ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ ማስገባት ትታ ወደ ውጭ መላክ ትችላለች?

የስንዴ ማሳ

የፎቶው ባለመብት, PM ABIY/FB

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ መምሬ መሠረት፣ ከዚህ በፊት ስንዴ ያመርቱ የነበረው በክረምት ዝናብ ብቻ ተጠቅመው ነበር።

ማሳቸው ውሃ የሚገባው በመሆኑ በበጋው ወራት ሽንኩርት እና ቲማቲም እያመረቱ ለገበያ ያቀርቡ እንደነበረም ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት ግን ‘ለምን አዲስ ነገር አልጀምርም’ በማለት በበጋ መስኖ ስንዴ ዘርተው ለማየት ወሰኑ።

“ይህ ነገር መሆን አለበት ብዬ በራሴ ተነሳሽነት የበጋ ስንዴ ማምረት ጀመርኩ። በዚያን ወቅት አንድም ሰው በበጋ ስንዴ መዝራት የጀመረ የለም። ፈጣሪ ይመስገን ተሳክቶልኛል” ይላሉ አቶ መምሬ።

ይህ የበጋ ስንዴ ምርት ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ እና እየሰፋ እየመጣ መሆኑን አቶ መምሬ አክለው ተናግረዋል።

ልክ እንደ አቶ መምሬ ሁሉ የሉሜ ወረዳው አርሶ አደር አቶ እንግዳ ብሩ፣ በበጋ መስኖ ተጠቅመው ጥሩ የስንዴ ምርት እንዳገኙ ይገልጻሉ።

እኚህ አርሶ አደር በዚህ ዓመት ብቻ ከስድስት ሄክታር መሬት 320 ኩንታል ስንዴ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፣ አዲስ ነገር ስለሆነ በፍርሃት እንደጀመሩት በመግለጽ አቶ እንግዳ “ያገኘነው ምርት ሸጋ ነው”  ብለዋል።

ይህ የበጋ ስንዴ ከክረምቱ ወቅት ምርት በላይ ትርፋማ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ እንግዳ ግሪሳ (የወፍ መንጋ)፣ የማዳበሪያ ወጪ እና ነዳጅ መፍትሔ ቢያገኝ ስንዴን በበጋ ማምረት “በጣም ትርፋማ” መሆኑን ገልፀዋል።

በመጀመሪያ የምርት ዓመት በአንድ ሄክታር ላይ ብቻ ስንዴ ዘርተው የነበሩት አቶ መምሬ፣ መንግሥት ያቀረበላቸውን ድጋፍ በማየት በዚህ ዓመት ወደ 5 ተኩል ሔክታር አሳድገውታል።

የበጋ ስንዴ በክረምት ወቅት ከሚመረተው በተሻለ ምርታማ እንደሆነ የሚናገሩት አርሶ አደሩ፣ ከአንድ ቀርጥ (የሄክታር አንድ አራተኛ) ከ16 ኩንታል በላይ ማግኘት እንደሚቻል ይናገራሉ።

አቶ መምሬ እንደሚሉት ከአንድ ሄክታር እስከ 64 ኩንታል ይገኛል።

ሽንኩርት እና ቲማቲም ማምረት አቁመው ወደ ስንዴ በመግባታቸው ያለውን ልዩነት ሲገልጹ “ይህ የበጋ ስንዴ ምርት ሥራው አድካሚ አይደለም። ትንሽ ማዳበርያ ብቻ ይፈልጋል እንጂ ሌሎች ብዙ ወጪዎች ስለሌሉበት ትርፋማ ነው” ብለዋል።

አቶ መምሬ ካገኙት የበጋ ስንዴ ምርት 250 ኩንታል ያህሉን መንግሥት በጥሩ ዋጋ (በኩንታል 3680) እንደተረከባቸው ጨምረው አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከራስ ፍጆታ አልፎ ወደ ውጪ ለመላክ የታቀደው ስንዴ

እንደ አሜሪካ ግብርና ቢሮ መረጃ ከሆነ በኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ዘርፍ ትልቅ እመርታ እያሳየ እና ምርታማነቱ እየጨመረ ነው።

የአሜሪካ የውጭ ግብርና ቢሮ ሪፖርት ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2022/2023 ዓመት ውስጥ 5.7 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ታመርታለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል።

ይህም ካለፈው የምርት ዘመን በ3.26 በመቶ ከፍ ያለ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት የስንዴ ምርት እንዲጨመር በርካታ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ያስታወሰው ይህ ሪፖርት፤ የኤክስቴንሽን ድጋፍ፣ የመስኖ ልማት፣ በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ የእርሻ ሥርዓት እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶች እንደሚያቀርብም ዘርዝሯል።

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት 70 በመቶ ያህል የአገር ውስጥ ፍላጎቷን የምታመርት ሲሆን፣ 30 በመቶ ያህሉን ደግሞ ከውጭ እንደምታስገባ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከውጭ ከምታስገባው የተወሰነውን ስንዴ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት የምትገዛ ሲሆን፣ ቀሪውን ደግሞ ከአሜሪካ በእርዳታ እንደምታገኝ የአሜሪካ የውጭ ግብርና ምርት ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ኢትዮጵያ በ2023 (እኤአ) ያላትን የስንዴ ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት ለሟሟላት እና ከባሕር ማዶ የምታስገባውን ለማስቀረት አቅዳ እየሰራች መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።

ይህንንም ለማሳካት በመላ አገሪቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት 1.3 ሚሊዮን አርሶ አደሮች በ30 ሺህ ክላስተር ተደራጅተዋል።

እያንዳንዱ ክላስተርም የተሻሻለ ዘር እንዲሁም ለአካባቢው ተስማሚ የሆነ ማዳበርያ እንዲጠቀም ይደረጋል።

እንዲሁም የኤክስቴንሽን ሠራተኞች ክትትል እና ድጋፍ በምርት ስብሰባ ወቅትም ብክነት ለመቀነስ የማሽን ድጋፍ ተደርጓል።

በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የስንዴ ምርት ጉዳይን የሚከታተሉት ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ፣ ክልሉ በስንዴ ምርት ላይ ዕቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው የስንዴ ምርትን ለመጨመር የተያዙትን አራት መሠረታዊ እቅዶች ሲያብራሩ “በምግብ ራስን መቻል፤ ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ ማምረት፣ በአገር ውስጥ የሚመረተውን ደግሞ ወደ ውጪ መላክ እና በእነዚህ ውስጥ የሥራ ዕድል መፍጠር” መሆናቸውን ገልፀዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፣ በመጀመሪያው ዓመት ላይ ከምርምር ተቋማት ጋር በመሆን ውጤታማነቱን በምርምር ለማረጋገጥ ተችሏል ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, PM ABIY/FM

ኢትዮጵያ እንዳቀደችው ስንዴ ወደ ውጭ መላክ ትችላለች?

ግንቦት 2022 እኤአ የቡድን ሰባት አገራት ሚኒስትሮች በጀርመን ባካሄዱት ስብሰባ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት፣ አክንዊሚ አዲሲና ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ስንዴ ከውጪ እንደማታስገባ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለአፍሪካ በሚያቀርበው የግብርና ቴክኖሎጂ ፕሮግራም አማካኝነት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለኢትዮጵያ አድርጓል።

በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ምርት በመጨመሯ በዓመት 26 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምርቷ ማደግ ችሏል ብለዋል።

ካለፈው ዓመት ጀመሮ ኢትዮጵያ ከውጭ አለማስገባቷን የሚናገሩት ፕሬዝዳንቱ፣ ለሚቀጥለው ዓመት በ2 ሚሊዮን ሄክታር ላይ ለማምረት ዕቅድ ስላላት ይህንን ምርት በ2023 ለጎረቤት አገራት ጅቡቲ እና ኬንያ ለመሸጥ ማሰቧን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሕዝብ ተወካዮች በበጋ ስንዴ ከፍተኛ ምርት መገኘቱን ገልፀው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የስንዴ ምርት እንዴት እንደተገኘ ሲያብራሩ መስኖ እንዲሁም የክላስተር ግብርናን በአስረጂነት ጠቅሰዋል።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የምታመርተውን ስንዴ ብትጨምርም በአገሪቱ ውስጥ በተከሰቱ የተለያዩ ግጭቶች የተነሳ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የዕለት እርዳታ የሚጠብቁ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።

እንዲሁም ለ19 ወራት የቀጠለውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የምግብ እህል እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥርን ከፍተኛ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳየው በ2022/2023 ብቻ 10 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የዕለት እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ አቁማ ወደ ውጭ መላክ ለመጀመር የያዘችው ዕቅድ አጣብቂኝ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል የሚል ስጋት አጭሯል።

ኢትዮጵያ እኤአ በ2023 ከባሕር ማዶ የምታስገባውን ስንዴ ለማቆም ማቀዷን ያስታወሰው የአሜሪካ ግብርና ቢሮ ሪፖርት በበኩሉ ባለው ውስን ሀብት እና ቴክኖሎጂ አንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት ያለውን ተግዳሮት ሲገልጽ “ከተጨባጭ እውነታው የራቀ እና ሊሳካ የማይችል” ብሎታል።።

ኢትዮጵያ በእርዳታ የምትቀበለውን ስንዴ ጨምሮ በየዓመቱ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጭ ታስገባለች።

ለዚህ የስንዴ ግዢም በየዓመቱ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደምታደርግ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊው አቶ ጌቱ እንደሚሉት በክልላቸው የስንዴ ምርት ከዚህ በፊት ከነበረው ከ42 እስከ 45 በመቶ ጨምሯል።

ባለፈው የምርት ዓመት የተገኘው ውጤት በመነሳትም በዚህ ዓመት 607 ሺህ ሄክታር የሚሆነውን በሁለት ዙር ለማምረት እንዳቀዱ የሚናገሩት አቶ ጌቱ፣ በዚህም በክልሉ 17 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃል ኪዳን ሽፈራው ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን፣ በዚህ ዓመት ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በልዩ ትኩረት በማልማት በበጋ መስኖ ስንዴ እንዲሸፈን መደረጉን ገልፀዋል።

አክለውም በ35 ሺህ ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል ተሰብስቦ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል የሚሆን ስንዴ ምርት ተገኝቷል ብለዋል።

“ከዚህ በመነሳት ስንዴን ስለወደድን ብቻ ሳይሆን ይህ ሰብል በተለያዩ የአገራችን የተለያዩ አየር ንብረቶች ሁሉ የሚመረት መሆኑን ስተለተረዳን በምግብ ራስን መቻል ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ ለመላክ አንደምንችል አረጋግጠናል” ይላሉ።