ሩሲያ የኔቶ አባል በሆነችው ሊቱዌኒያ ላይ ጠንካራ ዛቻ ሰነዘረች

ሩሲያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሩሲያ የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ግዛትና የኔቶ አባል በሆነችው ሊቱዌኒያ ላይ ጠንካራ ዛቻ ሰነዘረች።

ሩሲያ ዛቻውን የሰነዘረችው ሊቱዌኒያ የጭነት ዕቃዎች በድንበሯ በግዛቷ በኩል የሩሲያ ይዞታ ወደ ሆነችው ካሊኒንግራድ እንዳያልፉ ካገደች በኋላ ነው፡፡

ሊቱዌኒያ በበኩሏ ለሩሲያ ዛቻ ምላሽ ሰጥታለች፡፡

"እኛ የአውሮፓ ሕብረትን ማዕቀብ መሠረት አድርገን ነው ክልከላ የጣልነው" ብለዋል የሊቱዌኒያ ባለሥልጣናት፡፡

ካሊኒንግራድ፣ በፖላንድና በሊቱዌኒያ መካከል ያለ አንድ የሩሲያ ግዛት ነው፡፡

ግዛቱ የሩሲያ ይሁን እንጂ ከዋናው የሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር ድንበር አይጋራም፡፡ ሆኖም ካሊኒንግራድን የአውሮፓ አባል የሆኑት ፖላንድና ሊቱዌኒያ ያዋስኑታል፡፡

ይህ ግዛት ለሩሲያ ወሳኝ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡

ሩሲያ ለሊቱዌኒያ ባስተላለፈችው በዚህ ማስጠንቀቂያ ሊቱዌኒያ ጭነቶቹ እንዲያልፉ የማታደርግ ከሆነ "ብርቱ ቅጣት" ይጠብቃታል ብለዋል፡፡

"ሩሲያ ለዚህ ጸብ አጫሪነት ሊቱዌኒያን ትቀጣለች" ብለዋል ኒኮሊያ ፓትሮቭ የተባሉ አንድ ከፍተኛ የሩሲያ ባለሥልጣን፡፡ 

ሊቱዌኒያ በበኩሏ የእኔ ሚና የአውሮፓ ሕብረትን የማዕቀብ ውሳኔ ተፈጻሚ ማድረግ ብቻ ነው ብላለች፡፡

ከባልቲክ ባሕር ኩታ ገጠም የሆነው ካሊኒንግራድ ግዛት ከሩሲያ ርቆ የሚገኝ የሩሲያ ስትራቴጂክ ግዛት ከመሆኑ ባሻገር የሩሲያ የጦር ሰፈር የሚገኝበት ነው፡፡

ይህ የምዕራብ ግዛት የ2ኛው የዓለም ጦርነትን ተከትሎ ከጀርመን ለሩሲያ የተሰጠ ሲሆን፣ በኔቶ አባል አገራት የተከበበ ነው፡፡

አንድ ሚሊዮን ሰዎች የሚኖሩበት ካሊኒንግራድ በብዛት ከሩሲያና ከአውሮፓ ሕብረት በሚመጡ ጥሬ ዕቃዎች ላይ ጥገኛ የሆነ አካባቢ ነው፡፡

ትናንት ማክሰኞ ካሊኒንግራድን የጎበኙት ሚስተር ፓትሮቭ "ይህ ምዕራቡ ዓለም የተነኮሰው ተግባር ነው፤ …ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር ተግባር ነው፤ …ሊቱዌኒያ ለዚህ ድርጊቷ ትቀጣለች" ብለዋል፡፡

ይህ ሩሲያ ደጋግማ የምትሰነዝረው የቅጣት ዛቻ ምጣኔ ሃብታዊ ይሁን ወታደራዊ  የተባለ ነገር የለም፡፡

ሆኖም የሊቱዌኒያ ዕቀባ ተከትሎ ሩሲያ በአገሯ የሚገኙትን የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደርን ጠርታ ማብራሪያ ጠይቃለች፡፡

ምናልባት ሩሲያ እንደዛተችው ሉቲኒያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ከሰነዘረች የኔቶ አባል አገራት ምላሽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡

የኔቶ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 5፣ 'የየትኛውም አባል አገር ጥቃት የሁሉም አገር ጥቃት ነው' ይላል፡፡

አሜሪካ በሊቱዌኒያ ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት አጸፋ እንደሚኖረው ይፋ አድርጋለች፡፡