ሁለት ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ትግራይ እንዲገባ መንግሥት መፍቀዱ ተነገረ

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና ዴቪድ ቢዝሊ

የፎቶው ባለመብት, MoFA/FB

የምስሉ መግለጫ,

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና ዴቪድ ቢዝሊ

የኢትዮጵያ መንግሥት ለእርዳታ አቅርቦት ሥርጭት የሚውል በየወሩ ሁለት ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ መፍቀዱ ተነገረ።

ይህ የተነገረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊ ሮም ውስጥ በተነጋገሩበት ወቅት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ውይይቱን በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው የሚቀርበው ነዳጅ በክልሉ ውስጥ ከሚሰራጨው የእርዳታ አቅርቦት ጋር ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበት መስማማታቸው ተገልጧል።

በዚህም መሠረት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በየወሩ ሁለት ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ትግራይ ለማስገባት ዝርዝር ሰነድ አቅርቦ፣ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የተጠቀሰው መጠን ያለውን ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገባና ይህም በክልሉ ውስጥ ለሚሰራጨው የእርዳታ አቅርቦት ማጓጓዣ እንዲውል መንግሥት መፍቀዱን አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል። 

በተጨማሪም አስፈላጊ ናቸው የተባሉ ነገሮች በማስረጃ እስከተደገፉ ድረስ የፌደራል መንግሥቱ ወደ ትግራይ ክልል የሚገባውን የገንዘብ እና የነዳጅ መጠን ለመጨመር ዝግጁ እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን፣ ህወሓት በአየር የሚቀርበውን ሰብአዊ እርዳታ መከልከሉንም ተናግረዋል። 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 16/2014 ዓ.ም. እንዳስታወቀው በየቀኑ መድኃኒቶች፣ የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሁም የህጻናት አልሚ ምግቦች የሚላክበትን የአየር በረራዎችን ህወሓት ከረቡዕ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ መቀለ እንዳያርፉ ከልክለዋል።

የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ይህንን በተመለከተ በትዊተር ገጻቸው በኩል በሰጡት ምላሽ “አየር ማረፊያው በጊዜያዊነት የተዘጋው በነዳጅ እጥረት ምክንያት” መሆኑን አመልክተው በአጭር ጊዜው ውስጥ ሥራውን ይጀምራል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንደተናገሩት ህወሓት የነዳጅ እጥረት አለ የሚለውን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት ብቻ 137 ሺህ 913 ሊትር የጫኑ ሦስት ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ መግባታቸውንና ይህም ለእርዳታ አቅርቦት በቂ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን እንዳለውም በአጠቃላይ 920,309 ሊትር ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱን አመልክቶ፣ ህወሓት የነዳጅ እጥረት እንዳለ የሚናገረው "ለሌላ ጦርነት ለሚያደርገው ዝግጅት ሠራዊቱን ለማንቀሳቀስ የሚያስችለውን አቅሙን ለማጠማከር ነው" ሲል ከሷል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ጦርነቱ ተባብሶ ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ ወደ ትግራይ የሚገባው የሰብአዊ እርዳታ እና ነዳጅን አቅርቦት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።

በዚህም ሳቢያ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪ ለከባድ ችግር ተጋልጦ ቆይቷል።

መጋቢት ወር ላይ የፌደራል መንግሥቱ ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሲባል የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የእርዳታ አቅርቦት ወደ ክልሉ እንደገባና የነዳጅ እጥረት ግን እንዳለ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት በዚህ ወር እንዳለው መቀለ ውስጥ በሚገኙ መጋዘኖቹ ውስጥ ለ950,000 ሰዎች የሚበቃ ምግብ ቢኖረውም በነዳጅ ችግር ምክንያት ወደሚፈለገው ቦታ ማድረስ እንዳልተቻለ መግለጹን ኤፒ ዘግቧል።

የአውሮፓ ኅብረት የቀውስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺክ በኢትዮጵያ ባለፉት ቀናት ጉብኝት ካደረጉ በኋላ እንደተናገሩት “መጋዘኖች በእርዳታ አቅርቦት ሙሉ ቢሆኑም፣ ወደ ገጠሩ አካባቢ ሊደርሱ አልቻሉም” በማለት የነዳጅና የገንዘብ አቅርቦት እጥረትን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ በተለይም የነዳጅ አቅርቦቱን የህወሓት አመራሮች ለወታደራዊ አላማ ሊያውሉት ይችላሉ የሚል ስጋት ያለው ሲሆን፣ የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣኑም ይህንን የሚያስወግድ “የቁጥጥር ዘዴ” ተግባራዊ በማድረግ አቅርቦቱ እንዲፋጠን ጠይቀዋል።

ከተጀመረ ወደ 19 ወራትን ያስቆጠረው የትግራይ ጦርነት በአሁኑ ወቅት ጋብ ያለ ቢሆንም፣ የተለያዩ ወገኖች የማሸማገል ጥረት ቢያደርጉም አስካሁን ጦርነቱን የሚያበቃ ስምምነት ላይ አልተደሰም።