ከ20 ዓመት መራራቅ በኋላ የተጣመሩትን ፍቅረኛሞች ዳግም ምን ለያቸው?

የአቶ ኦልቀባእና ባለቤታቸው የሠርግ ስነ ስርዓት

የፎቶው ባለመብት, Olqeba Family

በውጣ ውረድ የታጀበው የአቶ ኦልቀባ እና የባለቤታቸው ታሪክ የተጀመረው ሆሮ ጉዶሩ ወለጋ፣ ሻምቡ ነው።

ስሜ ይቅር ያሉት ባለቤታቸው የትዳር ሕይወታቸውን እና ያሳለፉትን እንዲህ ነግረውናል።

ከኦልቀባ ቡርቃ ጋር በሻምቡ ከተማ አንድ አካባቢ ነው አድገን በፍቅር የወደቅነው። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም አንድ ክፍል ነው የተማርነው።

አብረን እናጠናለን፤ አብረን ወጥተን እንገባ ነበር።

በዚህ ጊዜ ነው ታድያ ፍቅር የጀመርነው።

ነገር ግን ልጆች ስለነበርን፣ ፍቅርን በወጉ አልያዝነውም። ከዚያ በኋላ እኔ ትዳር ከመሰረተች እህቴ ጋር ልቆይ ከወለጋ ወደ ጎንደር አመራሁ።

እርሱም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ፣ ወደ ነቀምቴ በመሄዱ በዚያው ተለያየን።

ከዚያ ወዲህ ተገናኝተን አናውቅም። በወቅቱ መገናኘት ቀላል አልነበረም። ስልክ ብዙ አልነበረም፤ ደብዳቤ ብንላላክም አይደርስም። ተጠፋፍተን ለዓመታት ቆየን።

እርሱም ነቀምቴ በነበረበት ወቅት፣ በዘመኑ ፖለቲካ ምክንያት ጥሩ ጊዜ አላሳለፈም። ለዘጠኝ ዓመት ታስሮ ነበር።

እኔ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጨርሼ፣ በነርሲንግ ተመርቄ፣ ሥራ ይዤ፣ የራሴን ሕይወት እየመራሁ ነበር።

ኦልቀባም ከእስር እንደተፈታ፣ ያቋረጠውን ትምህርት በአዳማ አጠናቅቆ፣ ሥራ ይዞ እርሱም የራሱን ሕይወት ይመራ ነበር።

መልሶ ያገናኘን፣ ዘመድ ነው።

ለእኔ ዘመድ የሆነች፣ ከእርሱ ጋር ደግሞ የአንድ አካባቢ የሆነች ልጅ አዲስ አበባ ትኖር ነበር።

እርሱ በአጋጣሚ ይህች ሴት ቤት ይሄዳል።

የፎቶ አልበም እያየ የእኔን ፎቶ አይቶ 'የት ታውቂያታለሽ?' ሲል ይጠይቃታል። ይህች ዘመዴ ደግሞ 'ዘመዴ ናት' ትለዋለች።

ከዚያ የት እንዳለሁ ሲጠይቅ፣ ነርስ መሆኔን እና አዲስ አበባ ራስ ደስታ ሆስፒታል እንደምሰራ ትነግረዋለች።

እርሱም ዛሬ ነገ ሳይል የምሰራበት ሆስፒታል ድረስ መጣ።

እኔ የነበረኝ መረጃ፣ በደርግ ዘመን እንደተገደለ ነበር።

አንድም ጊዜ በሕይወት አለ ብዬ አስቤ አላውቅም። ሆስፒታል አስጠርቶኝ ሳየው፣ አላወቅኩትም ነበር።

በኋላ ሳወቀው ግን እጅጉን ተገረምኩ። በፍርሃት ተውጬ ነበር።

ከሞት ተነስቶ የመጣ ነው መሰለኝ።

ፍቅር እንደገና

ከዚያ እንደ አዲስ ተዋወቅን፤ እንደ አዲስ መገናኘት ጀመርን። በልጅነት የዘነጋነውን እና የተዳፈነውን ፍቅራችንን ለሁለተኛ ጊዜ ማደስ ጀመርን።

ስናወራ እና ስንወያይ በሁለታችንም ልብ፣ ያልሞተ የተዳፈነ ፍቅር ነበር።

እርሱም በእኔ ውስጥ እኔም በእርሱ ውስጥ ነበርን።

ምክንያቱም፣ ያንን ሁሉ ዓመት እኔም ሳላገባ፣ እርሱም ሳያገባ ነው የቆየው።

እንደተማማለ ሰው ስንጠባበቅ ነበርን ማለት ነው።

የሕይወት ውጣ ውረድ ቢለያየንም፣ እኛ ግን መልሰን ፍቅራችንን ልንገነባ ተስማማን።

በዚሁ ወደ ትዳር ገባን፤ ፈጣሪ ምስጋና ይግባው ድል ባለ ሠርግ አዲስ የትዳር ሕይወት ጀመርን።

ኦልቀባ በጣም ጠንካራ እና ሕዝቡን ወዳድ ነው። ከዚህም የተነሳ በአዲስ አበባ የነበረውን የተሻለ ኑሮ ትቶ፣ በገጠር ሕዝብ ያገለግል ነበር።

በሥራው ቀልድ አያውቅም፣ ፊንጫ፣ ባኮ እና አምቦ በሚሰራበትም ወቅት የሕዝብ ፍቅር አፍርቷል።

የፎቶው ባለመብት, Olqeba

‘ችግሩ አእምሮው ላይ እንዳለ በፍፁም አላሰብንም’

ኦልቀባ አምቦ በሚሰራበት ወቅት እንደ ሁልጊዜው ከአዲስ አበባ እየተመላለስኩ እጠይቀው ነበር።

ኦልቀባ በዚያ ጊዜ  ታሞ ነበር።

ምግብ ሆዱ ውስጥ አይረጋለትም፤ ያስመልሰዋል። ያቀረብኩት ማዕድ ሳይነሳ እርሱ የበላው ይወጣል። እዚያው አምቦ ምርመራ ተደርጎለት ጨጓራው፣ ኩላሊቱ፣ ጉበቱ ታይቶ ምንም ችግር እንደሌለበት ተነገረው።

በኋላ እርሱ ሥራ ትቶ መሄድ ባይፈልግም በስንት ልመና ወደ አዲስ አበባ መጥቶ እንዲታከም አደረግሁ።

አሁንም ጨጓራ፣ ኩላሊት፣ ጉበት እና ጣፍያው ውስጥ ምንም ዓይነት ሕመም አልተገኘም። ግን ደግሞ ምግብ አይረጋለትም።

ይህንን ሕክምና እያደረግን ደግሞ አንደኛው ዐይኔ አያይም አለኝ።

አንዱን ዓይኑን ሸፍኖ በታመመው ዐይኑ እንዲያይ ስሞክር እውነትም አንዱ ዐይኑ አያይም።

ሆስፒታል ሄዶ ሲታይ ግላኮማ አለብህ፤ አንደኛው ዐይንህ ታውሯል፤ ሌላኛውም መጎዳት ጀምሯል ተባለ።

ለእርሱ መድኃኒት ወስዶ ደህና መሆን ጀመረ።

ከዚያ ደግሞ ሌላ ችግር መጣ። ሲራመድ ሚዛኑን መጠበቅ አቃተው። እንደ ሰከረ ሰው ይንገዳገድ ነበር።

ከጓደኞቼ ጋር ሐኪም ብናማክርም፣ ምክንያቱን ማወቅ አልቻልንም።

መጨረሻ ላይ የነርቭ ሐኪም (ኒውሮሎጂስት) አየውና ለጭንቅላት ኤምአርአይ ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ ሲመጣ፣ በጀርባው የጭንቅላቱ ክፍል፣ ትልቅ የካንሰር እባጭ እንዳለ ታወቀ።

ምግብ በሆዱ እንዳይቆይም፣ ሚዛኑን እንዳይጠብቅም ያደረገው እርሱ ነው ማለት ነው።

አዲስ አበባ ሲያዩት የነበሩ ሐኪሞች፣ የካንሰር እባጩ የመተንፈሻ፣ የእንቅስቃሴ ሚዛን እና የልብ ምት የሚቆጣጠሩ ነርቮች በሚገኙበት ስለበቀለ ሙሉ በሙሉ ማውጣት እንደማይቻል ነገር ግን መቀነስ እንደሚቻል ገለፁ።

እርሱንም ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ከአገር ውጪ ሕክምናውን ማግኘት ከቻልን ብቻ መሆኑን ነገሩን።

ወዲያውኑ ሕንድ አገር ከሚገኝ ሐኪም ጋር ተነጋግረን፣ እርሱም ሙሉ በሙሉ ማውጣት እንደማይቻል፣ 90 በመቶ ያህሉን አውጥቶ 10 በመቶው በራዲዮቴራፒ ሕክምና እንደሚስተካከል ነገረን።

ነገር ግን ለዚህ ሕክምና የሚሆን ገንዘብ ከየት ይምጣ?

ዶ/ር ሒሩት የምትባል ጓደኛዬ፣ ወንድሜ ይዳን እንጂ ገንዘብ ይተካል ብላ፣ ከባንክ አካውንቷ 400 ሺህ ብር አውጥታ፣ ጥግ የሌለው መልካምነት አሳየችኝ።

በዚህ መልኩ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ፣ ለሕክምና ወደ ሕንድ ይዤው ሄድኩ።

ሕንድ አገር ሰባት ሰዓት የፈጀ ቀዶ ሕክምና ተደረገለት። ጭንቅላት ውስጥ የነበረው እባጭም ወጣ።

ካንሰሩ ኤፔንዲሞማ [Ependymoma] የሚባል ሲሆን፣ ይህ የካንሰር ዓይነት ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል አይሰራጭም። ነገር ግን ወሳኝ የሆኑ፣ የጭንቅላት ነርቮች ይጎዳል ሲል ሐኪሙ ነገረን።

ሕክምናው በተደረገለት ጊዜ፣ ካንሰሩ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑን አስረዳን።

ይህ የካንሰር ዓይነት 'ተመልሶ ይበቅላል ወይ?' ብዬ ስጠይቅ፣ ዕድሉ በጣም አናሳ ቢሆንም እንደሚገጥም ተነገረኝ።

‘መልካም ሰው ለምን አይበረክትም’

ኦልቀባ ከሕንድ ሳንወጣ የአእምሮ ጭንቀት ምልክት ማሳየት ጀመረ።

በዚህም እኔም ከእርሱ ጋር ተቸገርኩ። ወደ አገር ቤት ልግባ ይህንን ሕክምና አልፈልግም ሲል ነበር።

ወደ አዲስ አበባ ከመጣን በኋላ የአእምሮ ሕክምና ዶክተር አይታው መድኃኒት ወስዶ ይሻለው ጀመር።

ወደ አገር ቤት ከተመለሰ በኋላም ሕንድ ከሚገኘው ሐኪሙ ጋር እየተመካከረ፣ የአእምሮ ሕክምናውንም እየወሰደ ለሰባት ዓመታት የሚዛን መጠበቅ ችግር ነበረው እንጂ በሰላም ሥራውን እየሰራ ቀጠለ።

በሰባተኛው ዓመት፣ እንደሌላው ጊዜ አእምሮው የሚገኝበትን ሁኔታ፣ በኤምአርአይ ታይቶ ለሐኪሙ ሲልክ ካንሰሩ ተመልሶ መብቀል እንደጀመረ ሐኪሙ ጻፈለት።

በዚህ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ሚዛኑን መጠበቅ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሶ ነበር።

መንገድ ላይ መውደቅ፣ የት እንዳለ ማወቅ ተሳነው፤ መዘንጋት ጀመረ። የሚታይበት ለውጥ በጣም ፈጣን ነበር።

በዚህ ምክንያት ተመልሼ ወደ ሕንድ ይዤው ሔድኩ።

በዚህኛው ዙር በራሱ መንቀሳቀስ ስላልቻለ፣ በተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቸር) ነበር የሚንቀሳቀሰው።

ሙሉ በሙሉ ይድንልኛል የሚል ተስፋ ባይኖረኝም፣ ልክ እንደ መጀመሪያው፣ ጥቂት ተጨማሪ ዓመታት ከኖረ ብዬ ነው ይዤው የሔድኩት።

የዚህኛው ዙር ሕክምና እንደ ቀዳሚው ስላልነበረ ቀዶ ሕክናው ሲደረግለት ነርቮቹ ሊነኩ እንደሚችሉ፣ ሕይወቱ ሊያልፍ እንደሚችልም ነገሩኝ።

ስለዚህም መፍትሔው ራዲዮቴራፒ ነው ተባለ።

የራዲዮቴራፒ ሕክምና ባለሙያው ደግሞ፣ እባጩ ድፍን ስለሆነ ትንሽ ካልተነሳ ጨረሩ ሊያልፍ አይችልም እናም ለውጥ አይኖረውም አለ።

በዚህ ምክንያት ቀዶ ጥገና ተደረገለት። ነገር ግን ከዚህ ሕክምና በኋላ የአተነፋፈስ ሥርዓቱን ጨምሮ ውስብስብ የጤና እክሎች ተከሰቱ።

በሕይወት እንደማይተርፍ ሳውቅ፣ ፈጣሪ በሰላም እንዲያሳርፈው መጸለይ ጀመርኩ።

በመጨረሻም እዚያው ሕንድ ሕይወቱ አልፋ አስከሬኑን ወደ አገር ቤት ይዤ መጥቼ አፈር አለበስኩት።

የፎቶው ባለመብት, Olqeba

የምስሉ መግለጫ,

አቶ ወልቀባ ከጓደኞቻቸው ጋር

በአሜሪካ ከሚገኘው የጆን ሆፒክንስ ዩኒቨርስቲ የጤና ማዕከል የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው፣ የጭንቅላት ካንሰር በጭንቅላት የትኛውም ክፍል ላይ ሊበቅል ይችላል።

ይህ ካንሰር ከሌሎች የሚለየው፣ ብዙ ጊዜ በሌሎች የሰውነት አካላት ውስጥ የማይሰራጭ ሆኖ ወሳኝ የሆኑ ነርቮችን በማጥቃት፣ ለሞት የሚያጋልጥ መሆኑ ነው።

በአሜሪካ ከ100 ሺህ አዋቂ ሰዎች መካከል በ30 በሚሆኑት ላይ ይህ የካንሰር ዓይነት ይገጥማል።

ጥቂት ስለ ጭንቅላት ካንሰር

እንደ ሌሎቹ የካንሰር አይነቶች ሁሉ በጭንቅላት ውስጥ የሚከሰተው የካንሰር አይነት መነሻ ምክንያቱ በትክክል ይህ ነው ተብሎ አይታወቅም። መንስኤው አይታወቅ እንጂ ይህንን አደገኛ ችግር የሚያስከትሉት የካንሰር ሴሎች አድገውና ተባዝተው በሰው በጭንቅላት ውስጥ ያጋጥማሉ።  

አንዳንዶቹ የካንሰር አይነቶች ጭንቅላት ውስጥ ተቀስቅሰው እዚያው የሚቆዩ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ከሌላ የሰውነት ክፍል ተነስተው ወደ አንጎል ሊሰራጩ ይችላሉ።  

በጭንቅላት ውስጥ ካንሰር ሲኖር ያልተለመደ ወይንም ከሌላው ጊዜ የባሰ የራስ ምታት፣ የዕይታ ብዥ ማለት፣ ሚዛንን ለመጠበቅ መቸገር፣ ግራ መጋባት እና እራስ መሳት ምልክቶች ናቸው።  

ይህንን ካንሰር ለማከም ቀዶ ሕክምና፣ የጨረር ሕክምና እና ኬሞቴራፒ በባለሙያዎች አገልግሎት ላይ ይውላሉ።