በቻይና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ 'ርካሽ' ተብለው የዘረኝነት ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ሴቶች

የቻይናው ማህበራዊ ሚዲያ  ኩአይሻ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቻይና ታዋቂ የሆኑት 'ዶይን' እና 'ኩአይሻ' የተሰኙት የአጭር ቪዲዮ ማጋሪያ የማኅብራዊ ትስስር ገጾች በየቀኑ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይጎበኟቸዋል።

ዶይን እና ኩአይሻ ለቻይናውያን የተሰሩ የቲክቶክ አቻ የሆኑ መተግበሪያዎች ሲሆን የሚተዳደረውም በአንድ ኩባንያ ስር ነው።

እነዚህን ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ከቻይና ውጪ የሚኖሩ የአገሪቱ ዜጎችም በስፋት ይጠቀሙባቸዋል።

ታዲያ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የቻይና ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ከኢትዮጵያውያን ሴቶች ጋር በዶይን እና ኩአይሻ አማካኝነት ብቅ ሲሉ ማየት እየተለመደ መጥቷል።

በቪዲዮዎች ምን ይታያል? ምን ይባላል?

ቢቢሲ በቻይና በስፋት የሚዘወተሩት የቪዲያ ማጋሪያዎች ላይ በቀጥታ የተሰራጩ ቪዲዮዎች በሌላ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጭነው ተመልክቷል።

በእነዚህ ቪዲዮዎች ቻይናውያን ግለሰቦች ከኢትዮጵያውያን ሴቶች ጋር ሆነው የቻይና ቋንቋ በሆነው ማንዳሪን የተለያዩ ቃላትን ሲያስደግሟቸው በመቀጠልም ማብራሪያ ሲሰጡ እና አልፎ አልፎ ሲነኳቸው ያሳያሉ።

በእነዚህ ቪዲዮዎች ላይ በማንዳሪን ቋንቋ የሚባሉትን ቤይጂንግ የሚገኘው የቢቢሲ ቢሮ ተርጉሟቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Social Media/YT

  • ቪዲዮ አንድ

በቪዲዮው ላይ አንዲት ሮዝ ሱሪ እና ነጭ ቲ ሸርት የለበሰች ሴትን ከበሰተኋላዋ እየተቀረጸች ትታያለች።

ቪዲዮውን የሚቀርጸው ሰው ግለሰቧ ትከሻዋን እየነካ አንድ ጊዜ ቆም ብላ ፊቷን እንድታሳይ ሌላ ጊዜ እንድትሄድ እያደረገ በማንዳሪን ቋንቋ ማብራሪያ ይሰጣል።

ኢትዮጵያዊቷ የምትራመደው መንገድ ላይ በቀን ሲሆን በዙሪያዋ የንግድ ሱቆች እንዲሁም የሰዎች እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ይታያል።

የማንዳሪን ቋንቋው ማብራሪያ እንዲህ የሚል ትርጉም አለው:

“ተመልከቷት! ሦስት ሺህ አር ኤም ቢ [የቻይና መገበያያ ገንዘብ] ሦስት ሺህ በድንብ ታወጣለች። ከቻይና ሕዝቦች ውበት ጋር የሚጣጣም ውበት ነው ያላት። ወረርሽኙ እዚህ ብዙም አሳሳቢ አይደለም። ‘ሃይሻይንግ’ ለሚፈልጉ ሁሉ!  [‘ሃይሻይንግ’  የሚለውን ቃል የቢቢሲ ቤጂንግ ቢሮ ትክክለኛ ትርጉሙን ባይደርስበትም ከአውዱ ለመረዳት እንደተሞከረው ከባሕር ማዶ መውለድ ለሚፈልጉ የሚል ትርጓሜ ሊሰጠው ይችላል።]”

የፎቶው ባለመብት, Social Media/YT

  • ቪዲዮ ሁለት

ይህ ቪዲዮ በቀጥታ ሲሰራጭ የነበረ ነው። በአንድ ቤት ውስጥ አንድ ቻይናዊ ግለሰብ በቅድሚያ የአንዲት አብራው ካሜራ ፊት የቆመች ሴትን ጣቶች በጣቶቹ አቆላልፎ እና እጇን ይዞ ይታያል።

በመቀጠል በማንዳሪን ቋንቋ እየጠየቀ በዚያው ቋንቋ አጭር ምላሽ [አዎ ወይም አይ የሚል] እንድትሰጥ ያደርጋል። ቆም ብሎ ወደ ካሜራ እየተመለከተ ማብራሪያውን ይቀጥላል።

ቀጥሎም ሌላ ሴት ወደ ካሜራው ዕይታ እንድትገባ አድርጎ ጣቱን በጣቷ አቆላልፎ ለሚጠይቃት ጥያቄ ጭንቅላቷን በመወዝወዝ ምላሽ ስትሰጥ ይታያል።

ከዚያም ሁለቱን ሴቶች በጋራ አቅፎ ለተመልካቾቹ ማብራሪያ ይሰጣል።

በቻይንኛ ቋንቋ የሚቀርበው ጥያቄ፤ የሚሰጡት ምላሽ እና የቻይናዊው ገለጻ እንዲህ የሚል ነው፡

ቻይናዊው: ቤት ትፈልጊያለሽ?

ኢትዮጵያዊቷ: አልፈልግም!

ቻይናዊው: እውነትሽን ነው?

ኢትዮጵያዊቷ: አዎ!

ቻይናዊው: ምንም ገንዘብ አትፈልጊም?  

ኢትዮጵያዊቷ: አልፈልግም።

ቻይናዊው: እርግጠኛ ነሽ?

ኢትዮጵያዊቷ: አዎ

ወደ ካሜራው እየተመለከተ ማብራሪያ ይሰጣል።

"ይህቺ አፍሪካዊ ሴት ናት። ኋላ ቀር በሆኑ ጎሳዎች የፍቅር አጋር በላም መለወጥ ይቻላል። በዚህ ዘመናዊ ዓለም መኪና፣ ቤት እና ለሙሽሪት ጥሎሽ መክፈል አያስፈልግም።

"በርካታ ቻይናውያን አለቆች እዚህ ትዳር መስርተው ልጅ እየወለዱ ነው። የሚወለዱት ልጆች እንደእኔ [ቆዳቸው] ነጭ ነው። እያደጉ ሲሄዱ እና ሲተልቁ ትንሽ ጠቆር ይላሉ።"

ሌላኛዋን ኢትዮጵያዊ ወደ ካሜራው በማምጣት ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እየጠየቃት ምላሽ ስትሰጥ ትታያለች።

የፎቶው ባለመብት, Social Media/YT

[ወደ ተመልካቾች በመዞር] እሷን የወደዳት ሰው አለ? ይህቺኛዋ ቁጥር አንድ ናት። [እየጠቆመ] ይህቺ ደግሞ ቁጥር ሁለት። ቁጥር አንድን የምትፈልጉ አንድ ብላችሁ ጻፉ። ቁጥር ሁለትን የምትፈልጉ ሁለት ብላችሁ ጻፉ።

"እነሱን የሚፈልግ አለ? መኪና፣ ቤት እና ገንዘብ አይጠይቁም። አሁን ላይ በቻይና የፍቅር አጋር ለማግኘት በመቶ ሺዎች ይጠይቃል። መኪና፣ ቤት እና ጥሎሽ ሲደማመር ደግሞ እስከ አንድ ሚሊዮን ይደርሳል" ይላል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ያህል ወጪ ማውጣት እንደማይጠበቅና ያለምንም ማስዋቢያ ሁሉም ተፈጥሯዊ ውበት እንዳለቸው አካላቸውን እየነካ በዝርዝር ያብራራል።

የቀጥታ ስርጭቱ ታዳሚዎችም ጥያቄ እያቀረቡ ማብራሪያ እና ምላሽ ይሰጠል።

ይህ ሁሉ ሲከናወን ግን በቪዲዮው ላይ የሚታዩትን ሴቶች ኢትዮጵያውያን ሴቶች በማግኘት ቀረጻው በፈቃዳቸው ይሁን ተገደው ለማረጋገጥ ቢቢሲ አልቻለም።

የፎቶው ባለመብት, Social Media/YT

  • ቪዲዮሦስት

ይህ የቀጥታ የማኅበራዊ ሚዲያ ቪዲዮ ስርጭት አፍሪካ ውስጥ ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ የሚተላለፍ መሆኑን የሚጠቅስ ነው።

ቪዲዮው ላይ አንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት በቀጥታ ከሚያሰራጨው ቻይናዊ ፊት ለፊት ቆማ በቻይንኛ የሚላትን ስደግም ትታያለች።

ከኋላዋ ሰልፍ በሚመስል መልኩ የቆሙ ሦስት ሴቶች ቪዲዮ የሚቀረጽበት ግቢ ውስጥ ይታያሉ። ቻይናው ኢትዮያዊቷን የሚለውን ያስደግማታል።

ከዚያም ወደ ሴቶቹ እያሳየ ገለጻ ያደርጋል ዕድሜ፣ ቁመት፣ ክብደት፣ ሥራና ቻይና መሄድ እንደሚፈልጉ በመጠየቅ ምላሻቸውን በቻይንኛ ይተረጉማል።

ይህንን ካደረገ በኋላም የቀጥታ ስርጭቱን ከሚመለከቱት ታዳሚዎች መካከል ስም በመጥራት የሚፈልጋትን ለማግኘት የደንበኞች አገልገሎትን ማነጋገር/ማግኘት እንደሚችል ይናገራል። በዚህም ሰዎችን በማገናኘት ተግባር ላይ የተሰማራ እንደሆነ ያመለክታል።

ዶይን በተባለው በዚህ የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በጥታ የሚተላለፉ ቪዲዮዎች ስርጭቱ ከተጠናቀ በኋላ መልሶ ማግኘት አይቻልም።

በዚህም ምክንያት እነዚህን ቪዲዮዎች ዶይን ላይ አይገኙም።

ቢቢሲ የተመለከታቸውና ኢትዮጵያውን እንስቶችን "ለገበያ" በሚያቀርብ በሚመስል ሁኔታ የተሰራጩት ቪዲዮዎች የተገኙት በቀጥታ ስርጭት ወቅት ተቀርጸው በሌላ ማኅበራዊ ሚዲያ ከተጫኑ በኋላ ነው።

በቻይናየሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምን ይላሉ?

በቻይና ዶይን እና ኩአይሻ በተባሉት ማኅበራዊ ሚዲያዎች ኢትዮጵያውያን ሴቶች ክብራቸውን ዝቅ በሚያደርግ መልኩ እንደሚቀርቡ በቻይና የሚኖሩ እና ስማቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉ ኢትዮጵያን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቋንቋውን እንደምትረዳ የነገረችን ኢትዮጵያዊት በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ “[ኢትዮጵያውያኑን] ቅርጻቸው እዩዋቸው እያሉ ታይት አስለብሰው ደስ የማይል ነገር ነው የሚያሳዩት” ስትል ገልጻለች።

“እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሴት፣ እንደ አንድ ማንዳሪን እንደሚችል ሴት ይሄንን ነገር ሳይ በጣም በጣም ነው የምናደደው“ ስትል ለቢቢሲ አሰተያየቷን የሰጠችው በቻይና ነዋሪዋ የሆነች ሌላ ኢትዮጵያዊት በሚታዩት ነገሮች እንደምታዝን ትናገራለች።

እንሷ እንደምትለው በቪዲዮው ላይ የሚታዩት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ቋንቋውን ይረዱታል ብላ እንደማታምን በመጥቀስ ከሚናገሩት በተጨማሪ ድርጊታቸው ክብረ ነክ ነው ትላለች።

"ብዙ ጊዜ ዳሌያቸውን እና የግል አካሎቻቸውን እየነኩ ነው የሚያሳዩት።... አንዳንዶቹ እንዲያውም ንግድ ያደርጉታል። ኢትዮጵያ መጥታችሁ ቆንጆ ሴቶች አሉ እናገናኛችኋለን ይላሉ። ያናድዳል ” ስትል ታስረዳለች።

በተለይ ልብስ በማይዘወተርባቸው የኢትዮጵያ አካቢዎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ ክብርን በሚነካ መንገድ ቪዲዮ እንደሚሰራ ሁለቱም አስተያየት ሰጪዎቻችን ለቢቢሲ ጠቅሰዋል።

“ሐመሮች ጋር ሄደው የሚሰሩት አንዳንድ ቪዲዮ በጣም ነው የሚያበሳጨው። ያንን ባህላቸውን እኔ እወደዋለሁ እኮራበታለሁ። እነሱ ኋላ ቀርነታችን እንደማሳያ ያቀርቡታል። ሴቶቹ ጡታቸውን፣ ወንዶቹ ደግሞ  ብልታቸውን እያሳዩ ነው የሚሄዱት ይላሉ” በማለት ቅሬታዋን ገልጻለች።

 ቻይናውያኑ ምን ይጠቀማሉ?

ቲክቶክ እና ዶይንን የሚያስተዳድረው ባይትዳንስ የተሰኘው ተቋም በዓለም እጅግ ትርፋማ ከሚባሉት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አንዱ ነው። ኩባንያው ባለፈው የአውፓውያን ዓመት 58 ቢሊዮን ዶላር አትርፏል።

በተመሳሳይ ኩአይሻ የተሰኘው በቻይና ተወዳጅ የቪዲዩ ማኅበራዊ ሚዲያ በዚህ ዓመት በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ 3 ቢሊዮን ዶላር ማትረፉን አሳውቋል።

ታዲያ እነዚህ በቻይና ሰፊ ተወዳጅነት ያላቸው ማኅበራዊ ሚዲያዎችን የሚያስተዳድሩት ተቋማት በቀጥታ ስርጭት ለሚተላለፉ እና ለሚጫኑ ቪዲዮዎች ገንዘብ ይከፍላሉ። ከዚህም ባሻገር በተለይ በዶይን ተመልካቾች ቪዲዮ ለሚሰሩ ሰዎች ጉርሻ የሚሰጡበት ሥርዓት አለው።

“[ከኢትዮጵያ ሆነው ቪዲዮውን የሚሰሩ ቻይናውያን] ብዙ ዕይታ ባገኙ ቁጥር ስለሚከፈላቸው በጣም ያልተገቡ ነገሮችን ያርባሉ” ይህም ምንነትን፣ የቆዳ ቀለምን፣ ጾታንና አገርን ባልተገባ መንገድ በመቅረብ ጥቅምን ለማግኘት ይሞክራሉ ትላለች በቻይና የምተገኘው ኢትዮጵያዊት። 

እንዲህ አይነት ይዘት ያlኣቸው ቪዲዮዎች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የአፍሪካ አገራት ውስጥ እየተሰሩ በቻይናውያን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ እየተበራከቱ መምጣታቸውንም አክላለች።

ተመሳሳይ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መለመዳcው በተጠቃሚዎቹ ዘንድ ስለኢትዮጵያውያኑ የተሳሳተ ግንዛቤን ሊፈጥሩና ሊያስፋፉ እንደሚችሉም ጠቅሳለች።

በተለይ የተጠቀሱት ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀረጹት ቪዲዮዎች ኢትዮጵያውን ሴቶችን የሚያራክሱ፣ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በቀላሉ ሊገኟቸው ሚችሉ ከማስመሰል አልፎ፣ የአገሪቱንም ገጽታ የሚያበላሽ እንደሆነ ኢትዮጵያውያኑ በቁጭት ይገልጻሉ።

“... እኛን የኢትዮጵያ ሴቶችን፣ የአፍሪካ ሴቶችን...ዝም ብለው ከመንገድ አንስተው እንደሚወሰዱት ነገር ምናምን ሊመስላቸው ይችላል - ቻይኖቹ።...እኛ ሴቶችም ብር ባያታልለን፣ የቆዳቸው መንጣት ባያታልለን ጥሩ ነው። እንዲህ የሚያደርጉት ክብራችንን ለሚያዋርድ አላማ ነው” ስትል ምክራለች።

ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው ለቢቢሲ አስተያየት የሰጡትን ጨምሮ ሌሎች በቻይና የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳዩን ቤይጂንግ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማሳወቃቸውንም ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ቢቢሲ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ መረጃው እንደሌላቸው፣ ነገር ግን ኢምባሲው ሁኔታውነ እንደሚያጣራ ምላሽ ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል ከቲክቶክ/ዶይን የአጠቃቀም መመሪያዎች ጋር በቀጥታ የሚቃረኑ ይዘቶችን በሚያሰራጩት ቪዲዮዎች ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ቢቢሲ ለቲክቶክ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም።