልም፤ መልዕክቱም ከማላውቀው ሰው ስለሆነ የደረሰኝ ማረጋገጥ ነበረብኝ። አሁን ባለንበት ሁኔታም እንደዚህ አይነት ነገር ስለማልጠብቅ ሽልማቱ አስደንቆኛል” ይላሉ።

ከ20 ዓመታት በፊት በላቲን አሜሪካ የሚገኘው ኧርዝ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት የነበሩ እና አሁን የጂሸራ ሊቀመንበር እና ፕሬዝደንት የሆኑትን ጆሴ ዛግሉል፣ ሽልማቱ ላይ ፈርመውበታል።

ይህንን ሲመለከቱ እውነት ነው ብለው ማመን እንደቻሉ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ምትኩ “ወደ ቤት ሄጄ ባለቤቴ እና ልጄን ሳሳያቸው ሁላችንንም አስደነቀን” ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ፣ እስከ አሁን በግል እና ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የሰሯቸው ከ200 በላይ የምርምር ሥራዎችን አሳትመዋል።

ፕሮፌሰር ምትኩ፣ በ1993 ዓ.ም የመቀለ ግብርና ኮሌጅ እንዲቋቋም ያደረጉ ሲሆን፣ ከ2000 እስከ 2011 ባሉ ዓመታት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት በመሆን አገልግለዋል።

ላለፉት ለ30 ዓመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አስተዳደር እና የሰው ኃይል ግንባታ እንዲሁም በተፈጥሮ ሃብት እና የአፈር ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ፕሮፌሰር ምትኩ ማን ናቸው?

‘ሁሉን አክባሪው ምትኩ’ 

ፕሮፌሰር ምትኩ እጽዋት እና አረንጓዴ አካባቢን ስለሚወዱ የተፈጥሮ ተሟጋች ናቸው።

በሆነ አጋጣሚ ሰዎች ለጥርስ መፋቂያ ነው ብለው ሲቆርጡ፣ ወይም የመንገድ ዳር ማስዋቢያ የሆኑ ሳር እና አበባዎችን ረግጠው አልያም ቀንጥሰው ሲሄዱ፣ ውሃ በቸልተኝነት ሲፈስ ካዩ ይቆጣሉ፤ ይጣላሉ።

የእጽዋትን ነገር ካነሳን አይቀር ፕሮፌሰር ምትኩ አሁን የመቀለ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ የሚጠራው ተቋም የግብርና ኮሌጅን ሲጀምሩት 42 ተማሪዎች እና ሦስት የዲግሪ ፕሮግራም ይዘው ግራር ስር ነበር የጀመሩት።

የዩኒቨርሲቲው ስም ሲነሳም ‘የዩኒቨርሲቲው አባት’ እየተባሉ ስማቸው አብሮ ይጠቀሳል።

ከዚያም በኋላ ዩኒቨርሲቲው 31 ሺ ተማሪዎች የሚቀበልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

ባልደረቦቻቸው ስለ ፕሮፌሰር ምትኩ የግል ባሕሪ ሲናገሩ፣ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ሁሉም ሰው አስተዋጽኦ አለው ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

እድገት ውጤታማ የሚሆነው ህንጻ እና የመንገድ ግንባታን ብቻ በማብዛት ሳይሆን፣ የሰው ኃይል ልማትን ሲጨምር ነው የሚል እምነት ያላቸው ሰው ናቸውም ይሏቸዋል።

የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ "ምትኩ ማንኛውም ሰው የሚሰጠውን አስተያየት የሚቀበል፣ ወጣቶች ላይ እምነት የሚጥል፣ ተማሪዎቹ እና ሠራተኞችን የሚያከብር ሰው ነው" ይላሉ።

ቤተሰባቸውም ይህንን ይመሰክራል። በተለይ ልጆቻቸውን እንደ ትልቅ ሰው ቁጭ አድርገው የሚመካከሩ፣ ቁጣን የማያውቁ አባት ናቸው ሲሉ ይገልጿቸዋል።

‘ከገበሬ ነው የምማረው’

የፕሮፌሰሩ የምርምር ሥራዎች የአፈር ለምነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።

አብዛኛዎቹ ሥራዎቻቸው ትግራይ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆኑ፣ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኘውን የአፈር አይነት በማጥናት መጀመራቸውን ይናገራሉ።

ሕዝቡ ለረጅም ዘመናት ኑሮው ግብርና ላይ ተመሰርቶ ስለኖረ ሰፋፊ የግብርና አካባቢዎች ተሸርሽረው እና ይዘታቸውን ቀንሶ ነበር።

በተጨማሪም ክልሉ ለረጅም ዓመታት ጦርነት የተካሄደበት እና በተደጋጋሚ ድርቅ በመጠቃቱ ምክንያት ለከፍተኛ በረሃነት ተጋልጧል።

ይህንን ታሪክ በመቀየር የግብርና ምርትን ማሳደግ የሚችሉ የምርምር ሥራዎችን ማካሄድ፣ ገበሬውን መደገፍ እና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጣ የማገዝ ኃላፊነት በዩኒቨርሲቲው እና በፕሮፌሰሩ ጫንቃ ላይ ወደቀ።

“ትልቁ ፈተና ከጦርነት የወጣ ሕዝብ ስለነበረ ድልድይ ያስፈልገው የነበር። ብዙ ነገር ወድሞ መንገድ የሚባል አልነበረም። ልማት ገና የሚጀመርባቸው ዓመታትም ስለነበሩ ገበሬው ባለው መሬት ላይ የሚያገኘውን ምርት ለማሳደግ የምናግዝበት መንገድ ላይ ነው ትኩረት ያደረግነው።"

ለዚህም አርሶ አደሩ በራሱ መንገድ ማዳበሪያ እንዲያመርት፣ የራሱን የመስኖ ሥራ ልምድ ተጠቅሞ ማልማት እንዲችል ማድረግ ቀዳሚው ተግባራቸው ነበረ።

ባለፉት 30 ዓመታትም በተፈጥሮ ሃብት ልማት ከገበሬው ጋር በመስራት የግብርና ምርትን ማሳደግ፣ የአፈር ለምነት እና የውሃ ምንጮች እንዲጎለብቱ፣ የከርሰ ምድር ውሃ መጠን ከፍ እንዲል፣ የመስኖ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲያድግ እና የደን ሽፋን እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ፕሮፌሰር ምትኩ እነዚህ ሥራዎችን ወደ ዓለም አቀፍ መድረኮች በመውሰድ እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ትልቅ ሥራ አከናውነዋል።

ለዚህም ከአራት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በረሃማነት በማጥፋት ላይ በተሰሩ ሥራዎች ተሸላሚ ሆናለች።

“እኔ የገበሬን ችግር በማየት ከገበሬው ነው የምማረው፤ እነዚህ ሥራዎችን ከእሱ ተምረን ሳይንስ ጨምረን ስንሰጠው ኑሮውን የሚያሻሽል ለውጥ ማምጣት እንደሚችል አሳይተውኛል። ለውጥ ካላመጡ ደግሞ እኔ የተጠያቂነት ኃላፊነት ይሰማኛል” በማለት ምሁራን የሚሰሯቸው ጥናቶች ኅብረተሰቡን ያሳተፉ መሆን አለባቸው ይላሉ።

ሆኖም የትግራይ ክልል ተመልሶ ጦርነት፣ ስደት እና የምግብ አቅርቦት እጥረት ችግሮች ውስጥ ገብቷል። በዚህ ምክንያት በርካታ ገበሬዎች በአግባቡ ማረስ አለመቻላቸው ይነገራል።

ጦርነቱ በብዙ መልኩ ገበሬውን ጎድቶታል የሚሉት ፕሮፌሰሩ “አርሶ፣ ምርጥ ዘር ተጠቅሞ ከድህነት እወጣለሁ የሚለውን ምኞቱን አኮላሽቶታል። በርካታ ገበሬዎች ተፈናቅለው ተረጂ ሆነዋል፤ አንዳንዶቹም ተመልሰው ማረስ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል” ብለዋል።

እንደ አንድ ምሁር ሁኔታው ቢያሳዝናቸውም “ሰላም ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ፤ ተመልሰን ማልማት ላይ ደግሞ ገበሬውን እናግዛለን የሚል ትልቅ እምነት አለኝ” ይላሉ።

ከዚህ ባለፈ በጦርነቱ ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች የሚሰሯቸው የምርምር ሥራዎች መሰናከላቸው እና ተማሪዎቻቸው መበተናቸውን የሚናገሩት ምሁሩ፣ “የጀምረናቸው ሥራዎች በሙሉ ተደናቅፈዋል፤ መቀለ ዩኒቨርሲቲ ላይ የነበረው ትልቅ ላቦራቶሪ ተቃጥሏል። ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

የማይስተጓጎል የእግር ጉዞ

የሦስት ልጆች አባት የሆኑት ፕሮፌሰር ምትኩ፣ ረጅሙ ሰዓታቸውን የሚያሳልፉት በዩኒቨርሲቲ ማስተማር፣ መስክ ላይ ከገበሬዎች ጋር በመሆን ደግሞ የምርምር ሥራዎችን በመስራት ነው።

ከዚህ ውጪስ ምን ያከናውናሉ?

አልፎ አልፎ ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ ምግብ ሲሰራ ይሳተፋሉ፤ በተለይ ከአትክልት የሚሰሩ ምግቦች ላይ የሚቀድማቸው የለም።

አውዳመት ሲሆንም እንዲሁ ተፍ ተፍ ይላሉ።

የጤና ሁኔታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጠዋት ተነስተው ቁርሳቸውን በሚፈልጉት መንገድ የሚያዘጋጁት እራሳቸው ናቸው።

አብዛኛውን ጊዜ ግን ማንበብ እና ለተማሪዎቻቸውን የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማድረግ ላይ እንደሚያሳልፉ ይናገራሉ።

“የምሰራቸው ሥራዎች በደንብ የሚገባው እና የሚረዳኝ ቤተሰብ ስላለ እንጂ ቤት ውስጥ ገብቼም የምሰራቸው ሥራዎች የቤተሰብ ሰዓትን እንደሚሻሙ አውቃለሁ” ይላሉ።

ከዚህ ሁሉ ደግሞ በየቀኑ አንድ ነገር አይስተጓጎልባቸውም፤ የእግር ጉዞ ማድረግ።

“ከጓደኞቼ ጋር ቢያንስ 10 ኪሎ ሜትር ዎክ እናደርጋለን። ለጤናችን ብቻ ሳይሆን፣ ለመወያየትና ሐሳብ ለማመንጨት እንጠቀምበታለን። 23 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ያደረግኩበት ቀንም አለ፤ ረጅሙ እሱ ነው።”