የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተወሰነ

የአፍሪካ ዋንጫ

በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ እንዲገፋ መወሰኑን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ አስታወቁ።

ውድድሩ በሚቀጥለው ዓመት ከሰኔ አስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ አይቮሪኮስት ውስጥ እንዲካሄድ መርሃ-ግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም፣ ወቅቱ በአገሪቱ ከባድ ዝናብ የሚጥልበት በመሆኑ ነው ለቀጣይ ዓመት የተሸጋገረው።

ደቡብ አፍሪካዊው የካፍ ፕሬዝዳንት የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር እየተካሄደባት ካለችው ሞሮኮ ዋና ከተማ ራባት ባስተላለፉት መልዕክት "በሚኖረው የአየር ሁኔታ ምክንያት ምንም ማድረግ አንደፍርም” ብለዋል።  

የዓለም ዋንጫ ከሌላው ጊዜ በተለየ በሚቀጥለው ዓመት ኅዳርና ታኅሣሥ ወር ላይ የሚካሄድ በመሆኑ፣ የአፍሪካ ዋንጫን ወደፊት ከማምጣት ይልቅ ወደ ቀጣይ ዓመት ማሸጋገሩ የግድ ሆኗል።

በዚህም ምክንያት የአፍሪካ ዋንጫ በዚህ ዓመት ካሜሩን ውስጥ እንደተካሄደው ሁሉ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ በጥርና የካቲት ይከናወናል።

የአውሮፓ ክለቦች በውድድር ላይ ሳሉ ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ተጫዋቾችን እንዲለቁ በመጠየቅ የሚነሳውን ውዝግብ ለማስቀረት ሲባል ካፍ በ2017 (እአአ) የአፍሪካ ዋንጫ በተለመደው ሁኔታ ሲካሄድባቸው ከነበሩት ጥርና የካቲት ወራት ወደ ሰኔ እና ሐምሌ ለማዘዋወር ወስኗል።

"በአውሮፓ ክለቦች ምክንያት ጥር ለውድድሩ አመቺ ወቅት አይደለም፣ ነገር ግን ለአሁን ያለን ብቸኛው አመራጭ እሱ ነው” ሲሉ የካፍ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።

በቀድሞው የካፍ ፕሬዝዳንት ኢሳ ሃያቱ የአመራር ዘመን የአህጉሪቱ መለያ የሆነውን የእግር ኳስ ውድድር ማካሄጃ ወቅት ወደ ሌላ ወቅት የማሸጋገሩ ጉዳይ ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል።

ሃያቱን የተኩት ማዳጋስካራዊው አህመድ አህመድ የአፍሪካ እግር ኳስን ለመምራት ወደ ሥልጣን በመጡ በአራት ወራት ውስጥ ከአባል አገራት ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር ለውጥ አድርገዋል።

የካፍ ዋና ፀሐፊ ቬሮን ሞሴንጎ ኦምባ እንዳሉት ምንም እንኳን በአህጉሪቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ያለው የአየር ሁኔታ ልዩነት ቢኖረውም ውድድሩን ቀድሞ ወደ ነበረበት ጥርና የካቲት የመመለስ ፍላጎት የለም።

ሰኔ እና ነሐሴ የዝናብ ወቅት መሆኑ እየታወቀ የውድድር ጊዜውን ወደ ሌላ ጊዜ የማሸጋገሩ ውሳኔ ለምን ዘገየ የሚለውን ጥያቄ ካፍ “ለአስተናጋጇ አገር አመቺነት” ሲባል መሆኑን ከመግለጽ ባለፈ ከባለሥልጣንት የተሰጠ ማብራሪያ የለም።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና ዋና ፀሐፊ የእግር ኳስ ውድድሩ የሚካሄድበት ወቅት በአንድ ዓመት መገፋቱን ያሳወቁት የአፍሪካ የሴቶች አግር ኳስ ዋንጫ ውድድር እየተካሄደ ከሚገኝበት ከሞሮኮ ነው።