ትውልደ ሴኔጋላዊው ካቢ ላሜ የዓለማችን ቁንጮ ቲክቶከር ሆነ

የ22 ዓመቱ የቲክቶክ ቁንጮ ካቢ ላሜ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

አሁን የቲክቶክን መንደር በተከታዮች ብዛት በበላይነት የሚመራው ትውልደ ሴኔጋላዊው ካቤ ላሜ ነው።

የ22 ዓመቱ ወጣት በቲክቶክ ላይ ቃል ሳያወጣ፣ በአካል እንቅስቃሴ ብቻ ትዝብቱን በማጋራት አሜሪካዊ ቲክቶከሮችን በልጦ የመተግበርያው ማማ ላይ ተቀምጧል።

ከዚህ ቀደም የአንደኝነቱ መንበር ተይዞ የነበረው በቻርሊ ዲ አሚሊዮ ነበር።

ላሜ በአሁን ሰዓት 142.8 ሚሊዮን ተከታዮች ሲኖሩት፣ ዲ አሚሊዮ ደግሞ 142.3 ሚሊዮን ተከታዮች በመያዝ ይከተላል።

በ2020 ኅዳር ላይ ዲ አሚሊዮ 100 ሚሊዮን ተከታዮችን በማስከተል የቲክቶክ መንደር አጋፋሪ ሆኖ ነበር።

ላሜ ወደ ቲክቶክ አምባ የተቀላቀለው በሚኖርባት ጣልያን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እግር ተወርች ተይዛ ማጣፍያው ባጠራት ወቅት ነበር።

በወቅቱ ዓለም ለኮሮናቫይረስ ወረርሽን እጇን ስትሰጥ ካቤ ከሥራው ተሰናበተ። እናም በሩን ዘግቶ ሞባይሉን አነሳ።

በተዘጋው የመኝታ ቤቱ ክፍል ውስጥ ቲክቶክ እጁን ዘርግቱ ተቀበለው።

ሰዎች ነገሮችን ሲያወሳስቡ ሲመለከት በቀላሉ እንዴት መከወን እንደሚቻል እጁን በመጠቆም ቃል ሳያወጣ በማሳየት ዝናን አጋበሰ።

ዛሬ የቲክቶክ መንደር ሰዎች ስሙን አንስተው የማይጠግቡት፣ የሠራው ሁሉ በአዕላፍ የሚታይለት፣ በዓለም አቀፉ ድግስ ላይ የሚጋበዝ ቱጃር ወጣት ነው።

የፎቶው ባለመብት, khaby.lame/tiktok

ይህ የቲክቶክ የዓለም ፈርጥ እንደ ሌሎች ቢጤዎቹ በቲክቶክ ላይ ሲደንስ አይታይም። እንደውም ለዳንስ አካሉ እሺ ብሎ የሚታዘዝለት አይመስልም።

አይዘፍንም፤ ቃለ ተውኔት ጽፎ በመተወን የሌሎችን ቀልብ ለመሳብም አይጥርም።

የሌሎችን ድምጽና ትወና ለማስመሰል ደፋ ቀና ሲል አይታይም።

ዝም ብሎ የሰው ልጅን ውስብስብ ተግባራት ይተቻል፤ እንደ ዘበት።

በመላው ዓለም ካሉ የቲክቶክ ከዋክብት ሁሉ ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው መካከል ቀዳሚው ነው። ከ142 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት።

በቲክቶክ ላይ የሚለጥፋቸው ቪዲዮዎች ቀላል እና አጭር ናቸው።

የእርሱ ትችቶች በንግግር የተደገፉ አይደሉም፤ በቀላል ድርጊት የታጀቡ አንጂ።

ውስብስብ በሆነ መንገድ ቀላል ነገርን የሚከውኑ ሰዎችን ቪዲዮ በማሳየት፣ እርሱ ያንኑ ተግባር ቀላልና ግልፅ በሆነ መልኩ ያሳየዋል።

ከዚያን እጁን በማወናጨፍ እና አንገቱን በመነቅነቅ ያበቃል።

ይህ በዓለም ላይ ዝነኛ የሆነው ቲክቶከር ማን ነው? ለምን ዝነኛ ሆነ?

ካቢ ላሜ በምዕራብ አፍሪካዋ አገር ሴነጋል ነው የተወለደው። አሁን ግን የሚኖረው ጣሊያን ነው።

የ22 ዓመቱ ወጣት ካቢ ቲክቶክን መጠቀም የጀመረው በመጋቢት ወር 2020 ነው፤ ኮሮናቫይረስ ዓለምን በተዋወቀበት ጊዜ እርሱ ቲክቶክን ተዋወቀ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ክፉኛ በደቆሰበት ወቅት እርሱም ከሚሠራበት ፋብሪካ ተሰናበተ። ካቢ በቀጥታ ወደ ቤተሰቦቹ አመራ።

ሌላ ሥራ ይፈልጋል ተብሎ ሲጠበቅ እርሱ ግን በየቀኑ ቲክቶክ ላይ ቪዲዮዎችን መለጠፍ ጀመረ።

ታዲያ ያኔ የቲክቶክ አካውንቱ ላይ ፈገግ የሚያሰኙ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ሲያጋራ እንዲህ በአንድ ጊዜ ስሜ በመላው ዓለም ይናኛል፤ ተግባሬ ብዙዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ብሎ ያሰበ አይመስልም።

ተንቀሳቃሽ ምስሎቹ የሚያተኩሩት እንዴት ሰዎች ያለምንም ተጨባጭ ምክንያት ነገሮችን እንደሚያወሳስቡ በማሳየት ነው።

እርሱ እንደሚለው በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች የእርሱን ቪዲዮዎች የወደዱት ሳቅን በሚያጭረው የፊት ገጽታው የተነሳ ስለሚያስቃቸው ነው።

ሌላው ደግሞ የእርሱን ሐሳብ ለመረዳት ቋንቋ ማወቅ ወይንም መናገር ፈጽሞ አለመጠየቁ እንደሆነ ያስረዳል።

ካቢ የእግር ኳስ አድናቂ ሲሆን በቪዲዮዎቹ ላይ የስፖርት ክለብ ቲሸርቶችን ለብሶ ይታያል።

የጁቬንተስ ደጋፊ የሆነው ካቢ፣ ኤዲ መርፊ እና ዊል ስሚዝም ከሚያደንቃቸው የሆሊውድ ከዋክብት መካከል ናቸው።