በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈጠረው የሰላም ተስፋ፡ እስካሁን የምናውቀው

ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ሰላማዊ ንግግር ለማካሄድ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ ማዋቀሩን አስታውቋል።

ለ19 ወራት የቆየው ጦርነት በንግግር እንዲያከትም በሁለቱም ወገኖች በኩል ፍላጎት እንዳለ የሚጠቁሙ መረጃዎች ባለፉት ሳምንታት ሲወጡ ቆይተዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከሳምንታት በፊት ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት፣ ከህወሓት ጋር የሚካሄደው የሰላም ንግግር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሚመራ ኮሚቴ አማካይነት የሚካሄድ ይሆናል።

ይህ ኮሚቴ የሰላም ንግግር የሚኖረውን ግብ እንዲሁም ምን እንደሚጠበቅ እየመረመረ እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር።

ኮሚቴው የሚደርስበትን ውጤት ለገዢው ብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካሳወቀ በኋላ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንግግራቸው ጠቁመዋል።

ይህ በአቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ኮሚቴ ከህወሓት ጋር ለድርድር እንደሚቀመጥም ጨምረው ገልጸዋል።

ከአደራዳሪዎቹ መካከል የቀድሞው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የአሁኑ የፍትሕ ሚኒስቴር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ይገኙበታል።

ለቀናት ከዘለቀ ስብሰባ በኋላ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ. ም. የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም ሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ግጭቱን በሰላም ለመፍታት ውሳኔ ላይ ተደርሷል።

ይህ የሰላም ንግግር በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የሚከናወን እንደሆነ የብልጽግና ፓርቲ መግለጫ ይጠቁማል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የቀጠፈውና የአገሪቱን ሰላም የናጠው ጦርነት በሰላም ንግግር የሚያከትምበት ዕድል እንዳለው የተሰማውን ዜና በርካቶች በበጎ ቢቀበሉትም፣ ፈተናዎችም ሊገጥሙት ይችላሉ።

የሰላም ንግግሩ ውስጥ ያሉ አንድ ከፍተኛ ዲፕሎማት “ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጠቃሚና ተስፋ ሰጪ ምልክቶች መኖራቸው እሙን ነው። ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸውን በፖለቲካዊ መንገድ ለመፍታት የደረሱበትን ውሳኔ ይገፉበታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ገልጸዋል።

ህወሓት ለሰላም ድርድሩ የሚልከውን ቡድን ገና ይፋ አላደረገም።

ድርድሩ ምን ሂደት ሊኖረው ይችላል? ማን ያደራድራል? የት ይካሄዳል? ለውይይት የሚቀርቡት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? የሚሉትን በተመለከተ ገና ዝርዝር መረጃዎች አልወጡም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሰላም ንግግር የሚሳተፈው የአፍሪካ ኅብረት በአደራዳሪነት ከተቀመጠ ብቻ እንደሆነ ገልጿል።

በተቃራኒው ህወሓት በአፍሪካ ኅብረት በኩል የተደረገውን የሰላም ጥረት ኮንኖ፣ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲያደራድሩ እንደሚፈልግ አስታውቋል።

  በኦባሳንጆ የተመራው የሰላም ጥረት

የሰሜኑን ጦርነት ለመግታት ከተደረጉ ግንባር ቀደም ጥረቶች በዋነኛነት የሚጠቀሰው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የሰላም ጥረት ነው።

ኦባሳንጆ አምና ነሐሴ ላይ በአፍሪካ ቀንድ ልዑክነት፣ በአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሕማት መሾማቸው ይታወሳል።

ከአዲስ አበባ መቀለ እየተመላለሱም ከሁለቱም ወገኖች አመራሮች ጋር በተደጋጋሚ ተነጋግረዋል።

ኦባሳንጆ በአንድ ዓመት ቆይታቸው፣ ሁለቱ ወገኖች ሰብአዊነትን የተመረኮዘ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ሰላም በማውረድ ስማቸው ከሚጠሩ አፍሪካውያን የዕድሜ ባለጸጎች አንዱ ኦባሳንጆ ናቸው።

በአንጎላ፣ በሞዛምቢክ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በናሚቢያ የሰላም ድርድር ውስጥ ተሳትፈዋል። በተጨማሪም ሁለተኛውን የላይቤርያ የእርስ በእርስ ጦርነት በማስቆምም ስማቸው ይነሳል።

የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ቻርልስ ቴይለር ሥልጣን ለቀው ናይጄሪያ በጥገኝነት እንዲኖሩም አመቻችተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ላይቤሪያን ከለቀቁ ከሳምንት በኋላ የሰላም ስምምነት በጋና፣ አክራ ተፈርሞ የላይቤሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት አክትሟል።

ኦባሳንጆ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ከመሆናቸው ከሁለት ወራት አስቀድሞ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ስድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ እንዲታዘቡ ወደ ኢትዮጵያ መላካቸው አይዘነጋም።

በኦባሳንጆ የተመራው ምርጫ ታዛቢ ቡድን “የተወሰኑ መሰናክሎች ቢኖሩም የቅድመ ምርጫ እና የምርጫ ሂደቱ የተካሄደው በሥርዓት፣ በሰላምና ተአማኒ በሆነ መንገድ ነው” ሲል መግለጫ አውጥቷል።

የተጠቀሱት መሰናክሎች ከሎጂስቲክስ፣ ከፖለቲካ፣ ከደኅንነት እና ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ናቸው።

በኬንያ የተመራው የሰላም ጥረት

ከኦባሳንጆ በተጨማሪ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታም የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም ጥረት አድርገዋል።

ኬኒያታ ምዕራባውያን አገራትን በማስተባበር በጎረቤት አገር ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን ሞክረዋል።

ከጎናቸው የቆሙት አገራት አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የአውሮፓ ኅብረት አገራት ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን በተደጋጋሚ ወደ ኬንያ ጋብዘው ግጭቱ በሰላም እንዲፈታ ጠይቀዋል።

ኬንያታ በአገራቸው የሚካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ከሁለት ወራት በኋላ ከመንበረ ሥልጣናቸው ይለቃሉ።

ኬንያ የጎረቤቶቿ ቀውስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚነካት አገር ናት። ለምሳሌ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ታስተናግዳለች።

ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች የሚኖሩበት ዳዳብ፣ ከዓለም ትልቁ የስደተኞች መጠለያ ነው።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ በኦባሳንጆ እና በኬንያታ የሰላም ጥረት መካከል ልዩነት አለ።

የትግራይ ኃይሎች ኦባሳንጆ “ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ይቀርባሉ” ሲሉ ከዚህ ቀደም ተችተዋል።

ህወሓት የኬንያ መንግሥትን አደራዳሪነት እንደሚቀበል ገልጿል።

በሌላ በኩል ታንዛኒያ የድርድሩን ተሳታፊዎች ለመቀበል ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

አቶ ጌታቸው እንደሚሉት፣ የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ ኦባሳንጆ ወደ አንድ ወገን ማዘንበል ትተው ለሰላም ድርድር የሚሆን የተዋቀረ ዕቅድ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋቸዋል።

ታንዛኒያ ከዚህ ቀደም ከድርድር ጋር በተያያዘ ስሟ ተነስቶ አያውቅም።

ባለፈው ወር ግን የአፍሪካ ኅብረት ድርድሩ በታንዛንያዋ አሩሻ እንዲካሄድ ሐሳብ አቅርቧል።

ምንጮች እንደሚሉት፣ ታንዛንያ የምትመጣው በአደራዳሪነት ሳይሆን ድርድሩ በአሩሻ እንዲካሄድ ፈቃደኛነት አሳይታለች።

የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ከማይስማሙባቸው ነጥቦች አንዱ የታንዛንያ ሚና ምን ይሁን? የሚለው ነው።

በክራይሲስ ግሩፕ ከፍተኛ ተንታኝ የሆነው ዊልያም ዴቪሰን እንደሚለው፣ ሁለቱም የሰላም ጥረቶች ወደ አንድ አቅጣጫ ቢያመሩም ኦባሳንጆ በታንዛኒያ ወደሚደረገው ድርድር የሚያመዝኑ ይመስላል።

“ይህንን ሐሳብ በዋነኛነት የሚቃወሙት የትግራይ ኃይሎች ናቸው። ኦባሳንጆ ወደ ፌደራል መንግሥቱ የቀረቡ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ፣ በኬንያ የሚመራ ድርድር ናይሮቢ ውስጥ እንዲካሄድ ነው የሚሹት” ሲል ያስረዳል።

“ለንግግር ሲዘጋጁ በኦባሳንጆ እና በኬንያ የሚመራው የሰላም ጥረት መጣመር አለበት። በሁለቱ መካከል ፉክክር ከተፈጠረ ስህተት ይሆናል። ይህ የሰላም ጥረት ግቡን መሳት የለበትም” ሲልም ያክላል። 

ሌላ የድርድር ሂደቱ ተሳታፊ የሆኑ ዲፕሎማት በተጀመረው ሂዳት ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው፣ ስጋታቸውንም እንዲህ አስቀምጠዋል።

“ድርድሩ ስሱ ነጥብ ላይ ነው ያለው። ግን ተስፋ ሰጪ ነው። ነገር ግን እንዳይቀለበስ መጠንቀቅ አለብን።”

በተደጋጋሚ ለንግግር የሚቀርቡት ነጥቦች

የሰላም ንግግሩ ሁለቱ ወገኖች ግጭት እንዲያቆሙ ከማድረግ ባሻገር፣ በከበባ ውስጥ ለሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች እፎይታ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም በአገሪቱ ያሉ ማኅበረሰቦችን የከፋፈሉ ጉዳዮችን ይዳስሳል ተብሎም ይገመታል።

የምዕራብ ትግራይን ጉዳይ እዚህ ጋር ማንሳት ይቻላል።

ለምለሙ፣ ስትራቴጂኩ እና በተፈጥሮ ሃብት የደረጀው ምዕራብ ትግራይ አሁን በአማራ ክልል ሥር ሲሆን፣ ቀድሞ በትግራይ ሥር ነበር።

ህወሓት በድርድር ወቅት ቅድሚያ የሚሰጠው ይህንን ግዛት መልሶ ወደ ትግራይ መከለል እንደሆነ አስታውቋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፍአለ እንዳሉት፣ የዚህን አካባቢ ይዞታ “ሕጋዊ ለማድረግ” ጥረቶች ተጀምረዋል።

የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ ገና አልተፈታም። በሰላም ንግግሩ ወቅት ዋነኛ ነጥብ እንደሚሆንም ይጠበቃል።

ሌላው ነጥብ ምርጫ ነው።

የፌደራል መንግሥቱ እና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ምርጫ እውቅና አይሰጡትም።

አዲስ የተመሠረተውን ክልላዊ መንግሥትም ይሁንታ ነፍገዋል።

ሌላው ጉዳይ ህወሓት በትግራይ ውስጥ ለተፈጠረው ቀውስ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የአማራ ክልል ኃይሎችም የወንጀል ተጠያቂነት ኃላፊነትን እንዲወስዱ መፈለጉ ነው።

ሕገ መንግሥቱ የሰጠውን መብት ተጠቅመው ሕዝበ ውሳኔ የማካሄድ ፍላጎትም አላቸው።

ሁለቱም ወገኖች ከድርድሩ የሚጠብቁትን ይፋ አድርገዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ብሔራዊ ጥቅምን እንደማያስነካ አስታውቋል።

ህወሓት በበኩሉ፣ “መስዋዕትነትን ለመቀነስ ሲባል ተጨማሪ መስዋዕትነት አንከፍልም” ብሏል። 

ዊልያም ዴቪሰን ስለ ድርድር ተስፋ እና ስጋቶቹን እንዲህ ገልጿል።

“ምንም ይሁን ምን ሰላም የማውረድ ሂደቱ በፈተና መሞላቱ አይቀርም። ይህም የሆነው ባለው አለመስማማት እና አለመተማመን ምክንያት ነው። ሌላ ዙር ግጭት የሚነሳ ከሆነ የሰላም ጥረቱ ሙሉ በሙሉ ይከሽፋል።”

የኤርትራ ሚና ምንድን ነው?

የአፍሪካ ቀንድ ከአህጉሪቱ ቀጠናዎች በነውጥ በመናጥ ይታወቃል።

አሥርታት የዘለቀው የሶማሊያው የእርስ በርስ ግጭት እና የደቡብ ሱዳን ቀውስ ይጠቀሳሉ። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ወደ ውዝግብ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት በ20 ወራት ውስጥ፣ ለ120 ሚሊዮን ዜጎች የደኅንነት፣ ማኅበራዊ እና የምጣኔ ሃብት ቀውስ መንስኤ ሆኗል። ጎረቤት አገራትንም አስግቷል።

ትግራይን በዋነኛነት የጎዳው ጦርነቱ በአማራ እና በአፋር ክልሎችም ቀውስን አስከትሏል።

ኢትዮጵያ ቀጠናውን በማረጋጋት እና ሽብርተኛነትን በመዋጋት ረገድ የምዕራቡ ዓለም ቀዳሚ አጋር ነበረች።

አሁን ግን በአገር ቤቱ ጦርነት ተውጣለች።

በሰሜኑ ጦርነት በቀጥታ ተሳታፊ የሆነችው ጎረቤት አገር ኤርትራም ሳትጠቀስ አትታለፍም።

 ኤርትራ በፌደራል መንግሥቱ በኩል ሆነው የትግራይ ኃይሎችን የተዋጉ ወታደሮች ልካለች።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የሚደረግ የሰላም ንግግር ኤርትራን መረበሹ አይቀርም።

በህወሓት እና በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መካከል ያለው ዓመታት የቆየ ቁርሾ፣ ለሰላም ንግግሩ ትልቁ መሰናክል ሊሆን ይችላል።

የኤርትራ ሠራዊት በጦርነቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተከሰሰ ሲሆን፣ ከፍተኛ አመራሮቹ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

የኤርትራ ብሔራዊ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ አብርሃ ካሳ ነማርያም እና የሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ኃላፊ ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ንብረት የሆነው ሕድሪ ትረስት ላይም ዕገዳ ተጥሏል።

ዊልያም እንደሚለው፣ ከአማራ ክልል፣ ከአፋር ክልል እና ከኤርትራ መንግሥት በኩል ስለ ሰላም ንግግሩ በጎ አመለካከት መኖር አለበት።

“የኤርትራ መንግሥት፣ በዋነኛነትም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከህወሓት ጋር የሚያደርጉትን ድርድር ስለመደገፋቸው ግልጽ መረጃ የለም። የኤርትራ ተቃውሞ ወደ ቀውስ ሊያመራ ይችላል?” ሲል ይጠይቃል።