ደጋግመን ብንዋሽ፣ ውሸታችን እውነት ሊመስለን ይችላል? ሰዎችንስ እናሳምናለን?

በጥላ ተሸፍና ፊቷ የማይታይ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤልዛቤት ሆልምስ፣ አና ሶረከን እና ሳይመን ሌቪቭ ውሸታሞች ናቸው።

ሦስቱም በአንድ ወቅት በውሸት ብዙዎችን አታለዋል።

ኤልዛቤት ‘ራሷን በራሷ ሚሊየነር ያደረገች ወጣት’ ተብላ በ2015 ተሸልማ ነበር። አሁን ግን በማጭበርበር ወንጀል ታስራለች።

አና፣ ከቤተሰቦቼ ከፍተኛ ሀብት ‘ወርሻለሁ’ ብላ በርካቶችን ካሳመነች በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ዘርፋለች።

ሳይመን፣ በውሸት 10 ሚሊዮን ዶላር ገደማ አጭበርብሯል።

አና፣ ኤልዛቤት እና ሳይመን ያታለሉት ዓለምን ብቻ አይደለም። እራሳቸውንም ጭምር እንጂ።

እውነታውን ክደው ‘የምናደርገው ነገር ትክክል ነው’ ብለው አምነዋል።

ራሳቸውን የሚያታልሉት ግን እነሱ ብቻ አይደሉም።

ብዙዎቻችን ራሳችንን እንዋሻለን።

ለምን? ስለራሳችን ጥሩ ስሜት እንዲሰማን። ሰዎችን ማሳመን ስለምንፈልግ።

ሳይንስ እንደሚለው፣ ውሸታችንን እኛው ካመነው፣ ሰዎችን በቀላሉ ማሳመን እንችላለን።

የሥነ ልቦና ተመራማሪዎች እንደሚሉት ሰዎች ራሳቸውን ሲያታልሉ ከቀልባቸው (conscious) ሆነው አይደለም።

ዞይ ቻንስ፣ በዬል ዩኒቨርስቲ የማርኬቲንግ መምህር ናት።

ሰዎች ራሳቸውን የሚዋሹት፣ "ስለራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ነው" ትላለች።

የአእምሮ ብቃት (IQ) ፈተና ተዘጋጅቶ ነበር።

ከተፈታኞቹ ጥቂቱ ከፈተና ወረቀታቸው ሥር የጥያቄዎቹ መልስ ተሰጣቸው።

መልሱ ካልተሰጣቸው ሰዎች የተሻለ ውጤት አስመዘገቡ።

ባይኮርጁም ጥያቄዎቹን መመለስ እንደሚችሉ ለራሳቸው መንገራቸውን ልብ ይሏል።

ተፈታኞቹ በቀጣይ የሚሰጣቸው ፈተና ላይ ምን ያህል እንደሚያገኙ በትክክል ከገመቱ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ተነገራቸው።

ከፍተኛ ውጤት እናመጣለን ብለው ራሳቸውን ስላሳመኑ ከፍተኛ ነጥብ ይጠሩ ጀመር።

ወደ ትክክለኛ ነጥባቸው የተጠጋጋ ግምት ገንዘብ እንደሚያስገኝ ቢነገራቸውም፣ ከፍተኛ ውጤት እናመጣለን ብለው ራሳቸውን ደልለው ገንዘቡን ማጣት በለጠባቸው።

ሳይንቲስት የተሳሳተ መረጃ ተጠቅሞ አንዳች ውጤት ሲያገኝ ራሱን እያታለለ ነው። ኮርጆ ዩኒቨርሲቲ የሚገባ ተማሪም እንዲሁ።

ዩሪ ጄንዚ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት አስተማሪ ነው።

በ2020 በሠራው ጥናት፣ አንድ ቡድን ወደ ኢንቨስትመንት አማካሪዎች እና ባለ ሀብቶች እንዲከፈል አደረገ።

አማካሪዎቹ፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ኪሳራ እና ትርፍ አጥንተው ባለ ሃብቶችን ካሳመኑ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ተነገራቸው።

እንደ አማካሪነታቸው ባለ ሀብቶቹን የሚጠቅማቸው የኢንቨስትመንት አማራጭ ከመምከር ይልቅ፣ እነሱን ባለድል የሚያደርጋቸውን ሐሳብ ለባለሀብቶቹ ተናገሩ።

“አማካሪዎቹ ለባለሀብቶቹ የሰጡት ምክር የተቃኘው ለራሳቸው ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ባደረገው ሐሳብ ነው” ይላል አጥኚው።

ትርፍ እና ኪሳራን ያሰሉት፣ ወደ ትርፍ ወይም ወደ ኪሳራ የሚያመራ ምክር ቢሰጡ፣ ስለ ራሳቸው ሊኖራቸው በሚኖራቸው አመለካከት ነው።

 ምሳሌውን ወደ ሕክምና ዘርፍ እንውሰደው።

ሐኪሞች በጣም ውድ መድኃኒት ሲያዙ፣ መድኃኒቱን ያዘዙት ስለታካሚያቸው ተጨንቀው እንደሆነ ራሳቸውን ያሳምናሉ።

ራስን ማሳመን እና ሰዎችን ማሳመን

ሰዎች ራሳቸውን ሲዋሹ፣ ሰዎችንም በቀላሉ መዋሸት እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ።

ሰዎች በሚያወሩት ነገር እርግጠኛ ሲሆኑ በራስ መተማመናቸው ይጨምራል።

የቢሄቪየራል ኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ፒተር ሽዋንድማን ጥናት የተሠራው በአእምሮ ብቃት ጥናት (IQ) ነው።

ተሳታፊዎቹ ፈተና ተሰጣቸው።

ፈተናው ሲያልቅ፣ ግማሾቹ ተሳታፊዎች ውጤታቸው ሳይነገራቸው፣ ምን ያህል ውጤት አስመዝግበው እንደሆነ እንዲገምቱ ከዚያም ዳኞች ፊት ቀርበው ውጤታቸው ከፍተኛ እንደሆነ እንዲያሳምኑ ተጠየቁ።

ግማሾቹ ተሳታፊዎች ግን ውጤታቸው ከፍተኛ እንደሆነ ዳኞችን እንዲያሳምኑ አልተጠየቁም።

የጥናቱ ውጤትም ይህ ነበር፦

ዳኞችን እንዲያሳምኑ የተጠየቁት ተፈታኞች እናመጣለን ብለው የገመቱት ውጤት ከፍ ያለ ነበር።

ምክንያቱም ዳኞችን ከማሳመናቸው በፊት፣ ውጤታቸው ከፍተኛ እንደሆነ ራሳቸውን ማሳመን አለባቸው።

ሰዎች አንድን ሐሳብ ከልባቸው የሚደግፉት ከሆነ ስለሐሳቡ ሌሎችን ለማሳመን ይቀላቸዋል።

የማታለል ‘ጥበብ’

አእምሯችን ውሸትን ‘እውነት ነው’ ብሎ ሊያሳምነን ይችላል።

ከሰው ሁሉ የላቅን ነን ብለን ራሳችንን እናምናለን። ይህ ማለት ውሳኔያችን ሁሌም ትክክል እንደሆነ እርግጠኛ ነን ማለት ነው።

ስለውሳኔው ትክክለኛነት የሚያምን ሰው፣ ስለውሳኔው ለሌሎች ሲያስረዳ በራስ መተማመን ተሞልቶ ይሆናል።

ይህ በራስ መተማመን ሰዎችም እንዲያምኑን ያደርጋል።

አና፣ ኤልዛቤት እና ሳይመን ሰዎችን ሲያታልሉ በአእምሯቸው ምን ሐሳብ እየተመላለሰ እንደነበር ልናውቅ አንችልም።

ሳይንስን ተመርኩዘን ስንገምት ግን፣ ምናልባትም የራሳቸውን ውሸት አምነውት ይሆናል። ምናልባትም ትክክል ነን ብለው አምነው ሊሆን ይችላል።

ሰው ትክክል ነኝ ብሎ ሲያምን ደግሞ ድርጊቶቹን ማጠየቅ ይቀንሳል።

ኤልዛቤት በማጭበርበር ፍርድ ቤት ቀርባም ድርጊቷን ደግፋ ተከራክራለች።

ሳይመን “እኔን የመሰለ ድንቅ ሰው የለም” ሲል ተደምጧል።

የሥነ ልቦና ተመራማሪዎች እንደሚሉት፣ በማጭበርበር የሚከሰሱ ሰዎች፣ አጭበርባሪ ነን ብለው ስለማያምኑ፣ ክሱ ሊያስቆጣቸው ይችላል።

ሰዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት ሲሹ ራሳቸውን የሚያታልሉበት መጠን ይጨምራል።

አንድ ሰው በልጦናል ብለን ስናስብ፣ ያንን ሰው ለመብለጥ ስንል ለራሳችን ትልልቅ ውሸቶች እንነግራለን።

ስለራስዎ ጥሩ እንዲሰማዎት ብለው፣ ራስዎ ለራስዎ የነገሯቸው ውሸቶች ወይም የተጋነኑ እውነታዎችን እስኪ ቆም ብለው ያስቡ?

ተሳስቼ ይሆን? ብለው ለራስዎ እውነተኛ ሆነው ይጠይቁ።

ትክክለኛውን መልስ ለማግኘት ሙሉ በሙሉ ለራስዎ ታማኝ መሆን ይገባዎታል።

ያኔ ስለራስዎ የጠራ እውነታ ላይ፣ በትንሹም ቢሆን ይደርሱ ይሆናል።