ዐጤ ምንሊክ ፎቶ የተነሱባት ካሜራ 'በሕይወት ተገኘች'

ይህ ጉዞ በዋናነት የዐጤ ምንሊክን የልብ ወዳጅና ምሥጢረኛ፣ ልዩ አማካሪና የቴክኒክ ሰው የነበረውን የስዊዛዊውን አልፍሬድ ኢልግ የልጅ ልጆች ዱካ ለማግኘት የተደረገ ሊባል ይችላል። እግረ መንገድም የንጉሥ ምንሊክን 106ኛ ሙት ዓመት ለመዘከር በቢቢሲ የተሰናዳ ልዩ ጥንቅር ነው።


አልፍሬድ ኢልግ የሚባል የስዊዝ ሰው አጤ ምንሊክን ለማግኘት ከዙሪክ ተነስቶ አንኮበር በገባ ልክ በመቶ አርባ ዓመቱ፣ እኔ የአልፍሬድን የልጅ ልጆች ለማግኘት ከናይሮቢ ዙሪክ ገባሁ።

አልፍሬድ ያኔ ከዙሪክ- አንኮበር ለመግባት ድፍን 8 ወራት ወስዶበት ነበር። እኔ ከናይሮቢ ዙሪክ ለመግባት ድፍን 8 ሰዓት እንኳ አልወሰደብኝ።  

አንዳንድ ነገሮች ግን በዘመን ርዝማኔ እምብዛምም አልተለወጡም፡፤ ኢልግና ምንሊክ ከ102 ዓመት በፊት ያነጠፉት ባቡር ከለገሀር ተነስቶ ወደ ‘ባሕረ ነጋሽ’ አልለጠቀም። በጣርማ በር ሰንጥቆ ደብረ ብርሃን አልዘለቀም።

ከ102 ዓመት በኋላም ኢልግና ምንሊክ በተገናኙባት በአንኮበር የሚያልፈው ሎንቺን እንጂ ባቡር አይደለም።

ዐጤ ምንሊክ አንድ አፍታ ካረፉበት ከታዕካ ነገሥት ባኣታ ለማርያም ቀና ብለው ባቡሩን ቢያዩት፤ አልፍሬድ ኢልግም አንድ አፍታ ከዙሪክ ፍሪድሆፍ ኢንተንቡል መካነ መቃብር ቀና ብሎ አንኮበርን ቢመለከት…ሁለቱም ሸለብታ ወስዶን እንጂ…መቼ ሞትን ይሉ ነበር?

ቀላሉ ባቡር፣ ያሬድ ኃይለሥላሴ እና አልፍሬድ ኢልግ

ቀላል ባቡር ስል ያሬድ ኃይለሥላሴ ታወሰኝ። ልበ ቀናው ያሬድ ኃይለሥላሴ። ዙሪክ ያለው ያሬድ ኃይለሥላሴ። በእናቱ ስዊዛዊ በአባቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊው፤ ያሬድ። ተወልዶ ያደገው እዚያው ነው። አፉን የፈታውም በጀርመንኛ ነው።

ታዲያ ይሄ ያሬድ የሚባለው ልጅ፣ "ከቀላል ባቡሩንና ከአልፍሬድ ኢልግ ጋር ምን አገናኘው?" ትሉ ይሆናል፤ ጥሩ ጥያቄ ነው። ሦስቱን የሚያገኛኘው የታሪክ መስመር የሚከተለው ነው።

ያሬድ ከዕለታት አንድ ቀን በአገሩ ዙሪክ ቀላል ባቡር በተሳፈረበት አጋጣሚ እንደ ሁልጊዜው መጽሐፍ ያነብ ነበር። አጠገቡ አንዲት በዕድሜ ጠና ያሉ ሴትዮ ገልመጥ እያሉ ይመለከቱታል። እርሱም በግማሽ ልብ ንባቡን ቀጥሏል።

"ይቅርታ የኢትዮጵያ ደም ያለብህ ይመስለኛል፤ ልክ ነኝ?፡" አሉት። በጀርመን አፍ ነው ታዲያ።

"ልክ ነዎት እማማ" አላቸው።

"እኔ ስላንተ ሕዝቦች ብዙ አውቃለሁ…" አሉት።

"እንዴት ሊያውቁ ቻሉ እማማ?"

"የኔ ቅድመ አያት ያንተን ንጉሥ ያማክር ነበር…።"

"ማን ይባላል ቅድመ አያትዎ? የሚሉኝ ንጉሥስ ማን ይሆን?”

"ንጉሥህ ካይዘር ምንሊክ ነው፤ የአያቴ ስም ደግሞ አልፍሬድ ኢልግ ይባላል" አሉት።

"ደነገጥኩ!" ይላል ያሬድ ያን ቀን የተፈጠረበትን ውስጠ-ስሜት ሲያስታውስ።

 "ያ ቀን ኢትዮጵያዊነቴንና ስዊዛዊነቴን የሚያስታርቅልኝ ክር ያገኘሁ ያህል ተሰማኝ"

@ዘሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

@ዘሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

ይቺው ናት ቀጭኗ ታሪክ። ይቺው ናት ኢትዮ-ስዊዛዊውን ያሬድን፣ ከስዊዛዊው ቢትወደድ አልፍሬድ ኢልግ ጋር ያስተሳሰረች የታሪክ ሰበዝ። ይልቅ ባቡር ውስጥ የመገናኘታቸው ምጸት ነው የሚደንቀው።

ምክንያቱም ለኢትዮጵያ ከባድ ባቡር ያዘረጋላትን መሐንዲስ አልፍሬድ ኢልግ ነው። ለዚያውም ዐጤ ምንሊክን ነዝንዞ፣ ነዝንዞ።

የከባድ ባቡራችንን ባለውለታ የልጅ ልጅ በዙሪክ ቀላል ባቡር ውስጥ በአጋጣሚ ያገኘው ያሬድ ታዲያ ወደ በኋላ ከቢቢሲ ዘጋቢ ጋር አደን ይወጣል፤ የአልፍሬድ ኢልግን የልጅ ልጆች በድጋሚ ለማግኘት…።

ከዚያች የባቡር አጋጣሚ በኋላ የት እንዳሉ እንኳ አያውቅም።

ፍለጋ ከመውጣታችን በፊት ግን መቅደም ያለበት ታሪክ ሳይኖር አይቀርም።

ለመሆኑ ማነው ይሄ አልፍሬድ ኢልግ …?

የቢትወደድ አልፍሬድ ኢልግ 'የአጭር አጭር' የሕይወት ታሪክ

በአራዳው ጊዮርጊስ፣ በፒያሳ እምብርት፣ ከደረታቸው ደደር፣ ከትከሻቸው ወደር፣ ከአንገታቸው ቀና፣ ከዕድሜያቸው ጠና፣ ከልጓሙ ዘና ብለው፣ 'አባ ዳኘው' ፈረሳቸውን ወደ ሰሜን አቅጣጫ የሶምሶማ የሚጋልቡት ዐጤ ምንሊክ 'እንዲያው ከርስዎ ሐውልት ሥር አንዲት ድንክ ሐውልት ልናቆም አሰብን፤ ያቺ ሐውልት የማን ትሁን? ቢባሉ ያለጥርጥር "የአልፍሬድ ኢልግ ነዋ" እንደሚሉ እገምታለሁ።

በዚህች አንቀጽ ቅሬታ የሚገባው አንባቢ መኖሩ እሙን ነው። "ስንት ጀብዱ የፈጸመ ያገር አርበኛ ሳለ፣ ከእምዬ ምንሊክ ጎን ፈረንጅ?!" የሚል የታሪክ አርበኛ አይጠፋም።

ለካንስ ፍርድ አዋቂው የምንሊክ ቀኝ እጅ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (ሀብቴ አባ መላ) ወደው አይደለም 'ነገርን ከሥሩ፣ ውሃን ከጥሩ' ይሉ የነበረ።

እስቲ ከመፍረዳችን በፊት የኢልግን ሕይወት እንመርምር…


ኢልግ የዐጤ ምንሊክ ሽርክ ነበር። ለሩብ ክፍለ ዘመን ያልተለያቸው ጥብቅ ምሥጢረኛ።

ምን ያህል ይወዱት እንደነበር ለመመስከር ሁለት ነጥቦች ብቻ ይመዘዙ ቢባል አንዱ የሚሆነው ንጉሡ "ቢትወደድ" የሚለውን እጅግ የላቀ ማዕረግ ብድግ አድርገው ያላንዳች ወለምዘለምታ ለአንድ ፈረንጅ መስጠታቸው ነው።

ያ ፈረንጅ ስዊዛዊው ኢልግ ነው። በአበሻ ምድር ያለርሱ "ቢትወደድ" የተሰኘ ፈረንጅም የለ!

ዐጤ ምንሊክ ኢልግን ታንጀታቸው ይወዱት ነበር። ባይወዱትማ ‘ስዩመ እግዚያብሔር’ ያሰኛቸውን 'ምድር አንቀጥቅጥ' ስማቸውን ብድግ አድርገው ለወንድ ልጁ ባልሰጡ።

ከኢልግ አራት ልጆች ሁለተኛው ወንድ ልጁ ስሙ ምንሊክ ይባላል። የተወለደውም በግንቦት 14፣1890 ባዲ’ሳባ ነው።

 "ልጅህን በንግሥናው ስማችን ልንጠራው ፈቅደናል!" አሉ ዐጤ ምንሊክ። የክርስትና አባትም ሆኑት። መስቀልም ከአንገቱ አኖሩለት።

ፈረንጁ ምንሊክ በእሪ በከንቱ ተወልዶ፣ በዙሪክ የሙቀት ማሽን አሻሻጭ ነጋዴ ኾኖ፣ ኖሮ ኖሮ ከዕለታት አንድ ቀን ሞተ። ዕድሜውን ሙሉ በምንሊክ ስም ተጠራ፤ መቃብሩን ባውሮጳ ሳይሆን አይቀርም።

በዙሪክ ቆይታችን ከአባቱ አልፍሬድ ኢልግ መቃብር ጎን ግን ፈልገን አጥተነዋል። የት ይሆን ያረፈው? እንዴት ዓይነት ሕይወትስ ኖሮ ሞተ?

ከአፍታ ቆይታ በኋላ ከኢትዮ-ስዊዛዊው ያሬድ ጋር መካነ መቃብሩን ፍለጋ እንወጣለን። ቤተሰብ ካለው እናፋልጋለን። ከዚያ በፊት ግን የአልፍሬድ ኢልግን ልጅነት መፈተሽ ሳይኖርብን አይቀርም።

ከዙሪክ አንኮበር ስንት የብርሃን ዘመን ነው?

በምሥራቅ ስዊዘርላንድ እንደነርሱ አቆጣጠር በ1854 ተወለደ፤ አልፍሬድ ኢልግ።

በዚህ የዘመን ስሌት ከሄድን አጼ ቴዎድሮስ ሽጉጣቸውን በጀግንነት ሲጠጡ ኢልግ የ16 ወይ የ17 ዓመት ጎረምሳ ቢሆን ነው።

ኢልግ ወላጅ አባቱን አያውቀውም። ከጋብቻ ውጭ ነዋ የተወለደው።

ያደገው ከእናቱ ማሪያ ማልዲና እና ከ2 የእንጀራ እህቶቹ ጋር ነበር። ያሳደገውም የእንጀራ አባቱ ኮሎኔል ኖቫነር ነው። ኖቫነር በቱርጋው ክፍለ አገር ፍራውንፌልድ ከተማ የሚያከራየው አልቤርጎ ነበረው።

በዚያ ዘመን ከጋብቻ ውጭ መገኘት ከሰው በታች ያደርጋል፤ ሰድቦ ለሰዳቢ ያሰጣል። ይህን ለማካካስ ኢልግ በትምህርቱ መላቅ ነበረበት።

ኮሌጅ ከመግባቱ በፊት ገና ጥንት ጣሊያንኛና ፈረንሳይኛን ጠጥቶታል። እንዲያውም እየዞረ ቤት ለቤት ያስጠና ነበር፤ ልክ እንደ ፖሊዮ ከታቢ።

አፉን የፈታው ደግሞ በጀርመንኛ ነው።

የኢልግ የእንጀራ አባት ያከራየው የነበረው አልቤርጎ፤ በቱርጋው @Baer, City Archive Frauenfeld

የኢልግ የእንጀራ አባት ያከራየው የነበረው አልቤርጎ፤ በቱርጋው @Baer, City Archive Frauenfeld

ኢልግ ከጋብቻ ውጭ መወለዱ ብስጭት ውስጥ ይከተው ነበር ይባላል። ሲበሳጭ በሥራ መጠመድ ነበረበት። ማሽን መጎርጎር ነበረበት። ማሽንም ባይሆን ያገኘውን ነገር…።

ልጅ እያለ ባደገባት የሰሜን ምሥራቅ ቱርጋው ክልል ባቡር ተዘርግቶ ነበር ይባላል፤ በያ ዘመን። ወጣቱ ኢልግ ታዲያ ባቡሩ ያስደምመው ነበር። ሀዲዱን እየተከተለ ሳይሮጥ አልቀረም፣ እንዴት ብረቶቹ እንደተቆላለፉ ለማየት። ሼ ከተፍተፍ…የሚለው የባቡር ድምጽ የነፍሱ ሙዚቃ ትሆን ይሆናል...።

ምናልባት ይህ በልጅነቱ የባቡር ቴክኖሎጂ ላይ መመሰጥ ይሆን ኋላ ጂቡቲና ለገሀርን እንዲያገናኝ ያደረገው? ማን ያውቃል!

ምናልባት ወላጅ አልባ መሆኑ ይሆን አጤ ምንሊክን 'አባቴ’ እንዲላቸው ያደረገው? ማን ያውቃል?


ኢልግ የተማረበት ዙሪክ ተግባረ ዕድ ኮሌጅ

ኢልግ የተማረበት ዙሪክ ተግባረ ዕድ ኮሌጅ

ለመሆኑ ኢልግ ወደ ሸዋ እንዴት መጣ?

የያኔዋ ስዊዘርላንድ እንደዛሬው የዓለም ዘናጯ አገር አልነበረችም። ያኔ ስዊዘርላንድ የብዙ ገበሬዎች አገር ነበረች። ሕዝቧም ሦስት ሚሊዮን ቢሰፈር ነው።

ኢልግ ከዙሪክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተመረቀ በ2 ዓመቱ የምንሊክ ጥሪ ደረሰው። ገና እኮ 25 ዓመቱ ነው። የዙሪክ ፖሊ ቴክኒክ የኛው ተግባረ ዕድ ነገር ነው። ቴክኒክ ያሰለጥናል። ስመ ጥር ነው ታዲያ።

እንኳን ያኔ ይቅርና አሁንም ሥመጥር ነው። ዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ እጅግ የላቁ የቴክኒክ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ነው። የሱ እኩያ ኤምአይቲ ነው። ኢልግ የተመረቀው ከዚሁ ግዙፍ ትምህርት ቤት ነበር።

ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ማሳካት የቻለው የምር ትምህርት ስለዘለቀው ይሆን?

አልፍሬድ ኢልግ ያነሳው ይህ ፎቶ ከንጉሥ ምንሊክ ጋር የነበረውን ቅርበት የሚያሳይ ነው።

ኢልግ ከኢትዮጵያዊያን ረዳቶቹ ጋር ዛሬም ድረስ እሪ በከንቱ አካባቢ በሚገኘው መኖርያ ቤቱ ቆሞ ይታያል። ጊዜው 1892 ነው። @ዙረክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

አልፍሬድ ኢልግ ያነሳው ይህ ፎቶ ከንጉሥ ምንሊክ ጋር የነበረውን ቅርበት የሚያሳይ ነው።

ኢልግ ከኢትዮጵያዊያን ረዳቶቹ ጋር ዛሬም ድረስ እሪ በከንቱ አካባቢ በሚገኘው መኖርያ ቤቱ ቆሞ ይታያል። ጊዜው 1892 ነው። @ዙረክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

ኢልግና ምንሊክ እንዴት ተገናኙ ታዲያ?

መቼስ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ሜዳሊይ ሸለሙት እንዳይባል ዐጤ ምንሊክ 'ንደሁ ከአገር ወጥተው አያውቁ።

ምን ያኔ እንኳን ስዊዘርላንድ ሊመጡ፤ እንጦጦም አልወጡ። ገና አንኮበር ናቸው፤ ገና የሸዋ ንጉሥ ናቸው። በነ ኢልግ አቆጣጠር’ኮ ገና 1887 ላይ ነን።

በዚያ ዘመን ኤደን ውስጥ አንድ የስዊዝ ኩባንያ  ነበር። ስሙም "ኤሸርና ፈረር" ይባላል። የዐጤ ምንሊክ ባለሟሎች ለዚህ ኩባንያ አስተዳዳሪዎች መልእክት ሰደዱ።

"ታላቁ ንጉሣችን የነቃ የበቃ ሙያተኛ ከየትም ፈላልጋችሁ ላኩልኝ ብለዋልና ባስቸኳይ…." የሚል።

ይሄ ኩባንያ ታዲያ መልእክቱን ከኤደን ወደ ዙሪክ አስተላለፈ። መልእክቱ ለማን ቢደርስ ጥሩ ነው? ለዙሪክ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን። ያኔ የኮሌጁ ዲን የኢልግ አድናቂ ነበሩ።

'ለሥራው ትክክለኛው ልጅ አለኝ፤ ስሙም የቱርጋው አልፍሬድ ኢልግ ይባላል' ብለው ለኩባንያው ጦማር ላኩ።

አልፍሬድ ኢልግ ሐሳቡ ሲቀርብለት አለማቅማማቱ ግን ይገርማል።

ምክንያቱም በዚያ ዘመን ኢትዮጵያን አንድ አውሮጳዊ ወጣት ምሩቅ ፈጽሞ ሊያስባት አይችልምና ነው። ያኔ ገና አድዋ በአውሮጳ አላስተጋባማ። ያኔ ገና ንጉሡ በምዕራቡ አልገነኑማ። ታዲያ አንድ የስዊዝ ጎረምሳ ሸዋን እንዴት ሊያስባት ይቻለዋል?

እርግጥ ነው ስዊዘርላንዳዊያን በዚያ ዘመን ስደት ብርቃቸው አልነበረም። ቢሆንም ዜጎቻቸው ወይ ወደ ጣሊያን ወይ ወደ ሆላንድ፣ ቢከፋ ቢከፋ ወደ ደቡበ አፍሪካ እንጂ ወደ ምሥራቅ አፍሪቃ…? ታይቶም ተሰምቶም አያውቅ!

አልፍሬድ ግን ጨከነ። ደመወዙ 5 ወይ 6ሺ ፍራንክ ነው የሚሆነው፤ ለዚያውም ባ'መት'ኮ ነው። ይሄ ገንዘብ በዚያ ዘመን ብዙ ብር ይሆን እንዴ…?ቢሆንም…!

‹‹በቃ አንድ ሁለት ዓመት ሸቃቅዬም ቢሆን እመለሳለሁ" ብሎ አስቦም ይሆናል፣ ያኔ።

የምንሊክ ፍቅር ጠልፎ እንደሚጥለው አላወቀ ይሆናል፤ ያኔ።

 ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በዚያች አገር እንደሚጸና አልገመተ ይሆናል፤ ያኔ።ከዙሪክ አንከቦበር፡ በባቡር-በመርከብ-በግመል በበቅሎ

የአሁኑ የዐብይ አሕመድ መቀመጫ ታላቁ ቤተመንግሥት በዚያ ወቅት የነበረው ገጽታ ይህ ነበር። 1898 በፊት የተነሳ ነው።

የአሁኑ የዐብይ አሕመድ መቀመጫ ታላቁ ቤተመንግሥት በዚያ ወቅት የነበረው ገጽታ ይህ ነበር። 1898 በፊት የተነሳ ነው።

ኢልግ በዚያ ዘመን ብቻውን መጓዝ አልተቻለመው። ሁለት የአገሩን ልጆች አስከትሏል። አንድ የማሽን ቅርጽ በመንደፍ የሚታወቅ ሰውና አንድ ሌላ ሲመርማን የሚባል አንጥረኛ።

ሦስቱም ከዙሪክ ወደ አንኮበር የተንቀሳቀሱት በነርሱ አቆጣጠር በ1878 ግንቦት ወር ላይ ነበር።  በኛ 1870 መሆኑ ነው።

ከዙሪክ ወደ ጄኔቭ፤ ከጀኔቫ ወደ ማርሴይ በባቡር ደረሱ። ከማርሴይ መርከብ ተሳፈሩ። በምስር-ሳይድ ወደብ አድርገው ቀይ ባሕርን አልፈው ኤደን ዳርቻ የስዊዝ ኩባንያ ቢሮ ሲደርሱ 6 ወር ሆኗቸው ነበር።

እንኳንም ከጉዟቸው ከ10 ዓመት ቀደም ብሎ የስዊዝ ቦይ ተከፈተ እንጂ ምንሊክ የጠሩት አቶ ኢልግ ጦቢያ ይደርስ የነበረው በዘውዲቱ ዘመን ይሆን ነበር።

እርግጥ ነው ጉዞው አልጋባ’ልጋ አልነበረም። በኤደን ለፍተሻ በሚል 4 ወር ታግተዋል። ያን ጊዜ ግብጽ ነበረች የአካባቢው አለቃ። ግብጽ ደግሞ ወደ ሸዋ የሚገባን እያንዳንዷን ነገር መበርበር ትወዳለች።

እነ ኢልግ ወጥተው ወርደው ከኤደን ተነስተው ሶማሊያ ጠረፍ ዘይላ ደረሱ። ከዘይላ ወደብ የምንሊክ ሰዎች አጀቧቸው፤ አጋሰስ ተጭኖ እጅግ አደገኛ የነበረውን የአፋርና የደናክል በረሃ አቋረጡ።

እነ ኢልግ በጉዞው ስንት ጊዜ ታመው እንደነበረ…

ከ8 ወር በኋላ አንኮበር ገቡ። ንጉሡም ደማቅ አቀባበል አደረጉላቸው።

አልፍሬድ ኢልግ፡ ከአንኮበር እስከ እሪ በከንቱ


ስዊዛዊው ኢልግ አንኮበር እንደደረሰ ዐጤ ምንሊክ 'እስቲ ዳይ ሽጉጥ ሥራልን' ሳይሉት አልቀረም። እሱም ሳይደነግጥ አልቀረም።

በዚያ ዘመን አውሮጳዊ ተጓዦች ጥይትም ሆነ የጥይት ማርከሻ መቀመም አይሳናቸውም የሚል አመለካከት ሳይኖር አልቀረም።

በዐጤ ምንሊክና በኢልግ ዙርያ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ኤልዛቤጥ ባሲዮ በዙሪክ ዩኒቨርስቲ የሰው ልጅ ባሕል ታሪክ ተመራማሪ ናቸው።

ለዚያም ይሆናል ኢልግ ገና አንኮበርን ከመርገጡ ሥራ የበዛበት።

የኢልግንና የምንሊክን ግንኙነት ያጠኑት ስዊዛዊ ዶ/ር ፒተር ገርበር ዙሪክ በሚገኘው ቤታቸው በተገናኘን ጊዜ እንደነገሩኝ ኢልግ በዐጤ ምንሊክ ትዕዛዝ አንኮበር አቅራቢያ መለስተኛ የጦር መሣሪያ ቁሳቁሶችን የሚሞርድ ማሽን ተክሎ ነበር።

ኢልግ ታዲያ የዐጤ ምንሊክ የጦር መሣሪያ አንጥረኛ ብቻ አልነበረም።

ጦር ሜዳ የዋለው ቁስላችንን አጠግግልን ይለዋል። እርሻ የሚውለው ማረሻችንን አሹልልን ይለዋል። ይህን ጊዜ ኢልግ በመጪዎቹ ዓመታት በአበሻ ምድር እንቅልፍ አልባ ሕይወት እንደሚጠብቀው ሳይጠረጥር አልቀረም።

የመጀመርያ ተግባሩም ለመንገድ ጥርጊያ ተራራን መናድ አልነበረም። የቋንቋን ግንብ ማፍረስ እንጂ። ከምንሊክ ሕዝቦች ጋ ልብ ለልብ ለማውጋት ቋንቋ የግድ መሆኑን አመነ።

ወትሮም ቋንቋ ይገራለታል። አማርኛ እንደ ባቡር ሥራ ፍዳውን አላበላውም። በአጭር ጊዜ አቀላጥፎ መናገር ቻለ። መናገር ብቻም ሳይሆን መጻፍና ማንበብንም ተማረ። አማርኛ ቋንቋን መማር ለርሱ የላላ የባቡር ብሎን የማጥበቅ ያህል ቀላል ነበር።

የሐረሩ ባለቅኔ ፈረንሳዊ አርተር ራንቦ በአንድ ወቅት "ምንሊክ ኢልግን የወደደው በታማኝነቱና አማርኛን ስላቀላጠፈለት ነው" ብሎ የጻፈው እውነት ሳይሆን አይቀርም።

አማርኛን ማሳለጥ እንደቻለ አንኮበር የሚገኘውን የንጉሡ መጋዘን ገባ። ባገኘው ቁሳቁስ ሁሉ አንዳች ጥቅም የሚሰጥ ነገር መሥራት እንዳለበት አመነ።

ዶ/ር ፒተር ገርበር

ከዚያ በኋላ ባለው ሕይወቱ ኢልግ ሙያው ይህ ነበር ተብሎ የሚበየን ነበረ’ንዴ? በፍጹም።

ጤና አዋላጅም፣ ብረት ቀጥቃጭም፣ ንግድ አሳላጭም፣ እንጨት አፋላጭም፣ ዝመና አ’ማጭም ሆኖ ኖሯል።

በሌላ ቋንቋ፣ ኢልግ ድልድይ ይጠግናል፤ የወታደር አጥንት ሲሰበርም ይጠግናል።

ፈንጣጣና ተስቦ ባጋጠመ ቁጥር 'ያን ፈረንጁን ጥሩት እንጂ" መባል ተጀመረ።

በአንድ ዛሬም ድረስ በሚገኝ ደብዳቤው 'ከስዊዝ ለራሴው ይዤው የመጣሁትን መድኃኒት የአገሬው ሰዎች አጫረሱኝ' ሲል ያማርራል።

ኢልግ ከልማት በተቀረው ጊዜው ከጃንሆይ ጋር ተንከራቷል። ወጥቷል፣ ወርዷል።

እንደዚያ ዘመን የወራሪ ጭፍሮች በቆዳ ቀለሙ ንጣት እየታበየ፣ እግሩን አንፈራጦ ፒፓ እያጤሰ በአውቅልህለው ፈረንጃዊ ምክሩን ከእንጦጦ አቀበት ኾኖ ወደታች አላዥጎደጎደም።

እንደ ቫይስሮይ አልሰራራውም። ጥቁርን አልናቀም። እንዲያ ቢሆንማ ንጉሥ ምንሊክስ መች ይለቁታል። በካልቾ ብለው ያባሩትም አልነበር…?

በዐጤ ምንሊክና በኢልግ ዙርያ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ኤልዛቤጥ ባሲዮ በዙሪክ ዩኒቨርስቲ የሰው ልጅ ባሕል ታሪክ ተመራማሪ ናቸው።

በዐጤ ምንሊክና በኢልግ ዙርያ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ኤልዛቤጥ ባሲዮ በዙሪክ ዩኒቨርስቲ የሰው ልጅ ባሕል ታሪክ ተመራማሪ ናቸው።

ዶ/ር ፒተር ገርበር

ዶ/ር ፒተር ገርበር

አልፍሬድ ኢልግ በአዲሳ'ባ

አራዳ ጊዮርጊስ ፈረሰኛው ምንሊክ ሥር ለአንድ ፈረንጅ አንዲት ድንክ ሐውልት ትቁም ቢባል መቆም ያለበት ለኢልግ ነው ብለው የሚያምኑ ታሪክ አዋቂዎች አሉ። ይህ ማለት ግን የኢልግ አስተዋፅኦ ድንክ ነበር ማለት ነው እንዴ? በፍጹም።

ኢልግ ለአዲስ አበባ ያላረገላት ነገር የለም። አዲሳ'ባ ለኢልግ ምንም አላረገችለትም እንጂ…። እንዲያውም ንፉግ ሆናበታለች።

ሌላው ይቅርና የገዛ ቤቱን ልታሳርስበት ዶዘር መላክ ነበረባት? ይህን ጉድ ኋላ እንመለስበታለን። ለጊዜው የኢልግ አስተዋጽኦ ላይ እናተኩር።


እርግጥ ነው አዲስ አበባን የቆረቆሯት እቴጌይቱ ናቸው። አዲስ አበባን ያነጻት ግን አልፍሬድ ኢልግ ነው። ምሶሶና ማገር አዋድዶ፣ ምስማር ከመዶሻ አዛምዶ…

አዲሳባን ጣሪያ ያለበሰስ ማነውና? የቱርጋው አልፍሬድ ኢልግ አይደለምን?

አዲስ አበባን ውሀ ያጠጣስ፣ ያዲሳባን መብራት ሊያበራ የሞከረስ? ቢትወደድ ኢልግ አይደለምን?

የኤሌክትሪክ ሽቦ ፍለጋ የንጉሡን መጋዘን በርብሮ የመዳብ ሽቦ ያገኘ…ባይሳካለትም ንጉሡን ከማሾ ብርሃን ሊያወጣ የሞከረ ኢልግ አይደለምን?

ለመጀመርያ ጊዜ ጃንሆይን በቧንቧ ውሃ ያጠጣቸው ኢልግ ከባድ ፈተና ገጥሞት እንደነበር ተደጋግሞ በታሪክ ይወሳል።

ውሃ ቁልቁል ይወርዳል እንጂ ሽቅብ አይወጣም ያሉ ሁሉ ድርጊቱን ሰይጣናዊ ሲሉ ኮነኑ፤ ኢልግንም አወገዙ። ለክፋቱ ደግሞ በመጀመርያ ሙከራው ከቧንቧው ውሃ ጠብ አልል አለ።

 ‹‹እኛስ ምን አልን ጃንሆይ!›› አሉ አውርቶ አደሮች። ለካንስ ማን እንደወተፈው ያልታወቀ አንዳች ነገር ቧንቧውን ዘግቶት ነበር።

ኢልግ ሸፍጡን ደረሰበት። ውሃም ሽቅብ ፈሰሰ፤ ጃንሆይም ፉት አሉለት…። ከዚያች ዘመን ጀምሮ እነሆ የአዲሳ'ባ ሕዝብ ውሃ ከቧንቧ ይቀዳል፤ (በፈረቃም ቢሆን።)


ኢልግ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ የመጀመርያው የባንክ ገዢ ልንለው እንችል ይሆን?

ምናልባት ራስ ተሰማ ቀድመውት ሊነሱ ይችላሉ። ቢሆንም የመጀመርያውን የሳንቲም ማምረቻ ማሽን ከቪዬና ገዝቶ ማምጣቱን አንዘንጋ።  ከዚያ በፊት በየማሪያ ቴሬዛ ጠገራ ብር ነበር ሕዝቡ 'የሚጠገረር'።

"የምንሊክ ዶላር" የሚባለው ነገር የመጣው በኢልግ ምክንያት ነበር ማለት ይቻላል።

ለነገሩ በዚያ ዘመን የነበረ ቁሳዊ ዝመና ሁሉ… ስልክ ቢሉ መኺና፣ ቴሌግራም ቢሉ ፖስታ፣ ሁሉም የኢልግ ልማታዊ እጅ አለበት፤ በአንድሜ ሆነ በሌላ።

እዚህ የማንዘረዝረው "ሁሉን ቢናገሩ…"ሆኖብን ነው'ይ…።

ከፋሽስት ጣሊያን ሊቃጣ የሚችልን ጥቃት ለመከላከል በንቃት ቤተ-መንግሥት የሚጠብቁ የንጉሡ ወታደሮች። 1928 ዓ.ም።

ከፋሽስት ጣሊያን ሊቃጣ የሚችልን ጥቃት ለመከላከል በንቃት ቤተ-መንግሥት የሚጠብቁ የንጉሡ ወታደሮች። 1928 ዓ.ም።

ከእንጦጦ ማርያም እስከ 4ኪሎ

ዐጤ ምንሊክ 'ዘመቻ’ ወርደው ነበር፤ ሐረርና አርሲ። እቴጌ ብቻቸውን ነበሩ። ፍል ፍል የሚለው ፍል ውሃ ማረካቸው። ቀድሞ በአንኮበር አሁን ደግሞ በእንጦጦ አቀበት ብርድ አንገሽግሿቸዋል። ከተራራው መውረድ ጓጉተዋል። አልፍሬድ የሠራላቸው የእንጦጦ ቤተ መንግሥት ምንም አይሞቅም።

ንጉሡ ከዘመቻው ተመልሰው ለዘመን መለወጫ እታች ግቢ ወደ አራት ኪሎ፣ የዛሬው ሂልተን አካባቢ ወረዱ አሉ፤ እንጦጦን ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናብተው።

ከዚያ ወዲያ ከሠራዊት ጋር የሚንከራተት ሳይሆን የጸና መንግሥታዊ መቀመጫ ተገኘ። ይህ የሆነው ግን በምንሊክ መልካም ፍቃድና በኢልግ ታታሪነት ነበር ማለት ይቻላል። 

ለምን ከተባለ ንጉሡ ብቻቸውን ቢወርዱና መኳንንቶቹንና መሳፍንቶቹን እርሳቸው ዙርያ ከነጭፍሮቻቸው እንዲሰፍሩ ባያ'ዙ ኖሮ የዛሬዋ አዲስ አበባ እውን አትሆንም ነበር ይሆናል።

አብሮ መዘንጋት የሌለበት ግን ያ ሁሉ ጭፍራ በዚያ እንዲሰፍር የቤት ግንባታ እጅግ ወሳኝ እንደነበር ነው። የሳር ክዳንም ቢሆን።

ይህን በማቀናጀት የኢልግ ሚና እጅግ ወሳኝ ነበር። ልክ የዛሬውን 40/60 የቤት ፕሮጀክት በዓመት ውስጥ አጠናቆ የማስረከብ ያህል። ይህ ተግባሩ የንጉሡንና የንግስቲቱን እልፍኝ ከማነጽ ይጀምራል።

ኢልግ ከአዲስ አበባ ውጭ ምናልባትም የመጀመርያዋን ድልድይ የዘረጋበት መንገድ ራሱ በአገሪቱ ዝማኔ ፈር ቀዳጅ የሚባል ነው።

ኢልግ ከአገሩ በመጣ ባጭር ጊዜ ውስጥ በዚህ የአበሾች ምድር የሰውንም ሆነ የእንሰሳቱን እንቅስቃሴ የሚገታ ዋናው ጉዳይ እንደ ስዊዘርላንድ የበረዶ ግግር ሳይሆን የወንዞች መሙላት እንደሆነ ተረዳ።

በክረምት ንጉሡን ጨምሮ ሠራዊቱም ሆነ ተራው ሕዝብ ከቦታ ቦታ መንከላወሱ ይገታል። ምክንያቱ ደግሞ የወንዞች መሙላት ነው።

ኢልግ ለምንሊክ ሕዝብ ድልድይ እጅግ ያስፈልገዋል ብሎ ተነሳ። ጃንሆይን ግን ለምን እንደሁ እንጃ የሚያሳካው አልመስላቸው አለ።

'አንዴት አድርገህ?' አሉት። ሚስማር ቀጥቅጬ፤ ብሎን አቅልጬ አላቸው። ሞዴል አምጣ አሉት። በአንዳች ቁሳቁስ ገጣጥሞ ድልድይ የሚመሰል ነገር ሠርቶ አመጣ። በኃያሉ ክንዳቸው ቢደቁሱት ብትንትኑ ወጣ። “በል አጠንክረው!” ተባለ።

በዚህ መልኩ የመጀመርያዋ ድልድይ እውን ሆነች።

ይቺ ድልድይ ዛሬ የምትገኘው የት ይሆን? ማወቅ አልቻልኩም። ፎቶዋን ብቻ ነው ማግኘት የቻልኩት። ካዲሳባ ውጭ በአዋሽ ወንዝ ላይ ተዘርግታ ለዘመናት እንዳገለገለች ግን እርግጥ ነው።

ያኔ ይቺን አጭር የብረት ድልድይን መገንባት ዛሬ አባይ በረሃ ላይ ተንጠልጣይ ድልድይ የመዘርጋት ያህል መሆኑን ልብ ይሏል።

ይቺ ድልድይ ተመርቃ ዕውን ከሆነች በኋላ አልፍሬድ ኢልግ ለጓደኛው አንዲት ደብዳቤ ጻፈ። ወደ ዙሪክም ሰደዳት።

ሚስተር ኸሪበርት ኩንግ በጻፉትና አቶ ዮናስ ታረቀኝ በተረጎሞት የኢልግን ሕይወት የሚያወሳ መጽሐፍ ገጽ 57 ላይ ይቺ ዙሪክ ለሚገኝ ጓደኛው የጻፋት ደብዳቤ ግሩም ተደርጋ ተተርጉማ ተቀምጣለች።

"የመጀመርያውን ድልድይ አጠናቀቅኩ።…ሸዋ በሥልጣኔ አንድ እርምጃ ወደፊት ሄደች…እዚህ አናት የሚበሳ ሐሩር፣ ተቅማጥ የሚያስከትል ዝናብ፤ ጺሜን ከሥሩ የሚነቅል ንፋስ አለ። ሌሊት ጅቦች ከጭንቅላቶቻችን ሥር የቆዳ ትራሶቻችንን ይሰርቃሉ።…"

ኢልግ ታላቁ መሐንዲስ

ኢልግ የማሽን መሐንዲስ መሆኑ በጀው። ገና ምንሊክ ከአንኮበር ወርዶ ወደ እንጦጦ አናት ላይ ሲወጣ ኢልግ አስቀድሞ ያደረገው ነገር ለመንገድና ለቤት ግንባታ የሚሆኑ ማሽኖችን ከአውሮፓ በአስቸኳይ ማስመጣት ነበር።

በዚያ ዘመን በአስቸኳይ ማለት ከዓመት በታች፣ ከመንፈቅ በላይ ሲሆን ነው።

በዚያ ላይ ድንበር ላይ፣ ወደብ ላይ ቅኝ ገዢዎች ነው ያሉት። ኢትዮጵያንና ንጉሣቸውን በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱት።

‘ይሄ ጥቁር ሰው ማሽን ከቀረበለት፣ መሣሪያ እንደልቡ ከገዛ እኛኑ መልሶ ይገዛናል’ የሚል ስጋት ነበራቸው። ስለዚህ ኢልግ እያንዳንዱን ጠቃሚ ቁሳቁስ የሚያስገባው በኮንትሮባንድ መሆኑን ልብ ይሏል።

በቅድሚያ ኖራ ማምረቻ ፋብሪካ ቢጤ ከፈተ። ማታ ማታ የግንባታ ንድፍ ላይ ተጠመደ። ያን ጊዜ ከተማዋ ላይ የሚታይ ሰማይ ጠቀስ የሚባል ነገር ቢኖር ዘለግ ያለ ቁጥቋጦ ብቻ ነበር ማለት ይቻላል።

እነ ምንሊክ ከአንኮበር ወደ እንጦጦ ቤት ሲቀይሩ የንጉሡንና የጣይቱን እልፍኝ ያቆመው ኢልግ ነው። ግንባታው ድንቅ የሚባል ባይሆንም ዛሬም ድረስ እንዳለው አለ።

ከዚያው ከእንጦጦ ሳይወርድ ዛሬ ባለ 8 ጎን ኪነ ሕንጻዊ ውበት የታደለውን የእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች ጋ በመሆን አስገነባ። በእቴጌ ትእዛዝ። ኢልግና የአገሩ ልጅ አናጢው ዚማመርማን ከበርካታ የጉራጌ ተወላጆችና የጎንደር እውቅ አናጢዎች ጋር በመሆን በግንባታ ተሳትፈዋል።

ምንሊክና እቴጌይቱ ለዚች ቤ/ክርስቲያን ሁነኛ ዛፍ ፍለጋ መናገሻ ጫካ ድረስ ተጉዘዋል። የሁለቱም ንግሥና እዚሁ ነበር ያደረጉት። ጳውሎስ ኞኞ እንደሚለው በንግሥናው ዕለት የድግሱ መጠን ባበሻ ምድር ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። 5ሺ በሬ ታርዷል። ይቺ ቤ/ክርስቲያን በዘውዲቱ ዘመን መልከኛ እድሳት ደርጎላታል።

ከዚያው ከእንጦጦ ሳይወርድ ቅዱስ ራጉኤልን ቆሞ አስገነባ፤በንጉሡ ትእዛዝ። የቅዱስ ራጉኤልን ግንባታ የመራው ሕንዳዊው ሐጂ ቃዋስ ነበር።

ወደ 4 ኪሎ ግቢ ሲወርዱ ደግሞ ከፈረንሳዊው ሊዮ ቼፍኔክ እና ከሕንዳዊው ሀጂ ቃዋስ ጋር በመተጋገዝ ግብር ማብያ አዳራሽን ገነቡ።

ዛሬ አንድነት ፓርክ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ የምንሊክ ዛኒጋባዎች ባንድም ሆነ በሌላ የኢልግ አሻራ  ያለባቸው የሆኑትም ለዚያ ነው።

ኢልግ የኋላ ኋላ ድልድይ ደጋግሟል። አንድዬ ድልድዩን በአዋሽ ወንዝ ዘርግቶ አላቆመም። አንድ በቀጨኔ፣ አንድ በአቃቂ አንጥፏል።

ይህ በቅርቡ እድሳት ያገኘው የግብር አዳራሽ በ1898 (እ.ኤ.አ) የተሠራ ነው፡፡ ኢልግና ፈረንሳዊው ሊዮን ተሳትፈዋል፡፡ የጉልበት ሥራው በአመዛኙ በሕንዶች የተፈጸመ ነው፡፡ @ የዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

የግብር አዳራሹ አሁን ያለው ገጽታ።

ቅዱስ ራጉኤል ቤተ-ክርስቲያን።

ይህ በቅርቡ እድሳት ያገኘው የግብር አዳራሽ በ1898 (እ.ኤ.አ) የተሠራ ነው፡፡ ኢልግና ፈረንሳዊው ሊዮን ተሳትፈዋል፡፡ የጉልበት ሥራው በአመዛኙ በሕንዶች የተፈጸመ ነው፡፡ @ የዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

የግብር አዳራሹ አሁን ያለው ገጽታ።

ቅዱስ ራጉኤል ቤተ-ክርስቲያን።

የኢልግን የልጅ ልጆች ፍለጋ

ኢትዮ ስዊዛዊው ያሬድ በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ከተረክናት ከዚያች የቀላል ባቡር አጋጣሚው በኋላ የአልፍሬድ ኢልግ ቤተሰቦችን አግኝቷቸው አያውቅም።

የቢቢሲ ዘጋቢን በዙሪክ መገኘት ተከትሎ ግን ወደ ዳግም አሰሳ ገባ። በመጨረሻ አድራሻቸው ከስዊዛዊያኑ የሰው ልጅ ባሕል አጥኚ ከሆኑት ባልና ሚስት ዶ/ር ኤልዛቤጥ ባሲዮ እና ዶ/ር ፒተር ገርበር ተገኘ።

ሁለቱ ባልና ሚስት አሁን ጡረታ ላይ ያሉ ምሁራን ናቸው። የዙሪክ ዩኒቨርስቲ የሰው ልጅና የባሕል ጥናት ክፍል ባልደረባም ነበሩ።

በዚህ ባለንበት ዘመን እንደነርሱ ኢልግን እና ዐጤ ምንሊክን ያጠና በድፍን ስዊዘርላንድ የለም። አዲስ አበባ ተመላልሰዋል። ድልብ መጽሐፍ ጽፈዋል። በርከት ያሉ ጥናታዊ ጽሑፎችን አሳትመዋል።

 ከሦስት ዓመት በፊት ዝክረ-ኢልግ 100ኛ ዓመትን፣ ስዊዛዊው መሐንዲስ ለዐጤ ምንሊክ የነበረውን ወዳጅነት፣ ለአገር ያበረከተውን አስተዋጽኦ በዙሪክና በኢልግ የመኖርያ ክልል ዘክረዋል፤ አዘክረዋል።

እነ ዶ/ር ኤልዛቤጥና ዶ/ር ፒተር ቤት በተጋበዝን ጊዜ ስለ አልፍሬድ ኢልግ ብዙ የማናውቃቸው ጉዳዮች እንዳሉ ተረዳን።

ለምሳሌ ኢልግ ኢትዮጵያዊት ሚስት አግብቶ እንደነበረና ስሟም ወለተማርያም እንደሚባል፤ ከርሷ የወለዳቸው ልጆችም እንደነበሩ፤ አሁን ግን የአልፍሬድ ኢትዮጵያዊ ዘር የት እንዳለ ብዙም እንደማይታወቅ ነገሩን።

ሆኖም ግን ክሪስቶፍ ካን የሚባል ሌላ ስዊዛዊAlfred Ilg – the White Abyssinian” የሚል አጭር ዘጋቢ ፊልሙ ላይ የኢልግ ኢትዮጵያዊ የልጅ ልጆች መጠቀሳቸውን ጠቁመውን አለፉ።

ባልና ሚስቱ ዶ/ር ፒተርና ዶ/ር ኤልዛቤት በአልፍሬድ ኢልግ ዙርያ ያሳተሟቸውን መጻሕፍትንም በገጸበረከት መልክ አበርክተውልን ሲያበቁ ኢልግ ወደ ዙሪክ ከተመለሰ በኋላ ይኖርበት የነበረው ቤት በእግር ይዘውን ሄዱ።

እነ ዶ/ር ፒተርና ዶ/ር ኤልዛቤት በዙሪክ ዲስትሪክት 7 በሚባል ሰፈር ነው የሚኖሩት። ኢልግ የኖረበት ቤት ደግሞ ዙሪክ ዲስትሪክት 8 በሚባል ክፍለ ከተማ፣ ፎሽትራሰ በምትባል ቀበሌ ነው የሚገኘው። አስፋልት ዳር።

 ከደጅ ቆመንም ቢሆን ጎበኘነው። የኢልግ ቤት ከነርሱ ሰፈር የ10 ደቂቃ የእግር መንገድ ቢሆን ነው። መሐንዲሱና እነርሱ በተለያየ ዘመን ቢኖሩም የሰፈራቸው ሰው ነበር ማለት ይቻላል።

ልንለያይ ስንል የኢልግ የልጅ ልጆችን አድራሻ ያውቁ እንደሆን አጥብቀን ጠየቅናቸው። የኢልግን የልጅ ልጆች ማግኘት ለብዙ ኢትዮጵያዊን ተራ ጉዳይ እንደማይሆን ከታሪክ ጥናታቸው የተረዱ ይመስላሉ። ዙሪካዊያን ለኢልግ ደንታ ባይኖራቸውም ኢትዮጵያዊያን ለኢልግ እንደሚደነግጡለት አልጠፋቸውም።

በብጣሽ ወረቀት አንድ ስምና ስልክ ጽፈው ሰጡን፤ የተጻፈው ስም ቨሪና እና ፊሊክስ ኢልግ ይላል። የመኖርያ አድራሻም ተጨምሮበታል።

በነገታው በዚህ ስልክ ደውለን ያገኘናቸው ሰው እንግሊዝኛ የሚረዱ አልነበሩም። በኢትዮ ስዊዛዊው ያሬድ ያላሰለሰ ጥረትና እርዳታ የኢልግ የልጅ ልጅ ተገኙ።

ለኚህ ሰው በስልክ የአያታቸው ወዳጅ ከነበሩት ከዐጤ ምንሊክ አገር የመጣን ጋዜጠኞች እንደሆንን ተነገራቸው። የምንገናኝበት ቀንና ሰዓት ተቆረጠ።

ያሬድ ኃይለ ሥላሴ አንዲት ትንሽዬ መኪና ውስጥ አስገብቶን አቀበት ወጥቶ፣ ቁልቁለት ወርዶ የኢልግ የልጅ ልጆች ቤት አደረሰን።

ከዙሪክ ወጣ ብላ የምትገኝ አንዲት ገጠራማ የባለጸጎች ‘ቀበሌ ገበሬ ማኅበር’ የምትመስል ሰፈር ናት ። ስሟም ኤልናኦ ኤፈረቲኮን ይባላል።

የነ ኢልግ የልጅ ልጆች ሰፈር ስንደርስ ነው ባዶ እጃችንን መግባት ነውር እንደሆነ ትዝ ያለን። በአካባቢው ኪዮስክ ፍለጋ ኳተንን። ኾኖም የረባ ነገር አላገኘንም። ኤልናኦ የገጠር ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነገር ናት አላልኳችሁም?

'እምዬ' ከሚባሉት ምንሊክ አገር መጥተን ባዶ እጃችንን…? ነውር ነው!

ራቅ ወዳለ ሱፐርማርኬት እንዳንሄድ ደግሞ አርፍደናል።

 ስዊዞች ቀጠሮ ላይ እንደ ስዊዝ ሰዓት ናቸው። ዝንፍ የለም። ምንም ማድረግ አልተቻለም፤ ጥሩ ፈገግታ ይዘን ባዶ እጅ ገባን። ባልና ሚስቱ ደጅ ድረስ ወጥተው ተቀበሉን።


የአልፍሬድ ኢልግ የልጅ ልጅ

ሳሎናቸው በአራቱም አቅጣጫ የዐጤ ምንሊክን ዘመን የሚያወሱ ትንንሽ ፎቶዎች ተሰቅለውበታል። ቀላልና ዝም ያለ ሳሎን ነው። የሚያብረቀርቅ ነገር የለውም። እንዲያውም የዚህ ዘመን ሳሎን አይመስልም።

በአንደኛው ግድግዳ ኢልግ ድሮ ያነሳቸው ፎቶዎች ወደ ሥዕል ተቀይረው ይታያሉ። አንድ ፓውል ግሪፍ የሚባል የድሮ ሠዓሊ ባለቀለም አድርጓቸው ነው እንጂ ባለቀለም አልነበሩም።

አልፍሬድ ኢልግ ኢትዮጵያዊት ሚስቱን ከፈታ በኋላ ፋኒ ጋቲገር የምትባል ስዊዛዊት አግብቶ ነበር። ከጋብቻቸው በኋላም ወደ ምንሊክ አገር ይዟት ሄዶ ነበር።

ይቺ ስዊዛዊት ባለቤቱ ፋኒ ጋቲገር ምንሊክ በላኩላት ውብ በቅሎ ተፈናጣ ወደ አንድ ቦታ ስትሄድ የሚያሳየው ምሥል በአንደኛው ግድግዳ በፎቶ ፍሬም ተሰቅሏል።

ዐጤ ምንሊክ ለፋኒ ጋቲገር የላኩላት በቅሎ ያምራል። 'በእግር እንዳትደክም ንጉሡ ናቸው ጂቡቲ ድረስ የላኩላት" አሉን አቶ ፌሊክስ ኢልግ።

የዚህ ፎቶ ቱባ ቅጂ ዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዝየም እንደሚገኝም ጠቆሙን።

አሁን እነሱ ሳሎን ላይ ተሰቅሎ የምናየው የፎቶ ቅጂው ወደ ሥዕል ተቀይሮ ነው።


ሽማግሌዎቹ ባልና ሚስት የኢልግ የልጅ ልጆች እየተቀባበሉ በጥልቅ ስሜት ያወራሉ። ከምንሊክ አገር ለመጣን ጥቁር  እንግዶች። እኛ ግን አንሰማቸውም። ለምን? ጀርመንኛ ነዋ የሚያወሩት።

ከልብ እንዳናወጋ ቋንቋ የአልፕስ ተራራ ሆነብን።

አያታቸው ኢልግ የመንዝ አማርኛን አቀላጥፎ በሮም ጣሊያንኛ ተቀኝቶ፤ በፖሪስ ፈረንሳይኛ ያዜም እንዳልነበረ የልጅ ልጆቹ ግን አማርኛውን ቀርቶ እንግሊዝኛውም በዞረበት አልዞሩም።

ደግነቱ ያሬድ ለልሳናቸው ቱርጁማን ሆነን። የኛን ጥያቄዎች በአማርኛ ተቀብሎ፣ በጀርመን አፍ ወደነርሱ ጆሮ አቀብሎ መልሶ ለኛ ጆሮ በአማርኛ ያስማማዋል።

ያሬድ ኃይለሥላሴ፣ ሚስተር ፊሊክስ ኢልግና ባለቤታቸው ቭሬኒ ኢልግ ከመኖሪያ ቤታቸው ደጅ።

ያሬድ ኃይለሥላሴ፣ ሚስተር ፊሊክስ ኢልግና ባለቤታቸው ቭሬኒ ኢልግ ከመኖሪያ ቤታቸው ደጅ።

የአልፍሬድ ኢልግ የልጅ ልጆች ስለ ዐጤ ምንሊክ ምን ያስባሉ?

አቶ ፊሊክስ ኢልግ ጁኒየር የአልፍሬድ ኢልግ የልጅ ልጅ ናቸው። የልጅ ልጅ ስንል ግን ትንትንሽ እንቦቀቅላ እንዳትጠበቁ። በ1940 ነው የተወለዱት።

አባታቸው አዲስ አበባ ነበር የተወለዱት። አባታቸው ድሮ ነው የተወለዱት። በፈረንጆች በ1904 ዓ.ም፤ ምንሊክ ከመታመማቸው ጥቂት ዓመት ቀደም ብሎ ማለት ነው ይሄ። እስከ 1976 በሕይወት ነበሩ።

የአቶ ፊሊክስ አባት ወንድም (የአቶ ፊሊክስ አጎት) ደግሞ ስማቸው ምንሊክ ነበር። አጤ ምንሊክ ናቸው በስሜ ይጠራ ብለው ምንሊክ ያሏቸው።

አሁን ቤታቸው የምንገኘው አቶ ፌሊክስ ኢልግ ጁኒየር እንደ አያታቸው አልፍሬድ ኢልግ ምህንድስና ነው የተማሩት። ወ/ሮ ቬሪና ኢልግን አግብተው ሁለት ልጆችን አፍርተዋል።

ስለ አያታቸው አልፍሬድ ኢልግ እና የኢትዮጵያ ታሪኩ ልጅ እያሉ እምብዛምም ዕውቀቱ አልነበራቸውም። ለማወቅም ያን ያህል ጉጉት እንዳልነበራቸው ለቢቢሲ ዘጋቢ ነግረውታል። የኋላ ኋላ ግን ታሪክ ማንበብ ሲጀምሩ ፍላጎታቸው ተነሳሳ…።

በተለይ አያታቸው ያማክሩት የነበረው ኢምፐረር ባለ ኃያል ክንድ እንደነበረ ሲረዱ…ስለ አያታቸው የማወቅ ፍላጎታቸው አደገ።

 “ልጅ እያለሁ የማስታውሰው እዚያ ዙሪክ የሚገኘው ቤታችን ውስጥ 'የኢትዮጵያ ክፍል' የምትባል ትንሽዬ እልፍኝ እንደነበረች ነው” ይላሉ አቶ ፊሊክስ።  

በዚያች ክፍል ከኢትዮጵያ የመጡ ቁሳቁሶች ታጭቀውባትም ነበር። ልጅ ሳሉ እዛች ክፍል መግባት አይፈቀድላቸውም ነበር። አያታቸው ብቻ ነበሩ መግባት የሚችሉት።

ሁልጊዜም የምትቆለፈዋ ‹‹የኢትዮጵያ ክፍል›› ውስጥ ምን እንደሚቀመጥ ለማየት ከልጅነታቸው ጀምሮ ያደገ አንዳች ጉጉት ሳያድርባቸው አልቀረም መቼም።

ይህን የልጅነት ትውስታ ነግረውን ሲያበቁ አንድ ጊዜ ጠብቁኝ ብለው ምድር ቤት ወረዱ። ‘እርሳቸውም ቤት ውስጥ ‹‹የኢትዮጵያ ክፍል›› ትኖር ይሆን?’ ብለን ጠረጠርን።

የተለያዩ ቁሳቁሶችን ይዘው ተመለሱ። ጎራዴ ሁሉ አልቀራቸውም። በይበልጥ ትኩረታችንን የሳበችው ግን አንዲት የሊስትሮ ዕቃ የመሰለች ሳጥን ነበረች።

ከዐጤ ምንሊክ በሥጦታ ለኢልግ እንደተሰጡት የሚገመቱ ጎራዴዎች

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የተነሱ ፎቶግራፎች በአብዛኛው በዚህ ካሜራ የተነሱ ናቸው።

ከዐጤ ምንሊክ በሥጦታ ለኢልግ እንደተሰጡት የሚገመቱ ጎራዴዎች

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የተነሱ ፎቶግራፎች በአብዛኛው በዚህ ካሜራ የተነሱ ናቸው።

ዐጤ ምንሊክ ፎቶ የተነሱባት ካሜራ 'በሕይወት ተገኘች'

ፊሊክስ ከምድር ቤት ያመጧት ‹‹የሊስትሮ ሳጥኗ›› ቫርኒሽ ቀለም ሲኖራት ልክ እንደ ደም ግፊት መለኪያ ጭምቅ ጭምቅ የሚደረግ ፊኛ በገመድ ተያይዞላታል። በሳጥኗ መሀል ትንሽዬ የሌንስ መነጽርም ይታያል።

የሚገርመው ታዲያ ይቺ ምንሊክን ፎቶ ቀጭ ያደረገች ካሜራ ዛሬም ድረስ በጤና አለች።

አልፍሬድ የሞተው የዛሬ 103 ዓመት ግድም ነበር። ይቺ ጉደኛ ካሜራ ዛሬም መኖሯ መቼም ታዓምር ነው።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም መሥሪያ ቤት እንዴትም ብሎ ይቺን ምሥል መቅረጫ በጁ ቢያስገባት ልታስገባለት የምትችለው የአዱኛ መጠን ይህ ነው አይባልም መቼም።  አዱኛው ቀርቶ ታሪካዊነቷስ…? መቼም ንጉሡ በበጎም ይሁን በተቃራኒው በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ቦታቸው ጉልህ መሆኑ አይካድም። መቼስ የአሁኗ ኢትዮጵያን ያዋለዷት እርሳቸው መሆናቸው አሌ አይባልም።

በምጡ አስጨናቂነት ላይ ብርቱ ልዩነት ቢኖርም።

ለማንኛውም አቶ ፊሊክስን የካሜራዋን አጭር የሕይወት ታሪክ አስረዱን አልናቸው።

ሚስተር ፍሊክስ ድሮ ምንሊክን ፎቶ ያነሳው ካሜራ ዛሬም ፎቶ ማንሳት እንደሚችል ለቢቢሲ ዘጋቢ ሲያሳዩት።

ሚስተር ፍሊክስ ድሮ ምንሊክን ፎቶ ያነሳው ካሜራ ዛሬም ፎቶ ማንሳት እንደሚችል ለቢቢሲ ዘጋቢ ሲያሳዩት።

ሚስተር ፍሊክስ ድሮ ምንሊክን ፎቶ ያነሳው ካሜራ ዛሬም ፎቶ ማንሳት እንደሚችል ለቢቢሲ ዘጋቢ ሲያሳዩት።

አያታቸው አልፍሬድ ኢልግ ይህንን ካሜራ ኢትዮጵያ ይዘውት መሄዳቸውንና ብዙዎቹ ታሪካዊ ፎቶዎች፤ (ይህንን ዘለግ ያለ የጉዞ ማስታወሻን አጅበው የምትመለከቷቸውን ፎቶዎች ጨምሮ)፣ የተነሱትም በዚህ ካሜራ እንደነበር አስረዱን።

አጼ ምንሊክ በዚህ ካሜራ ይሆን እንዴ መጀመርያ ፎቶ የተነሱት?

ይህንኑ ጥያቄ ለአቶ ፊሊክስ ማንሳታችን አልቀረም። ግምታቸውን ብቻ ነገሩን።

“ይህ ካሜራ በአውሮፓ መመረት የተጀመረው በ1893 አካባቢ ነበር። ከተመረተ ከ2 ዓመት በኋላ በ1895 ነው አያቴ አልፍሬድ ኢልግ ከሚስቱ ፋኒ ጋቲከር ጋር ከስዊዝ ወደ ኢትዮጵያ ይዘውት የሄዱት። ይሄ ማለት አያቴ ለ2ኛ ጊዜ ወደ ኢትጵያ ሲሄዱ ማለት ነው።…”

ስለዚህ...?

“…ከዚህ በመነሳት ይህ ካሜራ በናንተ አገር የመጀመርያው ባይሆን እንኳ ምናልባት ከመጀመርያዎቹ አንዱ እንደሆነ መገመት እችላለሁ። ለጊዜው የማረጋግጥልህ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙዎቹ ቀደምት ፎቶዎች የተነሱት በዚህ ካሜራ እንደነበረ ነው…።” አሉ፤ ሚስተር ፊሊክስ

የአልፍሬድ ኢልግ የልጅ ልጅ አቶ ፊሊክስ ከሊስትሮ ሳጥኗ ሌላ እጅግ የሚያማምሩ ጎራዴዎችና ሌሎች በርካታ ቁሳቁሶችን አስጎበኙን።

እነዚህን ‹‹የምንሊክ ስጦታዎች›› አያታቸው አልፍሬድ ኢልግ በእርግጥም ከዐጤ ምንሊክ ስለመቀበላቸው እንዲያረጋግጡልኝም ጠይቄያቸው ነበር፣ ሚስተር ፊሊክስን።

‹‹ይህንን በቀጥታ መመለስ ይቸግረኛል።…›› ብለው ጀመሩ።

“… ጎራዴዎቹን ኢምፐረሩ እንደሰጡት መገመት ይቻላል።” ሲሉ የሞአንበሳ ምልክቶቹን በማሳየት  አብራሩልን።

ስለ ዐጤ ምንሊክ ያላቸውን መረዳት በጠየቅኳቸው ጊዜ ንጉሡ አገሩን ለማዘመን ጉጉ መሪ እንደነበረ እንደሚረዱና ለዚያም ሲል ከምንም በፊት ለእጅ ባለሞያዎች ጥሪ ማድረጉን አውስተው፣ አያታቸውም የዚህ ታሪክ አካል በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን አጭር ማብራሪያ ሰጡኝ።

የሚገርመው ይህ ‹‹የምንሊክ ካሜራ›› ዛሬም ድረስ ይሠራል። ይቺ ተአምረኛ የምሥል ሳጥን ዛሬም ፎቶ አንስታ፣ አጥባ ተኩሳ ታደርቃለች።

 “እንዲያውም በቅርቡ ይህንን ቤቴን ፎቶ አንስቼ አጥቤበታለሁ።” ብለውናል ሚስተር ፊሊክስ።

በዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም የሚገኙት 700 ቁሳቁሶች

ዛሬ ወይ ጉድ ስንል የምንደመምባቸው የድሮ የአዲስ አበባ ፎቶዎች አብዛኞቹ የኢልግ ነበሩ። አጼ ምንሊክ በዙፋናቸው ተቀምጠው፤ አጤ ምንሊክ ምንሽራቸውን ይዘው፤ አጤ ምንሊክ ሻሻቸውን ጠምጥመው፤ አጤ ምንሊክ ከጣይቱና ከዘውዲቱ ጋር እራት ሲበሉ፣ እነዚህ ታሪክ ነጋሪ ፎቶዎች በሙሉ የኢልግ ናቸው።

ብዙዎቹ ምሥሎች ዛሬም በዙሪክ የሰው እና የባሕል ጥናት ሙዝየም ተከማችተዋል። ሌሎች ቁሳቁሶችን ጨምሮ በድምሩ 700 ይሆናሉ።

በዚህ አልፍሬድ ኢልግ ባነሳው ታሪካዊ ፎቶ ላይ ንጉሥ ምንሊክ ከቤተሰባቸው ጋር ይታያሉ፡፡በስተግራ ልጃቸው ዘውዲቱ፣ መሀል ላይ ባለቤታቸው ጣይቱ ይታያሉ፡፡ @ዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

በዚህ አልፍሬድ ኢልግ ባነሳው ታሪካዊ ፎቶ ላይ ንጉሥ ምንሊክ ከቤተሰባቸው ጋር ይታያሉ፡፡በስተግራ ልጃቸው ዘውዲቱ፣ መሀል ላይ ባለቤታቸው ጣይቱ ይታያሉ፡፡ @ዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

ሙዝየሙ ለዚህ ጽሑፍ ብቻ እነዚህን ፎቶዎች እንድንጠቀምባቸው በውሰት ለቢቢሲ አማርኛ ሲያበረክት ሙዚየሙ ራሱ እነዚህም ምሥሎች ያገኘው ከኢልግ ቤተሰብ በውሰት መሆኑን ግልጦልናል። መጀመርያ በ1950ዎቹ፣ በኋላም በ90ዎቹ።

ከዚያ በኋላ ግን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠበቁ በሚል የኢልግ ቤተሰብ አብዛኛዎቹን ምሥሎችና ቁሳቁሶች በቋሚነት ለሙዚየሙ አስረክቧል።

ቢቢሲ በአልፍሬድ ኢልግ የልጅ ልጅ በሚስተር ፊሊክስ ቤት በነበረው ዘለግ ያለ ቆይታ ከሰነዘራቸው ጥያቄዎች መሀል አንዱ ምናልባት አያታቸው አልፍሬድ ኢልግ ስለ ዐጤ ምንሊክ ተናግሮት በቤተሰብ ሲወርድ ሲዋረድ የሰሙትና የሚያስታውሱትን ለየት ያለ ታሪክ ካለ ይህንኑ እንዲያጋሩት ነበር።

ሁለት ነገሮችን ብቻ ማስታወስ ችለዋል።

አንዱ የምንሊክ የመጀመርያው የፎቶ አጋጣሚን የሚተርክ ነበር።

“አያታችንን ኢልግን በአንድ ወቅት ኢምፐረሩ ተቆጡት። ‘በአንድ ሳጥን ውስጥ እያስገባህ በአፍጢሜ እየዘቀዘለቅክ አጓጉል ነገር የምታደርገን ለምን ይሆን? ይህስ የተገባ ነውን?...’ ሲሉ።

“…ኢልግ ክው ብሎ ቀረ፤ ነፍሱ መለስ ስትልለት ንጉሡን ስለ ሌንስ ጥበብ አስረዳቸው። ፎቷቸውን አጥቦና አስጥቶ ሰጣቸው።"

ንጉሥ ምንሊክም “እንዲያ ነው ነገሩ!” ብለው ስቀው አለፉት።

 ከዚያች አጋጣሚ በኋላም ሹማምንቱ ሁሉ በዚያች ሳጥን ውስጥ አስገብተህ አስወጣን እያሉ አያቴን ይለምኑት ጀመር።

አቶ ፍሊክስ ከአያታቸው የሰሙት 2ኛው ታሪክ ከስልክ መስመር ጋር የተገናኘ ነው።

እሪ በከንቱ ከሚገኘው የኢልግ ቤት እና በምንሊክ ቤት መሀል ስልክ ተዘርግቶ መሥራት ጀምሮ ነበር። ነጉሡ በስልክ ሲያወሩ የተመለከቱ የምንሊክ ሰዎች ታዲያ ንጉሣችንን ምን ነካብን? አእምሮው ታውኮ እሆን ሲሉ ተጨነቁ መባሉን ከአያቶቻቸው ሰምተዋል።

ቢትወደድ ኢልግ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበር?

ኢልግ ኢትዮጵያ በቆየባቸው 28 ዓመታት በተለይ የመጨረሻዎቹን ዓመታት ያሳለፈው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ነው የሚሉ ሰነዶች አሉ። ይህ አከራካሪ ነጥብ ነው።

ሹመቱ በቀጥታ “ውጭ ጉዳይ” የሚል እንደነበር የሚያሳይ ይፋ ሰነድ ግን አልተገኘም። መደበኛ የምኒስትርነት ሹመቱም የተጀመረው እርሱ ከአገር ከለቀቀ አፍታ በኋላ ነበር።

ሆኖም የሥራ ድርሻው በአመዛኙ እንዲያ የሚመስል  ነበር ማለት ይቻላል። በተለይም የራስ መኮንንን ሞት ተከትሎ በርካታ የውጭ ግንኙነት ሥራዎች በኢልግ በኩል ማለፍ ነበረባቸው።

የአድዋን ድል ተከትሎ አውሮጳዊያኑ ጥቁሩን ኢምፐረር ካላገኘን ሞተን እንገኛለን ማለትን አበዙ። ጃንሆይም ለማየት ቆንስላም ለመክፈት የማይቋምጥ አልነበረም። የኢምፐረሩን ደጅ ለመርገጥ ግን መጀመርያ የኢልግን እጅ መጨበጥ ነበረባቸው።

ኢልግ የምንሊክን ሙሉ እምነት ለማግኘት ሦስት ጉዳዮች ሳያግዙት አልቀረም።

አነዚህም፤ አማርኛን ጨምሮ በርካታ የቅኝ ገዢዎችን ቋንቋ አቀላጥፎ መናገር መቻሉ፣ ውግንናው ከኢምፔሪያሊስቶች ይልቅ ለምንሊክ መሆኑን፣ ይኸውም የውጫሌ ስምምነትን የትርጉም ፍልሰት ጭምር በማጋለጥ ማስመስከሩ፣ እንዲሁም የኢልግ አገር ሁልጊዜም በገለልተኝነት የምትታወቀው ስዊዘርላንድ መሆኗ ናቸው።

ኢልግ ጣሊያን በውጫሌ የተበተበችውን ሸር የተረዳው የኢትዮጵያ ፖስታ አባል ለማድረግ ሲሞክር ነው። አገሩ ስዊዘርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲዊ ግነኙነት እንድትጀምር ሲወተውት፣ እንዲሁም በርሊንን ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሲያግባባ ‹‹እስኪ ከሮም ጋር ተማክረን እንነግርኻለን›› ይሉታል።


ኢልግ የምንሊክን መታመም ተከትሎ ወደ ዙሪክ ከተመለሰ በኋላ የኖረበት ቤት @A. Moser, Zurich, ca 1910 (Private collection)

ኢልግ የምንሊክን መታመም ተከትሎ ወደ ዙሪክ ከተመለሰ በኋላ የኖረበት ቤት @A. Moser, Zurich, ca 1910 (Private collection)

ሮም ደግሞ በኢትዮጵያ ጉዳይ ምናገባትና ነው እንዲያ የምትሉኝ ሲል 'አልሰሜን ግባ በለው' ይሉታል። ለካንስ ለአውሮጳዊያን ጦቢያችን የጣሊያን ሞግዚት ሆና ነበር የምትታያቸው። ጊዜ ሳያጠፋ ይህንኑ ለንጉሡ ሪፖርት አደረገ…

ኢልግ በውጫሌው ስምምነት ላይ የነበረውን አውንታዊ ሚና ተከትሎ ከጦርነቱ በኋላ በኢትዮጵያና ጣሊያን የሰላም ስምምነት ያረቀቀው ሰው ነው።

የአውሮጳ ልኡካን ድሉን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ሲተሙ ተቀብሎ ያነጋግር የነበረው እርሱ ነው። ልኡካኑ ጀርመን ይናገሩ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ ይናገሩ ሌላ ከአፋቸው እየቀለበ ለንጉሡ ወደ አማርኛ የሚተረጉመው ኢልግ ነበር።

በ1905 ምንሊክ ደም ግፊት የሚመስል ነገር አጋጠማቸው። መታመማቸውን ተከትሎ ድንጋጤም ሥልጣን ሽኩቻም ሊከተል እንደሚች ኢልግ ተነበየ። የውጭ መንግሥታትም ጥርጣሬ ገባቸው። ኢምፐረሩ ከሞተ አካባቢው ላይ ለውጦች እንደሚኖሩ ጠብቀዋል።

እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ1906 አልፍሬድ ወደ አገሩ መመለስ ፈለገ። ምንሊክ ግን አሻፈረኝ አሉ። ‹‹ቶሎ እመለሳለሁ›› ብሎ አባብሏቸው ሄደ። ቃሉን ግን አልጠበቀም።

በንጉሡ ላይ መጠነኛ ቅያሜ እንደነበረው ይገመታል። በሁለት ምክንያት፤ አንዱ፣ ከምንሊክ ቤተመንግሥት የማይጠፉት አውሮጳዊያን እርሱን ከንጉሡ ጋር ለማጋጨት ወሬ አስወርተውበታል። ያ ሳያበሳጨው አልቀረም።

እርግጥ ነው ንጉሡን እጀግ ያከብራቸዋል። ፈረንጅ ሆኖ ለያውም የጣሊያኑ አንቶንሊ ወዳጅ ኾኖ ሳለ ጃንሆይን ለውጫሌ አሳልፎ አልሰጣቸው።

“ንጉሥ ሆይ! ይህ ስምምነት የጣሊያንን ትርጉሙ ተፋልሷል” ካሏቸው ሰዎች አንዱ እርሱ እንደነበር ጠቅሰናል። ጣሊኖች በዚህ አቂመውበታል፤ የአውሮጳ ልጅ ኾኖ እንዴት ለጥቁር ያደላል ሲሉ። እርሱ ግን በምንሊክና በአገር አንድነት ሸብረክ አላለም።

ኢልግ የምንሊክን መታመም ተከትሎ ወደ ዙሪክ ከተመለሰ በኋላ የኖረበት ቤት @A. Moser, Zurich, ca 1910 (Private collection)

ይሁንና እንዲያ ያሉ ነገሮች ስላበሳጫቸው ይመስላል ፈረንጆቹ ከአድዋ ድኅረ ጦርነት የሰላም ስምምነት ጋር በተያያዘ ከሮም ገንዘብ ተቀብሏል ሲሉ ያስወሩበት። ይህ አልሆን ሲላቸው ደግሞ ከባቡሩ ፕሮጀክት ብር ዘርፏል አስባሉበት። ኢልግ በመጨረሻ ከባቡሩ ጋር የተያያዘ ሥራውን ለቀቀ።

ወደ አገሩ ሄዶ በዙሪክ ፎርትራሼ ሰፈር ከቤተሰቡ ጋር ኖረ። ኖሮ ኖሮም ሞተ። የዛሬ 103 ዓመት፤ በ1916 ዓ.ም፤ በፈረንጆች።

ምዕራፍ ሁለት

አልፍሬድ ኢልግና እሪ በከንቱ

ኢልግ የኖረበት ቤት እሪ በከንቱ ውስጥ አለ፤ ዛሬም ድረስ ‹‹እሪ!›› እያለ። የደረሰለት ግን የለም።

ያለበት ይዞታ አሳፋሪ የሚባል ነው።

በኢልግና በምንሊክ ዙርያ ጥናት ያደረጉት ስዊዛዊው የሰውና የባህል አጥኚ ዶ/ር ፒተር ገርበርን የኢልግ ቤት አሁን ያለበትን ይዞታ ሲመለከቱ ምን እንደሚሰማቸው በደብዳቤ በጠየቅኳቸው ጊዜ "It’s a shame!" ብለው ነበር የጻፉልኝ።

እውነትም አሳፋሪ ነው።

የዚህ ሁሉ ባለታሪክ መኖርያ በካይሮ ቢሆን ኖሮ ሚሊዮን የግብጽ ፓውንድ ባ'መት ያስገባ ነበር። የኢልግ ቤት ናይሮቢ ቢሆን ኖሮ ሚሊዮን ሽልንግ ያስገኝ ነበር። የኢልግ ቤት ለታሪክ ደንታ በማትሰጠው አዲስ አበባ ውስጥ በመሆኑ በዓመት ዚሮ አምስት ሳንቲም አያስገባም።

ገቢው ቀርቶብን ታሪክ ባልኮነነን። ለተሸከመው ታሪክ ሲባል እንኳ በወግ ቢያዝ ምን ነበረበት?

ልጅ እያሱ ትምህርታቸውን መጀመርያ የተከታተሉት በኢልግ መኖርያ ቤት ነበር።

ልጅ እያሱ ትምህርታቸውን መጀመርያ የተከታተሉት በኢልግ መኖርያ ቤት ነበር።

ፈረንጅ የኖረበት ቤት ሁላ ታሪካዊ ነው ወይ የሚል አንባቢ አይጠፋም። ይህ አንድም የኢልግን አስተዋጽኦ ካለመረዳት፤ ሁለትም የዚህን ቤት ምንነት ካለማወቅ የሚነሳ ነው የሚሆነው።

የኢልግ ቤት እርሱ ወደ አገሩ ዙሪክ ከተመለሰ በኋላ በኢትዮጵያ የመጀመርያው ዘመናዊ ትምርት ቤት ኾኖ አገልግሏል።

አጤ ምነሊክ ወደ ካይሮ ጦማር ሰደው የኮፕቲክ ክርስቲያን ጥብቅ አማኝ የሆኑ ዘመናዊ አስተማሪዎችን ባጣዳፊ ላኩልን ባሉት መሠረት 3 ግብጣዊያን ወደ አዲሳባ መጡ። በኢልግ ቤትም ተቀመጡ።

እነርሱ እንዲመጡ የሆነው ዘመናዊ ትምህርት ከእምነት ያጣላል የሚለውን አይቀሬ ተቃውሞ ቀድሞ ለመከላከል ነበር።

ኢልግ እያለ ቤቱ የዲፕሎማቶች መናኻሪያ ነበር። ኢልግ ወደ አገሩ ሲሄድ ቤቱ የመኳንንቱና መሳፍንቱ ልጆች ማዋለ ሕጻናት ሆነ። ምናልባት ከቄስ ትምህት ቤት ውጭ ዘመናዊ ትምህርት የሚሰጥበት የመጀመርያው ቤት ይኸው የኢልግ ቤት ነበር።

በኋላ ኢትዮጵያን ለ44 ዓመታት የሚመሯት አባባ ጃንሆይ (ያን ጊዜ ልጅ ተፈሪ) እዚሁ ኢልግ ቤት ነበር የተማሩት። ልጅ እያሱስ ቢሆን ፊደል የቆጠረው የት ሆነና…?

ልጅ እያሱ ትምህርታቸውን መጀመርያ የተከታተሉት በኢልግ መኖርያ ቤት ነበር።

የአርከበ እቁባይ ውለታ

የአርከበ ስም ‘አርከበ’ አይደለም፤ ዮሐንስ እቁባይ ነው። አርከበ የተባሉት በአንድ የትግል አጋጣሚ ነው። የቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ ሻእቢያ ሳሕል ላይ ተከበበችና በደርግ ጦር ድባቅ ልትመታ ስትል ታጋይ ዮሐንስ እቁባይ ጦር አስከትሎ ከተፍ አለ። ድልም አደረገ።

 “አርከበ”-ደረሰ፤ ከተፍ አለ ማለት ነው። ታጋይ ዮሐንስ እቁባይ ከዚህ ዘመቻ ወዲህ አርከበ እቁባይ ሆነው ቀሩ።

በአመዛኙ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘንድ መልካም ስም የነበራቸው ከንቲባ አርከበ ታዲያ ለሻእቢያ ብቻ አይደለም የደረሱለት፤ ለአልፍሬድ ኢልግም ደርሰውለታል።

በኮንዶሚንየም ፍቅር የወደቀችው አዲስ አበባ ከዕለታት በአንዱ እሪ በከንቱን መጥረግ ጀመረች። ወደ ‘96 ዓ. ም መሆኑ ነው።

 ያን ዘመን ባዶ ቦታ ባዲሳባ ማየት ነውር ሆኖ ይታይ ነበር። ከ“ልማት” ውጭ ቋንቋ ያልነበረው ኢህአዴግ የከተማ ልማትን የሚተረጉመው በጣባቡ ነበር፤ በፎቅ ቁመናና ብዛት።

ሰማይ ያልጠቀሰ ግንባታ ሁሉ ድህነትን መታከክ አድርጎ የመመልከት አባዜ ነበር።

በዚህ ልማታዊ ስካር ልማትም ጥፋትም ታይቷል። አድዋ ድልድይ አካባቢ የአርበኛ ራስ አበበ አረጋይ ቤት በሌሊት ወድሟል።

በቅርቡ እንኳ ቡፌደላጋር ትቢያ ሆኖ ለአረቦች ተሽጧል። በራስ ካሳ ሰፈር 100 ዓመት ሊደፍን ጥቂት የቀረው የደጃዝማች አምዴ አበራ ቤት አፈር በልቷል። እነ ሼክ ሆጄለም ‘ጃስ’ ተብለው ነበር።

በዚህ የተንሸዋረረ የልማት ስካር መሀል የኢልግ ቤት አፈር በልቶ ነበር፣ ለጥቂት።

ይሄ እሪ በከንቱ የሚገኘው የአልፍሬድ መኖርያ ትቢያ ሊሆን ሲል አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስና ጓደኞቻቸው ቀድመው እሪ አሉ። ፖለቲካዊ ሥልጣኑ በእጃቸው አልነበረም። የሚችሉት ‘እሪ’ ብሎ መጮኽ ብቻ ነበር። አደረጉትም።

እንደ ዕድል ሆኖ እነ አቶ ፋሲል ለአርከበ የሚቀርብ ወዳጅ ያውቁ ነበር። ደውለው እባክህን ድረስልን አሉት። ሰውየው ከንቲባ አርከበ ጋር ደውሎ  እባክዎ ክቡር ከንቲባ ይድረሱልን አላቸው፤ ደረሱለት።

በግቢው የነበሩ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ባይተርፉም፤ የዓሣ ርባታ ገንዳና ተጨማሪ እልፍኞቹ ባይተርፉም፤ ዋናው ቤት ግን ተረፈ። አርከበም ታሪክ ሠሩ።

"በነገርህ ላይ ዕድለኞች ነን፤ አንድ ሁለት ቀን ዘግይተን ቢሆን ኖሮ’ኮ ያን ታሪካዊ ቤት እናጣው ነበር" ይላሉ አርክቴክቱ ፋሲል፤ አጋጣሚውን ሲያስታውሱ።

የአልፍሬድ ኢልግ አራት ልጆች መሀል ሴት ልጁ ፋኒ ኢልግ በጋሪ ተጭና፣ ምንሊክ የተባለው ወንድ ልጁ እና ከወንድሙ ጋር "እሪ በከንቱ" ቤታቸው ግቢ ቆመው ይታያሉ።@ዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

በእሪ በከንቱ ኮንዶሚንየም መሀል ተጎሳቁሎ የሚገኘው የኢልግ ቤት የአሁን ገጽታ።

የአልፍሬድ ኢልግ አራት ልጆች መሀል ሴት ልጁ ፋኒ ኢልግ በጋሪ ተጭና፣ ምንሊክ የተባለው ወንድ ልጁ እና ከወንድሙ ጋር "እሪ በከንቱ" ቤታቸው ግቢ ቆመው ይታያሉ።@ዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

በእሪ በከንቱ ኮንዶሚንየም መሀል ተጎሳቁሎ የሚገኘው የኢልግ ቤት የአሁን ገጽታ።

"ደግሞ የአንድ ፈረንጅ ቤት…ፈረሰ አልፈረሰ…?"

የኢልግ የልጅ ልጆች እነ ፊሊክስ በቅርብ ዓመታት የአያታቸውን አገር፤ የምንሊክን አገር፤ የቢትወደድ ኢልግን አገር ለመጎብኘት አዲስ አበባ መጥተው ነበር። "ደማቅ አቀባበል ተደርጎልን ደስ ብሎን፣ በባለሥልጣናት እራት ተጋብዘን ነው የተመለስነው" አሉኝ።

"የአያታችሁ ቤት ግን ሄዳችሁ አያችሁት…?"  አልኳቸው።

"አዎ ሄደን ነበር፤ ሆኖም ከውጭ ብቻ አይተነው ነው የተመለስነው" አሉኝ።

ውስጥ ለምን አልገባችሁም? አልኳቸው።

"አንድ ቤተሰብ እየኖረበት ነው፤ እነሱን መረበሽ አስፈላጊ ስላልመሰለን ከውጭ ተመለስን" አሉኝ።

የአያታችሁ ቤት ውስጥ ግለሰብ እየኖረበት እንደሆነ ስትመለከቱ ቅሬታ አልፈጠረባችሁም? አልኳቸው።

"በፍጹም አልፈጠረብንም። ቤቱ ሰው እንዲኖርበት አይደለም እንዴ የተሠራው?" አሉኝ።

"አሁን ያለበትን ይዞታ ስታዩት ማለቴ ነበር..ደክርቷል'ኮ....

ስስ ቅሬታ እንዳደረባቸው በማይሸሽግ ፈገግታ፣ "...እንግዲህ መንግሥታችሁ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሌሎች ነገሮች ይኖሩታል ብለን እንገምታለን። እኛ የአያታችን ቤት ስለሆነ ብቻ እንዲህ ይሁን እንዲያ ይሁን ልንል አንችልም…" የሚል አስተያየት ሰጡኝ።

በዚሁ ጉዳይ ጎምቱውን አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስን ባወጋኋቸው ጊዜ እጅግ ተገርመው እንዲህ አሉ፡

“ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ አንድ የሚለው ነገር አለ፤ ሁልጊዜም የሚማርከኝ አባባል ነው፤ 'ኢትዮጵያዊያን ለታሪካችን ክብር አለን እንላለን። ስለታሪካችን ማውራትም እንወዳለን። ታሪካችንን በአካል መመስከር ለሚችል ‹‹ሊቪንግ ፕሩፍ›› ግን እምብዛም ግድ የለንም...”

“...የኢልግን ቤት ስናይ በዘመኑ የነበረውን የቤት አሠራር፣ አስተሳሰብ፣ ያን ጊዜ የደረሱበትን፤ ከየት እንደተነሳን እናያለን፤ ከዚያ ባሻገር ደግሞ ለኢትዮጵያ ጥልቅ ፍቅር የነበረውን አልፍሬድ ኢልግን ያስታውሰናል።...” ካሉ በኋላ፣ ‹‹በአንድ አገር የመጀመርያውን ዘመናዊ ትምህርት ቤት እንዴት እናፍርስ ይባላል።  ይሄን ማጥፋት በራሳችን ታሪክ ላይ ሞት መፍረድ አይደለም?" ይላሉ።

የኢልግ ቤት ዛሬም ይህን ግዙፍ ታሪክ እንደተሸከመ ጎብጧል። ተስፋ ይኖረው ይሆን?

ከመፍረስ መትረፉም አንድ ነገር ነው። አቶ አርከበ ባይደርሱለት ይሄን ጊዜ በ5ሺ ብር የሚከራይ ባለሦስት መኝታ ኮንዶምንየም ኾኖ ነበር።

‹‹ሦስት መኝታ ኮንዶምንየም እኮ የትም ልንሠራ እንችላለን። የኢልግን ቤት ካጣነው ግን በምንም አንተካውም። የንዋይ ግምት እንኳ የለውም'ኮ።” ይላሉ፣ አቶ ፋሲል፤ የዚህ አገር ሁኔታ እንዲያው ግርም እያላቸው።

የኢልግን ቤት ማን ነው የሚኖርበት?

የኢልግ ቤት አልፍሬድ ከሄደ በኋላ ትምህርት ቤት ሆነ ብለናል። ከዚያ ወዲያ ግን ዕድሜ ዘመኑን ሲንገላታ ነው የኖረው።

ለመሆኑ ለብዙ ዓመታት የዐጤ ምንሊክ ቀኝ እጅ የነበረን ሰው መኖርያ ቤት፣ ላለፉት 40 ዓመታትን ማን አደረበት ስንል ጠየቅን።

አቶ አብነት ገዛኸኝ ከሉንዱ ዩኒቨርስቲ ጋር ተሻርከው ከ9 ዓመት በፊት ያሳተሙት አንድ ጥናት በበይነመረብ አሰሳ መሀል ድንገት እጃችን ገባ።

የጥናት ወረቀቱ በግርድፉ ያን ጊዜ የነበረችውን አዲስ አበባን ያስረዳል።

አራዳ በምንሊክ ጊዜ ገበያ ናት። የቤተ መንግሥቱ ግቢ ደግሞ ፊት በር ከፍታው ላይ ነው ያለው። ሌላው ቦታ እምብዛምም ሰፋሪ አልነበረበትም። ገበያውና ቤተመንግሥቱ የሚያገናኘው  ዋና መንገድ ታዲያ የእሪ በከንቱ መንገድ ነበር።

ያ መንገድ የመጀመርያው ፒስታ መንገድ ሳይሆን አይቀርም፤ ባ’ዲ’ሳባ።

የኢልግ ቤትም በአራዳና በቤተመንግሥቱ መሀል መገኘቱ ልዩ ያደርገዋል።

ያን ጊዜ የአልፍሬድ ቤት የአውሮፓ ቀለም ነበረው። የአሳ መራቢያ ገንዳ፣ እሳት ማሞቅያ ያለው ሳሎን እና እንቁላል ቅርጽ ያለው ሰፊ በረንዳ።

ራሱ ነው ደግሞ ንድፉንም ግንባታውንም የመራው። ከዋናው ቤት አጠገብ እልፍኞች ነበሩት። ለአገልጋዮቹ መኖርያ ባር ነበረው።

መጀመርያ አልፍሬድ በኋላም ባለቤቱ ፋኒ በዚህ ቤት ወልደው ከብደዋል። ከ4ቱ ልጆቻቸው መሀል ምንሊክና ፍሊክስ የተወለዱት እዚህ ቤት ነው። ቦርቀውበታል።

በዛሬዋ ኤርትራ የተወለዱት ሎሬንዞ ትዕዛዝ (ብላቴን ጌታ) ዕውቅ ዲፕሎማት ነበሩ።@ጌቲኢሜጅስ

ኢልግ ወደ አገሩ ሲሄድ ግን ቤቱ የነ ልጅ እያሱ ትምህርት ቤት ሆነ። ዋናው ምንሊክ ትምህርት ቤት ሲከፈት ደግሞ የአጼ ኃይለሥላሴ አማካሪ፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ዲፕሎማትና ለአጭር ጊዜም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረቱ ሎሬንዞ ትእዛዝ (ብላቴን ጌታ) ገቡበት።

በጣሊያኑ የ5 ዓመት ቆይታ ደግሞ ጄኔራሎች ተፈራረቁበት። ከዚያ ብላቴን ጌታ ህሩይ ኖሩበት።

በመጨረሻም ይህን ቤት ደርግ ሲወርሰው ቀይ ባሕር ሆቴል ተባለ። የሆቴሌ ባለቤትም እዚያው ይኖር ነበር። ከዚያ ጀምሮ ኪራይ ቤቶች ወሰደው።

በ96 ዓ.ም በኮንዶሚንየም ግንባታ ምክንያት ከፊሉ ሲፈርስ እና ዐይነ ግቡ ያልሆነው ቢጫው የጋራ መኖርያ ሲደነቀርበት የኢልግ ቤት የነበረው የዕይታ አቀማመጥ ጭራሽ ውበቱን አጣ። ወዙም ነጠፈ፤ የአሳ ገንዳውም ፈረሰ።

ኾኖም የኢልግ ቤት አዘመመ እንጂ አልወደቀም። ጣር ላይ ነው እንጂ አላሸለበም…።

‹‹የአርትስ ሬዚደንስ›› ተደርጎ አዲስ አበባን ለሚጽፏት፣ ለሚሥሏት፣ ለሚቀኙባት እንደ ጋለሪም፣ እንደ ታሪክ መሰነጃም  ቢሆን ብሎ ‹‹ቲኬ አማካሪዎች›› ከአራዳ ሬኔሳንስ ማህበር ጋር በመተባበር ጥናት ሠርቶ ነበር። የዛሬ 9 ዓመት። ሆኖም አልተሳካለትም።

ይህ ማስታወሻ ለኅትመት በሚሰናዳበት ወቅት አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ‹‹ተስፋ አለ›› የሚል መረጃን አቀበሉኝ።

‹‹ሄሪቴጅ ዎች›› የሚባል ልዕልት አስቴር የሚመሩት ድርጅት አንድ ነገር ለማሳካት እየሞከረ ነው። ይህንን ታሪካዊ ቤት ለማደስ፣ ጋለሪ ለመክፈት፣ ብሎም ለታሪክ ለማቆየት።


በዛሬዋ ኤርትራ የተወለዱት ሎሬንዞ ትዕዛዝ (ብላቴን ጌታ) ዕውቅ ዲፕሎማት ነበሩ።@ጌቲኢሜጅስ

በዛሬዋ ኤርትራ የተወለዱት ሎሬንዞ ትዕዛዝ (ብላቴን ጌታ) ዕውቅ ዲፕሎማት ነበሩ።@ጌቲኢሜጅስ

የዐጤ ምንሊክ ‘ዙ’ በስዊዘርላንድ

ዐጤ ምንሊክ ከአገር አልወጡም፤ ስምና ዝናቸው ግን ባ'ለም ናኝቷል፤ በተለይ ጣሊያንን ድል ካደረጉ ወዲህ።

ያገሬው ነዋሪ ያሬድ ኃይለሥላሴ፣ ኢልግ የተማረበትን ኮሌጅ፣ የኢልግ አጽም የኖረበትን መካነ መቃብር አዟዙሮ ካስጎበኘን በኋላ እንዲህ አለ…

‹‹የዚች ከተማ ትልቁ "ዙ" ለመከፈቱ የዐጤ ምንሊክ  እጅ እንዳለበት ታውቃላችሁ?››

 አላመንነውም ነበር። ይዞን ሄደ። 

እጅግ ሰፊ የኾነው ይህ የዙሪክ መካነ እንሰሳት ወ አራዊት (ዙ) ሥራ አስኪጅ ስማቸው ሚስተር አሌክስ ሩብል ይባላል። ከምንሊክ አገር መምጣታችንን ብንነግራቸው ጊዜ ተነስተው ተቀበሉን። ቢሯቸውን ቆልፈው ራሳቸው ያስጎበኙን ጀመር።

ይህ ቦታ በሰሜን ተራሮች የተሰየመ ራሱን የቻለ ጥግ አለው። ሚስተር አሌክስ ሩብልን ይህ መካነ እንሰሳት-ወ-አራዊት እንዴት እንደተከፈተ ከያሬድ የሰማነውን ለማረጋገጥ ጠየቅናቸው።

ለመከፈቱ ዐጤ ምንሊክ በአጋጣሚ ምክንያት የሆኑት የዙሪክ የእንሰሳት መጠበቂያ (ዙ) የቀድሞ ገጽታ @ ጌቲ ኢሜጅስ

ለመከፈቱ ዐጤ ምንሊክ በአጋጣሚ ምክንያት የሆኑት የዙሪክ የእንሰሳት መጠበቂያ (ዙ) የቀድሞ ገጽታ @ ጌቲ ኢሜጅስ

"… ምንሊክ የተባለ የኢትዮያ ንጉሥ አልፍሬድ ለተባለ ስዊዛዊ አማካሪያቸው ትንንሽ የአንበሳ ደቦል ሰጥተውት ነበር፤ እዚህ ይዟቸው ሲመጣ ዙሪክ ያን ጊዜ የእንሳት ማቆያ ቦታ አልነበረም። ያኔ በስዊዘርላንድ የእንሰሳት ማቆያ የነበረው ባዜል ከተማ ብቻ ነበር።

ከባዜል ከተማ ጋር ደግሞ ዙሪክ የተፎካካሪነት ስሜት ነበረባት። በነዚህ ምንሊክ በላኳቸው ግልገል አንበሶች ምክንያት ታዲያ ለዚች ከተማ እንሰሳት መጠበቂያ ያሻል በሚል ውይይት ተጀመረ። ቆይቶ ይህ የምታዩት የእንሰሳት ማቆያ ማዕከል ተከፈተ ….።

የኢልግን ልብ የሰበረው "ሰባራ ባቡር"

ስለ ኢልግ የባጥ የቆጡን አውርተን ባቡሩን ሳናነሳ…?! ይኼ ነውር ነው።

እርግጥ ነው ሰባራ ባቡርን ከኢልግ የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም፤ የሰባራ ባቡር ታሪክ በአመዛኙ የአርመኑ ነጋዴ የሙሴ ሰርኪስ ታሪክ ነው። ጠቅላላ ስሜቱ ግን ኢልግን ይወክላል።

"ባቡሩ ሰገረ ስልኩም ተናገረ

ምንሊክ መልአክ ነው ልቤ ጠረጠረ"

  …ተብሎ ገና ሳይገጠም ኢልግ አንድ ትልቅ ሕልም ነበረው፤ ባቡር ማዘርጋት።

ኢልግ የቱርጋው ልጅ ገና ትንሽ ሳለ ባቡር መመልከቱን ገና ድሮ አውስተናል። ባቡር ያስፈነጥዘዋል። ሼ ከተፍ ሲል ልቡ ይመታል።

እና ካደገ በኋላም ይሄ አባዜው አለቀቀው ይሆናል። ለዚህም ይሆናል…ኢልግ በኢትዮጵያ ባቡርን ለማየት የተጋውን ያህል ሌላ ለምንም ነገር አልተጋም የሚባለው።

ባጭር አነጋገር፣ የዚያ ዘመን የምንሊክና የኢልግ ‹‹የሕዳሴው ግድብ›› ፕሮጀክታቸው ባቡሩ ነበር ማለት ይቻላል።

ከብዙ ንግግሮች በኋላ ምንሊክ በደብዳቤ ፈቀዱለት። ከፈረንሳዮች ጋር ኢትዮጵያን ወክሎ መደራደር እንዲችል የሚፈቅድ ደብዳቤ ተሰራጨ።

''መንገድ ካልተሠራ አገር እንደማይቀና ስለገባኝ የጢስ ሰረገላ ማስገባት ስለፈለግኩኝ…በአገሬ ንግድና ጥበብ ለማስፋፋት የሚተጋውን ሙሴ አልፍሬድ ኢልግን በዚህ ደብዳቤ ወክዬዋለሁ… ''

ይህ ንጉሥ ምንሊክ አንፋሮ አድርገው የሚታዩበት ፎቶ የተነሱት ከአድዋ ድል ማግስት ነው፡፡ እ.አ.አ በ1896 ዓ. ም @ዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

ይህ ንጉሥ ምንሊክ አንፋሮ አድርገው የሚታዩበት ፎቶ የተነሱት ከአድዋ ድል ማግስት ነው፡፡ እ.አ.አ በ1896 ዓ. ም @ዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

በባአታ ቤተክርስቲያን  ምድር ቤት የሚገኘው የምንሊክ መቃብር፣ በግራ የእቴጌ ጣይቱ በቀኝ የንግሥት ዘውዲቱ። @ጌቲ ኢሜጅስ

በባአታ ቤተክርስቲያን  ምድር ቤት የሚገኘው የምንሊክ መቃብር፣ በግራ የእቴጌ ጣይቱ በቀኝ የንግሥት ዘውዲቱ። @ጌቲ ኢሜጅስ

ዐጤውን አላሳፈራቸውም፤ በፖሪስ ቅርንጫፍ ቢሮ ከፈተ። እጅግ እልህ አስጨራሽ ድርድር አደረገ፤ ከፈረንሳይ፣ ከጣሊያን፣ ከእንግሊዝ ጋር።

ይህ ንጉሥ ምንሊክ አንፋሮ አድርገው የሚታዩበት ፎቶ የተነሱት ከአድዋ ድል ማግስት ነው፡፡ እ.አ.አ በ1896 ዓ. ም @ዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

እርግጥ ነው ምንሊክ ባቡሩን ወደውታል፤ ነገር ግን ፈርተውታል። ቅኝ ገዢዎችን ደጃቸው ድረስ አሳፍሮ  እንዳይመጣባቸው ነው ስጋታቸው።

ድንበሩንስ በወታደር ያስጠብቁታል። ባቡሩን እንዴት አድርገው። እርሳቸው ከባቡሩ ጋር የነበራቸው "ጠሌ-ፍቅር" ነበር የሚባለውም ለዚያ ነው። "Love-hate relationship" እንዲል ፈረንጅ።

ፈረንሳዮቹ ከተስማሙ በኋላ ፕሮጀክቱ ተንቀረፈፈ። ከጅቡቲ ለገሃር ይመጣል የተባለው ገና ጂቡቲም አልደረሰ።

ፈረንሳይ ፍራንኳን ከሰከሰች፤ የጉልበት ሠራተኞቹን ውሃ ጥም አቃጠላቸው። የሀዲዱን ብረት የሚሸከመው አግድሞሽ እንጨት ምስጥ ገዘገዘው።

ፕሮጀክቱ ጠላት በዛበት። ከ6 ዓመታት አበሳ በኋላ "ባቡሬ ፈጥኖ ገባ ድሬ" ተባለ። ከድሬ አዲስ አበባ ለመድረስ ግን ሌላ 15 ዓመታትን ያሻ ነበር።

ኢልግና ምንሊክ አምጠው የወለዱት ባቡር ለገሐር ሲደርስ ሁለቱም አፈር በልተዋል።  ምንሊክ በባእታ፣ ኢልግ በዙሪክ ፍሪድሆፍ ኢንተንቡል መካነ ቀብር።

በባአታ ቤተክርስቲያን  ምድር ቤት የሚገኘው የምንሊክ መቃብር፣ በግራ የእቴጌ ጣይቱ በቀኝ የንግሥት ዘውዲቱ። @ጌቲ ኢሜጅስ

ኖሮ ኖሮ ሞተ

‹‹ይሄ ንጉሥ እንደ አባት የምወደው ሰው ይመስላል። ምናልባት ለእሱ ስል ጥቂት ዓመታት እዚህ አገር እቆይ ይሆናል…›› ብሎ ነበር ኢልግ፤ ያኔ ገና አንኮበረን እንደረገጠ፤ በ1887…።

ሆኖም የምንሊክ ፍቅር አኖህልሎ አኖህልሎ ለድፍን 28 ዓመት አቆየው።

አባቴ የሚላቸውን የጃንሆይን መታመም ተከትሎ ግን ከኢትዮጵያ ወጣ፤ ዙሪክ እንደ 4ኪሎ አልተስማማችውም።

 በ1913 ሳምባ ምች መታው። በዚያኑ ዓመት የሚወዳቸው ሆኖም የተቀየማቸው፣ አባቴ የሚላቸው የንጉሥ ምንሊክ የሞት ዜና በይፋ ደረሰው። ልክ የዛሬ 106 ዓመት መኾኑ ነው።

ከሦስት ዓመት በኋላ በወርሃ ጥር፣ በጎርጎሮሲያዊያኑ 1916 ቢትወደድ አልፍሬድ ኢልግ አባቴ የሚላቸው ዐጤ ምንሊክ ወደ ሄዱበት ሄደ! ወደማይቀርበት።መሐመድ ሰልማን

ምሥሎች
ዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም

@Ethnographic Museum at the University of Zurich, Alfred Ilg collection

ተጨማሪ ምሥሎች
ጌቲ ኢሜጅስ
ቢቢሲ አማርኛ

አርትኦት
አሻግሬ ኃይሉ

Short Hand:- ጅባት ታምራት