ከሕጻናት መማር የመረጠው ሮፍናን

ሙዚቃ አቀናባሪ፣ ዲጄና ድምጻዊ ሮፍናን

የፎቶው ባለመብት, ROPHNAN

ሮፍናን አምና የለቀቀው ሙዚቃ፣ ሦስት (III) ሰው ነህ ይላል፤ ሰው ወይስ አገር? እና ሰከላ በተሰኙ ርዕሶች ማንነትን፣ አገርን፣ ታሪክን እና ትርክትን ያጠይቃል።

አሁን ደግሞ የሦስት ቀጣይ የሆነውን ስድስት (VI) ከዚያም ተከታዩን ዘጠኝ (IX) ይለቃል።

ሮፍናን ከዩኒቨርሳል ሚውዚክ ግሩፕ ጋር በመፈራረም ግንባር ቀደሙ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛም ሆኗል።

ላለፉት 2 ዓመታት ከመገናኛ ብዙኃን ጠፍቶ የቆየው ሮፍናን፤ ለዩኒቨርሳል ስለመፈረሙ፣ ስለቀጣይ አልበሙ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ከቢቢሲ ጋር ዘለግ ያለ ቆይታ አድርጓል።

ቢቢሲ፡ ከዩኒቨርሳል ጋር እንዴት ተፈራረማችሁ?

ሮፍናን፡ ከዓመት ከስምንት ወር በፊት ነበር ያናገሩኝ። አንድ ዓመት የወሰደ ስምምነት ነው። ሙዚቃ ሰምተው አርቲስቱን ወደነሱ መድረክ ያመጣሉ።

የወጣ ሙዚቃን ከሰሙ በኋላ ምን አዲስ ነገር እንጠብቅ? ብለው ይመጣሉ። በተከታታይ የሚወጡ ሁለት አልበሞች አሉኝ። ከሁለቱም ወደ ዐሥር ሙዚቃች ከሰሙ በኋላ ነው ለማስፈረም የጠየቁኝ።

እነሱ ለዓመታት ገበያው ላይ ገነው ቆይተዋል። እኛ አገር ግን ሙዚቃው እንደ ኢንዱስትሪ ራሱን ችሎ ቋሟል ብዬ ለማሰብ ይከብደኛል።

ሙዚቃውን ቢያንስ ቤተሰብ እየመራንበት፣ አንዳች ቦታ እየደረስንበት ስለሆነ ኢንዱስትሪ እንበለው እንጂ፣ ኢንዱስትሪ ለመባል አንድ ሙዚቃ በአግባቡ ተሽጦ፣ አድማጩና አርቲስቱ የሚገናኙባቸው መንገዶች ያስፈልጋሉ።

ምን ሂደቶችን አልፋችሁ ነው የተፈራረማችሁት?

እንደ ዩኒቨርሳል ዓይነት ትልቅ ተቋም ወደ እንደኛ ዓይነት አገር ሲመጣ የራሱ ፈተና አለው።

ሙዚቃ እንዴት ይሸጣል? የሚለው አንድ ፈተና ነው። የእኛ አገር የሙዚቃ ማከፋፈያ መንገድ በስምምነታችን ወቅት ትልቅ ፈተና ሆኖ ነበር።

እነሱ የሚሸጡት 'ስፖቲፋይን' በመሰሉ የበይነ መረብ መንገዶች ነው። እኛ አገር ደግሞ እነዚህ አይሠሩም። ለጊዜው ያለን አንድ መተግበሪያ 'አውታር' ነው።

የሰው ሙዚቃ የመግዛትና የመጫን ልምድም ገና አነስተኛ ነው። እኛ አገር ያለን ተቋም ከዩኒቨርሳል ጋር ስለተፈራረምኩ ሙዚቃዬን ከሸጥኩ በኋላ ዩኒቨርሳል ቆርጦ ይወስዳል ሲባል፣ የዚህ አገር ተቋም በዶላር መክፈል ይኖርበታል።

ያ ማለት እዚህ አገር ባለው ሥርጭት ሰው ጋር ላይደርስ ነው። ከዩኒቨርሳል ፍላጎት ጋር ሳይጣረስ እዚህ አገር ያለውን፣ ይዞኝ የመጣውን ማኅበረሰብ እንዴት ነው የምደርሰው? የሚለው ሌላ ትልቅ ጥያቄ ነበር።

መጨረሻ ላይ የእኛ ማኅበረሰብ በሚችለው፣ በሚፈቅደው መንገድ ሙዚቃዎቹን እንዲጭን፣ እንዲገዛ፣ ዩቲዩብ ላይ እንዲያይ መልካም ፈቃዳቸው ሆኗል።

እልህ አስጨራሽ ምልልስ ነበር።

ስምምነቱ ሙዚቃው የሚሠራበትና የሚሰራጭበትን መንገድ መወሰንን ያካትታል?

ዩኒቨርሳል ሙዚቃዬ ላይ ይሄ ይኑር፣ ይሄ ይቆረጥ ማለት ይችላል።

የራሳቸውን አሻራ ቢያስቀምጡም ስምምነቱ ላይ ሙሉ በሙሉ የአርቲስት ነጻነቴ ይከበራል። ማስኬድ የምፈልገው በዚህ መንገድ ብቻ ነው ብል የመቀበል ግዴታ አለባቸው። ግብአታቸው ግን ትልቅ ነው።

ነገሮችን የሚያዩት በዓለም አቀፍ ዐይን ነው። እኔ የሚያስፈልገኝም እሱ ነው። ከሆነ አገር ወይም ስቱዲዮ የሆነ ነገር እፈልጋለሁ ብላቸው ያመጡልኛል።

ለምሳሌ የምዕራብ አፍሪካ የሙዚቃ መሣሪያ ብፈልግ፣ ፈረንሳይ ወይም አቢጃን ካስፈረሟቸው አርቲስቶች፣ ያንን መሣሪያ ስቱዲዮ ውስጥ በከፍተኛ ጥራት ቀርጸው ይልኩልኛል።

ከዚህ ወይም ከዚያ አርቲስት ጋር በጥምረት መሥራት እፈልጋለሁ ብል፣ በራሳቸው መንገድ ያንን አርቲስት ያመጣሉ። ከዚህ አርቲስት ጋር ብትሠራ ብለውም ይጠቁማሉ።

አሁን በምታወጣው አልበም ላይ ትልልቅ ስም ካላቸው አርቲስቶች ጋር ተጣምረሀል?

‘ሦስት’ን ከዩኒቨርሳል ስምምነት በፊት ነው ያወጣሁት። ቀጥሎ የሚመጡት ‘ስድስት’ እና ‘ዘጠኝ’ እንዲሁም 3-6-9 ናቸው።

ዘጠኝ ላይ ከእነማን ጋር እንደተጣመርኩ አሁን መናገር አልችልም።

‘ስድስት’ ላይስ?

ዩኒቨርሳል ሙዚቃ ሲለቅ በዘረጋው ዓለም አቀፍ መዋቅር መሠረት ወራትን ጠብቆ ነው። በምን ራድዮ፣ በምን የሙዚቃ መዘርዝር (playlist) ይለቀቅ የሚለውም ይታያል።

በዚህ አካሄድ አሁን ለትውልዱ መድረስ አለባቸው የምላቸው መልዕክቶች ሊዘገዩብኝ ይችላሉ። እነሱ ‘ስድስት’ እንዲወጣ ያሰቡት ታኅሣሥ ላይ ነበር። ወደዚህ ለማምጣት ብዙ ታግለናል። አሁን አልበሙ እንዲወጣ ሲፈቅዱልን እነሱ ለዓለም አቀፍ አድማጭ ይሆናሉ የሚሏቸውን ሙዚቃዎች ወስደው ነው።

‘ስድስት’ ለትውልዴም፣ ለታናናሾቼም የሚሆን ስጦታ ነው። ለኢትዮጵያ የተጻፈ፣ ለትውልዴ የተጻፈ ደብዳቤ ነው።

ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ ከመሄዴ በፊት ይሄን ሁሉ ላደረገልኝና ላሳደገኝ ማኅበረሰብ አንድ ነገር ማቀበል፣ እንዲሁም ጠንካራ አቋምና መልዕክቶች ማስተላለፍ አለብኝ ብዬ የምፈልጋቸውን ሙዚቃዎች ለይቼ አውጥቻለሁ።

‘ስድስት’ ላይ ከጁልያን ማርሌ በስተቀር ሌሎቹ [አብሬያቸው የሠራኋቸው አርቲስቶች] ወደዚያኛው ነው የሄዱት።

ለዩኒቨርሳል በመፈረምህ ምን ተሰማህ? አንዱ በኢትዮጵያ ሙዚቃ የሚነሳው ክፍተት እንደ 'ኢትዮፒክስ' ያሉ ፕሮጀክቶች ካልመጡ ወይም እንደ 'አካሌ ውቤ' ያሉ የውጭ ባንዶች በኢትዮጵያ ሙዚቃ ምርምር ሲያደርጉ ካልሆነ፣ አገር በቀል ሙዚቃው እምብዛም ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ አይደርስም የሚለው ነው። ያንተ ለዩኒቨርሳል መፈረም ይሄን እንዴት ይቀይራል?

ካየኋቸው ብዙ ነገሮች በጣም ስሜታዊ ያደረገኝ ስምምነቱ የተፈረበት ቅጽበት ነው፡፡

ዕድሜዬን በሙሉ ነው ሙዚቃ የሠራሁት፡፡ ሙዚቃ የጀመርኩት በመቅዳት (recording) ነው፡፡

አሁንም ድረስ ያለኝ ባህሪ ነው፡፡ የ10 ዓመት ልጅ ሆኜ የእናቴን ድምጽ እቀዳ ነበር፡፡

ስምምነቱን መፈረም ልጅነቴ ጋ ነው የወሰደኝ፡፡ ቤተሰቦቼን እንዳመሰግን አደረገኝ፡፡

እናቴን “እኔ የምልሽ ምን እያረግሽ ነው? ዓመት በዓል’ኮ ደርሷል? ምን ታስቢያለሽ?” እያልኩ እቀዳት ነበር።

ወይ ዝፈኚልኝ ነው የምላት፡፡ ይሄን ሕጻን ልጅ በዚያን ሰዓት “ምን ያደረግልሃል?” ወይም “አርፈህ አጥና” ብትለው፣ ያ ልጅ እዚህ ላይደርስ ይችል ነበር፡፡

የውጭ አገር የሙዚቃ ቪድዮ ወይም ሽልማት ሲታይ የሆነ የሚያስቀና ነገር አለ።

ከዩኒቨርሳል ጋር የተፈራረምኩት እዚሁ አገር ሆኜ ነው። ስደት የምመኝ ሰው አይደለሁም፡፡ ስደት የሚባለውን መቀልበስ ይቻላል።

እኛ ሳይሆን እነሱ እንዲመጡ ማድረግ ይችላል፡፡ አገሬ ላይ ቁጭ ብዬ ለትውልዶች የዘለቀውን [በዓለም አቀፍ መድረክ ያለመድመቅ] መርገምት (generational curse) መስበሬ ነው ስሜታዊ ያደረገኝ፡፡

ይሄ ጅማሮ [ለሌሎች ሙዚቀኞችም] በር ይከፍታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለሙዚቃ ኢንዱስትሪያችን አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ ዩኒቨርሳሎችም በዚህ እርግጠኛ ናቸው፡፡ ትልቅ ተስፋ ይታየኛል፡፡

ለዩኒቨርሳል በመፈረም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ነህ?

አዎ። ከሌሎች ዓለም አቀፍ ሙዚቃ አሳታሚዎች ጋር ጂጂ እና አስቴር [ውጭ አገር ሆነው] መፈራረማቸውን አውቃለሁ፡፡

አገሬ ላይ ቁጭ ብዬ አልበሜን እሠራለሁ ብዬ በመፈረም ግን የመጀመሪያው ነኝ፡፡

ስምምነቱ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል?

‘ዘጠኝ’ ከወጣ በኋላ የ4 ዓመት ኮንትራት ነው፡፡

ስምምነቱ የገንዘብ ክፍያን ይጨምራል?

እነሱ አርቲስቱ ላይ ገንዘብ ያፈሳሉ። ሙዚቃው ሲከፋፈልና ከዓለም አቀፍ የሙዚቃ ጉዞ ደግሞ ጥሩ ተከፋይ ይሆናሉ።

ስለዚህ ዓለም አቀፍ ጉዞዎች ይኖሩሃል?

በራሳቸው የሚያመጧቸው ጉዞዎች ይኖራሉ፡፡ ትልቁ ግባቸው ሙዚቃዬን በዓለም ተደማጭነት ማስገኘት ነው፡፡ ከተደማጭነት ከሚገኘው ስኬት አንዱ ጉዞ ነው፡፡ ኮንሰርቶች፣ ፌስቲቫሎች ይኖራሉ።

የፎቶው ባለመብት, ROPHNAN

አምና ‘ሦስት’ን ለቅቀሀል። አሁን ደግሞ ‘ስድስት’ እና ‘ዘጠኝ’ ይጠበቃሉ። ለመሆኑ የ3-6-9 ትርጉም ምንድን ነው?

የሐሳቡ መነሻ የኒኮላ ተስላ ቀመር ነው።

የእነዚህን ቁጥሮች ምሥጢር ያወቀ የሁለንታን (universe) ቁልፍ እንዳገኘ ይቆጠራል ይላል።

ተስላ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም እነዚህ ቁጥሮች ምሥጢር አላቸው።

ለምሳሌ ሦስት ዘፍጥረትን፣ ሥላሴን፣ ሰውን ይወክላል፡፡ ሰው ስለ አጠቃላይ ሁለንታ ሲያስብ የቋንቋ፣ የዘር ወይም የድንበር ፖለቲካ ውስጥ ራሱን አያገኝም።  

እንደዚያ ዓይነት ነገር የሚያመጣው ነገሮችን አጥብቦ ከማየት ነው፡፡ የዓለምን ግዝፈት ለማየት ስንሞክር ከዓለም ጋር የሚያመሳስለን ቀመር እናገኛለን፡፡

ለእኩዮቼ ወይም ለታናናሾቼ ትልቁን ምሥል ለመስጠት ነው፡፡

ሌላው ነጥብ፣ አንድ መጽሐፍ ወይም ፊልም ቅጾች ኖረዋቸው ሐሳቦችን እንደሚገለጹት፤ ሙዚቃንም እንደዚያ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡

3-6-9 አመለካከታቸው፣ ድምጻቸው፣ አቅጣጫቸው የተለያየ ነው፡፡ አንድ የሚያደርጋቸው ነገርም አለ፡፡

እንደ ትውልድ በአብዛኛው የተሰጠን ዕውቀት በጣም የቅርብን ብቻ የሚያይ ነው፡፡

የሰው ልጅ አእምሮ ደግሞ የቅርብን ብቻ ካየ ዓለም እሷ ነች ብሎ ያስብና እሷ ላይ ይጣላል፡፡ ዓለምን ሰፋ አድርጎ የሚያስብ አእምሮ ግን የቅርብ ሳይሆን የሩቅን ማየት ይችላል፡፡

አሁን ቋንቋ፣ ብሔር፣ ዘር የምንላቸውን ጽንሰ ሐሳቦች ለእኛ እጅግ ገነው የሚታዩን ለነገሮች ካለን አመለካከት የተነሳ ነው፡፡

ለወጣቱ የሰፋ አጀንዳ መስጠት ወይም የሰፋ ምልከታ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ልንሆን እንችላለን፡፡ የዓለም ዜጎችም ነን፡፡ ዓለም ያየናል፡፡

እርስ በእርስ እንዲህ የምንሆን ከሆነ ሁልጊዜም ከዓለም በታች ሆነን እንቀራለን፡፡ ራሳችንን አጠገብ ለአጠገብ ብቻ የምናይ ከሆነ የዓለም ትልቅነት እንዴት ይገባናል?

ለዚህ ትውልድ የሚያስፈልገው ሉላዊነት (universality) ነው እያልክ ነው?

አንዱ መልዕክት እሱ ነው፡፡ ለምሳሌ ‘ስድስት’ የሚወክለው የ6 ዓመት ሕጻን ልጅን ነው፡፡

አልበሙ በሙሉ የተሠራው ከዚያ ሕጻን ልጅ አንጻር ነው፡፡ ያ ሕጻን ልጅ የምናደርጋቸውን፣ የምንናገራቸው፣ የምንወስናቸው አይቶ፣ ቃላት አሰካክቶ መናገር ቢችል፣ እንዲህ ብሎ ይናገራል ብዬ አስቤ ነው የሠራሁት፡፡

ይህንን ለማግኘት ከሕጻናት ጋር የተወሰነ ጊዜ ማሳለፍ ነበረብኝ፡፡ ከእነሱ ጋር ለመግባባት መሞከር ነበረብኝ፡፡

ከሕጻናት ጋር የሚደረግ ንግግር ወዳሰብነው አቅጣጫ ላይሄድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የሚግባቡት በራሳቸው መንገድ ነው፡፡ በጣም ያገዘኝ ሥዕል ነው፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ሕጻናት ማሳደጊያዎች በመሄድ ሕጻናትን እየሰበሰብን ይህን ስናደርግ ነበር፡፡ ቃላት እሰጣቸውና ወደ ሥዕል እንዲቀይሩልኝ እጠይቃቸዋለሁ፡፡

ለምሳሌ ፍቅር፣ ተስፋ ብዬ የሰጠኋቸውን ቃላት ወደ ምሥሎች ቀየሩ፡፡ በቀለም አመራረጣቸው፣ በአቀባባቸው፣ በአቅጣጫቸው እኔ ተነሳስቻለሁ።

በዚህ መነሳሳት (inspiration) ግጥም መጻፍና ሙዚቃ መሥራት ውስጥ እገባለሁ፡፡ የ6 ዓመት ልጅ ዕይታ በውስጣችን የማያረጀው (inner child) ማለት ነው።

ያለፉት ጊዜያት ወጣቶችን ሰቀቀን (trauma) ውስጥ ከተዋል። አሁንም እያለቀ ሳይሆን እየጨመረ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የምንወስናቸው ውሳኔዎች ጤነኛ ይሆናሉ ብዬ አላምንም፡፡ ተስፋ ይሆናሉ፣ መዳኛ ይሆናሉ፤ ብዬ የማስባቸው ሐሳቦች ሕጻናት ጋር አሉ።

ባሕሪያቸው ይቅር ባይነት፣ ነገሮችን ማሳለፍ፣ ለማንነት አለመገዛት ነው። እኔ እንዲህ ነኝ ብሎ ተገትሮ፣ ያንን ነገር ሰው ከመሆን በላይ አድርጎ መውሰድ ሕጻናት ጋር የለም፡፡ ሕጻናት ጋር ሰውነት ይቀድማል፡፡ ሕጻናት ጋር በትናንትና አለመታሰር፣ ነገን አለመፍራትና ዛሬ ላይ መኖር አለ፡፡

ከዚህ ዕይታ ተነስቼ ስጽፍ ሙዚቃዬ ጤነኛ ይሆናል።

ለምን መሰለሽ፤ ራሴን አላምነውም፡፡ ገለልተኛ አይደለሁም። እዚህ ትውልድ ውስጥ ስላለሁ አቋም ይኖረኛል፡፡ የሕጻናት ዕይታ ውስጥ ግን የበለጠ የማምነውና የበለጠ ትክክል የሆነ ነገር አያለሁ፡፡

የመጀመሪያው አልበምህ የኢትዮጵያን የተለያዩ አካባቢዎች ባሕልና ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን የሚያስተሳስር ገመድ የመፈለግ ጉዞ ነበር፡፡ አሁን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር፣ እየተፈጠረ ያለው ቀውስ ሰዎችን እንዴት እየጎዳ እንደሆነ ከማየት ተነስተህ ውስጣችን ያለውን እንቦቀቅላ ወደመፈለግ ያደረግከውን የምርምር ጉዞ እስኪ አስረዳን?

እያወቅን ነው እያላወቅን የመጣነው? የሚለውን አስባለሁ።

እያደግን በሄድን ቁጥር ምሁር እንሆናለን። አዋቂ እየሆንን እንመጣለን ብዬ ግን አላስብም፡፡ አዋቂነት ያለው ልጅነት ጋ ነው የሚል ድምዳሜ እንድሰጥ አድርጎኛል፡፡

ምሁር ስልሽ አንድ ነገር ላይ ብዙ መረጃ ያለው ሰው ማለቴ ነው፡፡ አንድ ሰው በጥልቀት ሄዶ የሕክምና ምሁር ሊሆን ይችላል፡፡

አዋቂነት ግን አንድን ነገር በጥልቀት ማወቅ ሳይሆን፤ አንድ ነገር ከሌሎች ነገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ወይም አንድ ትንሽ ነገር ከዓለም ጋር ያለውን ግንኙነት ማየት ነው፡፡

እነዚህን ነገሮች በሕጻናት አንደበት ተዘርዝረው ባናገኛቸውም በድርጊታቸው ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከአካባቢያቸው ጋር የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ዙርያቸውን ያከብራሉ፡፡ በአካባቢያቸው ይመረኮዛሉ፡፡ አንድነትን በተግባር ያውቁታል፡፡

እነሱ ጋ የእኔ የሚባልን ነገር ብዙ አታይም፡፡ ክብረ እኔ (ego) እነሱ ጋ አድጎ አይታይም፡፡ ተፈጥሯዊ ማንነት፣ መልካም አሳቢነትና ከሁሉም በላይ በሰው ጫማ ውስጥ መቆም መቻልን እነሱ ጋ አግኝቼዋለሁ፡፡ እኛ ጋ የሌለ ነገር ነው፡፡

አንድን ልጅ፣ ሌላ ሕጻን ፊት በጥፊ ብትመቺው፣ ያልተመታው ልጅ በድንጋጤ ያለቅሳል፡፡

በሌላ ሰው ጫማ ውስጥ የመቆም አቅማቸው ትልቅ ነው፡፡ እኛ ግን የራሳችን ቤት ካልመጣ፣ የሰው ቤት ያለ ነገር ሲያሳዝነን አይታይም፡፡

እዚህ ያደረሰንም እሱ ነው፡፡ የእኔ ሰላም እኔ ጋ ነው ያለው፡፡ የእኔ ደኅንነት ግን አጠገቤ ያለ ሰው ጋ ነው ያለው፡፡ የእሱም ደኅንነት እኔ እጅ ላይ ነው ያለው፡፡

የሰፈር ደኅንነት ሌላ ሰፈር ደኅንነት እጅ ላይ ነው ያለው፡፡ በሕጻንነት ይሄ በደንብ ገብቶን ኖረናል፡፡ ኢጓችንን አውርደን፣ በማንናገረው ቋንቋና በማንከተለው ሃይማኖት ውስጥ ላሉ ሰዎች ሐዘኔታ አጥተናል።

ክርስትና እንደ ሕጻናት ካልሆናችሁ መንግሥተ ሰማያትን አትወርሱም ይላል፡፡

ልጆች ማን እንደነበርን ያስታውሱናል፡፡ የገነባነውን ማንነት ያወርዱትና አስቀምጠው ያሳዩናል፡፡ ማየት ከቻልን ማለቴ ነው፡፡

የማንነትን ጥያቄ ደጋግመህ ታነሳለህ፡፡ ማንነት በተለያየ መንገድ ይገለጻል፡፡ አንዱ አተያይ ማንነት እንደ ፈሳሽ ያለ (fluid) ነው ይላል፡፡ ማንነት ይገነባል፤ ይፈርሳልም። አንተ በደረስክበት ማንነት ምንድን ነው?

ማንኛውም ማንነት ላይ መቆም ይቻላል፡፡ ያ ማንነት የሌላ ሰው ሕመም እንዳይሰማን የሚያደርግ ከሆነ ትክክለኛ ማንነት አይደለም፡፡ በአንድ ቋንቋ ውስጥ መወለድ፣ በአንድ አካባቢ ማደግ የሰው ልጆች በዝግመተ ለውጥ ያመጡትና የሚያሳምረን ልዩ ቀለም ነው፡፡

ዓለም ልሙጥ ብትሆን አትማርክም፡፡ ባሳደጉን፣ ባስተማሩን፣ ባገኘናቸው ሰዎችና በዓለም ሁነቶች ማንነት እንገነባለን፡፡

የሰው ልጅ ያለ ባሕል አይኖርም። ነገር ግን የትኛውም ማንነት ውስጣችን ካለው እምቦቀቅላ (inner child) የሚያወጣን ከሆነ መልካም ማንነት አይደለም።

የሰው ሐዘን የማይሰማን፣ የሰው ነገር የማይቆረቁረን ደረጃ ላይ ከደረስን እና የእኔነት ግንቡ ተልቆ ከሰው በላይ እንደሆንን ከተሰማን፣ ያ ትክክለኛ ማንነታችን አይደለም፡፡

እዚህ ስለተወለድኩ የተሻልኩ ነኝ ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም፡፡ የትኛውም ማንነት በተወለድንበት ቦታ፣ ባየናቸው ሰዎችና በተማርናቸው ትምህርቶች የሚቀየር እንጂ እውነተኛ ማንነታችን አይደለም፡፡

እኔና አንቺ ኖርዌይ ተወልደን ቢሆን፣ ማንነት ብለን የምንጠራቸው ነገሮች ቅርጻቸው ወደዚያ አካባቢ ይቀየራል፡፡ የሰው ልጅ በተወለደበት ቦታ ማንነት ይገነባል፡፡

ማንነቱ ከሰው እንደሚበልጥ ቢነግረው ግን፣ ያ ከመሠረታዊ ማንነቱ ወይም ተፈጥሮ ከለገሰችው ማንንት የወጣ ነው፡፡

የፎቶው ባለመብት, ROPHNAN

ጦርነት የተፋፋመበት፣ በየቀኑ ግድያ የምንሰማበት፣ መፈናቀል የበዛበት ጊዜ ላይ ነን። አንተ ደግሞ “በቋንቋና በብሔር ፖለቲካ ውስጥ ራሳችንን አናገኝም” ትላለህ፡፡ ታዲያ “የእኔ” የምትለው ትውልድ ራሱን ወደ የትኛው ማንነት ይውሰድ?

ታሪክን ዞር ብለን እንይ፡፡ ታሪክ መማሪያና ዛሬን ማስተካከያ ቢሆን መልካም ነው፡፡

ዝም ብሎ በታሪክ መኩራትም መልካም አይደለም። ታሪክ ሊያኮራን የሚገባው ተቀብለነው፣ ከውስጡ መልካም ነገር ይዘን፣ የእኛን ሕይወት ካሻሻልንበት ነው።

የእኛን ሕይወት ማጥፊያ ከሆነ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ማንነት መፈተሽ አለበት፡፡ ሰው በጣም ሲከፋው ቤተሰቦቹ ቤት ሄዶ ጭንቀቱን አራግፎ ይመለሳል አይደል?

አሁን ወደ ሰውነት ወይም ወደተነሳንበት ማንነት የምንሮጥበት ጊዜ ነው፡፡ ሰው ነን ስንል የሰው ሁሉ ሕመም ይገባናል፡፡ ሁሉም ሰው የራሱ ታሪክ አለው፡፡ ታሪክ ለሌላ እኩያዬ፣ ሌላ ገጽታ እንዳለው መረዳት አለብኝ፡፡

ማናችንም ከመቶ፣ ከሺህ ዓመት በፊት አልኖርንም። የምናውቀው የተወሰኑ ዐሥርት ዓመታትን ነው፡፡ ሌላው ተጽፎ ያነበብነው ነው፡፡

ታሪክ እንደ ፀሐፊው ሊበረዝ እንደሚችል ማወቅ አለብን፡፡ ስለምንጽፈው ታሪክ እንጂ ስለተጻፈ ታሪክ መሞት የለብንም፡፡ ስለተጻፈ ታሪክ ማንም ሰው መሞት የለበትም፡፡

በአብዛኛው የገነባነው ማንነት የተሰበከ ማንነት ነው፡፡ የተነገረን ማንነት እንጂ የኖርነው ማንነት አይደለም፡፡

ከተነገረን ማንነት የኖርነው ማንነት ይበልጣል፡፡ ይሄ በግልጽ የሚታየን ራቅ ስንል ነው። የተሰጠንን ማንነት አንድ ጊዜ እንደ ልብስ አውልቀን አስቀምጠነው፣ እንደ ሰው ወይም እግዚአብሔር እንደፈጠረው ሰው ራሳችንን ካየን በኋላ ሌሎች ማንነቶችን ደግሞ ከዚያ በኋላ ብናጠይቃቸው መልካም ነው፡፡

ለእኔ ቀላሉ መንገድ ራሴን አለማመን ነው፡፡ ጭንቅላቴ ውስጥ የሚመጡ ሐሳቦችን መካድ ግዴታዬ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም እውነት ይሄ ነው ወይ? ብዬ መጠየቅ አለብኝ፡፡ ታሪክ በውሸት ተጽፎ እኩዮች በጋራ ካመኑበት ትክክል የመሆን አቅም ያገኛል።

ለምሳሌ በብዙ ነገሥታት ሥልጣኔ ያለፉ አፍሪካውያን ከአፍሪካ ተወስደዋል፡፡ ታሪካችን ከቅኝ ግዛት እንዳልጀመረ ይታወቃል፡፡ አፍሪካዊያን ካሪቢያን ተወስደው የተጻፈላቸው ታሪክ ግን አፍሪካዊያን “ባሪያ እንደሆኑ” ያስተምራል። ማንም ሰው ታሪኩን ጽፎ ራሳቸውን በዚህ መንገድ እንዲቀበሉ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ታሪክ ሲነገረን ከዛሬ ጋር ማገናዘብ አለብን፡፡

‘ሦስት’ ላይ ሁሉም ትውልድ የራሱ አድዋ እንዳለው ጽፌያለሁ፡፡ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን አድርገው የጋራ የሚሉትን መሰናክል ያሸነፉበት ነው፡፡ የጋራ የምንለው ብዙ ነገር ስላለን ይሄንን አሁንም ልናደርገው እንችላለን። ያንን [አድዋ] መማሪያ ካላደረግነውና ዝም ብለን መፎከሪያ ካደረግነው ግን ነገሩን ያብሰዋል።

የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚንከባለል ጎማ ራሱን የሚደግም ነው፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን የእርስ በእርስ ጦርነት አሳልፏል፡፡

አይንስታይን እንደሚለው እርምጃ ሳይወስዱ ስህተትን እየደጋገሙ ለውጥ መጠበቅ እብደት ነው፡፡ የሆነ ነገር መቀየር አለበት፡፡

በትናንት ታሪክ ስንኮራ የዛሬ ማንነታችን ቆሻሻ ከሆነ የውሸት ኩራት ነው፡፡ ያንድን ሰው ሕመም አልቀበልም ስንል የዚያን ሰው ሕመም እናብስበታለን። እዚህ የከተተንም ያ ነው፡፡ ከአገር ፍቅር ጀምሮ ሁሉንም ነገር ማጠየቅ አለብን፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ መጠን እና መንገድ ሁላችንም ሰቆቃ (trauma) ውስጥ እያለፍን ነው። አንተ እያለፍክበት ያለው ሰቆቃ እንደ ሰውም፣ እንደ ሙዚቀኛም ምንድን ነው ያደረገህ?

ራሴን እንዳላምን አደረገኝ፡፡ ሰው ከበሽታው ለመዳን ታምሜያለሁ የሚለውን መቀበል አለበት፡፡

ማንኛውም ሰው ሙሉ መረጃ ስለሌለው እኔም የተሳሳተ አቋም ሊኖረኝ እንደሚችል አስባለሁ።

ማንንም ሰው [ሳልፈርጅ] ለመስማት ዝግጁ መሆን እንዳለብኝ ተምሬያለሁ፡፡

አሁን ያለው ሐዘን እንደ ሰው በብዙ ይጎዳል፡፡ ያማል፣ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ከሕጻናቱ የተማርኩት ነገር፣ ይቺ አገር ለእኔ ተስፋ ከሆነችው በላይ ለእነሱ የበለጠ ተስፋ እንደሆነች ነው።

እግራቸው ሮጦ መሰደድ እንኳን አይችልም፡፡ ይሄ ሐሳብ መልሶ ያነሳኛል፡፡ ኃላፊነት እንዳለብኝ፣ ይቺ አገር የእኔ ብቻ እንዳልሆነች፣ የሚመጣው ትውልድ የራሱን ዕድል መሞከር እንዳለበት ይሰማኛል።

ለእነሱ ዕድል ስትይ ድጋሚ ለመጻፍ፣ ድጋሚ ለመሞከር ትነሻለሽ፡፡ በሕመሜ ምክንያት ወገንተኛ (biased) እንዳልሆን ከሕጻናት ለመማር ሞክሬያለሁ፡፡

በእያንዳንዷ የአገራችን ክፍል በዚህ ሁለት ዓመት ያየነውን እልቂት እና የሰው ልጆች መከራ፣ ከላይ ያሉ ሰዎች የተናገሩትን ንግግር፣ እኛ የደገፍንበትን ወይም የተቃወምንበትን ምክንያት ለ6 ዓመት ልጅ ባብራራለትስ ብለን እናስብ።

ሕጻኑ በጣም የማሳዝን ወይም አእምሮዬ ዝቅ ያለ ሰው እንደሆንኩኝ ነው የሚረዳው፡፡ ሰው እንዴት እንደዚህ ያደርጋል? ነው የሚለው።

ያለፍናቸውና አሁንም የምናልፋቸው ነገሮች በእኛ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥም እጅግ አሳዛኝ ሆነው ይጻፋሉ። በዚህ እኮራለሁ የሚል ካለ፣ ምናልባትም ነገሮችን በግልጽ ያላየ ብዬ አልፈዋለሁ፡፡