የቀድሞው የቴሌቭዥን አቅራቢና አዲሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር

ያይር ላፒድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ያይር ላፒድ

ያይር ላፒድ ለወራት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የቆዩት ናፍታሊ ቤኔትን በመተካት በመጪው ዓመት ኅዳት አስከሚደረገው ምርጫ ድረስ የእስራኤል ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ።

ያይር ከናፍታሊ ቤኔት ጋር የመሰረቱት ጥምር መንግሥት ባለፈው ሳምንት መፈረሱን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን የተረከቡት።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ ማን ናቸው?

የያይር ላፒድ የፖለቲካ ጉዞ አጭር የሚባል ነው። 10 ዓመት ብቻ። ቀድሞ ግን የቴሌቪዥን የፖለቲካ ውይይት አዘጋጅ ነበሩ። ህልማቸው ግን ትልቅ ነው። ዓላማቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ነበረ።

አሁን በተጠባባቂነት ቦታውን ተረክበዋል። በተገቢው ቦታ የተቀመጡ ተገቢው ሰው መሆናቸውን ማስመስከሪያ ጊዜያቸው ላይ ናቸው።

ይህ ሁሉ የሚሆነው አገራቸው አራት ዓመት እንኳን ሳይሆን ለአምስተኛ ጊዜ ወደ ምርጫ ለመግባት በዝግጅት ላይ ባለችበት ወቅት ነው።

ላፒድ የቴሌቭዥን አቅራቢ ብቻ ሳይሆኑ ቡጢኛም ነበሩ። አማተር ቦክሰኛ ሆነው ተጫውተዋል።

የቀድሞው አማተር ቦክሰኛ ከወግ አጥባቂው ቤንጃሚን ኔታንያሁ (በነገራችን ላይ ኔታንያሁ ለረዥም ዓመታት እስራኤልን የመሩ ሰው ናቸው) ብርቱ ፉክክር ይገጥማቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።  

እአአ በ2021 ላፒድ የማይመስል በተባለለት ጥምረት ኔታንያሁን ለዓመታት ከተቆናጠጡት መንበር አስለቅቀዋቸዋል።

የእስራኤል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክኔሴት ይባላል። ምክር ቤቱን ለመበተን የተካሄደውን ድምጽ ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ላፒድ ሥልጣኑን ተረከቡ። ይህ ርክክብ እውን የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት የሃይማኖት ብሔርተኛው ናፍታሊ ቤኔት ጋር በነበራቸው የሥልጣን መጋራት ስምምነት መሠረት ነው።

በመጪው ዓመት ጥቅምት ወይም በኅዳር ላይ ምርጫ ይካሄዳል። ቀጥሎ አዲስ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ እና ምናልባትም ምንም አይነት ጥምረት መመስረት ካልተቻለ ሌላ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ ላፒድ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ መንበሩን ይዘው ይቆያሉ።

"ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ ምርጫ ብንሄድ እንኳ የሚያጋጥሙን ፈተናዎች ቆመው አይጠብቁንም" ሲሉ ላፒድ ተናግረዋል። ይህንን ያሉት ፍትጊያ በዝቶበት ነበር የተባለው ጥምር መንግሥታቸው ማብቃቱን ለመግለፅ ከቤኔት ጎንቆሙው ነው። ጥምረቱ መፍረሱ በምክር ቤት ውስጥ የነበረውን አነስተኛ የበላይነት እንዲያጣ ምክንያት ሆኗል።

በመግለጫቸው ወቅት የምርጫ ዘመቻ ላይ ያሉ ይመስል ነበር። እስራኤልን እየገጠማት ነው ያሏቸውን አንገብጋቢ ጉዳዮች ዘርዝረዋል። ከከፍተኛ የኑሮ ውድነት ጀምረው በጋዛ ሰርጥ፣ በሊባኖስና በኢራን ውስጥ ያሉ የደኅንነት ስጋቶችን ዘርዝረዋል።

ኔታንያሁ በሙስና ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት እየተመላለሱ ነው። የቀረበባቸው ክስንም ይክዳሉ።

“እስራኤልን ዲሞክራሲያዊነቷን ለማሳጣት የሚዝቱ ኃይሎችን” ለመጋፈጥ ቃል ገብተዋል። ይህም ኔታንያሁ ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል።

ያይር ላፒድ በጎርጎሮሳዊያኑ 1963 ቴል አቪቭ ውስጥ ነው የተወለዱት። እናታቸው ፀሐፊ ናቸው። አባታቸው ከዘር ተኮር ትቃት የተረፉ ናቸው። ላፒድ የአባቱ ልጅ የሚባሉ ናቸው። አባትም እንደልጃቸው ጋዜጠኛ ነበሩና ወደ ፖለቲካው ዓለም መጡ። አባት መንግሥት እና ሃይማኖት በተለያየ መንገድ መጓዝ አለባቸው (ሴኩላሪዝም) የሚለው አመለካከት ደጋፊ በመሆናቸው ይታወቃሉ።  

ላፒድ በአገራቸው ሠራዊት ውስጥ አገልግለዋል። በወቅቱ ለአንድ ወታደራዊ መጽሔት ዘጋቢም ሆነው ሰርተዋል። ዩንቨርስቲ አልዘለቁም። የጋዜጣ አምዶችን፣ መጽሐፎችን እና የተለያዩ ጽሑፎችን ጽፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

ወደ ቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት ከመግባታቸው በፊት ጥሩ ቁመናቸውን ተጠቅመው ሙዚቃዎች ላይ ከመሳተፍ ባለፈ በፊልም ላይም ተውነዋል።

የቴሌቭዥን ዜና አንባቢ በነበሩበት ወቅት ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉ ባለሥልጣናትን በማፋጠጥ ይታወቃሉ። ለዓመታት ግን አንድ እንደ ጥላ የሚከተላቸው ጉዳይ አለ። በወቅቱ ቤንጃሚን ኔታንያሁ የአገሪቱ የግምጃ ቤት የበላይ ነበሩ። ላፒድ እና ኔታንያሁ ለቃለ መጠይቅ ተገናኙ።

በዚህ ወቅት ላፒድ “ስለ ኢኮኖሚክስ ምንም የማውቀው ነገር የለም” አሉ። ይኼው አሁን ድረስ ብዙዎች ይህንን ንግግር በየጊዜው ይመዙባቸዋል “ስለ ኢኮኖሚክስምንም የማውቀው ነገር የለም” እያሉ።  

የላፒድ የፖለቲካ ጉዞ የተጀመረው በ2011 ከነበሩት የማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ተቃውሞዎች ጀርባ ተንጠልትሎ ነው። የሽ አቲድ (ወደፊት ተስፋ አለ እንደ ማለት ነው) ፓርቲን አቋቋሙ። ለመካከለኛው መደብ የዕለት ጉርስ ጉዳዮችን ለመፍታት ቃል ገብተው ነው የጀመሩት።

በ 2013 ምርጫ በከፍተኛ ቤቶች ዋጋ፣ በትምህርት ማሻሻያዎች እና በብዙ ዓለማዊ እስራኤላውያን ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን አክራሪ የአይሁድ ማኅበረሰብ አባላትን ከግዴታ ወታደራዊ አገልግሎት ነፃ በማድረግ ላይ በማተኮር ጠንክራ ተፎካካሪ መሆናቸውን አሳይተዋል።

የሽ አቲድ በመጨረሻም በ​​ኔታንያሁው ሊኩድ ፓርቲ የሚመራውን ጥምረት ተቀላቀለ። ላፒድም እስከ 2014 መገባደጃ ድረስ የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው አገለገሉ። በሁለቱ ግንባር ቀደም የፖለቲካ ሰዎች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ከኃላፊነታቸው እንዲሰናበቱ ተደረገ።

በተከታታይ ምርጫዎች ላፒድ የኔታንያሁ ተቃዋሚ ሆነው በዚህም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደጋጋሚ ተፋለሙ። ፖሊስ እአአ በ2018 ኔታንያሁ ላይ የሙስና ክስ መሰረተባቸው። ላፒድ ደግሞ በአንዱ ክስ ላይ እንደ ቁልፍ ምስክር ሆነው ተቆጠሩ።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሚቀጥለው ወር ወደ እስራኤል ያቀናሉ። ላፒድ ፕሬዝዳንቱን የማግኘት ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር በመስከረም ወር በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይም ንግግር ያደርጋሉ።

እስራኤል ከፍልስጤማውያን ጋር ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ግጭት ውስጥ ትገኛለች። በዚህ ረገድ ከቅርብ ጊዜ በፊት ከነበሩት መሪዎች ለዘብተኛ አመለካከት ይኖራቸዋል ተብሎይጠበቃል።

ላፒድ የሁለት አገር መፍትሄ ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል። በአንዳንድ ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ግን አቋማቸው ጠንካራ ነው።

ቀደም ሲል በቃለ ምልልስ ላይ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ሆና መቀጠል እንዳለባት ግልፅ አድርገዋል። የከተማዋን ምሥራቃዊ ክፍል ፍልስጤማውያን የወደፊቷ አገር ርዕሰ መዲናችን ነች ብለው ያቀረቡት የይገባኛል ጥያቄ ሙሉ በሙሉ “ምንም ታሪካዊ መሰረት የሌለው ውሸት ነው” ሲሉ ይገልጻሉ።

ቤንጃሚን ኔታንያሁ ለስድስተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን እያለሙ ነው። ተቀናቃኛቸውን በደኅንነት ላይ በተለይም ከኢራን እና ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ደካማ አድርገው ለመሳል ይፈልጋሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የያይር ላፒድ ፈተና የሚጀምረው እስራኤልን ከጠላቶቿ መከላከል እንደሚችሉ በማረጋገጥ ነው። ቀጥሎም ውስጣዊ አንድነትን ማስበቅ መቻላቸውን ማሳየት አለባቸው። አንዳንዶች የቴል አቪቭ ጥቂት ልሂቃንን ነው የሚወክለው የሚሉ ተቃዋሚዎችንም ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።

በአክራሪ ጥንታዊ ፓርቲዎች ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻ ተፈጥሮባቸዋል። ላፒድ ዓላማቸውን ለማሳካት ከተለያዩ አጋሮች ጋር መሥራት እንደሚችሉ አሳይተዋል። ኔታንያሁን ለመተካት ከቀድሞው ወታደራዊ አዛዥ እና የአሁኑ የመከላከያ ሚንስትር ቤኒ ጋንትዝ ጋር መሥራት ችለዋል።

ለመጀመሪያጊዜ የአረብ እስላማዊ ፓርቲን ያካተተው ጥምር መንግሥት ባለው የፖለቲካ ልዩነት ዘመን ባሳየው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ አድናቆትአግኝቷል። ስኬቶቹ መካለከልም በሁለት የኮሮናቫይረስ ሞገዶች ወቅት አገሪቱን ማስተዳደር፣ ከሦስት ዓመታት በኋላ የእስራኤልን የመጀመሪያ በጀት ማጽደቅ እና ከዋሽንግተን እና ከአረብ አጋሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ጥቂቶቹ ናቸው።

ቀድሞ በተደረገ ቅድመ የሕዝብ አስተያየት ሊኩድ በመጪው ምርጫ ከፍተኛ መቀመጫ እንደሚያገኝ ይገመታል። ሆኖም ከአጋሮቹ ጋር ተደምሮም በፓርላማው ሚኖረው መቀመጫ አገር ለማስተዳደር የሚያስፈልገው አብላጫ ቁጥር እንደሌለው ያሳያል።

በሚቀጥሉት ወራት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያ ቤት የሚቆዩት ያይር ላፒድ እስራኤላዊያን ድምጽ ከሰጡ በኋላም የሥልጣን ዘመናቸውን ለማስቀጠል ይሠራሉ።