Got a TV Licence?

You need one to watch live TV on any channel or device, and BBC programmes on iPlayer. It’s the law.

Find out more
I don’t have a TV Licence.

ቀጥታ ዘገባ

የተጠቀሱት ሰዓቶቸ የዩናይትድ ኪንግደም ናቸዉ

 1. በኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛው የኮሮናቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር ተመዘገበ

  ቢቢሲ አማርኛ

  በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ መገኘቱ በይፋ ከታወቀ ወዲህ እስካሁን በአንድ ቀን በተደረጉ ምርመራዎች ሁሉ ከተገኘው ከፍተኛው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዘገበ።

  ባለፉት 24 ሰዓታት ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው 7334 ናሙናዎች ላይ በተደረገው ምርመራ ቫይረሱ በ704 ሰዎች ላይ ሲገኝ ይህም እስካሁን በአገሪቱ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከተገኘው እጅግ ከፍተኛው ነው።

  ቫይረሱ መገኘቱ ከተረጋገጠባቸው ሰዎች መካከል ከፍተኛው ወይም 551ዱ በመዲናዋ በአዲስ አበባ ውስጥ የተገኙ መሆናቸው ተገልጿል።

  በተጨማሪም ከትግራይ 39፣ ከኦሮሚያ 30፣ ከጋምቤላ 26፣ ከአማራ 21፣ ከሲዳማ 11፣ ከድሬዳዋ 10 እና ከሌሎችም ክልሎች ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

  የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ባወጡት በሽታውን የተመለከተ ያለፉት 24 ሰዓታት ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት አስከ ዛሬ በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 10 ሺህ 207 ሆኗል።

  ሪፖርቱ ጨምሮም 196 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን አመልክቶ አጠቃላይ በአገሪቱ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች አሃዝ 5137 ሲደርስ፤ ሦስት ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል ከእነሱም መካከል በሁለቱ ላይ ቫይረሱ የተገኘው አስከሬን ላይ በተደረገ ምርመራ ነው።

  እስከ ዛሬ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች አጠቃላይ ቁጥርም 170 ሆኗል።

  በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ከታወቀ በኋላ እስካሁን ለ331 ሺህ 266 ሰዎች ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ በ10 ሺህ 207 ሰዎች ላይ የተገኘ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ አገግመዋል።

 2. በዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያ አምባሳደር

  በዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያ አምባሳደር የአገራቸው የደህንነት ተቋም የኮሮናቫይረስ ክትባት ምርምርን ለመስረቅ ሙከራ አድርጓል በሚል የቀረበውን ክስ ውድቅ አደረጉ።

  ተጨማሪ ያንብቡ
  next
 3. በኢራን በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች እየጨመረ መሆኑ ተገለፀ

  ማስክ ያደረጉ ሴት

  በኢራን ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ተጨማሪ 209 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሲሞቱ፤ 2 ሺህ 182 አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

  የአገሪቷ የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንደተናገሩት በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል1 ሺህ 324 የሚሆኑት ሆስፒታል ገብተው ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።

  ይህንንም ተከትሎ ባለሥልጣናት ሰዎች እንዳይሰባሰቡ፣ አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

  ትናንት ፕሬዚደንት ሃሰን ሩሃኒ 25 ሚሊየን የአገሪቷ ሕዝቦች በቫይረሱ መጠቃታቸውን ተናግረዋል። ፕሬዚደንቱ አክለውም በሚቀጥሉት ጥቂት ወራትም 35 ሚሊየን ሰዎች ስጋት ላይ እንደሆኑም አስጠንቅቀዋል።

  ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱን የጤና ሚንስቴር አሃዝ ዋቢ በማድረግ እንደተናገሩት፤ ህሙማንን ለማከም ኢራን አሁን ካላት ሁለት እጥፍ የሆስፒታል አልጋዎች ያስፈልጋታል ብለዋል።

  ይሁን እንጂ የጤና ባለሥልጣናት የሰዎችን ለቫይረሱ የመጋለጥ እድላቸውን በሚያመለክት የደም ምርመራ ላይ የተመሰረተ ነው፤ ይህም አሁን ያለውን የወረርሽኙን ደረጃ አያመለክትም በማለት የፕሬዚደንቱን ግምት አጣጥለውታል።

  የኢራን ጤና ሚኒስቴር እስካሁን 13 ሺህ 791 በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው ማለፉን አርብ ዕለት አስታውቋል።

 4. የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች ኮሮናቫይረስ ያስከተለው የምጣኔ ኃብት ቀውስ ላይ እየተወያዩ ነው

  ቻንስለር አንጌላ መርክልና ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን
  Image caption: የሕብረቱ መሪዎች ከወራት በኋላ ፊት ለፊት ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

  የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች ለሦስተኛ ቀን በመሰባሰብ ኮሮናቫይረስ ያስከተለውን የኢኮኖሚ ቀውስ ዳግም ለማንሰራራት የሚያስችላቸውን ውይይት እያደረጉ ነው።

  መሪዎቹ የ7 ዓመታት በጀት አንድ ትሪሊየን ዩሮ ላይ ለመነጋገርና አባል አገራቱ ወረርሽኙ ካሳደረባቸው ተፅእኖ እንዲያገግሙ የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ላይ ለመነጋጋር በብራስልስ የተገናኙት አርብ ዕለት ነበር።

  ይህም አገራቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉ በኋላ መሪዎቹ ፊት ለፊት ተገናኝተው ያደረጉት የመጀመሪያ ውይይታቸው ነው።

  በውይይቱ ላይ አንዳንድ አገራት በሕብረቱ ለዚህ ያቀረበው 857 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ፤ ከድጋፍ ይልቅ በብድር መልክ መቅረብ እንዳለበት ያምናሉ።

  የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንጌላ መርክል እንዳሉት እስካሁን መሪዎቹ በገንዘብ ድጋፉ ላይ መስማማት ስላልቻሉ፤ ምን አልባት ዛሬ በሚያካሂዱት ውይይት ላይም ስምምነት ላይ ላይደርሱ ይችላሉ።

  በርካታ በጎ ፈቃድ ቢኖርም፤ ሌሎች በርካታ አቋሞች ደግሞ መኖራቸውን መሪዋ ተናግረዋል።

  ያለ ዕቅድ እየተካሄደ ያለው የሦስተኛው ቀን ስብሰባ እንዲካሄድ የተወሰነው በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ቀን ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መመዝገባቸውን ተከትሎ ነው።

  የዓለም ጤና ድርጅት ቅዳሜ እለት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ24 ሰዓታት ውስጥ በ260 ሺህ መጨመሩን አስታውቋል።

  ባለሥልጠናት እንዳሉት ይህ ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር ነው ። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥርም ከሩብ ሚሊየን ተሻግሯል። ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

  የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ቅዳሜ እለት ባወጣው መረጃ በዚህ ዕለት በዓለማችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ14ሚሊየን ማለፉን አመልክቷል።

 5. በቼክ ሪፐብሊክ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

  ደስታቸውን በአደባባይ የሚገልፁ ሰዎች
  Image caption: ከጥቂት ሳምንታት በፊት የገደቦች መላላትን ተከትሎ በርካቶች ደስታቸውን ሲገልፁ ነበር

  በቼክ ሪፐብሊክ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 4ሺህ 764 መድረሱ ተገለፀ። ይህም ሚያዚያ ላይ ከነበረው 4ሺህ 737 የሚበልጥ ነው ተብሏል።

  ሆኖም በርካቶች በአንፃራዊነት አንድ ሰው ከኮሮናቫይረስ ነፃ መሆኑን ለማሳወቅ ረጅም ጊዜ መውሰዱን በመግለፅ የዚህን መረጃ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ከተውታል።

  አሁን ላይ 135 ሰዎች በበሽታው ተይዘው ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ሚያዚያ ወር ላይ ወረርሽኙ ተባብሶ ከነበረበት ወቅት ላይ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው ተብሏል። ሚያዚያ ወር ላይ ይህ ቁጥር 450 ነበር።

  ከእነዚህም መካከል ኦክስጅንና ሌሎች አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያዎች ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ጥቂቶች ናቸው።

  በሌላ በኩል ቅዳሜ ዕለት 113 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ አብዛኞቹ የተገኙት በሰሜን ምስራቅ ኢንዱስትሪ አካባቢዎች ነው።

  አርብ ዕለት ባለሥልጣናት በአገሪቷ ሰሜን ምስራቅ የአገሪቷ አካባቢዎች ገደቦችን ያጠበቁ ሲሆን፤ ግዴታ የነበረው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግም እንደገና ተጥሏል፤ ምግብ ቤቶች አገልግሎት የሚሰጡበትም ሰዓት ተወስኗል።

  በቼክ ሪፐብሊክ ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ 13 ሺህ 885 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 358 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

 6. የታይላንድ ሰልፈኞች የኮሮናን ሕግ በመጣስ ለተቃውሞ ወጡ

  የተቃውሞ ሰልፈኞች

  በታይላንድ መንግሥትን ለመቃወም አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች መሰባሰብ የሚከለክለውን የኮሮናን ሕግ መጣሳቸው ተገለፀ።

  በመቶዎች የሚቆጠሩት እነዚህ ተቃዋሚዎች አደባባይ የወጡት መንግሥት ሥልጣኑን እንዲለቅና ምክር ቤቱ እንዲገነጠል ለመጠየቅ ነው።

  በዚህም በዋና ከተማዋ ባንኮግ ለተቃውሞ በወጡ ወጣቶችና በፖሊስ መካከል ግጭት ተፈጥሯል።

  በቱሪዝምና በወጪ ንግድ ላይ የተመሰረተው የታይላንድ ኢኮኖሚ በወረርሽኙ ሳቢያ ክፉኛ ተጎድቷል።

  ይህም ከዚህ ቀደም በመንግሥት ተቺዎች ላይ ጥቃትና መጥፋት ለመፈፀሙ፤ እንዲሁም ገዥው ፓርቲ በባለፈው ዓመት ምርጫ እንዲያሸንፉ አድርጓቸዋል በሚል በሚተቸው የሕገ መንግሥት ማሻሻያን በተመለከተ በቀድሞው የመንግሥት ጦር ኃላፊ ፕራዮት ቻን ኦ ቻ ላይ ከተፈጠረው ቁጣ ጋር ተደማምሮ ሁኔታውን አባብሶታል።

  የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ከፖሊስ ጋር
 7. በዓለማችን በአንድ ቀን ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛው ቁጥር ተመዘገበ

  በጋሪ አትክልት የሚሸጥ ሰው
  Image caption: ሕንድ በኮሮናቫይረስ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች

  በዓለማችን በ24 ሰዓታት ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ260 ሺህ መጨመሩን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

  ይህም ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ በአንድ ቀን ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር ነው ተብሏል።

  እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ በአንድ ቀን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሩብ ሚሊየንን ሲሻገር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

  ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረባቸው አገራትም አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሕንድና ደቡብ አፍሪካ መሆናቸው ተገልጿል።

  በዓለማችን በወረርሽኙ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በ7 ሺህ 360 የጨመረ ሲሆን ፤ ይህም ከግንቦት ወር መጀመሪያ ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።

  እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መረጃ በአጠቃላይ በዓለማችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ14 ሚሊየን የተሻገረ ሲሆን፤ ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል።

 8. እንደምን አደራችሁ

  የኮሮናቫይረስ ህመምተኛ በኢትዮጵያ

  የኮሮናቫይረስ የማኅበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለባት ኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 9 ሺህ 503 ደርሷል።

  ከእነዚህም ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት 4 ሺህ 941 አገግመዋል። በትናንትናው ዕለት የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ አገሪቱ እስካሁን 167 ዜጎቿን በኮሮናቫይረስ አጥታለች።

  የምርመራ አቅሟን እየጨመረች ባለችው ኢትዯጵያ እስካሁን ድረስ 323 ሺህ 932 የላብራቶሪ ምርመራዎች መከናወናቸውን ከጤና ሚኒስቴርና ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጫ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

  በሕብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት እየተስተዋለ በመሆኑ ሕዝቡ በሽታውን የመከላከያ መንገዶች ተግባራዊ በማድረግ እራሱንና ሌሎችን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ባለሙያዎች እየመከሩ ነው። ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዘ መረጃዎችን በቀጥታ ዘገባችን እዚህ ታገኛላችሁ

 9. ተጨማሪ 356 ሰዎች ላይ ኮቪድ-19 ሲገኝ አብዛኞቹ የተገኙት አዲስ አበባ ውስጥ ነው

  ቢቢሲ አማርኛ

  በኢትዮጵያ ተጨማሪ 356 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ሲገኝ ከእነዚህ መካከል ሁለት ሦስተኛው ህሙማን አዲስ አበባ ውስጥ በተደረገ ምርመራ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተገለጸ።

  የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ያወጡት በሽታውን የተመለከተ ያለፉት 24 ሰዓታት ሪፖርት እንዳመለከተው 6886 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ ነው 356ቱ በወረርሽኙ እንደተያዙ የተረጋገጠው።

  በዚህም መሰረት አስከዛሬ በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 9503 ሆኗል። ሪፖርቱ ጨምሮም 41 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን አመልክቶ 4 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ከእነሱም መካከል በሦስቱ ላይ ቫይረሱ የተገኘው አስከሬን ላይ በተደረገ ምርመራ ነው።

  ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ አዲስ አበባ ውስጥ የተገኙ ሲሆን ቁጥራቸውም 255 ሲሆን፤ ከትግራይ 48፣ ከኦሮሚያ 14 ሰዎች ሲሆኑ ከሌሎቹ ክልሎችም የተወሰኑ ሰዎች ላይ በሽታው ተገኝቷል።

  በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ከታወቀ በኋላ እስካሁን ለ323 ሺህ 932 ሰዎች ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ በ9503 ሰዎች ላይ ተገኝቷል።

  ከእነዚህም መካከል 4941 ሰዎች ባለፉት ወራት ውስጥ በተደረገላቸው ህክምና ከወረርሽኙ አገግመዋል። ከበሽታው ጋር በተያያዘም አስካሁን 167 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

 10. የቻይናዋ ግዛት አዲስ ታማሚዎችን በማግኘቷ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ጀመረች

  ቻይና

  የቻይናዋ ዢንጂያንግ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ኡሩምኪ ውስጥ 16 የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ከተገኙ በኋላ ባለስልጣናት አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው ተገለጸ።

  አርብ ዕለት ከተገኙት አዳዲስ ህሙማን በተጨማሪ 11 ምንም ምልክት የማይታይባቸው ነገር ግን ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ተገኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪም 269 በጥብቅ ክትትል ውስጥ መሆናቸውንም የሮይተርስ ዜና ወኪል ዘግቧል።

  የአካባቢው አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ በርካታ የመኖሪያ አካባቢዎች ዝግ እንዲሆኑ ተደርገው መውጣትና መግባት ተከልክለዋል። ነዋሪዎች እንዳሉት ከመኖሪያ አካባቢዎቹ መውጣት ባይቻልም እዚያው ውስጥ ግን ከቤት ውጪ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አድርጎ መንቀሳቀስ ግን ይቻላል።

  በከተማዋ ያለው ከምድር በታች የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በበሽታው ስጋት ሳቢያ ከሐሙስ ጀምሮ መዘጋቱም ተነግሯል።

  ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ ባለው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ይከናወኑ የነበሩ ከ600 በላይ በረራዎች አርብ ዕለት እንዲሰረዙ ተደተርገዋል።

  የከተማዋ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ኃላፊ ለአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት የተከሰተው ወረርሽኝ “በአጠቃላይ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ አይደለም” ሲሉ ተናገግረዋል።

 11. የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለማግኘት እየሰሩ ያሉ ተቋማት የስርቆት ኢላማ ሆነዋል

  ሞባይልና የኮሮናቫይረስ ምሰል

  ሩሲያዊያን የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች [ሃከርስ] የኮሮናቫይረስ ክትባት ለመስራት እየጣሩ ያሉ ተቋማትን ኢላማ ማድረጋቸውን የብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎት ቡድን አስጠነቀቀ።

  የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የመረጃ መረብ ደኅንነት ማዕከል፤ መረጃ መንታፊዎቹ ከሞላ ጎደል "የሩሲያ የደኅንነት አገልግሎት አካል" እንደሆኑ በመምሰል እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁሟል።

  ቡድኑ ከኮቪድ -19 ክትባት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለመስረቅ በኮምፒዩተሮች፣ በመረጃ ቋት አሊያም የኮምፒዩተር መረቦች ላይ ጉዳት ለማድረስ ሆነ ተብሎ የተሰራ ሶፍትዌር መጠቀሙን ተቋሙ አስታውቋል።

  በተቋሙ የኦፕሬሽኑ ዳሬክተር ፖል ቺቸስተር ድርጊቱን "አስቀያሚ" ብለውታል።

  ይህ የደኅንነት ተቋሙ ማስጠንቀቂያ የወጣው በዩናይትድ ኪንግደም፣ በካናዳና በአሜሪካ የመረጃ መረብ ደኅንት ተቋማት አማካይነት ነው። ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ የሩሲያ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች የኮቪድ-19 ክትባት ምርምርን ኢላማ ማድረጋቸው ተነገረ

 12. የአውስትራሊያው የልብስ አምራች ኩባንያ ባስነገረው ማስታወቂያ ቅጣት ተጣለበት

  የአውስትራሊያው የልብስ አምራች ኩባንያ ሎርና ጄን ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ባስነገረው የልብስ ማስታወቂያ ሕግን ጥሷል ተብሎ ወደ 40 ሺህ የሚጠጋ ዶላር ቅጣት ተጣለበት።

  ድርጅቱ “ጸረ-ቫይረስ ልብስ” በማለት ተላላፊ በሽታዎችን ሊከላከል ይችላል የሚል የልብስ ማስታወቂያ በማስነገሩ ነው ቅጣቱ የተጣለበት።

  ድርጅቱ እንዳለው “አልባሳቱ ከኬሚካል ነጻ በሆነ መንገድ የሚመረቱ በመሆናቸው ልብሶቹን የሚጠቀሙ ሰዎችን ከቫይረስና ከባክቴሪያዎች ይከላከላሉ” ብሏል።

  የአውስትራሊያ የጤና መስሪያ ቤት ምክትል ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆን ስኬሪት “እንዲህ አይነቶቹ ማስታወቂያዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ትክክለኛ ያልሆነ መተማመን ማድረግ የሚጠበቅባቸውን የእጅ ንጽህናንእና አካላዊ ርቀትን መጠበቅን የመሳሰሉ ጥንቃቄዎችን እንዳያደርጉ ሊያዘናጉና አደገኛ ውጤቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ” በማለት የማስታወቂያወንተቃውመዋል።

  የልብስ አምራች ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ፤ “ሰዎች እራሳቸውን እና ሌሎች ከቫይረሱ ከመጠበቅ እንዲዘናጉ ለማድረግ ሳይሆን ከወረርሽኙ በፊት ከአጋሮቻችን ጋር ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ስናዘጋጀው የነበረ ምርት ነው” ብሏል።

 13. ኮሮናቫይረስ ምስል

  ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ተነስቶ ሰው ከማይኖርበት አንታርክቲክ ውጪ ሁሉንም የዓለማችንን አህጉራትን ያዳረሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት የምድራችን ዋነኛ የጤና ስጋት ሆኗል። ኮቪድ-19 በመባል የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ሲሆን፤ መጀመሪያ ትኩሳት ቀጥሎም ደረቅ ሳል ከሳምንት በኋላ ደግሞ የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል። እስካሁን በቫይረሱ ከ18 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተያዙ ሲሆን ከ690 ሺህ በላይ የሚሆኑ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያስችል ክትባትም ሆነ መድኃኒት አልተገኘም።

  ተጨማሪ ያንብቡ
  next
 14. የኢራኑ ፕሬዝደንት 25 ሚሊዮን ኢራናውያን በቫይረሱ ተጠቅተዋል አሉ

  ሃሰን ሩሃኒ

  የኢራን ፕሬዝደንት ሐሰን ሩሃኒ 25 ሚሊዮን ኢራናውያን በኮሮናቫይረስ መጠቃታቸውን እና ሌሎች 35 ሚሊዮን ደግሞ የቫይረሱ ስጋት እንዳለባቸው መናገራቸው ተገለጸ።

  ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱን የጤና ሚንሰቴር አሃዝ ዋቢ በማድረግ እንደተናገሩት፤ ህሙማንን ለማከም ኢራን አሁን ካላት ሁለት እጥፍ የሆስፒታል አልጋዎች ያስፈልጋታል ብለዋል።

  እስካሁን በኢራን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ይፋዊ አሃዝ 269 ሺህ 440 የሚል ነበር።

  ፕሬዝደንት ሩሃኒ ወደ 14 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ማለፉን ጠቅሰው ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ባለፉት 150 ቀናት ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታሎች መግባታቸውን ተናግረዋል።

  የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ እስካሁን ድረስ በኢራን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 270 ሺህ ገደማ መሆኑን እና ህይወታቸውን የጡ ሰዎች ደግሞ 13 ሺህ 800 መሆኑን ያሳያል።

 15. ፕሪሚየር ሊግን የተቀላቀለው የሊድስ ደጋፊዎች ክልከላዎችን ጥሰው አደባባይ ወጡ

  የሊድስ ዩናይትድ ደጋፊዎች

  ሊድስ ዩናይትድ የእግር ኳስ ቡድን ከ16 ዓመታት በኋላ ወደ የፕሪሚየር ሊጉ መመለሱን አረጋግጧል።

  በዚህም ደስታቸውን መቆጣጠር ያቃታቸው የሊድስ ዩናይትድ ደጋፈዎች መንግሥት የኮሮናቫይረስ ለመከላከል ያስተላለፋቸውን እግዶች ወደ ጎን በመተው በብዛት ሆነ በአደባባይ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

  የሊድስ ዩናይትድ ደጋፊዎች

  የሊድስ ክለብ ባለቤት አንድሬያ ራድሪዛኒ እና ፖሊስ ደጋፊዎች በቤት እንዲቆዩ ቢያስጠነቅቁም የቡድናቸው ውጤት በደስታ ካሰከራቸው ደጋፊዎች ግን ሰሚ ጆሮ አላገኙም።

  በእንግሊዝ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ሲባል ሰዎች የፊትና የአፍ መሸፈኛ ጭምብል ከማድረግ በተጨማሪ ቢያንስ የ1 ሜትር አካላዊ ርቀታቸውን መጠበቅ አለባቸው።

 16. አሜሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች መመዝገቧን ቀጥላለች

  አሜሪካ

  በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ እንደቀጠለ ነው።

  እስካሁን በአገሪቱ ከ3.6 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 139 ሺህ ሰዎች ገደማ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

  በየዕለቱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ አዲስ ቁጥርን እያስመዘገበ በመጨመር ላይ ይገኛል። ትናንት አርብ በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከ70 ሺህ በላይ ነበር።

  ከ30 በላይ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፤ ቴክሳስ፣ ፍሎሪዳ እና የአሪዞና ግዛቶች ደግሞ ክፉኛ የተጠቁ የአሜሪካ አካባቢዎች እንደሆኑ ተነግሯል።

  ባለስልጣናት በቴክሳስ ግዛት እና ሜክሲኮ ድንበር አቅራቢያ የሚገኙ ሆቴሎች ወደ ጤና ማዕከልነት በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚለወጡ ተናግረዋል።

 17. የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ ኃያላን አገራትን ወቀሱ

  አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የዓለም ታላላቅ አገራት የኮሮናቫይረስን ወረርሽኝ ለመዋጋት ተባብረው አልሰሩም ሲሉ ጠንካራ ወቀሳ ሰነዘሩ።

  ዋና ጸሃፊው በቢቢሲ ሬዲዮ 4 ላይ ቀርበው እንደተናገሩት በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ፣ በቻይናና በሩሲያ መካከል ያለው ግንኙነት አጋጥሞ በማያውቅ ሁኔታ ተዳክመውል ብለዋል።

  "የአሁኗ ዓለም በሁለት ወይም በበርካታ ኃያላን የምትመራ ልትሆን አትችልም። በብዙ መልኩ ትርምሶች ይታያሉ። መግባባት አለመኖርና በኃያላን መካከል ያለው ፉክክር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብቻ ሳይሆን ለዓለም ዋነኛ ፈተና ነው” ብለዋል።

  ጉቴሬዝ ጨምረውም የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በሊቢያ፣ በየመን፣ በሶሪያና በአፍጋኒስታን ላሉትና በዓለም ዙሪያ ለሚካሄዱ ግጭቶች መፍትሄ እንዲፈልግ ጥሪ አቅርበዋል።

  ዋና ጸሃፊው ጉቴሬዝ በዚህ ወረርሽኝ እየተስፋፋ ባለበት ጊዜ ባለጸጋ አገራት ድሃ አገራትን ለመርዳት አስፈላጊውን ነገር አላደረጉም ሲሉ ተችተዋል።

  የዓለም መንግሥታት የኮሮናቫይረስ ክትባት የሁሉም አቅም ያገናዘበና ተደራሽ እንዲሆን መደገፍ እንዳለባቸው ጠቅሰው “ሁሉም ሰው ከወረርሽኙ የተጠበቀ ካልሆነ፤ ሁላችንም የተጠበቅን አንሆንም” ሲሉ ተናግረዋል።

 18. በብስክሌቱ ማኅበራዊ እርቀትን ስለመጠበቅ የሚያሳስበው ኬኒያዊ

  አይዛክ እና ብስክሌቱ

  ኬኒያዊው ሰዎች ማኅበራዊ ርቀታቸውን በመጠበቅ እራሳቸውን እና ሌሎች ከኮሮናቫይረስ እንዲጠብቁ ባልተለመደ መልኩ እያስታወሰ ነው።

  ወጣቱ ይህን መልዕክቱን የሚያስላልፈው በሚጋልበው ብስክሌት አማካኝነት ነው።

  በመዲናዋ ናይሮቢ ተገቢውን ርቀት ለማሳየት ተራርቀው በብስክሌቱ ላይ በተገጠሙት ጎማዎች ላይ 'ማኅበራዊ' እና 'ርቀት' የሚሉ ቃላትን አስፍሮ ከተማዋን ሲዞር ይውላል።

  አይሳክ እና ብስክሌቱ

  ስሙ አይዛክ ታሪታ ይባላል። አይሳክ ሆነ ብሎ ባልተለመደ ሁኔታ የብስክሌቱን ጎማዎች ያራራቃቸው ሰዎች ማኅበራዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ዕለታዊ ሥራቸውን መከወን እንደሚችሉ ለማስታወስ ነው ተብሏል።

  ከዚህ በተጨማሪም ትኩረት ለመሳብ በየዕለቱ በመገናኛ ብዙሃን ላይ በቀጥታ እየቀረቡ የበሽታውን ሁኔታ ዝርዝር የሚያቀርቡትና ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡትን የአገሪቱን ጤና ሚኒስተር ፎቶም በብስክሌቱ ላይ አድርጎ በከተማዋ ውስጥ ይዘዋወራል።

 19. ዝነኛዋ የቦሊዉድ ተዋናይትና ቤተሰቧ በኮቪድ-19 ተይዘው ሆስፒታል ገቡ

  አይሽዋርያ ከባለቤቷ እና ሴት ልጇ ጋር

  የቀድሞ ‘ሚስ ዎርልድ’ እና ዝነኛ የቦሊውድ ተዋናይት አሽዋይሪያ ራኢ ባቻቻን እና የቤተሰቧ አባላት በኮቪድ-19 ተይዘው ሙምባይ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተዘገበ።

  በኮቪድ-19 የተያዙት የአይሽዋሪያ ቤተሰብ አባላት፤ ዝነኛ ተዋናይ የሆነውም ባለቤቷ አበጂሼክ እና የ8 ዓመት ሴት ልጇም መሆናቸው ተነግሯል።

  ዝነኞቹ የቤተሰብ አባላት በኮሮናቫይረስ የመያዛቸው ዜና በመላው ሕንድ ድንጋጤን መፍጠሩ በስፋት ተዘግቧል።

  በሺዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎቻቸው የቤተሰብ አባላቱ በቶሎ እንዲያገግሙ የጸሎት ፕሮግራም አሰናድተው ነበር ተብሏል።

  ትናንት አርብ ሕንድ ከ35 ሺህ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን፤ ይህም በአገሪቱ በጠቅላላው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን ከ1 ሚሊዮን አሻግሯል።

  በሕንድ እንካሁን 25,602 ሰዎች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።

 20. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሕዝቡ ጭምብል እንደያደርግ አላዝም አሉ

  ፕሬዝዳናት ትራምፕ ጭምብል አድርገው

  የአሜሪካው ፕሬዝዳናት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት ዜጎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልን እንዲያደርጉ እንደማያዙ አስታወቁ።

  ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት የአገሪቱ የተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አንተኒ ፋውቺ የግዛቶችና የአካባቢ አስተዳዳሪዎች ሕዝቡ ጭምብል እንዲጠቀም በተቻለ አቅም “እንዲያስገድዱ” መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።

  ዶክተር ፋውቺ እንዳሉት የፊትና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ በሽታውን ለመከላከል “በጣም አስፈላጊ ስለሆነ፤ ሁላችንም ልንጠቀምበት ይገባል።”

  ነገር ግን ትናንት አርብ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልን መጠቀም ግዴታ መደረግን እንደማይስማሙበት “ሕዝቡ ነጻነት ሊሰጠው ይገባል” በማለት አመልክተው።

  በአሜሪካ ውስጥ ጭምብል የመጠቀም ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ የፖለቲካዊ ውዝግብ ምንጭ ከሆነ ወራት ተቆጥረዋል።

  በአገሪቱ ያሉ የአብዛኞቹ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች ማንኛውም ሰው ከቤቱ ውጪ በሚሆንበት ጊዜ ጭምብል ማድረግን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ አድርገውታል።

  ለረጅም ጊዜ ጭምብል ማድረግን ሲቃወሙ የነበሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ጭምብል አድርገው ታይተዋል።