በባሕር ዳር ከተማ በአራት ቦታዎች የቦምብ ፍንዳታ እንደተፈጸመ ፖሊስ ገለጸ

ባሕር ዳር

በአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባሕር ዳር ውስጥ በተለያዩ አራት ቦታዎች ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙንና በድርጊቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳለው ጥቃቱ ሰኞ ሰኔ 20/2014 ዓ.ም ምሽቱ 1 ሰዓት ተኩል አካባቢ በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ በተመረጡ የተለያዩ ስፍራዎች የተፈጸሙ ሲሆን በሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም።

ከዚሁ ጥቃት ጋር ተያይዞ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም የተንቀሳቀሱ ናቸው ያላቸውን ግለሰቦች ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተገልጿል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር መሠረት ደባልቄ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት “ኅብረተሰቡን ለማሸበር ያለመ ወንጀል መፈፀም የፈለጉ ኃይሎች በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በአራት ቦታዎች ላይ ቦንብ አፈንድተዋል” ብለዋል።  

ይህንንም ተከትሎ ፖሊስ ባደረገው ክትትል ጥቃቱን ፈጽመዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ከጥቃቱ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 14 ተባባሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው በክልልና በፌደራል የፀጥታ አካላት ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ኮማንደር መሠረት ተናግረዋል።

ፖሊስ እንዳለው በጥቃቱ ተጠርጥረው በተያዙ ግለሰቦች ቤት በውስጥ በተደረገ ፍተሻ 2 ቦንብ፣ 3 ብሬን ጠመንጃ፣ አንድ ስናይፐር ጠመንጃ እና በርካታ የተለያዩ አይነት ጥይቶች መገኘታቸው ተገልጿል።

ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ የአማራ ክልል መስተዳደር በክልሉ ውስጥ ማካሄድ በጀመረው ሕግ የማስከበር ዘመቻ በተለያዩ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው መነገሩ ይታወቃል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንም መንግሥት በክልሉ ሕግ ለማስከበር እየሰራ መሆኑን፣ በተለይም በአማራ ክልል የተደራጁ ሕገወጦችን ወደ ሕግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን የፖሊስ ቃል አቀባይዋ አመልክተዋል።

በባሕር ዳር ከተማ የተፈጸሙት የቦምብ ጥቃቶች ኢላማ ያደረጓቸው ቦታዎች የትኞቹ እንደሆኑ በፖሊስ ያልተገለጹ ሲሆን፣ ፍንዳታዎቹ ግን በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ያደረሱት ጉዳት እንደሌለ ፖሊስ ተናግሯል።

ፍንዳታዎቹ የታለሙት የከተማዋን ነዋሪ ለማሸበር እና የአማራ ክልልን ሰላም ለመንሳት በመሆኑ፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል እየወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፖሊስ ገልጿል።