በአውሮፓ የቦክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው ትውልደ ኢትዮጵያዊ

ጋብርኤል ዶሰን በግጥሚያ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዚህ ዓመት አርሜኒያ ውስጥ በተካሄደው የአውሮፓ የቦክስ ሻምፒዮና ላይ አየርላንድን ወክለው በቡጢው መድረክ ለመፎካከር ከተሰለፉ መካከል ጋብርኤል ዶሰን አንዱ ነበር።

ትውልደ ኢትዮጵያዊው ጋብርኤል በዚህ ስፖርት በአየርላንድ ውስጥ ዝናው ከፍ ያለ ነው።

በአርሜኒያ በተካሄደው የቦክስ ሻምፒዮና ላይም ስለብቃቱ መገናኛ ብዙኃን በአንድ ድምጽ ተርከዋል።

የዶሰን ፈጣን ቡጢዎች፣ ተጋጣሚዎቹን ለመከላከልም ሆነ ለማጥቃት ፋታ ነስተው መታየታቸው ተመስክሯል።

እነርሱ ጋብርኤልን፣ ጋቢ እያሉ ያቆላምጡታል።

የጋልዌዩ ቡጢኛም የሚሉትም አሉ። መኖሪያ አካባቢውን በማጣቀስ።

ጋብርኤል ለአገሩ አየርላንድ ወርቅ በማምጣት ባንዲራዋ ከፍ ብሎ አንዲውለበለብ፣ ስሟ በቡጠኞች እና በሻምፒዮናው አዘጋጆች ዘንድ እንዲናኝ አድርጓል።

የ22 ዓመቱ ጋቢ፣ የወርቅ ሜዳልያውን ያጠለቀው እንግሊዛዊው ሉዊስ ሪቻርድሰንን አሸንፎ ነው።

ሉዊስ ከጋቢ በቀኝ በኩል የሚሰነዘርበትን ፈጣን ቡጢ መቋቋም አለመቻሉን በቦክስ ሜዳው ላይ እና ዙሪያ የነበሩ ሁሉ ታዝነበዋል።

ቢቢሲ ጋብሬል ዶሰንን ስለ ድሉ ሲጠይቀው፣ “ጥቁር አፍሪካዊ የኢትዮጵያ ልጅ፣ ሆኜ በቦክስ የአውሮፓ ሻምፒዮና በመሆኔ ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል” ብሏል።

በዚህ ድል በኩራት ልባቸው ሐሴት ካደረገ ሰዎች መካከል ደግሞ እናቱ ምሥራቅ ተስፋዬ አንዷ ነች።

“ልጄ እኔን እና ቤተሰቦቼን ብቻ ሳይሆን፣ . . .አጠቃላይ ጥቁር አፍሪካውያንን አኩርቷል። የአውሮፓ ሻምፒዮና መሆኑ ለየት ያለ ስሜት አለው” ትላላች።

ጋብርኤል በዚህ ውድድር ላይ የወርቅ ሜዳልያ በማጥለቅ ሻምፒዮና ለመሆን በመጀመሪያ የስፔን ተወዳዳሪውን፣ በመቀጠል የቡልጋርያን፣ ወደ ፍጻሜ ለማለፍ ደግሞ የኖርዌይ ተጋጣሚዎቹን በዝረራ አሸንፏል።

“አሁን እኔ በቦክስ የአውሮፓ ሻምፕዮን ነኝ። ነገር ግን ያሸነፍኩ ቀን ለማመን ደቂቃዎች ፈጅቶብኛል። ጥቁር አፍሪካዊ፣ የአየርላንድ ዜጋ ሆኜ፣ ደግሞም ከኢትዮጵያ የተገኘሁ ሆኜ በአውሮፓ መድረክ ላይ ሻምፒዮና መሆኔ፣ በጣም አስገርሞኛል። በዚያ ቅጽበት የተሰማኝን መግለጽ ከባድ ነው” ይላል ጋብርኤል።

እናቱ ምሥራቅ ተስፋዬ ደግሞ፣ ውድድሩ መክፈቻ ላይ ጋብርኤል ከተጋጣሚው ጋር ሲገናኝ አየርላንዳውያን በአጠቃላይ በጉጉት ሲጠብቁ እንደነበር አስታውሳለች።

ሲያሸንፍ የተሰማቸውንም ስትናገር  “ዜጎቻቸውን በሙሉ ይወዳሉ። ጥቁር ነጭ ሳይሉ። እርሱ ሲያሸንፍ መላ አገሪቱ ላይ ትልቅ ደስታ ነበር” ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, Misrak Tesfaye

የምስሉ መግለጫ,

ጋብርኤል ዶሰን በአርሜኒያ በተካሄደው የአውሮፓ ቦክስ ሻምፒዮና ላይ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል

ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ ሻምፒዮን

ጋብርኤል የተወለደው አይቮሪኮስት ውስጥ ነው።

አባቱ የላይቤሪያ ዜግነት ያለው ሲሆን በእናቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነው።

ከዓመታት በፊት እናቱ በአይቮሪኮስት በስደተኝነት ትኖር ነበር። ያኔ ነው የዶሰን አባት እና ምሥራቅ የተገናኙት።

ዶሰን እና ምሥራቅ ተጋብተው ጋብርኤል በተወለደ በሁለት ዓመቱ ወደ አየርላንድ አመሩ።

ጋብርኤል ዘጠኝ ዓመት ሲሞላው ደግሞ የቦክስ ሥልጠና መውሰድ ጀመረ።

በ16 ዓመቱ ለአየርላንድ ታዳጊ ቡድን ተመርጦ፣ በአውሮፓ መድረክ አገሩን አየርላንድን በመወከል ለንደን ላይ ተወዳደረ።

እኤአ በ2019 የአየርላንድ ብሔራዊ ቦክስ ውድድር ላይ ተሳትፎ በአንደኝነት ማሸነፍ ችሏል።

ጋቢ ገና ስፖርት ሲጀምር ‘በኪክ ቦክሲንግ’ እንደነበረ ይናገራል።

ከቦክስ በተጨማሪ ዋና፣ እግር ኳስ እንዲሁም ቴክዋንዶ የእርሱ የስፖርት ምርጫዎች ናቸው።

በቴክዋንዶ ስፖርትም የጥቁር ቀበቶ ማግኘቱን ለቢቢሲ ገልጿል።

እድሜው 19 ሲሞላ፣ ወደ ቦክስ አመዝኖ ለብሔራዊ ቡደን ተመረጠ።

ጋብርኤል በቦክስ ቡድን ውስጥ ታቅፎ ሥልጠና ሲያደርግ መቆየቱን ይናገራል።

ከአየርላንድ ብሔራዊ ቡድን ጋር በመሆን ደግሞ ከማክሰኞ እስከ አርብ ልምምድ ያደርግ ነበረ።

የፎቶው ባለመብት, Misrak Tesfaye

የምስሉ መግለጫ,

ጋብርኤል ዶሰን ከቤተሰቡ እና ከጓደኞቹ ጋር

በስፖርት ፍቅር የወደቀው ቤተሰብ

ጋብርኤል ለቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን፣ አረን ዶሰን የሚባል ታናሽ ወንድም አለው።

አረን በእግር ኳስ ብቃቱ ይታወቃል። የእንግሊዙ ቼልሲ እግር ኳስ ቡድን ለታዳጊ ክለቡ መልምሎት እንደነበር እናቱ ምሥራቅ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት ተናግራለች።

“እኔም ከእርሱ ጋር መሄድ ስለነበረብኝ ለሌሎች ልጆቼ ብዬ መሄድ አልቻልኩም። በዚህ ምክንያት ይህ ዕድል አመለጠው። ለሌሎቹ በማሰብ ነው እዚህ የቀረሁት” ትላለች።

ነገር ግን አረን፣ በአሁኑ ወቅት ለጎልዌይ ከተማ ስለሚጫወት “አሁንም ዕድል አለው ብዬ አምናለሁ”  ስትል ተስፋዋን ተናግራለች።

የጋብርኤል እህት ኢቭ ዶሰን ደግሞ 17 ዓመቷ ሲሆን፣ በእግር ኳስ ለአየርላንድ ከ19 ዓመት በታች የእግር ኳስ ቡድን ተመርጣለች።

አንድ የስኮትላንድ እግር ኳስ ቡድን ሊያስፈርማት ጠይቋት የነበረ ሲሆን፣ ትምህርቷን መጨረስ እንዳለባት ቤተሰቡ በመወሰኑ እናቷ ወደ ስኮትላንድ እንዳትሄድ እንደከለከለቻት ለቢቢሲ ተናግራለች።

እናታቸው ምሥራቅ ልጆቿ ለስፖርት ስላላቸው ፍቅር ስትጠየቅ፣ “በአንድ ሳምንት ሰባቱንም ቀን መኪና ውስጥ ነው ውለን የምናድረው፣ መኪናችንን እንደ ቤት ነው የምንጠቀመው፣ ቀን ቀን ትምህርት ቤት ይውላሉ። አድርሼያቸሁ እመልሳቸዋለሁ።

“ከዚያ በኋላ ደግሞ ለሥልጠና ወደ ተለያዩ ቦታዎች አደርሳቸዋለሁ። በየሁለት ሳምንቱ ደግሞ ወደ ተለያዩ ቦታዎች እወስዳቸዋለሁ። እኔ ደግሞ እነርሱን ለማሳደግ እና ለማስተማር ሥራ እሰራለሁ። ሕይወታችን ይህንን ነው የሚመስለው” ትላለች።

ጋብርኤል እዚህ ስኬት ላይ ለመድረስ ከ10 ዓመት በላይ ወስዶበታል። አሁን የልፋቱን ውጤት በማየታቸው ቤተሰቡ ደስተኞች ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Misrak

የምስሉ መግለጫ,

የጋብርኤል እህት በእግር ኳስ ተጫዋችነቷ ትታወቃለች

ጋቢ ከአርሜኒያ ወርቅ አሸንፎ ወደ አየርላንድ ሲመለስ ቤተሰቦቹ እና የእግር ኳስ ቡድኑ ደማቅ አቀባበል አድርጎለታል።

ይህ ግን ለእናቱ ምሥራቅ ተስፋዬ ስሜት የሚበርዝ ነበር። ኢትዮጵያ ወገኖቹ መካከል ቢሆን ይሄኔ ደስታውና ሆታው የተለየ ነበር ስትል አስባ እንደ ከፋት ለቢቢሲ ተናግራለች።

እናት ምሥራቅ ለላለፉት 11 ዓመታት ልጆቿን ብቻዋን ማሳደጓን ትናገራለች።

“የልጆቼን ሕልም ለማሳካት ቀንና ሌሊት ነው የምሰራው። አንዳንዴ ማሽን አልያም ሰው መሆኔን እጠራጠራለሁ፤ እራስ ደካማ ሆኖ ልጆችን በርቱ ማለት አይቻልም። ሰርቶ ለልጆችህ ማሳየት ያስፈልጋል።”

ከአየርላንድ ምንም እርዳታ እንደሌላት የምትናገረው ምሥራቅ፣ ከፍተኛ ሥራ ዕድል ስላለ ሰርታ ያሰበችው ደረጃ መድረስ እንደምትችል ትናገራለች።

ጋብርኤል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የእናቱን የትውልድ ስፍራ ማየት ሕልሙ ነው።

“የእናቴ ትውልድ ቦታ ሐረጌ ስለሆነ አንድ ቀን ሄጄ ብጎበኝ ብዬ አስባለሁ።”

ጋብርኤል በቶኪዮ ኦሊምፒክ በቦክስ ውደድድር ለመሳተፍ እየተዘጋጀ ሳለ በደረሰበት ጉዳት የተነሳ ሳይሳካለት ቀርቷል።

ቀጣዩ የኦሊምፒክ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ግን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።