የሩሲያ ጄኔራሎች እየተሰወሩ ያለበት ምስጢር ምንድነው?

ሜጀር ጄኔራል ካናማት ቦታሼቭ

የፎቶው ባለመብት, Кanamat Botashev

የምስሉ መግለጫ,

ሜጀር ጄኔራል ካናማት ቦታሼቭ

ባለፈው ግንቦት እጅግ ውስብስብ ነው የሚባለው ኤስዩ-25 ጄት ተመታ። ከዶንባስ ሰማይ ላይ ተምዘግዝጎ ወደቀ።

ከጄቱ ይልቅ የአብራሪው ማንነት አነጋገረ።

ይህን ዘመናዊ ጄት ሲያበሩ የነበሩት የ63 ዓመቱ የሩሲያ ጄኔራል ነበሩ። 

እኚህ ጄኔራል እንዴት እንዲህ ዓይነት ጄት ሊያበሩ ይችላሉ?

አንደኛ ጄኔራሉ በጡረታ ከተገለሉ ድፍን 10 ዓመት ሆኗቸዋል።

ደግሞስ እኚህ ጡረተኛ ይህን ዘመናዊ ጄት ማብረር ለምን አስፈለጋቸው?

ደግሞስ ከዚህ ቀደም ባልተመለደ መልኩ የሩሲያ ጄኔራሎች በየጦር ግንባሩ የሚያዋጉት ለምንድነው? ማዋጋቱንስ ያዋጉ፣ ለምንድነው በብዛት እየሞቱ ያሉት?

ጄኔራል በዋዛ “አይሞትም”

ሜጀር ጄኔራል ካናማት ቦታሼቭ እጅግ የተዋጣላቸው አዋጊ ናቸው።

እጅግ የተከበሩ የጦር ሜዳ ሰው ናቸው።

በባለኮከብ ማዕረጋቸው፣ በገፋ ዕድሜያቸው፣ ጄት ያበሩ ነበር፣ በዚያች መጥፎ ዕለት።

ቢቢሲ እኚህ ጄኔራል ስለምን ጄት ሊያበሩ ቻሉ ሲል በቅርብ የሚያውቋቸውን ሦስት የመኮንኑ ቤተሰብ የቀድሞ ባልንጀሮቻቸውን አነጋግሮ ነበር።

እነርሱ እንደሚሉት ከሆነ ጄኔራሉ፣ “በቃኝ በዚህ ልዩ ዘመቻ አልሳተፍም” ማለት አይችሉም። በሩሲያ እንዲያ ብሎ ነገር የለም።

“ልዩ ዘመቻ” የሚለው ቃል ሩሲያ የዩክሬንን ወረራ የምትገልጽበት መንገድ እንደሆነ ልብ ይሏል።

“እኔ በሕይወቴ እንደ ጄኔራል ቦታሼቭ ሰማይ በጄት መቧጠጥ የሚወድ ሰው አላዩሁም” ይላሉ አንድ እሳቸውን በቅርብ የሚያውቁ ሰው፣ ለቢቢሲ።

“ከእርሱ ሥር ሆኜ በማገልገሌ ኩራት ይሰማኛል” ይሉና ያክሉበታል።

ይሁንና እኚህ ጄኔራል ጡረታ ከወጡ አሥርታት የተቆጠሩላቸው ሰው ናቸው።

ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ በዚህ ጦርነት መሳተፋቸው ብዙም ስሜት አይሰጥም። ስሜት ከሰጠም አንድ የሚነግረን ነገር አለ ማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ጄኔራሉ ሲያበሩት የተከሰከሰው ኤስየ-27 ተዋጊ ጄት የዚህ አይነት ነው

የሚሞቱ ጄኔራሎች መብዛት

ጄኔራል ቦታሼቭ በዚህ ጦርነት የተገደሉ ብቸኛው የሩሲያ የጦር ጄኔራል አይደሉም።

ምንም እንኳ በትክክል በዚህ ጦርነት ስንት የሩሲያ ወታደሮች ሞቱ ለሚለው እርግጡን አሃዝ ማግኘት ባይቻልም እንዲሁ በጠቅላላው ግን አንድም ጄኔራል በዚህ ዘመን ሲሞት አስገራሚ ይሆናል።

ለምን?

ለንጽጽር ያህል አሜሪካንን እንጥቀስ።

አሜሪካ ሜጄር ጄኔራል ሃሮልድ ግሪንን በአፍጋኒስታን ጦርነት በ2014 ስታጣ ጉድ ተብሎ ነበር።

ምክንያቱም አንድ የአሜሪካ ጄኔራል በጦርነት አውድማ ሲገደል ጄኔራል ሃሮልድ ከ40 ዓመት በኋላ የመጀመሪያው ነበሩ።

ለምን? በቃ ጄኔራል እንደዋዛ በቀላሉ አይሞትማ።

ዩክሬን በትንሹ 11 የሩሲያ ጄኔራሎችን ገድያለሁ ስትል ዓለም ጉድ ያለው ለዚህ ነበር።

ይሁንና የዩክሬንን አሃዝ ሳያላምጡ መዋጥ የሚከብድ ነው።

ለምሳሌ ሩሲያ ቢያንስ ከአስራ አንዱ ሞቱ ከተባሉ ጄኔራሎቿ ሦስት የሚሆኑትን አልሞቱም ብላ ምሥላቸውን በአንድም በሌላም መንገድ ዓለም እንዲያየው አድርጋለች።

ይሁንና እስከ 8 የሩሲያ ጄኔራሎች በዩክሬን ጦርነት እንደሞቱ ይገመታል። ይህ በየትኛውም መመዘኛ ትልቅ ቁጥር ነው።

ከእነዚህ መካከል ቢያንስ አራቱ ስለመሞታቸው አስተማማኝ መረጃ አለ።

ቀሪዎቹን አራቱን ደግሞ ሩሲያም እስከዛሬ ለማስተባበል አልሞከረችም። ምናልባት ሞተው ይሆናል።

በማያሻማ ሁኔታ መሞታቸው የተረጋገጠላቸው አራት ናቸው። ከጄኔራል ቦታሼቭ ሌላ የሞቱት ቀሪዎቹ ሦስት ጄኔራሎች የሚከተሉት ናቸው።

1ኛ፡- ሜጄር ጄኔራል አንድሪይ ሱክሆቬትስካይ፤ በመጋቢት አንድ ቀን ተገደሉ። አንድ ጡረታ የወጡ የሩሲያ ከፍተኛ የጦር መኰንን በትዊተር ሰሌዳቸው እንዳሉት ጄኔራሉ የተገደሉት ከኪዬቭ ብዙም በማትርቀው ሆስቶሜል አካባቢ በጠላት አነጣጥሮ ተኳሽ ጥይት ነው።

2ኛ፡- ጄኔራል ቭላድሚር ፍሮሎቭ ናቸው። በሚያዝያ 16 ተገደሉ። በሴይንት ፒተርስበርግ የቀብር ሥርዓታቸው በመፈጸሙ የመሞታቸው ዜና እርግጥ መሆኑ ታወቀ።

3ኛ፡- ሜጀር ጄኔራል ሮማን ኩቶዞቭ በሰኔ 5፣ በዶንባስ አንድ ዘመቻ ሲመሩ ተገደሉ።

የሩሲያ ብሔራዊ ጣቢያ ጋዜጠኛ የሆነው ሰው በቴሌግራም ገጹ ይህን ማረጋገጡ የጄኔራሉ ሞት ዜና እርግጥ መሆኑን አመላከተ።  

የምስሉ መግለጫ,

ሜጄር ጄኔራል አንድሪይ ሱክሆቬትስካይ

ጄኔራሎቹ ስንት ናቸው?

ለምንድነው ግን በትክክል ስንት ጄኔራሎች እንደሞቱ የማይታወቀው?

አጭሩ መልስ፤ በሁለት ምክንያቶች የሚል ነው።

አንደኛ ዩክሬናውያን በትክክል ስንት የሩሲያ ጄኔራሎችን እንደገደሉ አያውቁም።

ሁለተኛ ሩሲያውያን የጄኔራሎቻቸውን ሞት ጥብቅ ምሥጢር ያደርጉታል።

በሩሲያ ወትሮም የወታደሮች ሞት ዜና ብሔራዊ ወታደራዊ ምሥጢር ተደርጎ ይወሰዳል።

ይህ በጦርነት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሰላሙም ጊዜ ያለ ነው። 

ሩሲያ እንኳን የጄኔራሎቿን፣ የተራ ወታደሮቿን ሞትም እርግጡን አትገልጽም።

ሩሲያ መጋቢት 25 ላይ 1 ሺህ 351 ወታደሮች ሞቱብኝ ካለች ወዲህ አሃዙን ቀይራው አታውቅም።

ሩሲያ ይህን ያለችው ጦርነቱ በተጀመረ በአንድ ወር ውስጥ ነው። አሁን ጦርነቱ 4ኛ ወሩን ይዟል። የሞቱባት ወታደሮች ቁጥር ግን አሁንም እዚያው ላይ ናት።

ቢቢሲ ይፋ የሆኑ መረጃዎን በመፈተሽና የሟች ቤተሰቦችን በማናገር በጥምር በሠራው አንድ ምርመራ በትንሹ 3 ሺህ 500 የሩሲያ ወታደሮች በጦርነቱ ሞተዋል።

እነዚህ ቢቢሲ በስምና በማዕረጋቸው ጭምር ያወቃቸው ናቸው፤ ያላወቃቸው ሲደመሩ ቁጥሩ ከዚህ በእጅጉ የሚልቅ ጥርጥር የለውም።

የምስሉ መግለጫ,

ጄኔራል ቭላድሚር ፍሮሎቭ

የጄኔራሎቹ ሞት ምን ያመለክታል?

የአንድ ጄኔራል ሞት በጦርነት ብዙ ቁጥር ተደርጎ ይታሰባል።

ከፍተኛ የሩሲያ የጦር መኰንኖች ሞት ስለ ጦርነቱ የሚነግረን ታዲያ ምንድነው?

የሩሲያ ጦር ኃይሎች እስከ 1 ሺህ 300 ጄኔራሎች አሉት።

ጄኔራሎች በጦርነት ደንብ መሠረት ወደ ውጊያ ግንባር እምብዛምም አይጠጉም። በግንባር የሚገኙት የፊት አዋጊዎችና ተዋጊዎች ናቸው።

የጄኔራሎች የመሞት ዕድል ዝቅተኛ የሚሆንበት አንዱ ምክንያትም ይኸው ነው።

ሩሲያ ከላይ በአሃዝ ከተጠቀሱት ጄኔራሎች ብዙዎቹን በጡረታ ያሰናበተች የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ለከፍተኛ መኮንኖቿ ጥሪ አድርጋ በድጋሚ በጦር ሜዳ ሳታሰማራቸው አልቀረችም።

ለዚህም ነው በርካታ የሩሲያ ጄኔራሎች ራሳቸውን ባልጠበቁት ጊዜና ባልጠበቁት ቦታ አግኝተውታል የሚባለው።

ለሞታቸው ሁነኛው መንስኤም ወደ ግንባር ሄደው በጄኔራል ሳይሆን በመካከለኛ መኰንኖች ሊመራ ይገባ የነበረን ጦርነት ለመምራት መገደዳቸው ሳይሆን አይቀርም።

የምዕራብ አገራት የጦር ደኅንነት አዋቂዎች እንደሚገምቱት ከሆነ ደግሞ የተንኮታኮተ የመዋጋት ፍላጎት በሩሲያ የጦር ኃይል አባላት ዘንድ በስፋት ተንሰራፍቷል።

ይህን ለመለወጥ ደግሞ ከፍተኛ መኰንኖች፣ ጄኔራሎች ሳይቀር ወደ ግንባር ይዘምታሉ። የተዋጊ ወታደሮችን ሞራል ከፍ ለማድረግ መሆኑ ነው።

ሌላው የሚጠቀሰው እነዚህ በዕድሜ የገፉ ጄኔራሎች እጅግ ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴ እጥረት ስለገጠማቸው በቀድሞ ጊዜ ያገለግሉ የነበሩ የራዲዮ መገናኛዎችን ለመጠቀም ይገደዳሉ።

ይህም ደግሞ ወደ ግንባር ቀረብ እንዲሉ ያደርጋቸዋል። ለሞት የሚጋለጡትም በዚሁ የተነሳ ነው ይላሉ የምዕራብ ተንታኞች።

የአሜሪካ ሚዲያዎች እንደሚሉት ደግሞ የዩክሬን የወታደራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ሆን ብሎ ከፍተኛ የሩሲያ ወታደራዊ መኰንኖችን ዒላማ ያደረገ ጥቃትን ያቀነባብራል።

ይህም የአነጣጥሮ ተኳሽ [ስናይፐር] ግድያን መሠረት ያደረገ ነው። ለዚህ ስኬት ከአሜሪካ ለዩክሬን የተሰጡ ዒላማ የማይስቱ መሣሪያዎች እና የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤት የሚያቀብላቸው የጄኔራሎቹን መገኛ ስፍራ የሚያሳይ መረጃ እጅግ ጠቅሟቸዋል።

የምስሉ መግለጫ,

ሜጀር ጄኔራል ሮማን ኩቶዞቭ

ጄት አብራሪው ጄኔራል

ለመሆኑ ጄኔራል ቦታሼቭ ለምን ጄት ማብረር ይወዳሉ?

እኚህ ጄኔራል ተዋጊ ጄት በማብረር ሳይለከፉ አልቀሩም።

ሕይወታቸው የበራሪና የአብራሪ ነው።

በፈረንጆቹ 2012 ከጦር ኃይሎች የተባረሩትም የበረራ ስህተት በመሥራታቸው ነበር።

ያልተፈቀደላቸውን አውሮፕላን አስነስተው ሲያበሩ ተከሰከሱ። ሕይወታቸው በተአምር ተረፈ።

ከዚያ በኋላም ከጥፋታቸው አልታረሙም።

ሰፊ ልምምድን የሚፈልገውና ያለ ልዩ ፍቃድ በጭራሽ የማይበረውን ኤስዩ-27 ተዋጊ ጄት አስነስተው አበረሩ።

ይህን ፍቃድ ማን እንደሰጣቸው አይታወቅም።

እያበረሩ ሳለ ጄቱ ከቁጥጥራቸው ውጪ ሆነ። ሆኖም እሳቸውና ወዳጆቻቸው ለ2ኛ ጊዜ በተአምር ተረፉ።

ነገር ግን ያን ቀን በዋዛ አልታለፉም።

ቆይ ግን፣ ከዚህ ሁሉ ክስተት በፊትም በፈረንጆቹ 2011 ተመሳሳይ ጥፋት አጥፍተዋል ጄኔራሉ።

ኤስዩ-34 ጄት ማብረሪያ ክፍል በመግባት ቦምብ ጣይ ጄት ይዘው ተንሸራሽረው ተመልሰዋል። በቃ እንዲሁ።

በመጨረሻ ይሄ የማብረር ዛራቸው ጣጣ ውስጥ ከተታቸው።

ከዚህ ተደጋጋሚ ጥፋት የተነሳ የሩሲያ ፍርድ ቤት 75 ሺህ ዶላር ቅጣት እንዲከፍሉ በይኖባቸው ነበር።

ምንም እንኳ የከሰከሱት ጄት በሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቢሆንም እሳቸው የተፈረደባቸው 75 ሺህ ዶላር ብቻ ነበር።

ታዲያ ጄኔራሉ በቀደም ሲሞቱ ገና የዚህን ዕዳ ግማሹን እንኳ ከፍለው አልጨረሱም ነበር።

ጄኔራሉ ከዚህ ጥፋት በኋላ ከጦሩ ተባረው ‘ዶሳፍ’ በሚባል የበጎ ፈቃደኞች ማኅበር ውስጥ ገብተው ነበር።

የዚህ የሩሲያ በጎ ፈቃድ ማኅበር ዋና ሥራ ወጣቶችን ለውትድርና ማነሳሳት ነው።

የጄኔራሉ ጡረታ 360 ዶላር ነበር።

ዕዳቸውን እየከፈሉ ሳለ የዩክሬን ጦርነት መጣ። አመላቸውም አብሮ ወጣ። ጄት አስነስተው ማብረር ጀመሩ።

ጄኔራሉ ቀደም ብለው ለከሰከሱት ጄት አገሪቱ የጣለችባችን ይህን መቀጮ ለመክፈል የሚያስችል ገንዘብ አልነበራቸውም።

እሱን ዕዳ ሳይከፍሉ ሌላ ጄት አስነስተው አበረሩ።

ለዕዳ ባበቃቸው ጄት ተከስክሰው እስከ ወዲያኛው አሸለቡ። በዶንባስ ግዛት!