ከቁርዓን ትምህርት እስከ ፒኤችዲ -የጎልማሳው ዓይነ ስውር የትምህርት ጉዞ

አቶ ጀማል አብዱል ቃድር

የፎቶው ባለመብት, Jamal abdulqadir

ጀማል አብዱልቃድር ይባላሉ። የስድስት ልጆች አባት የሆኑት ጀማል በ1960 ዓ.ም በምዕራብ አርሲ አዳባ ነው የተወለዱት።

አቶ ጀማል ከልጅነታቸው ጀምሮ የዓይን ብርሃናቸውን ማጣታቸውን ያስታውሳሉ።

ይኹን እንጂ ዓይናቸውን ማጣታቸው ትምህርታቸውን እስከ ከፍተኛ ትምህርት ለመግፋት አላገዳቸውም።

በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተማሩ ነው።

በልጅነታቸው ቁርዓን መቅራታቸውን የሚናገሩት አቶ ጀማል፣ እንዴት መነሻ ሆኗቸው አሁን የደረሱበት ደረጃ አንደደረሱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ላለፉት 24 ዓመታት፣ በመምህርነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ጀማል፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሰበታ የልዩ ፍላጎት መምህራን ኮሌጅ በእንግሊዘኛ መምህርነት እያገለገሉ ነበር።

አቶ ጀማል መጀመርያ በብሬል ማንበብን የጀመሩበትን ቀን ፈጽሞ እንደማይረሱት ይናገራሉ።

"በሕይወቴ ውስጥ በጣም የተደሰትኩበት ቀን ቢኖር ለመጀመርያ ጊዜ ብሬልን ያነበብኩበት ቀን ነው" ይላሉ።

የዓይን ብርሃናቸውን ያጡት እንዴት ነው?

አቶ ጀማል የዓይን ብርሃናቸውን ያጡት በጨቅላ እድሜያቸው ነው።

"የ5 ዓመት ሕጻን ልጅ እያለሁ ከሌሎች ልጆች ጋር እየተጫወትን ሳለ፣ የሆነ ልጅ ዓይኔ ሽፋሽፍት ላይ ወጋኝ። በዚያ ምክንያት ነው የዓይኖቼን ብርሃን ያጣሁት።" ይላሉ።

ይህ አደጋ በደረሰባቸው ጊዜ ቤተሰቦቻቸው ወደ ሕክምና ተቋም ወስደዋቸው የነበረ ቢሆንም የዓይናቸውን ብርሃን መልሶ ማግኘት ሳይቻል ቀርቷል።

"በዚያን ወቅት የአይን ብርሃኔን በማጣቴ በጣም ተደናግጠው፤ በጣም አዝነው ነበር።" የሚሉት አቶ ጀማል አባታቸው ካደጉ በኋላም 'ሀብቴ ሁሉ ጠፍቶ ዓይንህ ቢድን ኖሮ ፍላጎቴ ነበር' ይሏቸው ነበር።

አቶ ጀማል በሕክምና እርዳታ የዓይን ብርሃናቸውን መልሰው ማግኘት ባይችሉም ፊደል ለመቁጠር ጥረት ማድረጋቸውን ቀጠሉ።

መደበኛ ትምህርት እንዴት አንደጀመሩ

አቶ ጀማል እንደ እኩዮቻቸው ደብተር ይዘው ወደ ትምህርት ቤት በመሄድ መማር ቢፈልጉም የዓይናቸው ብርሃናቸውን በማጣታቸው የተነሳ ይህንን ማድረግ ሳይችሉ ቀሩ።

ቤተሰቦቻቸው ግን የእስልምና ትምህርት ወደ ሚሰጥበት በመላክ ሃይማኖታዊ ትምህርት እንድያገኙ አደረጓቸው።

"እኔ በምኖርበት የገጠር ከተማ ሌላ ዓይነስውር አልነበረም። በዚህ ምክንያት ቤተሰቦቼ የእስልምና ትምህርት ወይንም ቁርዓን እንድቀራ አደረጉ። የሃይማኖቱን ትምህርት ከጀመርኩ በኋላ ለመደበኛው ትምህርት ፍላጎት እንዳለኝ ለቤተሰቦቼ ተናገርኩ"

አቶ ጀማል ከዚያ በኋላ በአዳባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ዓይነስውር መምህር በመኖራቸው እርሳቸው ጋር በመሄድ ከፊደል ዘር ጋር ተዋወቁ።

በወቅቱ በአዳባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ግለሰብ አቶ ጀማልን የብሬል ትምህርት በማስተማር የመሪነት ሚናውን ተጫውተዋል።

ከዚያ በኋላም በብሬል ገጾች ላይ ተከትቦ የተቀመጠ እውቀትን ማንበብ ቻሉ።

"በሕይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ ደስ የተሰኘሁት ብሬል ማንበብ የጀመርኩ ቀን ነው።"

ከዚያ በኋላ በሰበታ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ገብተው ለመማር እድል አገኙ።

የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በዚያው ሰበታ ጨረሱ።

የከፍተኛ ትምህርታቸውን ጉዞ የጀመሩት ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በዲፕሎማ በመመረቅ ነው። በመቀጠልም የመጀርያ ዲግሪያቸውን እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተምረው አጠናቅቀዋል።

አቶ ጀማል የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነት እና ኮሙኑኬሽን አግኝተዋል።

ለ24 ዓመት በማስተማር ሙያ ያሳለፉ ሲሆን፣ ለአምስት ዓመታት ደግሞ በኦሮምያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ውስጥ መስራታቸውን ይናገራሉ።

አቶ ጀማል በሕይወታቸው ውስጥ የዓይናቸውን ብርሃን በማጣታቸው ምክንያት ያዘኑበትን ቀን ሲያስታውሱ፣ ለሁለተኛ ዲግሪያቸው የመመረቂያ ወረቀት ጽፈው ባስረከቡበት ወቅት፣ የጽሑፍ ግድፈት እንዳለው ሲነገራቸው እነደሆነ ያስታውሳሉ።

እነዚያ ግድፈቶች በቀላሉ መስተካከል ይችሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ይኹን እነጂ የሶስተኛ ዲግሪያቸውን በሚማሩበት ወቅት በቴክኖሎጂ እና በሰው ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ይናገራሉ።

"ፐፒኤችዲ ወይንም የሶስተኛ ዲግሪሕን ስትማር የተለያዩ የፍልስፍና መሰረቶችን ማንበብ ይጠይቅሃል" የሚሉት አቶ ጀማል ኮምፒውተር አዳፕቲቭ የሚባል ቴክኖሎጂ በመጠቀም የጥናት ወረቀታቸውን እየሰሩ አንደሆነ እናገራሉ።

በዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ካገኙት ጠቀሜታ በመነሳትም ሌሎች እንደርሳቸው የዓይን ብርሃናቸው የተጎዳ ተማሪዎች በዚህ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ይመክራሉ።

'ለሌሎች ዓይነ ስውራን ሞዴል እሆናለሁ'

አቶ ጀማል የፒኤችዲ ትምህርታቸውን እንዲማሩ የደገፋቸው የኦሮምያ ትምህርት ቢሮ እንዲሁም የሰበታ የልዩ ፍላጎት መምህራን ኮሌጅ ናቸው።

"ወደፊት ለሌሎች ዓይነ ስውራን ተማሪዎች ሞዴል በመሆን በመምህርነት ለመቀጠል ፍላጎት አለኝ" ይላሉ።

በዚሁ ዓላማቸውም ስኬትን እያገኙ መሆኑን አክለው ያነሳሉ።

ዓይነስውራን ተማሪዎች ያገኙትን አማራጮች ተጠቅመው በትምህርታቸው ሲገፉ፣ ማሕበረሰቡ ደግሞ እነርሱን በስራ ላይ በማሳተፍ እድል ከሰጣቸው የትኛውንም ዓይነት ችግር ማሸነፍ ይችላሉ ብለው እነደሚያምኑ ይገልጻሉ።

አቶ ጀማል አሁን የጀመሩትን ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ዓይነስውራንን ሊረዱ የሚችሉ የተለያዩ ምርምሮች ላይ ማተኮር ፍላጎት አላቸው።