Got a TV Licence?

You need one to watch live TV on any channel or device, and BBC programmes on iPlayer. It’s the law.

Find out more
I don’t have a TV Licence.

ጭምቅ ሃሳብ

 1. የኢቲ 302 የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት
 2. ''አብራሪዎቹ ትክክለኛውን ቅደም ተከተል ተከትለዋል''
 3. የመጀመሪያ ደረጃ ከመውጣቱ በፊት ምን ተብሎ ነበር?
 4. ኬንያውያን የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ቦይንግን ሊከሱ ነው
 5. ''በአብራሪዎቻችን እንኮራለን'' የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ቀጥታ ዘገባ

የተጠቀሱት ሰዓቶቸ የዩናይትድ ኪንግደም ናቸዉ

 1. ጥያቄ ውስጥ የወደቀው ኤምካስ ምንድን ነው?

  ኤምካስ ምንድን ነው?

  ከዚህ አደጋ ጋር በተያያዘ የአውሮፕላኑ የደህንነት መጠበቂያ ሥርዓት ለሚደረገው ምርምራ ዋነኛው ጉዳይ ሆኗል።

  ኤምካስ የተባለውና አውሮፕላኑን በከፍተኛ ሁኔታ ወደላይ እንዳይወጣ ወይም ወደታች እንዳያሽቆለቁል ለመቆጣጠር እንዲቻል ተብሎ የተሰራ ሥርዓት ነው።

  በአውሮፕላኑ ዝግ ሲል በትክክለኛው አቅጣጫ እንዲበር ለማስቻል የሚፈለገውን ኃይል ለማግኘት ወደ ላይ ወይም ቁልቁል በመሄድ ወደሚፈለገው ከፍታ ይመለሳል። ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን በአውሮፕላኑ ክንፎች በኩል ያለውን የመቆጣጠሪያ አቅም በመቀነስ አውሮፕላኑ እንዲወድቅ ሊያደርገው ይችላል።

  በተለመደው ሁኔታ አውሮፕላኑን ከዝግታ ለማውጣት አብራሪው የአውሮፕላኑ አፍንጫ ወደታች እንዲያዘቀዝቅ ያደርጋል። አደጋው በደረሰበት ቦይንግ 737 ማክስ አይነት አውሮፕላኖች ላይ ያለው የመቆጣጠሪያ ሥርዓት (ኤምካስ) ግን እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ሲከሰት አውሮፕላኑን እራሱ አስተካክሎ ወደ ትክክለኛው ቦታ ይመልሰዋል።

 2. የበረራ አስተናጋጆች ከአደጋው በኋላ የነበራቸው የሥራ ስሜት

  የበረራ አስተናጋጆች ከአደጋው በኋላ በነበራቸው በረራ ምን ተሰማቸው?

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ሠራተኞች በኢቲ 302 ሕይወታቸውን ባጡ ሰዎች የተሰማቸውን ስሜት በልቅሶ ሲገልጡ
  Image caption: የበረራ አስተናጋጆች ሐዘናቸውን ሲገልጡ

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 መጋቢት 1/2011 ዓ.ም ጠዋት 2፡38 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ለሚያደርገው በረራ ጉዞ በጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወድቆ ተከስክሷል። በአደጋው የበረራ ሠራተኞችን ጨምሮ 157 ግለሰቦች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

  አደጋው በመላው ዓለም ድንጋጤን የፈጠረና ያሳዘነ ነበር። ታዲያ በረራ የዘወትር ሥራቸው ለሆነው የበረራ አስተናጋጆች ከአደጋው በኋላ በነበራቸው በረራ ምን ተሰምቷቸው ነበር?

  ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች የበረራ አስተናጋጅ ስለአደጋው የሰማችው ቤት ውስጥ ከቤተሰብ ጋር ተሰብስበው እየተጫወቱ እንደነበር ታስታውሳለች። ከዚያም ድንገት ስልኳ አቃጨለ "ተርፈሻል?" ለማለት ከጓደኛዋ የተደወለ ስልክ ነበር። የሰማችውም ያኔ ነው። "በፍፁም ላምን አልቻልኩም ነበር " ትላለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የሐዘን መግለጫ ሲያወጡ የሚወራው ሁሉ እርግጠኛ መሆኑን እንዳረጋገጠች ትናገራለች።

  ያው የሥራ ጉዳይ ነውና ይህች የበረራ አስተናጋጅ አደጋው በተፈጠረ ዕለት ማታ ወደ ታይላንድ፣ ባንኮክ በረራ ነበራት። ይሁን እንጂ ቤተሰቦቿ እንዳትሄድ አጥብቀው ተማፅነዋት እንደነበር ታስታውሳለች። "እናቴም፣ አያቴም፣ ሁሉም ዛሬ ከቤት አትወጭም! እንደዚህ ሆኖ ይወጣል? ሰው ሞቱን ነው ወይ የሚፈልገው?" ሲሉ ከልክለዋት ነበር።

  በጊዜው እርሷም ፍርሃትና ጭንቀት ገብቷት እንደነበር አልደበቀችም "ከበረራ በፊት ውይይት ስናደርግ ሕይወታቸው ያለፉት አስተናጋጆች ትዝ ይሉን ነበር፤ ድባቡ ያስጠላ ነበር፤ ከባድ ነበር ...እንቅልፍ ሁሉ ነስቶኝ ነበር" ትላለች።

  "አደጋው የደረሰው አውሮፕላኑ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ስለነበር የተከሰከሰው፤ እኛም አውሮፕላኑ ገና ሲነሳ ሁሉም እያለቀሰ ነበር፤ አገልግሎት መስጠት ተስኖን ነበር" ስትል ታስታውሰዋለች።

  ከበፊት ጀምሮ ከቤት ስወጣ "ለእግዚያብሔር አደራ ሰጥቼ ነበር የምወጣው፤ አሁንም ይህንኑ ማድረግ የዘወትር ተግባሬ ነው" ትላለች።

  የሕግ ምሩቅ የሆነችው ይህች አስተናጋጅ ቤተሰቦቿ በአደጋ ምክንያት በስጋት መኖራቸው አልቀረም ታዲያ "አባቴ በተመረቅኩበት ትምህርት እንድሠራ ማስታወቂያዎችን እያየ ሞክሪ!... እስከመቼ ተሳቀን እንኖራለን" ሲሉ ይወተውቷት ነበር። እርሷ ግን ሥራዋን አብዝታ ስለምትወደው የእነርሱን ውትዎታ ከቁብም አልቆጠረችው።

 3. ቦይንግ ማክስ ኤይት ምን ይመስላል?

  ቦይንግ ማክስ ኤይት የተሰኘው አውሮፕላን ርዝመት፣ የወንበር ቁጥር፣ ርቀትና ሌሎቹም የአውሮፕላኑ ገፅታዎች እነሆ

  የቦይንግ ማክስ ኤይት ገፅታዎች
 4. ጥቁሩ ሳጥን ምንድን ነው?

  Video content

  Video caption: ጥቁሩ ሳጥን፤ በአውሮፕላኖች ላይ የሚደርስ አደጋን ለሚደረግ ምርመራ ጠቃሚ መረጃን የሚይዝ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ነው።
 5. በኢትዮጵያና በኢንዶኔዢያ የደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ምን ያመሳስለዋል?

  በኢትዮጵያና በኢንዶኔዢያ የደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ምን ያመሳስለዋል?

  በኢንዶኔዢያው አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ ለማወቅ በተደረገው የምስለ በረራ ሙከራ ላይ እንደተደረሰበት አውሮፕላኑ ቁልቁል በአፍንጫው ባህር ላይ ሊከሰከስ መሆኑን ያወቁት ከ40 ሰከንዶች ያነሰ ጊዜ ሲቀራቸው መሆኑን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

  የኢንዶኔዢያው አውሮፕላን እ.ኤ.አ ኦክቶበር 26 ድረስ ብቻ ስድስት ያህል ችግሮች ገጥመውት ነበር። እነዚህ የገጠሙት ችግሮች በአየር ላይ እያለ ያለውን ፍጥነትና የከፍታ መረጃውን ያካትታሉ።

  አውሮፕላኑ ከክንፎቹ እና በአየር ፍሰቱ መካከል ያለውን አቅጣጫ የሚለካውንም ችግር ገጥሞት ነበር። አደጋው ከመድረሱ በፊት በነበረው በረራ አብራሪው አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞት እንደነበር የሚያሳይ ምልክት ልኳል።

  የኢንዶኔዢያ አውሮፕላን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደሚያሳየው አውሮፕላኑ አፍንጫው የመደፈቅ ሁኔታ ሲገጥመው የማስጠንቀቂያ መልዕክት የሚያሳው መሳሪያ በበረራው ውስጥ በሙሉ በርቶ ነበር።

  ይህንንም ተከትሎ ቦይንግ ኤምካስን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ለአብራሪዎች መመሪያ ቢያወጣም፤ ነገር ግን በአውሮፕላኑ ላይ ያለውን ሥርዓት የሚቆጣጠረው ሶፍትዌር ላይ ያስፈልግ የነበረው መሻሻያ ዘግይቶ ባለፈው ሳምንት ነው ይፋ የተደረገው።

  በተጨማሪም በበረራ ወቅት ችግር በሚያጋጥም ጊዜ አብራሪዎችን ሊያስጠነቅቅ ይችል የነበረው የማስጠንቀቂያ መብራትም አደጋው በደረሰባቸው ሁለቱ የኢትዮጵያ እና የኢንዶኔዢያ አውሮፕላኖች ላይ አልተገጠመም ነበር።

  ከሁለቱ አደጋው ከደረሰባቸው አውሮፕላኖች የተገኙ የበረራ መረጃዎች ተመሳሳይነት እንዳላቸው መርማሪዎች አመልክተዋል።

  የአውሮፕላኖቹን ወደ ላይ የመውጣትና የመውረድ ፍጥነት ንባብ እንደሚያመለክተው ሁለቱም አውሮፕላኖች ከፍና ዝቅ እያሉ እንደነበሩና አብራሪዎቹም ይህንን በመቆጣጠር አውሮፕላኖቹ ከፍ ብለው እንዲበሩ ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

  ሁለቱን አደጋዎች ምን ያመሳስላቸዋል?
 6. ኢቲ 302 ላይ ምን ተከሰተ?

  ኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ላይ ምን ተከሰተ?

  አውሮፕላኑ ወድቆ የተከሰከሰበት ስፍራ

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 መጋቢት 1/2011 ዓ.ም ጠዋት 2፡38 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ለሚያደርገው በረራ ጉዞ ቢጀምርም ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ችግር ገጥሞታል።

  አውሮፕላኑ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም 48 ኪሎሜትሮችን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምሥራቅ ተጉዞ ከቢሾፍቱ አቅራቢያ ባለችው ቱሉ ፈራ መንደር ውስጥ ነበር ወድቆ የተከሰከሰው።

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ ያሬድ ጌታቸው ችሎታን በተመለከተ አብራሪው ከ8ሺህ ሰዓታት በላይ የማብረር ልምድ እንዳለው በመጥቀስ "የሚያስመሰግን ብቃት" አለው ብሏል።

  አደጋው በደረሰበት ዕለትም አብራሪው ያሬድ ጌታቸው ችግር እንደገጠመውና ተመልሶ ለማረፍ ለበረራ ተቆጣጣሪዎች መልዕክት አስተላልፎ ነበር።

 7. በአደጋው ጊዜና በኋላ ሊደርጉ የሚገባቸው የሪፖርቲንግ ግዴታዎች

  አየር በረራ አደጋ ምርመራ በሚደረግበት ግዜ፤ በአደጋው ጊዜና በኋላ ሊደርጉ የሚገባቸው የሪፖርቲንግ ግዴታዎች

  በቺካጎ ስምምነት እክያ/ተቀጽላ 13 መሰረት፡ የምርመራው ባለቤት የሆነ አገር፡ አደጋው የደረሰበት ሁኔታ የሚገልጽ መረጃ ወድያውኑ ካልተላከ በስተቀር አደጋው በደረሰበት በ30 ቀናት ውስጥ ለዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) የመጀመርያ የሪፖርቱን ውጤት ይፋ ማድረግ ይጠበቅበታል።

  የመጀመርያው ደረጃ የምርመራ ውጤት ሪፖርት በምስጢር ሊያዝ ይችላል፤ አልያም አደጋው የደረሰበት ሀገር ለህዝብ ይፋ ሊያደርግ ይችላል። በምስጢር እንዲያዝም ሆነ ይፋ እንዲሆን የአገሪቱ ፍላጎትና መብት ነው።

  እንዲሁም ደግሞ ምርመራ እንዲካሄድ እያደረገ ያለው ሃገር፣ በተቻለ መጠን በ12 ወራት ውስጥ የመጨረሻ ደረጃ ምርመራ ለህዝብ ይፋ ማድረግ ይጠበቅበታል።

  ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን፣ ቢያንስ በየዓመቱ ምርመራው የደረሰበትን ደረጃና ያለበትን ሁኔታ እንዲሁም በሂደት ያጋጠሙ ችግሮች ተከታትሎ በዝርዝር ለህዝብ የማሳወቅ ግዴታ አለበት።

  ICAO Logo
 8. ጥቁሩ ሳጥን (ብላክ ቦክስ) ምንድን ነው?

  ጥቁሩ ሳጥን (ብላክ ቦክስ) ምድን ነው? አገልግሎቱስ?

  ጥቁሩ ሳጥን ፤ በአውሮፕላኖች ላይ አደጋ ከደረሰ በኋላ ለሚደረግ ምርመራ ጠቃሚ መረጃን የሚይዝ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ሲሆን በአውሮፕላኖች የኋለኛ ክፍል ውስጥ ይገኛል።

  ጥቁሩ ሳጥን ወይም በአየር ትራንስፖርት ባለሙያዎች ዘንድ የበረራ መረጃ መመዝገቢያ ተብሎ የሚታወቀው ከአደጋ በኋላ በቀላሉ ለማግኘት እንዲቻል ደማቅ ብርቱካናማ ቀለም አለው።

  መጠኑም የጫማ መያዣ ካርቶን የሚያክል ሲሆን ፤ በውስጡም ሁለት ክፍሎችን ይዟል። የበረራ መረጃ መመዝገቢያ እና የበረራ ክፍል ድምፅ መቅጃ።

  የበረራ መረጃ መመዝገቢያው የአየር ሙቀት መጠን፣ ፍጥነት፣ ከፍታ፣ የነዳጅ መጠንና የመሳሰሉትን የ25 ሰዓታት መረጃ ይይዛል።

  የበረራ ክፍል ድምፅ መቅጃ የበረራ ሠራተኞችን ንግግር፣ የአውሮፕላኑን የሞተር ድምፅና ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር የተደረጉ ምልልሶችን ጨምሮ ሁሉንም ድምፆች ቀርፆ ይይዛል።

  የድምፅ መቅጃው ለሁለት ሰዓታት ያህል ድምፅ የሚቀዳ ሲሆን መርማሪዎች አደጋው በቴክኒክ ችግር ይሁን በሰዎች ስህተት መከሰቱን ለመለየት ያግዛል።

  በጥቁሩ ሳጥን ውስጣዊ ክፍል መረጃውን ማስቀመጫ ሰሌዳ በሙቀት ማገጃ ተሸፍኖ ይገኛል። ይህም እስከ 1000 ዲግሪ ሴሊሺየስ የሚደርስ ሙቀትን ለአንድ ሰዓት የሚቋቋም ሲሆን በጨዋማና በሌሎች ፈሳሾች ውስጥ ሳይበላሽ እንዲቆይ ተደርጎ የተሠራ ነው።

  ሳጥኑ ውሃ ውስጥ ከገባበት ጊዜ አንስቶ እንደ አውሮፕላኑ ዓይነት ከ30 እስከ 90 ቀናት ድረስ የማይቋረጥ ፤ ያለበትን ቦታ አመላካች የአልትራሳውንድ ምልክት ይሰጣል።

  አንዳንዶች ጥቁሩ ሳጥን መረጃዎችን በሳተላይት በኩል ወዲያው ማስተላለፍ ቢችል ከአደጋ በኋላ ሳጥኑን በመፈለግ የሚጠፋውን ጊዜ ያስቀራል ይላሉ።

  ጥቁሩ ሳጥን
 9. ''በአብራሪዎቻችን እንኮራለን'' የኢትዮጵያ አየር መንገድ

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን እቀበላለሁ አለ

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ የደረሰውን አደጋ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ የመጀመሪያ ደረጃውን የምርመራ ውጤት እንደሚቀበለው ገልጿል።

  አየር መንገዱ የምርመራ ቡድኑን ትጋት የተሞላበትን ሥራ አድንቆ፤ በመጀመሪያ ደረጃው ሪፖርተ ላይ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች በቦይንግ የሚታዘዘውንና በአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት ባለስልጣን ተቀባይነት ያለውን የደህንነት ቅደም ተከተል ተግባራዊ በማድረግ በበረራው ላይ ያጋጠማቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ በቁጥጥር ስር ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸው በግልጽ አመልክቷል ሲል አስፍሯል።

  አብራሪዎቹ ተገቢውን እርምጃ ቢወስዱም ያጋጠማቸው ያልተቋረጠ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ማሽቆልቆል ችግርን ለመቆጣጠር ሳይችሉ መቅረቱን ጠቅሷል።

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ተወልደ ገብረማሪያምም ከመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ጋር በተያያዘ “ፓይለቶቹ እጅግ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚጠበቅባቸውን ተገቢ እርምጃ በመውሰድ ያላቸውን ከፍ ያለ ሙያዊ ብቃት በማስመስከራቸው አየር መንገዱ እንደሚኮራባቸው ተናግረዋል።

  View more on twitter
 10. እነማን በኢቲ 302 ምርመራ ላይ ተሳተፉ?

  ዳግማዊት ሚገስ

  ከደቂቃዎች በፊት የትራንስፖርት ሚንስትሯ ዳግማዊት ሞገስ የኢቲ 302 መከስከስ ምክንያት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ሲያቀርቡ በዓለም በምረመራው ላይ የትኞቹ አካላት ተሳታፊ እንደነበሩ ይፋ አድርገዋል።

  በዚህም መሠረት አቀፉ አሠራር መሠረት አደጋው የተከሰተበት ሃገር በዋና ሰብሳቢነት እያስተባበረ ሂደቱ ውስጥ የሚሳተፉት አካላት አምራቹ አገር፣ አውሮፕላኑን ዲዛይን ያደረገው ሃገር፣ የመዘገበው እና አውሮፕላኑን የገዙ ሃገራት ናቸው ብለዋል።

  በተጨማሪም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ምርመራውን የሚመራው ሃገር ሲወስን ባለሙያ የሆኑና እውቅና የተሰጣቸው አካላት ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ሚኒስትሯ እንዳስቀመጡት በዚያ መሠረት ''ሥራውን የሠራነው ከአሜሪካው ናሽናል ትራንሰፖርት ሴፍቲ ቦርድ ኦፍ አሜሪካ ጋር በመሆን ነው። ይህ ተቋም ሲመጣ ቦይንግም ከአሜሪካ ሲቪል አቬሽን ተቋምም ሰዎች ተካተው 18 አባላት ያሉት የባለሙያዎችን ቡድን ይዞ መጥቷል።''

  እነርሱ የምርመራ ቡድኑ አባል ናቸው። በተጨማሪም አደጋው በተከሰተበት ሃገር ጥሪ የመጡ ከፈረንሳይ የአውሮፕላን አደጋ የሚያጣራ ቡድን፣ መረጃው ወደ ሃገር ቤት ከመጣ በኋላ ደግሞ የአውሮፓ ሕብረት አቬሽን ሴፍቲ ጋር በመሆን ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በጋራ ተሠርቷል። በዓለም አቀፉ አሠራር መሠረትም ዛሬ በ26ኛው ቀን መግለጫው ተሰጥቷል።

  የተጠቃለለው ሪፖርት ዋና ዋና እውነታዎችን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይወጣል።

 11. ኬንያውያን የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ቦይንግን ሊከሱ ነው

  ከኢቲ 302 አደጋ ጋር በተያያዘ ኬንያውያን የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ቦይንግን ሊከሱ ነው

  ኢቲ 302 በተከሰከሰበት ስፍራ የፌደራል ፖሊስ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰብስበው
  Image caption: አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ስፍራ

  በኢቲ 302 መከስከስ ሕይወታቸውን ከአጡት 157 ሰዎች መካከል 32ቱ ኬንያውያን ነበሩ። የሟች ቤተሰቦች እንደሚሉት ከሆነ አየር መንገዱ እና ቦይንግ ለመሞታቸው ኃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው። የሟች ቤተሰቦች ኬንያ እና አሜሪካ በሚገኙ የጠበቃ ቡድን የተወከሉ ሲሆን ክሱንም በአሜሪካ እንደሚሆን እንደሚመሰርቱ አሳውቀዋል።

 12. የተጎጂ ቤተሰቦችን ለመካስ ምን ታስቧል?

  ለተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ ለመስጠት ምን ታስቧል ተብለው የተተየቁት ሚንስትሯ፤ ''የካሳ ጉዳይ ህጉን ተከትሎ ይፈፀማል። ሕጋዊ አሰራሩን ተከትሎ በአቃቤ ህግ በኩል ይፈፀማል።'' ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

  አክለውም አየር መንገዱ ከአደጋው በኋላ የገበያ መቀዛቀዝ እንዳልገጠመው ተናግረዋል።

 13. ''ምርመራውን የዓለም አቀፍ አሰራርን ተከትሎ የተሰራ ነው''

  ዳግማዊት ሞገስ

  ምርመራውን የዓለም አቀፍ አሰራርን ተከትሎ የተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ለምርመራው የሚያስፈልጉ ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

  አደጋው የተከሰተበት ሃገር በዋናነት ምርመራውን ያስተባብረዋል፣ አውሮፕላኑ አምራች፣ አውሮፕን ዲዛይን ያደረገው ሃገር፣ አውሮፕላኑ የተመዘገበበትና የአውሮፕላኑ ባለቤት የሆነው ሃገር እንዲሳተፉ ይጠበቃል።

  በዚህም መሰረት ከኢትዮጵያ፣ ከአሜሪካ፣ ከፈረንሳይ እና ከአውሮፓ የአየር ትራንስፖርት ባለስልጣን አጣሪ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። በተለይ ከአሜሪካ በኩል 18 የሚደርሱ መርማሪዎች በሂደቱ መሳተፋቸውን ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

  በተለይ የፈረንሳይ ባለሙያዎች የአውሮፕላኑን መረጃ መመዝገቢያውን በተገቢው ሁኔታ ለምርመራ እንዲሆን በመገልበጥ ከተሳተፉ በኋላ በምርመራው እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦላቸው ተሳትፈዋል።

 14. የደህንነት ምክረ ሀሳቦች

  በመርማሪ ቡድኑ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች

  የመርማሪ ቡድን

  በትራንስፖርት ሚንስትሯ በኩል የተረበው የደህንነት ምክረ ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸው

  - ተደጋጋሚ የሆነ እና አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስቸገረ አፍንጫውን የመድፈቅ ሁኔታ አምራቹ በድጋሚ ሊፈትሸው ይገባል

  - ይህ የአውሮፕላን ስሪት የሚመለከታቸው አካላት የበረራ ቁጥጥር ስርዓት እንዲያረጋግጡ

 15. ሰበርየኢቲ 302 የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶች ይፋ ሆኑ

  የኢቲ 302 መከስከስ ምክንያት የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶች ይፋ ሆኑ

  የኢቲ 302 የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶች ይፋ ሆኑ
  Image caption: የኢቲ 302 የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶች ይፋ ሆኑ

  የትራንስፖርት ሚንስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ኢቲ 302 የተከሰከሰበትን የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶች ይፋ አደረጉ።

  ሚንስትሯ የሚከተሉትን ነጥቦች አንስተዋል።

  -አውሮፕላኑ የፀና መብረር የሚያስችል ፈቃድ አለው

  -አብራሪዎቹ ይህንን በረራ ማድረግ የሚያስችላቸው ብቃትና የምርመራ ፈቃድ አላቸው

  -አውሮፕላኑ ለበረራ ሲነሳ በትክክለኛ መስመር ለመብረር በሚያስችለው ሁኔታ ላይ ነበር

  -አብራሪዎቹ አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለውን ቅደም ተከተል ሰርተዋል ነገር ግን አልቻሉም።

 16. የኢቲ 302 ሪፖርትን በመጠባበቅ ላይ

  የተከሰከሰውን አውሮፕላን ተከትሎ የተደረገውን ምርመራ ውጤት ይፋ ሊደረግ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

  በአዲስ አበባ በትራንስፖሪት ሚኒስትር ቢሮ ውስጥ የተለያዩ የሃገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሪፖርቱን በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

  እኛም በስፍራው ተገኝተን የምርመራውን ውጤት እየተጠባበቅን ስለሆነ እንደደረሰ በቀጥታ እናቀብላችኋለን።

  በመንገድ ትራንስፖት መሥሪያ ቤት
  መግለጫውን እየተጠባበቁ ያሉ ጋዜጠኞች
 17. የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ከመውጣቱ በፊት ምን ተብሎ ነበር?

  Ethiopian

  ከሳምንታት በፊት አደጋ ስለደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎች ሲወጡ ነበር። አደጋው ከመድረሱ በፊት በሁለቱ አብራሪዎች መካከል የተደረገን ምልልስ ጠቅሶ ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው፤ የአውሮፕላኑ የሬዲዮ ግንኙነት ከመቋረጡ በፊት አንደኛው አብራሪ "ቀና አድርገው! ቀና አድርገው!" በማለት ለባልደረባው ሲናገር ተሰምቷል።

  በአውሮፕላኑ ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለውን ሥርዓት አብራሪዎቹ ቢጠቀሙም አደጋውን ለማስቀረት እንዳልተቻለ እየተደረገ ላለው ምርመራው ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለጋዜጣው ተናግረዋል።

  አደጋ ከደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የበረራ መረጃ መሰብሰቢያ ሳጥን ውስጥ ከተገኘ የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ መሰረት አደጋው ከመድረሱ በፊት እያሽቆለቆለ ያለውን አውሮፕላን ሊታደግ ይችላል የተባለው የአውሮፕላኑ ሥርዓት እንዲሰራ ተደርጎ እንደነበር አመልክቷል።

  ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል የተባለው ጋዜጣ ስለአደጋው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ስማቸው ያልተጠቀሱ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የአውሮፕላኑ ከፍታና ዝቅታ ለመቆጣጠር እንዲያስችል ተደርጎ የተሰራው የኮምፒውተር ሥርዓት ችግር እንዳለው አመልክቷል።

 18. የኢቲ 302 ቅድመ-ሪፖርት

  የኢቲ 302 ሟቾች

  እንደምን አረፈዳችሁ?

  የትራንስፖርት ሚንስቴር ዛሬ 04፡30 ላይ የኢቲ 302 መከስከስ ምክንያትን ሲያጣራ የነበረው ቡድን ቅድመ-ሪፖርቱን ያቀርባል ብሏል።

  እኛም ይህንኑ እየተከታተልን የተለያዩ ዘገባዎችን እናደርሳችኋላን።