እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው የኢትዮ-ሱዳን ውዝግብ

ካርታ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮቼን ገድሏል ስትል ሱዳን ክስ አሰምታለች።

የሱዳን መንግሥት ድምፅ የሆነው ሱና እንደዘገበው አንድ ሲቪልን ጨምሮ ሰባት ወታደሮች በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተገድለዋል።

የሱዳን መከላከያ ኃይል ሰኔ 19 ቀን 2014 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሱዳናውያኑን ከገደሉ በኋላ “አስክሬናቸውን ለሕዝብ በአደባባይ አሳይተዋል” ሲል ከሷል።

የሱዳን መንግሥት በመግለጫው ለድርጊቱ “ምላሽ እሰጣለሁ” ሲል ዝቷል።

ኢትዮጵያ ግን ይህ ሆን ተብሎ በሱዳን በኩል የተፈጸመ ጠብ ጫሪነት ያስከተለው ጉዳት መሆኑን በመግለጽ፣ ውጥረቱ ረግቦ አለመግባባቶች በንግግር መፍትሔ እንዲገኝላቸው ጠይቃለች።

በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ለዘመናት በቆየው ውዝግብ ምክንያት በሁለቱ አገራት ሠራዊቶች መካከል ግልጽ ወታደራዊ ግጭት ከዚህ በፊት እምብዛም ባይስተዋልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ውጥረቱ እያየለ መጥቷል።

ቢቢሲ ሱዳን አጋጥሟል ላለችው ክስተት ከኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ባለፈው ወር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ መንግሥት የአልፋሻጋን ጉዳይ "በወዳጅነት ለመፍታት ሰላማዊ የውይይት መንገድን ይመርጣል” ማለታቸውን ይታወሳል።

ሆኖም "የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ በነበረበት ወቅት ሱዳን የድንበር ማካለሉን መጣሷ በጣም አሳዛኝ ነው” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሱዳን ኃይሎች ኢትዮጵያውያንን አፈናቅለዋል፤ ንብረታቸውንም አውድመዋል ሲሉ ከሰዋል።

እስከ አሁን እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች ምን ይላሉ?

ሱዳን ትሪቡን የተሰኘው የግል አውታር ባለፈው ሳምንት ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የሱዳን ወታደሮች በድንበር አካባቢ በምትገኘው አል-ቁሬይሻ ከተማ ላይ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ ነው ግጭት የተቀሰቀሰው።  

ሱዳን፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት እና ሚሊሻዎች በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችን ለመጠበቅ በሚል ሠፍረዋል መባሉን ተከትሎ እርምጃ የሚወስዱ ወታደሮች መላኳ ይነገራል።

በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት የወጡ ዘገባዎች ከሰዱን ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የምዕራብ ጎንደሯ መተማ ከተማ ግጭቶች እንደነበሩ ይጠቁማሉ።

በመተማ ከተማ በሚገኘው ሽመት መገዱቃ በተባለው ቀበሌ፤ በሱዳን ታጣቂዎች ተፈጸመ በተባለው ጥቃት የአካባቢው አርሶ አደሮች የግብርና ሥራቸው እንደተስተጓጎለ ተገልጧል።

የአሜሪካ ድምጽ፤ የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቁን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ “በአንድ ዓመት ውስጥ በእርሻ ሥራ የተሰማሩ 246 ባለሀብቶች ሥራቸውን አቁመዋል” ብሏል።

እንደ አልጀዚራና ሮይተርስ ያሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሱናን ጠቅሰው የሱዳን መንግሥት "እርምጃ እውስዳለሁ" ማለቱን ዘግበዋል።

በዚህም ሳቢያ ሱዳም በአዲስ አበባ ያሏትን አምባሳደር የጠራች ሲሆን፣ በተጨማሪም በካርቱም ያሉትን የኢትዮጵያን አምባሳደር በመጥራት ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠያቋ ተዘግበወል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ የሱዳን ወታደሮች ድንበር አልፈው በመግባት ግጭቱን መቀስቀሳቸውን ገልጾ፣ በሱዳን በኩል የቀረበውን ውንጀላ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ግጭቱ የተከሰተው በህወሓት ድጋፍ የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው በገቡ የሱዳን መደበኛ ወታደሮች መሆኑን በመግለጽ የሱዳንን ክስ አጣጥሎታል።

ጨምሮም በሱዳን ሠራዊትና በአካባቢው ሚሊሻዎች መካከል በተከሰተው ግጭት በጠፋው ህይወት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚያዝን ገልጾ ምርመራ እንደሚደረግ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ክስተት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ለማደናቀፍ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ መሆኑን በማመልከት፣ የሱዳን መንግሥትም ከስተቱን የበለጠ ከሚያባብስ እርምጃ እንደሚቆጠብ ተስፋ እንዳለው ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

ግጭቱ እንዴት ተቀሰቀሰ?

የትግራይ ጦርነት በተቀሰቀሰ በቀናት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የይገባኛል ውዝግብ ከሚነሳባት የአልፋሻጋ አካባቢ ለቆ ወጣ።

ጦርነቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ድንበሬ ነው የምትለው አልፋሻጋ በሱዳን ጦር እጅ ወደቀ።

ለዘመናት ኢትዮጵያ፤ የሱዳን ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት ቆስቋሽ ድርጊት ፈፅመዋል ስትል ትከሳለች።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በቅርቡ "የሱዳን ወታደራዊ ኃይል በድንበር አካባቢ ወደ ተጨማሪ ቦታዎች ዘልቆ ለመግባት የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው" ሲሉ ተደምጠው ነበር።

አምባሳደሩ አክለው፤ ችግሩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት መሞከር "ፍርሃት ወይም መወላወል አይደለም" ብለዋል።

"አካባቢውን ከግጭት ለመጠበቅ ሲባል ኢትዮጵያ ነገሮች እንዳይካረሩ ለማድረግ እየጣረች ቢሆንም ይህ ታጋሽነት ገደብ አለው" የሚል አስተያየት አክለዋል።

ኢትዮጵያ አለመግባባቱን በድርድር ለመፍታት ሱዳን የያዘችውን መሬት መልቀቅ አለባት የሚል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች።

ሱዳን በበኩሏ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ያለውንና በቅርቡ መልሳ የወሰደችውን መሬት እንደማትለቅ አስታወቃ ነበር።

"ሱዳን ከአልፋሻጋ ይዞታ ቅንጣት ታህል እንደማትሰጥ ሜጀር ጀነራል ሀይደር አልቲራፊ አረጋግጠዋል። ለወታደራዊ ኃይል ምልመላ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል" ይላል የሱዳን መንግሥት ድምፅ የሆነው ሱና ዘገባ።

አልፋሻጋ ለምን አወዛጋቢ ሆነ?

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በይገባኛል የምትወዛገብብት አካባቢ ረዥም የግዛት ድንበር ነው ያላት። ሁለቱም አገሮች ለም ነው የሚባለውን ፋሻጋ አካባቢን እጅጉኑ ይፈልጉታል።

ይህ በሁለቱ አገራት ዐይን ውስጥ ያለው አካባቢ የአልፋሻጋ ማዕዘን ወይም የአልፋሻጋ ጥግ ተብሎ ይጠራል።

በዚህ ድንበር ሁለቱም አቅጣጫ የሚገኙ ገበሬዎች ባሻገራቸው ያሉ ለም መሬቶች ላይ ያማትራሉ።

የአልፋሻጋ ማዕዘን በደቡብ ምሥራቅ ሱዳን የምሥራቃዊ ገዳሪፍ በአዋሳኝ የሚገኝ ለም መሬት ነው።

የአልፋሻጋ መሬት 250 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 600 ሺህ ኤክር አሊያም ከ240 ሺህ በላይ ሄክታር ለም መሬትን የሚሸፍን ነው። ለለምነቱ ምክንያት የሆኑት እንደ አትባራ፣ ሰቲት እና ባስላም ወንዞችም በቅርብ ይገኛሉ።

ሁለቱ መንግሥታት ከዚህ ቀደም ይህንን አወዛጋቢ ድንበር በድጋሚ ለማስመር፣ የጋራ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና የአካባቢው ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

የቅኝ ግዛት ስምምነቶች

በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ድንበሮች ብዙውን ጊዜ ውዝግብ ሲያነሱ ይስተዋላል።

ከአስርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያና ሶማሊያ በኦጋዴን የተነሳ ጦርነት አድርገዋል።

እንዲሁም ከ20 ዓመታት በፊት በባድመ ይገባኛል ምክንያት ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ውስጥ ገብተው እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።

ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያና ሱዳን ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረውን 744 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ድንበራቸውን ለይቶ ለማመላከት የሚያስችል ንግግርን መልሰው ጀመሩ።

በዚህ መፍትሄ ለመስጠት አስቸጋሪ የሆነው አካባቢ ፋሻጋ የሚባለው ነበር።

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1902 እና በ1907 በነበረው የቅኝ ግዛት ስምምነት መሰረት ዓለም አቀፉ ድንበር ወደ ምሥራቅ ይዘልቃል። በዚህም ሳቢያ መሬቱ ወደ ሱዳን የሚካተት ይሆናል።

ነገር ግን ቦታው ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት ሲሆን የግብርና ሥራ በማከናወንም የሚጠበቅባቸውን ግብር ለኢትዮጵያ መንግሥት ሲከፍሉም ቆይተዋል።

ሁለቱ አገራት ሲደረጉ በነበሩ የድንበር ድርድሮች አማካይነት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 2008 ከመግባባት ደርሰው ነበር።

በዚህም ኢትዮጵያ ለሕጋዊው ድንበር ዕውቅና ስትሰጥ ሱዳን ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ በስፍራው ያለችግር ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ፈቀደች።

ይህም አስከ ቅርብ ጊዜ በድንበር አካባቢ ያሉ የነዋሪዎችን ህይወት ሳያደናቅፍ ኢትዮጵያ ግልጽ የድንበር መለያ እንዲኖር እስክትጠይቅ ድረስ ቀጥሎ ነበር።

በሁለቱ አገራት መካከል ከስምምነት የተደረሰበትን የዚህ የድርድር ልዑክ የተመራው የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣን በሆኑት በአባይ ፀሐዬ ነበር።

ህወሓት ከማዕከላዊው መንግሥት የሥልጣን መንበር ሲወገድ የአማራ ክልል መሪዎች ከሱዳን ጋር የተደረሰው ስምምነት በአግባቡ ሳያውቁት የተደረገ ድብቅ ውል ነው ሲሉ ተቃውመውታል።

ቱርክ ባለፈው ዓመት፤ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ያላቸውን የድንበር ውዝግብ በውይይት እንዲፈቱ ለማሸማገል ጥያቄ አቅርባ ነበር። 

ነገር ግን ሱዳን ሠራዊቷን ከተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች እንደማታስወጣ ስትገልጥ ኢትዮጵያ ደግሞ የሱዳን እርምጃ ወረራ መሆኑን በመግለጥ ድርድር ከመደረጉ የሱዳን ኃይሎች ድንበሯን ለቃ እንድትወጣ ትጠይቃለች።