Got a TV Licence?

You need one to watch live TV on any channel or device, and BBC programmes on iPlayer. It’s the law.

Find out more
I don’t have a TV Licence.

ቀጥታ ዘገባ

የተጠቀሱት ሰዓቶቸ የዩናይትድ ኪንግደም ናቸዉ

 1. በኤርትራ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 6 ደረሰ

  የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ

  ኤርትራ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ማግኘቷን አስታወቀች።

  የኤርትራ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ሁለቱም ግለሰቦች ባለፈው ሰኞ ኤር አረቢያን በመጠቀም ከዱባይ ወደ አስመራ የገቡ ናቸው።

  በዚህም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በአጠቃላይ 6 ደርሷል።

  በአገሪቱ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መንግስት የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

  በመሆኑም ከነገ ጀምሮ ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ኮሌጅ ድረስ ያሉ የትምህርት ተቋማት እንዲዘጉ ተወስኗል።

  በተጨማሪም የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫዎች እንዲቋረጡ ተደርጓል።

  ኤርትራ ከትናንት ዕኩለ ሌሊት ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ የሚደረጉ በረራዎችን ማገዷ ይታወቃል።

 2. ሰበርበኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን ተሻገረ

  ቢቢሲ አማርኛ

  በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሆነ።

  በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ መሠረት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 510,108 ሆኗል።

  ቫይረሱ የሚሰራጭበት መጠን ፍጥነት አሁንም እንደጨመረ ነው።

  እንደማሳያም፤

  ቫይረሱን የመጀመሪያዎቹን 100 ሺህ ሰዎች ለመያዝ 67 ቀናት ነበር የወሰደበት።

  2ኛውን 100ሺህ ሰው ለመያዝ 11 ቀናት

  3ኛውን 100ሺህ ሰው ለመያዝ 4 ቀናት

  4ኛውን 100ሺህ ሰው ለመያዝ 3 ቀናት እንዲሁም፤

  5ኛውን 100ሺህ ሰው ለመያዝ የወሰደበት 2 ቀናት ብቻ ናቸው።

  ቻይና 81,782፣ ጣሊያን 80,539፣ አሜሪካ 75,233 አንዲሁም ስፔን 56,197 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በማስመዝገብ በቅድመ ተከተል ተቀምጠዋል።

  22,993 በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸውን ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ ያሳያል።

 3. ዛሬ በጣሊያን የሟቾች ቁጥር 662 ሆኗል

  ሳን ጁሴፔ ቤ/ክርስቲያን በኮሮናቫይስ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች አስክሬን ወደ ማረፊያ ቦታቸው ከመወሰዳቸው በፊት። ዛሬ መጋቢት 17 ቤርጋሞ ጣሊያን።
  Image caption: ሳን ጁሴፔ ቤ/ክርስቲያን በኮሮናቫይስ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች አስክሬን ወደ ማረፊያ ቦታቸው ከመወሰዳቸው በፊት። ዛሬ መጋቢት 17 ቤርጋሞ ጣሊያን።

  በኮሮናቫይረስ ምክንያት በጣሊያን የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ አይደለም።

  የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ባለፉት 24 ሰዓታት የሟቾች ቁጥር 662 ደርሷል።

  ይህ በእንዲህ እንዳለ በኮሮናቫይረስ ስርጭት ክፉኛ ተጎድተው ከነበሩት ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል የቫይረሱ ስርጭት ወደ ደቡብ ጣሊያን በፍጥነት እየተሻገረ ነው።

  ሮም የምትገኝበት ላዚዮ እና ካምፓኒአ ግዛቶች በቀጣይ በርካቶች ህይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉባቸው የጣሊያን ደቡባዊ ግዛቶች ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት ሰፍኗል።

 4. ኮሮናቫይረስ፡ የአፍሪካ ውሎ

  ኡጋንዳ የንግድ ተቋማት እንዲዘጉ አዛለች። ፖሊስም ይህን ለማስፈጸም ሰዎችን በካምፓላ ጎዳና ላይ ሲያሯሩጥ ታይቷል።
  Image caption: ኡጋንዳ የንግድ ተቋማት እንዲዘጉ አዛለች። ፖሊስም ይህን ለማስፈጸም ሰዎችን በካምፓላ ጎዳና ላይ ሲያሯሩጥ ታይቷል።

  በ46 የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ መሰራጨቱ ተረጋግጧል።

  የአፍሪካ አገራትም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ዘርፈ ብዙ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።

  ኡጋንዳ፡ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን አግዳለች። የንግድ ተቋማት ድርጅቶቻቸውን እንዲዘጉ መንግሥት ውሳኔ አስተላልፏል። ፖሊስም ይህን ለማስፈጸም ሰዎችን በካምፓላ ጎዳና ላይ ሲያሯሩጥ ታይቷል።

  ናይጄሪያ፡ የ200 ሚሊዮን ዜጎች መኖሪያ የሆነችው ምዕራብ አፍሪካዊት ናይጄሪያ፤ በአገር ውስጥ የሚደረጉ ጉዞዎችን እንደምታስቆም ይፋ አድርጋለች።

  ኬንያ፡ የመጀመሪያው በኮሮናቫይረስ የሞተ ሰው ዛሬ አስመዝግባለች።

  ደቡብ አፍሪካ፡ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ እንቅስቃሴን የማገድ አዋጅ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ ይጀምራል። በድንጋጤ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በሰፊው ሸመታ ላይ ይገኛሉ። በሎተሪ 7.4 ሚሊዮን ራንድ ያሸነፈው ደቡብ አፍሪካዊውም ሽልማቱን ለመውሰድ የመንግሥት ድንጋጌ እስኪያልቅ 3 ሳምንታት መጠበቅ ይኖርበታል ተብሏል።

 5. ቻይና ለውጪ አገር ዜጎች ድንበሯን ዝግ አደረገች

  በቻይናዋ ሸንጋይ አየር ማረፊያ የአየር ማረፊያ ሠራተኛ ከተጓዥ ቻይናዊ ጋር
  Image caption: በቻይናዋ ሸንጋይ አየር ማረፊያ የአየር ማረፊያ ሠራተኛ ከተጓዥ ቻይናዊ ጋር

  የቻይና መንግሥት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የውጪ አገር ዜጎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ክልከላ አደረገ።

  የቻይና ቪዛም ይሁን በቻይና የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው የውጪ አገር ዜጎች ወደ ቻይና መግባት አይፈቀድላቸውም ተብሏል።

  የቻይና መንግሥት ከዚህ ውሳኔ የደረሰው በአሁኑ ወቅት በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የሚረጋገጡ ሰዎች፤ ከሌሎች አገራት ወደ ቻይና የገቡ እንጂ በቻይና የሚገኙ ሰዎች ባለመሆናቸው ነው ተብሏል።

  ክለከላው ከሁለት ቀናት በኋላ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል።

 6. ፓንጎሊን ከኮቪድ-19 ጋር ግነኙነት ያለው ቫይረስ ተሸካሚ ነች ተባለ

  ፓንጎሊን
  Image caption: ፓንጎሊን

  ፓንጎሊን የተባለችው አጥቢ እንስሳ ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ ቫይረስ ተሸካሚ መሆኗን አንድ ጥናት አረጋገጠ።

  አያይዞም የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የፓንጎሊን ዝውውር እና ግብይት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል።

  ከዚህ ቀደም ለኮሮናቫይረስ መነሾ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩት ፓንጎሊን እና የሌሊት ወፍ ናቸው።

  ጉንዳን በሊታዋ ፓንጎሊን በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በሕገ-ወጥ መንገድ የምትዘዋወር እና የምትሸጥ እንስሳ ስትሆን በመጥፋት አደጋ ላይ ያለች አጥቢም ነች።

  ፓንጎሊን እስያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ለመድሃኒትነት ትፈለጋለች። በሌላ በኩል የፓንጎሊን ስጋ ለበርካቶች ወደር የማይገኝለት ምግብ ነው።

 7. የኮሮናቫይረስ ከሰሜናዊ ጣልያን ወደ ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል እየተዛመተ ነው ተባለ

  ጣሊያን አምቡላንስ

  በኮሮናቫይረስ ስርጭት ክፉኛ ተጎድታ የነበረችው ሎምባርዲ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀነሷል ተባለ።

  ምንም እንኳ በሰሜናዊቷ ጣሊያን የኮሮናቫይረስ ስርጭት መጠን ቀነሰ ቢባልም በደቡባዊ ጣሊያን እየሆነ ያለው ግን ሌላ ነው።

  በደቡባዊ ጣሊያን የቫይረሱ ስርጭት በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ ነው ተብሏል።

  ሮም የምትገኝበት ላዚዮ እና ካምፓኒአ ግዛቶች በቀጣይ በርካቶች ህይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉባቸው ግዛቶች ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት ሰፍኗል።

  ጣሊያን እስካሁን 7,503 የሚሆኑ መሞታቸውን እና 74,386 ደግሞ መያዛቸውን ሪፖርት አድርጋለች።

 8. የG20 አገራት 5 ትሪሊዮን ዶላር ወደ ዓለም ገበያ ፈሰስ ሊያደርጉ ነው

  ኦሳካ ተካሂዶ በነበረው የG20 አገራት ስበሰባ ላይ የተሳተፉ አገራት ሰንደቅ ዓላማ
  Image caption: ኦሳካ ተካሂዶ በነበረው የG20 አገራት ስበሰባ ላይ የተሳተፉ አገራት ሰንደቅ ዓላማ

  የG20 አገራት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተዳከመውን የዓለም ኢኮኖሚ ለመደገፍ 5 ትሪሊዮን ዶላር ወደ ዓለም ገበያ ፈሰስ ለማድረግ ቃል ገቡ።

  ይህ የአገራቱ ውሳኔ ይፋ የተደረገው በሳዑዲ አረቢያ ተካሂዶ በተጠናቀቀው የቪዲዮ ኮንፍረንስ ላይ ነው።

  ሁለቱን የሰሜን አሜሪካ አገራት ጨምሮ፤ የደቡብ አሜሪካዎቹ አርጀንቲና፣ ብራዚል እና ሜክሲኮ የG20 አባል አገራት ሲሆኑ፤ ከመካከለኛው ምስራቅ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ ተጠቃሽ አባል አገራት ናቸው። ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ እና ሕንድ ከኢሲያ በአባላት ዝርዝር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ብቸኛዋ አፍሪካዊት የG20 አባል አገር ነች።

 9. የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መቼ ይቆማል?

  Coronavirus

  በየአገራቱ ለወትሮ የሰው ግርግር የሚያደምቃቸው ከተሞችና ቦታዎች የኮሮናቫይረስ መምጣትን ተከትሎ ሁሉም ነገር ፀጥ ረጭ ብሏል።

  የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቆሞ ህይወት ወደነበረበት የሚመለሰው መቼ ነው? ብዙዎች በአእምሯቸው የሚያውጠነጥኑት ነገር ነው።

  የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እንግሊዝ በሶስት ወራት ውስጥ የቫይረሱን ስርጭት ትገታለች ብለዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር ቢቻልም ግን የቫይረሱ ማብቂያ ገና እንደሆነ ተናግረዋል።

  ወረርሽኙን ማስቆም ረዥም ጊዜ ምናልባትም ዓመታት ሊወስድ ይችላል ሲሉም ፍርሃታቸውን ገልፀዋል።

  የዚህን ዘገባ ተጨማሪ ይህን በመጫን ያንብቡ

 10. ሰበርባለፈው ሳምንት ብቻ 3 ሚሊዮን አሜሪካውያን ሥራ አጥ ነን አሉ

  በአሜሪካ በሳለፍነው ሳምንት ብቻ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሥራ አጥ ሆነናል ማለታቸውን ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘገበ።

  እነዚህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የአሜሪካ መንግሥት ተቀጣሪ ላልሆኑ ዜጎቹ የሚሰጠውን ጥቅማ ጥቅም እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል።

  ይህ ክስተት በአሁኑ ወቅት የዓለምን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየጎዳ ከሚገኘው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ተገልጿል።

 11. ኮሮናቫይረስ እንዳለብን እንዴት ማውቅ እንችላለን?

  Video content

  Video caption: ኮሮናቫይረስ እንዳለብኝ እንዴት ላውቅ እችላለሁ?

  የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን ከሌሎች የበሽታ ምልክቶች የሚለያቸው ምንድን ነው?

  አንድ ሰው የተወሰኑ ምልክቶችን በማየቱ 'የኮሮናቫይረስ ይኖርብኝ ይሆን?' ብሎ እራሱን ሊጠረጥር ይገባል?

  ይህ በዋናነት የሚረጋገጠው በምርመራ ቢሆንም፤ የተወሰኑት ምልክቶችን ቀድሞ ማወቁ በፍጥነት ወደ ሕክምና ለመሄድ ያግዛል።

 12. የአሜሪካ ኤምባሲ የቆንስላ አገልግሎት ክፍል ላልተወሰነ ጊዜ ተዘጋ

  US Embassy Addis Ababa

  በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት የቆንስላ አገልግሎት ክፍሉን ላልተወሰነ ጊዜ ዘጋ።

  ከዚህ ውጪ ያሉት የኤምባሲው ክፍሎች ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ቢቢሲ ከኤምባሲው ተረድቷል።

  ኤምባሲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከቫይረሱ ስርጭት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ስርጭቱን ለመግታት ከሚያደርገው ጥረት አንጻር ኤምባሲውን በጊዜያዊነት የቆንስላ አገልግሎቱን ማቋረጥ አስፈልጓል ብሏል።

  ኤምባሲው ለዜጎቹ ጭምር ያደረግ የነበረውን የፓስፖርት እድሳት፣ ከአገር ውጪ የወሊድ እና የሞት ምዝገባን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን እንደማይሰጥ አስታውቋል።

 13. በአሜሪካ በከሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ 1000 አለፈ

  AFP

  በአሜረካ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ 1ሺህ በላይ ሆኗል።

  እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ አሁናዊ አሃዝ ከሆነ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 1046 ነው።

  ከእነዚህ መካከል በኒው ዮርክ ብቻ 280 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።

  ኒው ጄርሲይ እና ካሊፎርኒያ ከኒው ዮርክ በመቀጥል በበሽታው ብዙ ሰዎች የተያዙባቸው ግዛቶች ናቸው።

 14. ኮሮናቫይረስ ከሌሎች ቫይረሶች በምን ይለያል?

  ኮሮናቫይረስ ከሌሎች ቫይረሶች በምን ይለያል? በርካታ የቫይረስ አይነቶች አሉ፤ ኮሮናቫይረስ ግን ከእነዚህ ቫይረሶች የሚለይባቸው የራሱ ምልክቶች አሉት። ምልክቶቹና አጠቃላይ የቫይረሱ ባሕሪን እንዲሁም የመከላከያ መንገዶችን ማወቅ በጣም ይጠቅማል።

  Video content

  Video caption: ኮሮናቫይረስ ከሌሎች ቫይረሶች በምን ይለያል?
 15. በትግራይ ክልል እንቅስቃሴዎች ለሁለት ሳምንታት ታገዱ

  ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል
  Image caption: ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል

  በትግራይ ክልል ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም በገጠርና በከተማ መካከል የሚደረግ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ እንዲቀረጥ መወሰኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል አስታወቁ።

  ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ ትናንት የትግራይ ክልል መንግሥትና ሥራ አስፈጻሚ የኮረናቫይረስ በሽታን ለመከላከልና ለመግታት ያወጣውን የአስስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አብራርቷል።

  በዚህም መሰረት በትግራይ ክልል ውስጥ ከከተማ ወደ ከተማ፣ ከገጠር ወደ በከተሞችና በገጠሮች መካከል የሚደረግ ማናቸውም እንቅስቃሴ እንዲቆም ተውስኗል ብለዋል።

  በተጨማሪም ህዝብ በብዛት የሚሰበብባቸው የገበያ ቦታዎች መታገዳቸውንና ሠርግና ተዝካር የመሳሰሉ ማኅበራዊ ሥነ ሥርዓቶች እንዳይካሄዱ መወሰኑን ዶ/ር ደብረጽዮን አብራርተዋል።

  ይህ ክልከላ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ሊራዘም እንደሚችልም አመልክተዋል።

  በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን 12 በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፤ በትግራይ ክልል በበሽታው ተጠርጥረው ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች ውጪ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች የሉም።

 16. የ97 ዓመቷ አዛውንት ከኮሮናቫይረስ በሽታ አገገሙ

  በጨለማው መካከልም ብርሃን መኖሩን የሚያሳይ መልካም ዜና ከወደ ደቡብ ኮሪያ ተሰምቷል።

  የደቡብ ኮሪያው ዮንሃፕ ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ በአገሪቱ አንዲት የ97 ዓመት አዛውንት በኮሮናቫይረስ ተይዘው ነበር፤ ነገር ግን ተከታታይ የህክምና ድጋፍ አግኝተው በማገገም ወደ ጤናቸው መመለስ ችለዋል።

  ስለአዛውንቷ የተባለ ሌላ ተጨማሪ ነገር የለም፤ ነገር ግን ከቫይረሱ በማገገም ብቸኛዋ በእድሜ የገፉ ሴት አይደሉም።

  በመጋቢት ወር መጀመሪያ አካባቢ አንድ የ100 ዓመት አዛውንት በተመሳሳይ ከቫይረሱ ማገገማቸውን የቻይናው ዥንዋ የዜና ወኪል ዘግቧል።

  ዜናው እንዳለው እስካሁን የኮሮናቫይረስን አሸንፈው ወደ ቀድሞ ጤናቸው መመለስ የቻሉት ብቸኛው የእድሜ ባለጸጋ ናቸው ብሏል።

 17. ቀላሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መከላከያ መንገድ፡ እጅን መታጠብ

  ማንኛውንም አይነት ነገሮች ከነኩ በኋላ እጅዎን አዘውትረው በሳሙናና በውሃ በደንብ አድርገው ይታጠቡ።

  View more on facebook
 18. ኡጋንዳ በሕዝብ ማመላለሽ ተሽከርካሪዎች እገዳ ጣለች

  የሕዝብ ትራንስፖርት

  የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በሕዝብ ማመላለሽ ተሽከርካሪዎች ላይ ለ14 ቀናት የሚቆይ እገዳ መጣሉን አስታወቁ።

  ፕሬዝዳንቱ በቴሌቪዥን ቀርበው እንደተናገሩት እገዳው ከሕዝብ ማመላለሸ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ የሞተር ሳክል ታክሲዎችንም የሚመለከት ነው።

  የግል ተሽከርካሪዎችም ከሦስት በላይ ሰዎችን ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ ተከልክለዋል።

  በተጨማሪም ለወትሮው በሰዎች የሚጨናነቁት የአገሪቱ ገበያዎች የምግብ ምርቶችን ብቻ እንዲሸጡ ተፈቅዶላቸዋል።

  ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንቱ ትምህርት ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶችና ሲኒማ ቤቶች እንዲዘጉ ያዘዙ ሲሆን ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ከአንድ ወር በላይ እንደይካሄዱ ከልክለዋል።

  በመዲናዋ ካምፓላ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩት በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ የሚሰሩ ሰዎች በፖለቲከኞች ዘንድ ከፍ ያለ ተሰሚነት ያላቸው ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ በእነሱ ላይ ብዙ ጊዜ እገዳ ላለመጣል ጥንቃቄ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

  ምናልባትም የጣሉት እገዳ ለሁለት ሳምንታት ብቻ መሆኑ ከሚያደርጉት ጥንቃቄ የተነሳ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

  በኡጋንዳ የስምንት ወር ህጻንን ጨምሮ 14 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል።

 19. ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ያዩት ነገር አሳስቧቸዋል

  ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ

  ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አዲስ አበባ ውስጥ ተዘዋውረው በሽታውን ለመከላከል በሕዝቡ መደረግ ያለባቸው ነገሮች ሙሉ ለሙሉ እየተደረጉ እንዳልሆ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ገልጸዋል።

  "የሚጠጋን ቫይረስ የለም ሲሉ የነበሩ አገራት ያሉበትን እያየን አንዘናጋ" ያሉት ፕሬዝደናንቷ የተመለከቱት ነገር ሳያሳስባቸው አልቀረም፤ ስለዚህም በባለሙያዎች የተሰጡ "መመሪያዎችን በመተግበር በኩል ገና ብዙ ይቀረናል" በማለት ጽፈዋል።

  ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ጨምረውም የበሽታው ምርመራ በስፋት ባለመደረጉ ያለው ትክለኛ ሁኔታ ስለማይታወቅ በአገር ደረጃ ተቀናጅቶ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

  View more on twitter
 20. በሸቀጦች ላይ ጭማሪ በሚያደርጉ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወሰድ ከንቲባው ገለጹ

  የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰድን እርምጃ በቅርብ እንደሚከታተሉት ገለጹ።

  ምክትል ከንቲባው በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ እንዳሰፈሩት “ጤፍ፣ ሳሙና፣ ውሃና የመሳሰሉት ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የምታደርጉ ነጋዴዎች ድርጊታችሁ ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን ከሰብአዊነት ውጪ ነው” ብለዋል።

  አስተዳደራቸው ይህንን ጉዳይ እየተመለከታተለው መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው “እኔ እራሴ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ከፍ ያለ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በቅርብ እከታተላለሁ” ብለዋል።

  ጨምረውም “እንደ ሰው በሌሎች ችግር ላይ ማትረፍን አንፈቅድም” በማለት ድርጊቶቹ ተገቢ ያልሆነና ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖችንን የሚጎዳ መሆኑን ገልጸው “ይህንን ፈተና እናልፈዋለን፤ ግለሰቦችና የንግድ ተቋማትም በአስቸጋሪ ጊዜ ለሰብአዊነትና ለፍቅር በሚያደርጉት ተግባራት ይመዘናሉ” ብለዋል።

  View more on twitter