Got a TV Licence?

You need one to watch live TV on any channel or device, and BBC programmes on iPlayer. It’s the law.

Find out more
I don’t have a TV Licence.

ቀጥታ ዘገባ

የተጠቀሱት ሰዓቶቸ የዩናይትድ ኪንግደም ናቸዉ

 1. ለሶስት ወር ያህል በቤት ውስጥ ዘግተው ከተቀመጡ የዉሃን ነዋሪዎች ምን እንማራለን?

  Video content

  Video caption: ሦስት ወራትን ዝግ ሆና የቆየችው ውሃን ከተማ ነዋሪዎች ምን ይላሉ?
 2. ማክዶናልድስ በቻይና አፍሪካውያንን ይቅርታ ጠየቀ

  ማክዶናልድስ ማስታወቂያው መውጠዓቱን እንዳወቀ ምግብ ቤቱን መዝጋቱን አስታውቋል

  በቻይናዋ የኢንዱስትሪ ከተማ ጓንዡ ውስጥ የሚገኝ አንድ የማክዶናልድስ ቅርንጫፍ ምግብ ቤት አፍሪካዊያን ገብተው እንዳይጠቀሙ በመከልከሉ ድርጅቱ ይቅርታ ጠየቀ።

  ጥቁሮች ወደ ምግብ ቤቱ መግባት እንደማይችሉ የሚያመለክት ማስታወቂያን ተለጥፎ የሚያሳይ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ በስፋት ሲሰራጭ ታይቷል።

  በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምግብ ቤቶችን የሚያስተዳድረው ማክዶናልድስ ቻይና ውስጥ በሚገኘው ቅርንጫፉ በኩል ስለተለጠፈውን የክልከላ ማስታወቂያ እንዳወቀ ምግብ ቤቱን ለጊዜው እንዲዘጋ ማድረጉን አሳውቋል ቻይና ውስጥ ጥቁሮች እንዳይገቡ የከለከለው ምግብ ቤት ይቀርታ ጠየቀ

 3. በህንድ የኮሮና ህግን ተላልፈው የወጡ ስደተኞችን ፖሊስ በኃይል በተነ

  በህንድ የነበረው ሰልፍ

  በህንዷ ግዛት ሙምባይ የኮሮናን ህግ ተላልፈው የወጡ ስደተኛ ሰራተኞችን ፖሊስ በኃይል መበተኑ ተዘግቧል።

  ሰራተኞቹ አስገዳጁ ቤት የመቀመጥ ውሳኔ በዛሬው እለት ይነሳል የሚል ሃሳብ ስለነበራቸው ነው ወደየቤታቸው ለመሄድ በባቡር ጣቢያ እንደተገኙ የአገር ውስጥ ሚኒስትር አኒል ዴሽሙክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

  ምንም እንኳን በመጀመሪያው ቤት የመቀመጥ ውሳኔ በነገው እለት ያበቃል ተብሎ የተወሰነ ቢሆንም በዛሬው እለት ለተጨማሪ ሶስት ሳምንት መራዘሙን የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ አስታውቀዋል።

  ነገር ግን የተቃዋሚ ኃይሎች በበኩላቸው እነዚህ ሰልፈኞች የተሰበሰቡት ምግብና ስራ በማጣታቸው ነው ብለዋል። አብዛኛዎቹ ሰራተኞች በቀን በሚከፈላቸው የሚተዳደሩ ሲሆን ቤት የመቀመጥ ውሳኔውን ተከትሎ ምንም አይነት ገቢ እንዳያገኙ ሆነዋል ብለዋል።

  በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ከሙምባይና ደልሂ ተነስተው ወደመጡባቸው መንደሮች በእግራቸው መጓዝ ጀምረዋል።

  ነገር ግን ጉዞ ያልጀመሩት የከተሞችና የተለያዩ ግዛቶች ድንበር መዘጋትን ተከትሎ መውጫ አጥተው አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

  በዛሬው እለት በስደተኞችና በቀን ሰራተኞች እንዲሁም በፖሊስ መካከል የተፈጠረው ግብግብ በአገሪቷ ውስጥ ሁለተኛው ግጭት የተሞላበት ክስተት ነው ተብሏል።

  ከጥቂት ቀናት በፊት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኛ ሰራተኞች ሱራት በምትባል ግዛት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው የነበረ ሲሆን በርካታ ሱቆችም ተቃጥለዋል።

  View more on twitter
 4. ኡጋንዳ ድንበር የመዝጋትና የሰአት እላፊ አዋጇን አራዘመች

  ጉልት ቸርቻሪ ሴትዮ

  የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የኮሮናቫይረስ መዛመትን ለመግታት የወሰዷቸው እርምጃዎች ለ21 ተጨማሪ ቀናት እንዲራዘሙ ውሳኔ አሳልፈዋል።

  አገሪቷ ህዝባዊ እንቅስቃሴ መገደብን ጨምሮ ሌሎች ውሳኔዎችን ካሳለፈች አስራ አራት ቀናትን ያስቆጠረች ሲሆን፤ እነዚህ እርምጃዎችም ይቀጥላሉ ተብሏል።

  ከእርምጃዎቹ መካከል ኡጋንዳን የሚያዋስኑ ድንበሮችን ጨምሮ ኢንተቤ አለም አቀፍ አየር ማረፊያን መዝጋት፣ ከምሽት ጀምሮ እስከ ጥዋት ያለ የሰአት እላፊና ህዝባዊ ትራንስፖርቶች እንዲቆሙ ማድረግ ይገኙበታል።

  በተራዘሙት ሶስት ሳምንታትም የጤና ባለሙያዎች ሁኔታውን እንዲገመግሙ እንዲሁም አገሪቷ አስገዳጁን የለይቶ ማቆያ ከመጀመሯ በፊት ከውጭ አገራት የገቡ 18ሺ መንገደኞችን የመቆጣጠር ስራ እንደሚሰራ ተነግሯል።

  በአየርም ሆነ በመኪና የሚገቡ ጭነቶች ወደ አገር ውስጥ የመግባት ፈቃድ አላቸው።

  በኡጋንዳ ውስጥ 5ሺ 600 ሰዎች ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 54ቱ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፤ ስምንቱም አገግመዋል።

 5. ከኮሮና ህመም ያገገመችው ደቡብ አፍሪካዊት የጥላቻ ንግግሮችን አስተናግጃለሁ ትላለች

  የህክምና ባለሙያዎች በደቡብ አፍሪካ

  አለም አቀፉ የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ያለባቸውን ሰዎች ማግለልም ሆነ መድልዎ መፈፀም ከቫይረሱ በላይ ጎጅ ነው በሚል አስጠንቅቆ ነበር።

  በደቡብ አፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ተደራራቢ ችግሮችን በማስተናገድ ላይ ናቸው። ከህመሙ ጋር ያለ ትግል እንዲሁም በማህበረሰቡ የሚደርስባቸውን ጥቃትም እያስተናገዱ ነው።

  ስሟን መግለፅ ያልፈለገች አንዲት የኮሮና ቫይረስ ታማሚ የደረሰባትን መገለል ለቢቢሲ ጋዜጠኛ አጋርታለች።

  "የባለድርሻ አካላት አንድ ስብሰባ ነበር። ኮሮና ቫይረስ መያዜን ጠቅሸ ስብሰባው ላይ መገኘት እንደማልችል አንድ ኢሜይል ላኩኝ። እንዲህ ጉዳዩ እንደ እሳተ ገሞራ ይፈነዳል ብዬ አላሰብኩም"

  "ጥላቻ የተሞላባቸው መልእክቶች ደረሱኝ። ያለፈቃዴም ኮሮና መታመሜ መገለፅ ጀመረ፤ በዚህም መሰረታዊ የሚባል የመብት ጥሰት ደርሶብኛል"

  የምትለው ይህቺ ግለሰብ ጎረቤቶቿም ትበክለናለች በማለት መፍራት ብቻ ሳይሆን ማግለል ጀመሩ። ከዚያም ፖሊስ እንዲሁም አምቡላንስ ጠሩ።

  ይህንን ሁሉ በማየት ደቡብ አፍሪካውያንን ትማፀናለች።

  "በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች የበለጠ ተጠቂ መሆን የለባቸውም። ሰውነታችን ውስጥ ያለው የመቋቋም ሁኔታ በቫይረሱ ተዳክሟል። እናም ከዚህ በላይ መጨናነቅ አያስፈልገንም። ጭንቀት በራሱ የሰውነትን የመቋቋም ኃይል ስለሚያዳክም። ጊዜው አሁን የአንድነት፣ የደግነት፣ የጥሩነት፣ የመተሳሰብና የመረዳዳት መንፈስ ሊጎለብት የሚያስፈልግበት ወቅት ነው። ይህንን ማድረግ ስንችል ነው ኮሮናንም ማሸነፍ የምንችለው" ብላለች።

  የጤና ባለሙያዎችም መገለልና መድልዎ ሰዎች ከመመርመር ሊያግዳቸው እንደሚችልም በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።

  "አሁን ዋነኛ ችግራችን ሰዎች ከቫይረሱ ይልቅ ሊደርስባቸው የሚችለውን መገለል መፍራት ጀምረዋል። በዚህ አይነት አያያዝም ምልክቱ ቢታይባቸውም ላይመረመሩ ይችላሉ። ጉዳዩን የበለጠ አስፈሪ ያደርገዋል" በማለት ሲቡሌሌ ኩዋግዋና የተባለች የስነ ልቦና ባለሙያ አስረድታለች።

  አክላም " ተመርምረው ቫይረሱ ቢገኝባቸውም ያለውን መገለል በመፍራት ላይናገሩ ይችላሉ። ይህ ከፍተኛ ችግር ነው። ምክንያቱም ኮሮናን ለመታገል ዋነኛውና ዋነኛው ጉዳይ ምርመራ ነው"

 6. በዩናይትድ ኪንግደም በኮቪድ-19 ምከንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 12ሺህ አለፈ

  የጤና ባለሙያዎች ወደ አምቡላንስ ሕሙማንን ሲያስገቡ

  በዩናይትድ ኪንግደም ሆስፒታሎች ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምከንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 12ሺህ107 መድረሱን የጤና ባለስልጣናት አስታወቁ።

  በዩናይትድ ኪንግደም በአጠቃላይ 93 ሺህ 873 ሰዎች የኮቪድ-19 ተገኝቶባቸዋል።

  በአሁኑ ሰዓት በእንግሊዝና ዌልስ ከሚከሰቱ አምስት ሞቶች ከአንድ በላይ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ነው ተብሏል።

  በተያያዘ ዜና ዩናይትድ ኪንግደም በሰኔ ወር ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ውድቀት ይገጥማታል ተብሎ ተተንብይዋል።

  ይህ ትንበያ የተሰራው በአሁኑ ሰዓት የተጣለው ቤት የመቀመጥ መመሪያ ለሶስት ወር ይዘልቃል በሚል መሆኑ ተነግሯል።

  ነገር ግን የተጣሉት ገደቦች የሚነሱ ከሆነ ምጣኔ ሃብቱ የማንሰራራት ተስፋ አለው ተብሏል።

 7. የአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ምርመራን "ከአቅሜ በታች እየሰራሁ" ነው አለ

  ባህርዳር ከተማ

  በአማራ ክልል ያሉ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ መሣሪያዎች በተለያዩ ምክንያቶች መመርምር ከሚችሏቸው ናሙናዎች ያነሰ እየመረመሩ መሆኑ ተገለጸ።

  የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማህተመ ኃይሌ እንደተናገሩት በባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሃን እና ወልዲያ ውስጥ ስድስት የመመርመሪያ መሳሪያዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

  ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የሚመረመሩ ናሙናዎቸን ቁጥር ለማሳደግ ተጨማሪ ክፍሎች ማስፈለጉና የምርመራው ሂደት ረጅም ሰዓት መውሰዱ በርካታ ናሙናዎችን እንዳይሠሩ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።

  መሣሪያዎቹ የሚያስፈልጉት ነገሮች ከተሟሉላቸው በ24 ሰዓታት ውስጥ 372 ናሙናዎችን የሚመረምሩ ናቸው። በዚህም በክልሉ በ24 ሰዓት 2232 ናሙናዎችን ለመርመር የሚያስችል አቅም መኖሩን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

  ባህር ዳር የሚገኘው የአማራ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሥራ የጀመረ ሲሆን እስካሁንም 68 ናሙናዎችን መመርመሩን አስታውቀዋል። ውጤቱንም ለፌደራል መላካቸውን ገልፀዋል።

  በባህር ዳር በሚገኙት ሁለት መመርመሪያ መሣሪያዎች በቀን 744 ናሙና መመርመር የሚቻል ቢሆንም እየተሠራ የሚገኘው ከ96 እስከ 100 ናሙና ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

  ለምርመራ ሥራው የሰለጠኑ ባለሙያዎች በቅርቡ ሥራ ለሚጀመሩት ማዕከላት ሳይቀር መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል ዳይሬክተሯ።

 8. በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ኩፍኝ እንዳያባባስ ተሰግቷል

  በኩፍኝ የተያዘ ታዳጊ

  በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የኩፍኝ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት መኖሩ ተገለፀ።

  የኩፍኝ ወረርሽኝ ይኖራል ተብሎ የተሰጋው የክትባት መርሃ ግብሩ በኮቪድ-19 ምክንያት ስለተስተጓጎለ ነው ተብሏል።

  የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ኃላፊዎች እንዳሉት በ37 የዓለማችን አገራት የሚገኙ 117 ሚሊዮን ሕጻናት በወቅቱ ክትባታቸውን ላያገኙ ይችላሉ።

  በአውሮፓ በርካታ አገራት የኩፍኝ መከላከያን ማስከተብ እየቀረ በመምጣቱ ሕጻናት በኩፍኝ መጠቃታቸው ተነግሯል።

  ዩናይትድ ኪንግደም ከኩፍኝ ነጻ አገር የሚለውን ስም መነጠቋ የተሰማ ሲሆን፤ ለዚህም ደግሞ ምክንያት ነው የተባለው የኩፍኝ በሽታ እየተስፋፋ በመምጣቱ ነው።

  የኩፍኝ በሽታ ሳል፣ ሽፍታ እንዲሁም ትኩሳት የሚኖረው ሲሆን ሁለት ክትባት በመውሰድ ብቻ መከላከል ይቻላል።

  በተለያዩ አገራት የኩፍኝ ክትባት በነፃ ይሰጣል።

 9. ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ለ19 የአፍሪካ አገራት የብድር እፎይታ ጊዜ ፈቀደ

  የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወደ አፍሪካ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በርካታ አገራት ዜጎቻቸው በቤት እንዲቀመጡ አዝዘዋል፤ እንቅስቃሴ ከልክለዋል

  የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤም ኤፍ) ለ19 የአፍሪካ አገራት የአስቸኳይ ጊዜ የብድር እፎይታ ፈቀደ።

  የብድር እፎይታ ጊዜው ለስድስት ወራት የሚቆይ ነው የተባለ ሲሆን ይህም ገንዘባቸውን የኮሮናቫይረስን ለመከላከል እንዲያውሉት ታስቦ መሆኑ ተገልጿል።

  ቡርኪናፋሶ፣ ቻድ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ እና ሞዛምቢክ ከብድር እፎይታው ተጠቃሚ ከሆኑ አገራት መካከል ናቸው ተብሏል።

  ቀሪዎቹ ደግሞ ቤኒን፣ ኮሞሮስ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋምቢያ፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳዋ፣ ላይቤሪያ፣ ማዳጋስካር፣ ማላዊ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ሩዋንዳ፣ ሳኦቶሚና ፕሪንሲፔ፣ ሴራሊዮንና ቶጎ ናቸው።

  የመብት ተከራካሪዎችና ተሟጋቾች በአፍሪካ የኮሮናቫይረስን መከላከል ለማገዝ ከተጠየቁት መካከል ለአገራት የሚደረግ የብድር ስረዛ እና እፎይታ ነበር።

 10. ዴንማርክ ሌሎች የአውሮፓ አገራት በራቸውን እየከፈቱ ነው

  ዴንማርክ

  ዴንማርክ የእንቅስቀሴ እቀባዋን ለማላላት ተፍ ተፍ እያለች ነው። ከነገ ረቡዕ ጀምሮ 11 ዓመትና ከዚያ በታች ያሉ አዳጊዎች ወደ ትምህርት ቤት መመለስ ይችላሉ።

  ይህን ለማድረግ ከአውሮፓ አገሮች ቀዳሚዋ ናት።

  ዴንማርክ ከወራት በፊት ወረርሽኙ ሲጀማምር ሰሞን ትምህርት ቤቶችንም ሆነ የንግድ ተቋማትን ለመዝጋት ከቀዳሚ አገራት ተርታ ነበረች።

  "ከሚያስፈልገን ጊዜ በላይ በራችንን መዝጋት ያለብን አይመስለንም" ብለዋል ክብርት ጠቅላይ ሚኒስትር ሜት ፍሬድሪክሰን።

  ከሞላ ጎደል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዴንማርክ በቁጥጥር ሥር የዋለ ይመስላል። መንግሥት የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት እንደገና ማንቀሳቀስ ይፈልጋል።

  ዴንማርክ እየወሰደችው ያለው እርምጃ ግን ግብታዊ የሚባል አይደለም። በከፍተኛ ጥንቃቄ እየሆነ ያለ ነው። ንግዶችና ሌሎች እንቅስቃሴዎች እየተከፈቱ የሚመጡትም ቀስ በቀስ ነው። ተጨማሪ ለማንበብዴንማርክ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የዘጋችውን በሯን ለመክፈት ለምን ቸኮለች?

 11. አንድ ሚሊዮን የፊት ጭምብሎችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች ኢትዮጵያ ደረሱ

  PPE

  የዓለም ጤና ድርጅት የላካቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የፊት ጭምብሎች ኢትዮጵያ መድረሳአቸውን የአለም አቀፉ የምግብ ድርጅት በትዊተር ገፁ አስታውቋል።

  ከፊት ጭምብሎች በተጨማሪ፣ የእጅ ጓንቶች፣ ለጤና ባለሙያዎች የሚሆኑ አልባሳት እንዲሁም ለህሙማን የሚሆኑ የኦከስጅን መተንፈሻዎች (ቬንትሌተሮች) ይገኙበታል።

  እነዚህ የህክምና ቁሳቁሶች የተባበሩት መንግሥታት የኮቪድ-19ን ለመታገል "የተባበረ ትግል' ብሎ የነደፈው ፕሮጀክት አካል ነው።

  በአለም ምግብ ፕሮግራም አጓጓዥነት ከመጡት የህክምና ቁሳቁሶች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስተባባሪነት የመጡት የቢሊየነሩ ጃክ ማ እርዳታዎች ተካተውበታል።

  የአፍሪካ ህብረት በአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና ክትትል አማካኝነት ቴክኒካዊ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን የህክምና ቁሳቁሶችን ማከፋፈሉም የስራ ድርሻው እንደሆነ የአለም አቀፉ ምግብ ድርጅት በመግለጫው አትቷል።

  የህክምና ቁሳቁሶቹ ወደ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ታንዛንያ ወደሚገኙ ማዕከላት የሚከፋፈሉ ሲሆን በመቀጠልም ወደ ሌላ አፍሪካ አገራት ይከፋፈላሉ

  View more on twitter
 12. የፓኪስታኗ ካራቺ ከተማ ፖሊስ መንገዶችን በኮንቴይነር ዘጋ

  የከተማዋ ፖሊስ

  የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ ሆኖባቸዋል በተባሉ የመኖሪያ መንደሮች መግቢያና መውጫዎች ላይ ፖሊስ ኮንቴይነሮችን መደርደሩ ተገልጿል።

  ፖሊስ እንዳለው ሰዎች ወደ መንደሮቹ እንዳይገቡና ነዋሪዎቹም እንዳይወጡ በማሰብ ነው እርምጃው የተወሰደው።

  ቫይረሱ በእጅጉ በተስፋፋበቸው በነዚሁ መንደሮች ብዙ ሰዎች ላይ ምርመራ ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን የፖሊስ ኃላፊው ሳይድ ሙራድ አሊ ሻህ ገልጸዋል።

  በፓኪስታን ከ5 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ቢያንስ 90 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

 13. ሰበርበኢትዮጵያ ተጨማሪ 8 ሰዎች ቫይረሱ ተገኘባቸው

  ሊያ ታደሰ

  ባለፉት 24 ሰአታት ኢትዮጵያ ውስጥ 447 ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ አዲስ ስምንት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደስ በፌስቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል።

  በዚህም መሰረት በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር ወደ 82 ከፍ ብሏል።

  በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች መካከል የኤርትራ፣ እንግሊዝ እና ሶማሊያዊ ዜግነት ያላቸው ይገኙበታል። የተቀሩት 5ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

  ስምንቱም በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ወይም በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ናቸው ተብሏል።

  ከ100 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት እስካሁን መመርመር የቻለችው 4557 ሰዎችን ብቻ ሲሆን 63 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ።

 14. ከሳኡዲ አረቢያ የሚመለሱት ስደተኞች በኮሮናቫይረስ ምክንያት አይደለም ተባለ

  ፎቶ ፋይል። እአአ 2013 ላይ ከሳዑዲ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ስደተኞች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ።
  Image caption: ፎቶ ፋይል። እአአ 2013 ላይ ከሳዑዲ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ስደተኞች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ።

  የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ከሳኡዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ እየተደረጉ ያሉት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኮሮናቫይረስ ምክንያት አይደለም አለ።

  በውጪ ጉዳይ ሚንስትር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ ዮሐንስ ሾዴ፤ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳኡዲ መንግሥት ጋር ባለው ዲፕሎማሲያዊ ግነኙነት ሲመለሱ ነበር ብለዋል።

  አቶ ዮሐንስ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች መመለሳቸውንም ያስታወቁ ሲሆን፤ ከሳኡዲ መንግሥት ጋር በሚደረግ ግነኙነት መሠረት ስደተኞቹ ከሳኡዲ ከመነሳታቸው በፊት ለ14 ቀናት ተለይተው የሚቆዩበት ቦታ ዝግጁ ሲሆን እንደሚመጡ ተናግረዋል።

  የዚህን ዜና ሙሉ ዘገባ እዚህ ማግኘት ይችላሉ፡ ኮሮናቫይረስ፡ ከሳኡዲ አረቢያ የሚመለሱት ስደተኞች በኮሮናቫይረስ ምክንያት አይደለም

 15. ትራምፕ የእንቅስቃሴ ገደቡን የማስነሳት ሙሉ ስልጣን አለኝ አሉ

  Trump

  ፕሬዝደንት ትራምፕ ከአሜሪካ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች እና የሕግ ባለሙያዎች አረዳድ በተጻረረ መልኩ በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ተጥሎ የሚገኘው የእንቅስቃሴ ገደብ የማንሳት ሙሉ ስልጣን አለኝ አሉ።

  "ውሳኔውን የሚሰጠው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ነው" ሲሉ ተናግረዋል፤ ፕሬዝደንት ትራምፕ ትናንት በሰጡት ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ።

  የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ግን በግዛቶች ውስጥ ሕግ እና ሥርዓት መከበሩን የሚያረጋግጡት ግዛቶቹ እራሳቸው ናቸው ይላል።

  በምሥራቅ እና በምዕራብ አሜሪካ የሚገኙ 10 ግዛቶች ጥብቅ የሆነውን ከቤት ያለመውጣት ትዕዛዝን ለማንሳት እያሰቡ ይገኛሉ።

  ትራምፕ ጨምረውም የፈረንጆቹ ሜይ 1 (ሚያዚያ 23) የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ታልመው ተፈጻሚ ሲደረጉ የነበሩት ጥብቅ መመሪያዎችን ማላላት የሚጀምሩበት ዕለት እንደሚሆን ተናግረዋል።

  አሜሪካውያን ወደ ምግብ ቤቶች አትሂዱ፣ እጅግ አስፈላጊ ካልሆኑ በስተቀር ከጉዞዎች እራሳችሁን ቆጥቡ እንዲሁም ከ10 ሰዎች በላይ በአንድ ቦታ አትሰባሰቡ የሚሉት ጥብቅ መመሪያዎች የሚያበቁት ሚያዚያ 22 ነው።

 16. ኮሮናቫይረስ የዓለም የምግብ አቅርቦት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

  Getty

  ብዙ አገራት እንቅስቃሴ ገተዋል። ይህን ተከትሎም በመደብሮች የምግብ እጥረት መከሰቱ እየተነገረ ነው።

  በሌላ በኩል ሬስቶራንቶችና ሌሎችም የመስተንገዶ አገልግሎት ሰጪዎች በመዘጋታቸው፤ ምግብ አምራቾች ክምችታቸው ሊበላሽ እንደሆነ ገልጸዋል።

  የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በምግብ አቅርቦት ዘርፍ ላይ በተለያየ መንገድ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።

  ለምሳሌ የወተት ምርት ሲትረፈረፍ፤ የዱቄት ፈላጊ ደግሞ በእጅጉ ጨምሯል።

  ተጨማሪ ይመልከቱ፡ ኮሮናቫይረስ የዓለም የምግብ አቅርቦት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

 17. ኦስትሪያ አነስተኛ ሱቆችን መክፈት ጀመረች

  ኦስትሪያ

  ኦስትሪያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተላለፉ ጥብቅ መመሪያዎችን ማላላት ጀምራለች።

  ከዛሬ ጀምሮ አነስተኛ ሱቆች መከፈት ይጀምራሉ ተብሏል።

  ስፋታቸው ከ400 ስኴር ሜትር በታች የሆኑ ሱቆች፣ አበባ መሸጫ ቤቶች እና የመሳሰሉት አነስተኛ ሱቆች ከዛሬ ጀምሮ ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ ይጀምራሉ።

  ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ኦስትሪያዊያን ከቤታቸው ሲወጡ የፊት እና አፍ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ እና ከሌሎች ሰዎች ቢያንስ የ3 ሜትር ርቀት መጠበቅ ይኖርባቸዋል ተብሏል።

  ኦስትሪያ ከ14,000 በላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች የሚገኙባት አገር ስትሆን፤ 368 ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ህልፈተ ህይወት መዝግባለች።

 18. ቻይና የአፍሪካውያንን የብድር እፎይታ መመልከት እችላለሁ አለች

  ከሁለት ዓመት በፊት ተካሂዶ በነበረው የጂ20 አገራት ውይይት ላይ የተሳተፉት መሪዎች
  Image caption: ከሁለት ዓመት በፊት ተካሂዶ በነበረው የጂ20 አገራት ውይይት ላይ የተሳተፉት መሪዎች

  ቻይና የአፍሪካ አገራትን የብድር እፎይታ "ለመመልከት ዝግጁ ነኝ" አለች።

  ቻይና በጊዜያዊነት የአፍሪካ አገራት የብድር ክፍያቸውን በማቆም ጥሬ ገንዘቡን ለኮሮናቫይረስ ስርጭት መከላከል ተግባር ላይ እንዲያውሉ ልትፈቅድ እንደምትችል ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

  ለአፍሪካ አገራት ዋነኛ የብድር ምንጭ የሆነችው ቻይና ባለፉት ሁለት አስረተ ዓመታት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ብድር ለአፍሪካ ሰጥታለች።

  የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ለሬውተርስ ሲናገሩ "የአፍሪካ የብድር እዳ ምንጭ ውስብስብ ነው። ዓለም አቀፍ የብድር እፎይታውን ጥሪ ተቀብለን ከተቀረው ዓለም አቀፍ ማህብረሰብ ጋር ያሉ አማራጮችን እያጠናን ነው" ብለዋል።

  ቻይና በዚህ ሳምንት ለውይይት ቀጠሮ የያዘው የጂ-20 አባል መሆኗ ይታወቃል። የጂ-20 አባል አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ይረዳ ዘንድ የብድር እፎይታ እንዲደረግ ከውሳኔ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

  ዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ እና የዓለም ባንክ ለአገራት የብድር እፎይታ እንዲደረግ ጫና እያሳደሩ ነው።

 19. ክልከላውን የተላለፉት የሕዝብ እንደራሴ በቁጥጥር ስር ዋሉ

  የኬንያ ወታደሮች በናይሮቢ

  በኬንያ ኮሮናቫይረስን ተከትሎ የምሽት ክበቦች ላይ የተጣለውን እገዳ የተላለፉ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

  የፈረንጆቹን ፋሲካ ለማክበር በሚል በመሸታ ቤቶቹ ውስጥ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የሕዝብ እንደራሴ፣ ዳኛ እና የፖሊስ አባላት ይገኙበታል።

  የመዲናዋ ናይሮቢ ፖሊስ እንዳስታወቀው እገዳውን ተላልፈው ሲሰሩ የነበሩ በርካታ መሸታ ቤቶች ላይ እርምጃ ወስዷል።

  ፖሊስ በመሸታ ቤቶቹ ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ያደረገው የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት ጥቆማ እንደሆነም ታውቋል።

 20. በካርቱም ለሶስት ሳምንት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ሊገደብ ነው

  ካርቱም

  በሱዳኗ ዋና ከተማ ካርቱም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ ለሶስት ሳምንታት የሚቆይ የእንቅስቃሴ ገደብ ሊጣል ነው።

  የመንግስት ቃል አቀባዩ ፋይሰል ሳሊህ እንዳሉት የእንቅስቃሴ ገደቡ የካርቱም መንትያ ከተማ በሆነችው ኦምዱርማንም ተግባራዊ ይሆናል።

  በሱዳን ባሳለፍነው የሳምንቱ መጨረሻ 10 ተጨማሪ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን በአጠቃላይ በአገሪቱ 29 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል። አራት ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

  በእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት የምግብ ሱቆችና መድሃኒት ቤቶች ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ክፍት ይሆናሉ ተብሏል።

  ሰራተኞች ደግሞ ደሞዝ የሚከፈልበት የሶስት ሳምንት እረፍት የሚወጡ ይሆናል።