ከፈታኝ የየመን ስደት ጉዞና ስቃይ በኋላ ከቤተሰቦቹ ጋር መቀላቀል ያልቻለው ወጣት

ገና የአፍላ ጎረምሳ ሳለ ወደ የመን ተሰድዶ የነበረው ዲኔ አሕመድ ኩላሊቶቹ ስራቸውን በማቆማቸው ወደ አገር ቤት መመለሱን ይናገራል

የ18 ዓመቱ ዲኔ አሕመድ ከኢትዮጵያ ከመውጣቱ በፊት በትምህርቱ ጎበዝ ተማሪ ነበር።

አባቱ በትምህርቱ እንዲገፋ በጣም ያበረታቱት ነበር። ስድስተኛ ክፍል ሳለ ሦስተኛ ከመውጠቱ በስተቀር በየክፍሉ አንደኛ እና ሁለተኛ ነበር የሚወጣው።

ሰባተኛ ክፍል ደርሶ አንድ ወር እንደተማረ በአካባቢው በነበረ ግጭት የተነሳ ትምህርት ቤቱ ተዘጋ።

ከዚያም የሚወደውን ትምህርት መማር 'ካልቻልኩ ለምን ከአገር ውጥቼ ራሴን አላሻሽልም' ብሎ ወደ ውጪ ማማተር ጀመረ።

ከዚያ በኋላም ግብፅ ለሚገኝ እና አብሮት ለተማረ አንድ ደላላ ደወለለት።

እርሱ ደግሞ ድሬዳዋ ለሚገኝ ለሌላ ደላላ ደወለለት።

ለመሄጃም 15 ሺህ እንደሚያስፈልግ ደላላው ቢነግረውም፣ በወቅቱ እጁ ላይ የነበረው 3000 ብር ብቻ ነበር።

ዲኔ ተወልዶ ያደገበትን ምሥራቅ ወለጋ ለቆ አስከ ድሬዳዋ የሚያደርሰውን ከፍሎ በቀረው ደግሞ ልብስ ገዛዝቶ በእጁ ላይ ምንም ገንዘብ አልቀረውም ነበር።

ዲኔ የስደት ጉዞውን እንዲህ በአንደበቱ ይተርከዋል. . .

ውሃ ተሰፍሮ የሚቀርብበት የስደት ጉዞ

ድሬዳዋ ከደረስኩ በኋላ ከሌሎች ስደተኞች ጋር ደላላዎቹ ወደ ሶማሊያ በረሃ ወሰዱን።

እዚያም የምንበላው እና የምንጠጣው አልነበረንም።

ዛሬ ከበላን በሚቀጥለው ቀን ሳንበላ ልንውል እንችላለን።

ውሃ ተሰፍሮ ነበር የሚቀርብልን። አንድ ሊትር ለሁለት ሰው ነበር የሚሰጠው።

ሶማሊያ ከደረስን በኋላ ደግሞ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲላክ በማለት ለቤተሰቦቻቸን አስደወሉን።

ገንዘብ የሌላቸውን ወንድ ሴት ሳይሉ ይደበድቧቸው ነበር።

በዚያ ዓይነት ሁኔታ እየተቸገርን ሁለት ወር ቆየን።

ብዙ ልጆችም ከአጠገባችን ሞቱ። ገሚሶቹ በጂቡቲ በኩል እኛን ትተው ሄዱ።

እኛ ደግሞ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሄድ ሁኔታዎች እየተመቻቸልን እያለ እኔ ታመምኩ።

በረሃ ውስጥ ለረዥም ቀናት ከመጓዛችን የተነሳ፣ እንዲሁም ውሃ እና ምግብ በማጣት በጣም ተዳክሜ ነበር።

ከእኛ ጋር ወደ ሳዑዲ ለመጓዝ ከቀሩት መካከል 450 የሚሆኑት ሞተዋል።

ከእነዚያ መካከልም ስማቸውን የማውቃቸው ልጆች ይገኙበታል።

‘ከእነርሱ ማምለጥ አይቻልም’

ቤተሰቦቻችን ገንዘብ የሌላቸው ከሆነ ስልክ ያስደውሉና እየሰሙ ይደበድቡናል።

የሚፈልጉት ገንዘብ ካልተላከ አንድ ዓመት ቢሆንም ያስቀምጡናል እንጂ መውጫ የለም።

እየደበድቡን እጃቸው ላይ ስንደክም ደግሞ ወደ መኪና መንገድ አውጥተው ይጥሉናል።

እኔ ከዚያ በኋላ ነው ለቤተሰቦቹ ደውዬ ደላላ አጅ ላይ መሆኔን እና ገንዘብ እንዲልኩልኝ የጠየኳቸው።

እነርሱም ወዲያውኑ ከተለያየ ቦታ አሰባበስበው ገንዘቡን ላኩልኝ።

መጀመሪያ ላይ ቤተሰቦቼ ተመለስ ብለውኝ ነበር፤ እኔ ነኝ እምቢ ያልኩት።

ቤተሰቦቼ 15 ሺህ ሲልኩልኝ ደላሎቹ ከዚያ አንስተው መንገድ አስጀመሩን።

በበረሃ ውስጥ አንድ ሳምንት ሙሉ በእግር ሄድን። በመሸብን ስፍራ እያደርን ሲነጋ ደግሞ ተነስተን ጉዞ አንቀጥል ነበር።

ከአንድ የባሕር ዳርቻ እንዳደረሱን፣ ሌላ ቡድን ከኋላችሁ ስላለ ከእነርሱ ጋር ስለምትሄዱ በማለት አንድ ሰዋራ ስፍራ አጉረው አስቀመጡን።

ከመካከላችን ተስፋ ቆርጠው ወደ ኋላ የሚመለሱ ነበሩ።

ገሚሶቹ ደግሞ ከእኛ እኩል መራመድ አቅቷቸው በረሃ ውስጥ ቀርተዋል።

ደላሎቹ የሚፈልጉትን ገንዘብ ካገኙ፣ በማንኛውም ቦታ ብንሞት ጉዳያቸው አይደለም።

ከባሕሩ ዳርቻ ላይ ከደረስን በኋላ ደግሞ ሌሎች ደላሎች ወደ የመን ለማሻገር ገንዘብ ይጠይቃሉ።

ሲፈልጉ መቶ ሺህ ብር አምጡ ይላሉ። በተለይ በረሃ ውስጥ ሰው በሌለበት አስረው የሚያሰቃዩበት ቦታ አላቸው።

ገንዘብ የለኝም ከተባሉ ስትደክም አውጥተው ይጥሉሃል። በሆነ አጋጣሚ የተባበሩት መንግሥታት ሰዎች ካላገኙ በስተቀር በየመንገዱ ላይ የሚያልቁት የትየለሌ ናቸው።

ሰላም ማጣት የወለደው ጭንቀት

አገሬ እያለሁ ተማሪ ነበርኩ። እናትና አባቴ ጋር ሆኜ ነበር ስማር የነበረው።

በኋላ ላይ ከሰላም ማጣት የተነሳ ሄደን የምንማርበት ቦታም አልነበረም።

በዚህ ሁኔታ ነበር ደብተሬን እና መጽሐፍቶቼን፣ ወላጆቼን ትቼ ወደ የመን ያቀናሁት።

ወደ የመን የሄድኩት ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

በሶማሊያ በረሃ በእግር ጉዞ፣ በውሃ ጥም እና በረሃብ የተጎዳው ሰውነቴ አልቻለም፤ ታመምኩ።

የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ሆስፒታል ካስገቡኝ በኋላ ኩላሊቶቼ ሥራቸው መስተጓጎሉ ተነገረኝ።

በተለይም የመን ከገባሁ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት (የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት) ሰዎች ናቸው ወስደው ሲያሳክሙኝ የነበሩት።

በየመን የኩላሊት እጥበት ሲደረግልኝ ቆየሁ።

ከአገሬ ስወጣ ሰርቼ ተሻሽዬ ትልቅ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብዬ ነበር። ነገር ግን እንዳሰብኩት አልሆነልኝም።

ከዚያ ሁሉ ፈታኝ ጉዞ በኋላ ለህመም በመዳረጌ ነበር።

የመን ደርሼ ሆስፒታል ከገባሁ በኋላ የአይኦኤም ሰዎች ወደ አገር ቤት ለመመለስ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻችሉኝ ይነግሩኝ ነበር።

እኔ ግን ሳዑዲ አረቢያ ካልሄድኩ በስተቀር ሞቼ እገኛለሁ አልኩኝ።

በሆስፒታሉ ውስጥ ሐኪሞች ይመክሩኛል፤ በዚሀ እድሜህ ሄደህ መንገድ ላይ ከምትቀር ወደ አገርህ ተመልሰህ እናትና አባትህ ጋር እንድትኖር አጥብቀን እንመክርሃለን ይሉኝ ነበር።

እውነቱን ለመናገር እንደ አባት ነበር የሚረዱኝ፤ የሚመክሩኝ። ውለታቸውን ፈጣሪ ይመልስ።

የተባበሩት መንግሥታት ሰዎች ሆስፒታላቸው በማስገባት አክመው ይንከባበከቡኝ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጉዞ ወደ አገር ቤት

በስደት አገር እያለ ብዙ ልጆች ከአጠገቤ ሞተዋል። ወደ ሳዑዲ በመሄድ ላይ ሳሉ ተመትተው፣ የመን እኔ የተኛሁበት ሆስፒታል ከመጡ በኋላ የሞቱ ብዙ ናቸው።

ከዚያ በኋላ ነው ከዚህ ይልቅ አገር ቤት መመለስ ይሻለኛል ብዬ የወሰንኩት።

ወደ አገር ቤት የተመለስኩ ቀን በጣም ትልቅ ደስታ ተሰምቶኝ ነበር።

እዚያ በነበርኩበት ወቅት ከቤተሰቦቸ ጋር መገናኘት አልችልም ነበር።

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩ በኋላ ግን ከቤተሰቦቼ ጋር በስልክ ተገናኝቻለሁ።

ይኹን እንጂ እኔ ከአገር ከወጣሁ በኋላ አካባቢያችን ሙሉ በሙሉ በግጭት የተነሳ እንዳልነበር ሆኗል።

ቤተሰቦቼ በአሁኑ ወቅት መኖሪያ ቤታቸውን እና ያላቸውን ነገር ሁሉ አጥተው፣ ተፈናቅለው ወደ ሌላ አካባቢ ሄደዋል።

መጥቼ ለቤተሰቦቼ የደወልኩ ቀን ከብቶቻቸውን ሀብታቸውን እና ያላቸውን ነገር ሁሉ ትተው ነፍሳቸውን ለማትረፍ በመሸሽ በሰው እጅ ላይ ወድቀው እንደሚገኙ ነገሩኝ።

ቤተሰቦቼ መፈናቀላቸውን በሰማሁ ጊዜ በጣም አዘንኩኝ። እኔ ላደርግላቸው የምችለው አንድም ነገር የለም።

እኔ ከአገር እንደወጣሁ ኩላሊቴን ስለታመምኩ፣ አሁንም ሕክምና ላይ በመሆኑ ሰርቼ ልደርስላቸው አልታደልኩም።

አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ስደውልላቸውም፣ ‘እንዴት እንደምንመጣ ቸግሮን ነው እንጂ መጥተን ብናይህ ጥሩ ነበር’ ይላሉ።

እንደ ሃሳባቸው ቢሆን ከመጣሁ ዕለት ጀምሮ መጥተው ቢያዩኝ ይወዱ ነበር። ነገር ግን እኔን መጥቶ ለማየት የሚያስችል ገንዘብ እጃቸው ላይ የለም።

አሁን እኔም ወደ ትውልድ ስፍራዬ ብመለስ የምሄድበት ቦታ ስለሌለኝ ቅርብ ወደ ሆነው ከተማ፣ ነቀምቴ አካባቢ ተመልሼ ሰርቼ የምኖርበት ትንሽ ነገር ባገኝ አልያም ያቋረጥኩትን ትምህርቴን ብቀጥል ደስ ይለኛል።