Got a TV Licence?

You need one to watch live TV on any channel or device, and BBC programmes on iPlayer. It’s the law.

Find out more
I don’t have a TV Licence.

ቀጥታ ዘገባ

የተጠቀሱት ሰዓቶቸ የዩናይትድ ኪንግደም ናቸዉ

 1. ጣልያን በሳምንቱ ከፍተኛ የሚባለውን ሞት መዘገበች

  ሁለት መነኮሳት ቀብር ላይ

  ጣልያን በሳምንቱ ከፍተኛ የሚባለውን የ262 ሰዎች ሰዎች መዝግባለች።

  በባለፈው ሳምንት በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጠነኛ መሻሻል ታይቶባት በነበረችው ጣልያን በባለፉት ሃያ አራት ሰአታት ውስጥ ከፍተኛ የተባለው 262 ሞቶች ተከስቷል።

  ይህም አሃዝ በሃገሪቷ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 31 ሺህ 368 አድርሶታል፤ ይህም ቁጥር ከአሜሪካና ከዩናይትድ ኪንግደም በመከተል ሶስተኛ አድርጓታል።

  በጣልያን ውስጥ በብሄራዊ ደረጃ የሚጠቀሰው የሟቾች አሃዝ በመንከባከቢያ ማዕከላት በኮሮናቫይረስ የሞቱን አያካትትም።

  ምንም እንኳን አሁንም ቢሆን የሟቾች አሃዝ ከፍተኛ ቢሆንም ጣልያን ያወጣቻቸውን ህጎቿን በተወሰነ መልኩ ማላለት ጀምራለች። ዜጎቿ ቤተሰብ፣ ዘመድ እንዲጎበኙ ከመፍቀድ በተጨማሪ፤ ፓርኮች፣ ፋብሪካዎችና የተለያዩ ህንፃዎችም አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

 2. በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ስራ ያጡ ሰዎች ቁጥር 36.5 ሚሊዮን ደረሰ

  አሜሪካውያን ጭምብል አጥልቀው

  በአሜሪካ በባለፈው ሳምንት ብቻ 2.98 ሚሊዮን ሰዎች ስራ ማጣታቸውን ተከትሎ፣ ወረርሽኙ ከተነሳበት እለት ጀምሮ ስራ ያጡ ሰዎች ቁጥርን ወደ 36.5 ሚሊዮን አድርሶታል።

  በኮሮና ክፉኛ እየተጠቃችው ባለችው አሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እንዲሁም የሟች ቁጥር ከአለም ቀዳሚ ያደረጋት ሲሆን የምጣኔ ኃብቱም ጫና በጣም ከፍተኛ ነው ተብሏል።

  ስራቸውን ያጡ ሰዎችም የመንግሥትን እርዳታ በመሻት ድጎማ እንዲደረግላቸው የተለያዩ ቅፆችንም በመሙላት ላይ ናቸው።

  ምንም እንኳን የስራ አጡ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቢያሻቅብም ወረርሽኙ ከተከሰተበት ከሁለት ወራት በፊት ጋር ሲነፃፀር በባለፉት ሳምንታት መቀነስ ማሳየቱን የአሜሪካ የሰራተኞች ዘርፍ አስታውቋል። በባለፈው ወር 20.5 ሚሊዮን ስራ አጦች የተመዘገቡ ሲሆን ይህም የስራ አጡን ቁጥር ወደ 14.7 በመቶ አሻቅቦታል ተብሏል።

  ይህንንም አሃዝ በመመልከት የሃገሪቷን ኢኮኖሚ የሚያዳሽቅ መጥፎ ጊዜ ነው ተብሏል።

 3. በእንግሊዝ ከ400 ሰዎች አንዱ ኮሮናቫይረስ አለበት

  ዩናይትድ ኪንግደም በመንገድ ላይ ምርመራ ሲደረግ

  በእንግሊዝ ከ400 ሰዎች መካከል አንደኛው ኮሮናቫይረስ እንዳለበት በ11ሺህ ቤቶች ላይ የተሰራ የዳሰሳ ጥናት አሳየ።

  ጥናቱ ባካተታቸው መኖሪያ ቤቶች የሚገኙ ግለሰቦች እስከ ሰኞ ድረስ፣ ለሁለት ሳምንታት ያህል፣ ናሙና እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር ተብሏል።

  በዚህም ወደ 148 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው መገኘታቸውን ጥናቱን የሰሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

  እነዚህ ምርመራውን ያደረጉት ሰዎች ሆስፒታል የገቡ እንዲሁም በአረጋውያን ክብካቤ መስጫ ማዕከል ያሉትን አላካተተም።

  እንደ ብሔራዊ የስታትስቲክስ ባለስልጣን ከሆነ በእነዚህ ሥፍራዎች የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ ነው።

  በዚህ የዳሰሳ ጥናት እንደታየው በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች ናቸው ተብሏል።

  በእንግሊዝ ሆስፒታሎች ብቻ 24 ሺህ 519 ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሲሆን፤ ከሆስፒታሎች ውጭ የሞቱ ሰዎች ጋር ሲደመር አጠቃላይ የሟች ቁጥር 33 ሺህ 614 ደርሷል።

 4. የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከቻይና ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሊያቋርጡ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ

  የአሜሪካው ፕሬዝዳንትና የቻይናው አቻቸው

  የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቻይና ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የያዘችበትን መንገድ ዳግም ኮንነው ከቤይጂንግ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሊያቋርጡ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ።

  ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ከፎክስ ቢዝነስ ጋር በነበራቸው ቆይታ " በርካታ ልናደርጋቸው የምንችላቸው ነገሮች አሉ። አጠቃላይ ግንኙነታችንን ማቋረጥ እንችላለን" ብለዋል።

  " አሁን፣ ብናደርገው ምን ይሆናል?" በማለት የጠየቁት ትራምፕ፣ " አጠቃላይ ግንኙነታችንን ብናቋርጥ 500 ቢሊየን ዶላር ልናድን እንችላለን" ሲሉ ለራሳቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።

  ይህ ገንዘብ አሜሪካ ከቻይና ጋር ላላት የሁለትዮሽ ንግድ ልዩነት ነው።

  ከዚህ በፊት ዋሺንግተን ቻይናን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንደተከሰተ አካባቢ መረጃዎችን ከቀሪው ዓለም በመሸሸግ በመወንጀል ከቫይረስ ጋር በተያያዘ ካሳ ለማስከፈል ጫና ማድረግ ትፈልግ ነበር።

  ቻይና ይህንን ተደጋጋሚ ውንጀላ ስታስተባብል ቆይታለች።

  የትራምፕ ፀረ ቻይና አቋም በብዙዎች ዘንድ የዳግም ምርጫ ቅስቀሳ ስልት አካል እንደሆነ ይታያል።

 5. የኪዩባ ዶክተሮች በደቡብ አፍሪካ ስራቸውን ሊጀምሩ ነው

  የኪዩባ ዶክተሮች

  ደቡብ አፍሪካ ከኮሮናቫይረስ ጋር የምታደርገውን ትግል ለማገዝ ከኩባ የመጡ ሁለት መቶ ዶክተሮች የሁለት ሳምንት የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን አጠናቅቀው ወደ ስራ ሊገቡ መሆናቸው ተገልጿል።

  ዶክተሮቹ በፕሪቶሪያ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ በለይቶ ማቆያ እንደነበሩና ይህንንም አጠናቀው ስራ ሊጀምሩ መሆናቸውንም አስመልክቶ "አስቸጋሪውንም ተግባር ለመጋፈጥ ዝግጁ ነን" ማለታቸውን በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኩባ ኤምባሲ ድረገፅ ያወጣው መግለጫቸው አስፍሯል።

  "በኩባም ሆነ በደቡብ አፍሪካ ለተወሰነ ጊዜ በለይቶ ማቆያ የነበረንን ጊዜ አጠናቀናል። አሁን ወደ ሃገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች በመሰማራት አስቸጋሪውን ነገር ግን ይህንን የተቀደሰና የተከበረ ተግባር ለመወጣት ዝግጁ ነን" ብለዋል።

  ኩባ አለም አቀፍ ትብብርን ለማሳየት ዶክተሮቿን በተለያዩ ቦታዎች እያሰማራች ሲሆን ይህ ተግባር ግን በአሜሪካ ዘንድ ትችት ገጥሞታል።

  ዶክተሮቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ መምጣታቸውን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካን ለምን ዶክተሮቹን ተቀበለች በሚል እንዲሁም ኩባ ከዚህ ወረርሽኝ እያተረፈች ነው በሚል አሜሪካ ብትተችም ኩባ በበኩሏ ውንጀላውን አጣጥላዋለች።

 6. በባንግላዴሽ የሮሂንጃ ስደተኞች ጣቢያ ማዕከል ኮሮናቫይረስ ተከሰተ

  የኮክስ ባዛር የሰስደተኞች ጣቢያ ማዕከል

  በባንግላዴሽ የሚገኘውና በአለም ላይ ትልቁ በሚባለው የስደተኞች ጣቢያ ማዕከል ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሁለት የሮሂንጃ ስደተኞች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

  ኮስስ ባዛር ተብሎ በሚጠራው የስደተኞች ጣቢያ ማዕከልም ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ የመጀመሪያዎቹ እንደሆኑም የሮሂንጃ ስደተኞች መላሽ ኮሚሽን ዶክተር አስታውቀዋል።

  በቫይረሱ የተያዙት ሁለት ግለሰቦችም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ባለስልጣናቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

  ከህሙማኑ ጋር ግንኙነትና ንክኪ የነበራቸውንም ስደተኞችንም የመለየት ስራ የተሰራ ሲሆን፤ 1900 ስደተኞችም ለምርመራ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ገብተዋል።

  በኮክስ ባዛር ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የሮሂንጃ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፤ መጠለያ ማዕከሉም ለባለፉት ሁለት ወራት ያህል የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎበታል።

 7. ሞሪሽየስ የኮቪድ-19ን ትግል በድል ተወጥተነዋል አለች

  በሞሪሽየስ ጭምብል ያጠለቁ ሰዎች

  በሞሪሽየስ ባለፉት 17 ቀናት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች አለመገኘታቸውን ተከትሎ ከኮቪድ-19 ጋር የሚደረገውን ትግል በድል ተወጥተነዋል ብላለች። ሆኖም ጦርነቱን ሙሉ በሙሉ አላሸነፍነውም መባሉንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የሃገሪቱን ጤና ሚኒስትር ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

  የጤና ሚኒስትሩ ካይሌሽ ጃጉታፓል በሃገሪቱ ውስጥ ከሁለት ሳምንታት በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ላለመገኙቱም ማህበረሰቡ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

  " ከኮሮናቫይረስ ጋር የሚደረገውን ትግል በህዝቡ ትብብር ድል አድርገነዋል። መንግሥት የቫይረሱን መዛመት ለመግታት ያሳለፋቸውን አስገዳጅ የቤት ውስጥ መቀመጥን ጨምሮ፣ የድንበሮች መዘጋት እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴዎችን ማቆምን ህዝባችን በፀጋ ተቀብሎታል" ብለዋል።

  አክለውም "ነገር ግን ጦርነቱ አላለቀም፤ ጥንቃቄ ማድረጋችንን እንቀጥል" የሚል ምክርም አስተላልፈዋል።

  በሞሪሽየስ ደሴት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 332 ሲሆን አስር ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል። በአፍሪካ ካሉ ሃገራትም አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ውሳኔንም ያሳለፈች የመጀመሪያዋ ሃገር ናት።

  ምንም እንኳን ሃገሪቷ ውስጥ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ባይኖሩም ህዝቡ ጥንቃቄ ማድረጉን እንዲቀጥልና ያሉትንም መመሪያዎች እንዲተገበር መንግሥት ትዕዛዝ አስተላልፏል።

  በዚህ ሳምንት አንዳንድ መደብሮች የሚከፈቱ ሲሆን ገበያዎች ግን ተዘግተው እንደሚቆዩ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

  ከዚህም በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች እስከ ነሐሴ ድረስ ተዘግተው የሚቆዩ ሲሆን፣ የባህር ዳርቻ መዝናኛዎችም ጋር ድርሽ ማለት አይቻልም። በሰርጎችና ቀብር ስነ ስርአቶች ላይ አስር ሰዎች በተገኙበት መካሄድ ይችላል ተብሏል።

 8. በቤሩት የእንቅስቃሴ ገደቡ ከመጀመሩ በፊት ነዋሪዎች ሲሸምቱ

  በሌባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ስምንቱ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው እየተነገረ ነው። የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር በሌባኖስ ውስጥ ስላለው የኮሮናቫይረስ ክስተት መረጃዎችን በሚያቀርብበት ድረገጽ ላይ ስምት ኢትዮጵያዊያን በበሽታው እንደተያዙ ያመለከተ ሲሆን፤ በቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ግን ስለተጠቀሰው አሃዝ ከአገሪቱ መንግሥት የተሰጠው መረጃ እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግሯል። በሊባኖስ እስከ አሁን ድረስ 886 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከእነዚህ መካከል ስምንቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ካወጣው የህሙማኑ ዜግነት ዝርዝር መረዳት ይቻላል። . . .

  ተጨማሪ ያንብቡ
  next
 9. ሳኖፊ

  ለፈረንሳዩ ግዙፉ የመድኃኒት ኩባንያ ሳኖፊ፤ የኮቪድ-19 ክትባትን መስራት ከቻለ ለአሜሪካ ገበያ ቀድሞ መስጠት "ተቀባይነት እንደሌለው" የፈረንሳይ ሚኒስትር አስጠነቀቁ። በሳኖፊ ከፍተኛ የበላይ ኃላፊ ፓል ሁድሰን "የአሜሪካ መንግሥት ምርምሩ ላይ ቀድሞ ኢንቨስት በማድረጉ በብዛት ቀድሞ የማዘዝ መብት አለው" ብለው ነበር። በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ ቤተ ሙከራዎች ለኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ምርምር እያደረጉ ቢሆንም ክትባቱን ለማምረት ግን ዓመታት ይወስዳል እየተባለ ነው። . . .

  ተጨማሪ ያንብቡ
  next
 10. ኒውዚላንዳዊያን ፀጉራቸውን ለመቆረጥ ሌሊቱን በሙሉ እየተሰለፉ ነው

  ፀጉር ቤት

  በኮሮናቫይረስ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉ በርካታ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኒውዚላንድ ዕቀባዋን በማላላቷ የንግድ መደብሮች ሥራ ጀምረዋል።

  ከእነዚህም መካከል ፀጉር ቤቶች ሥራ በመጀመራቸው በቤት ውስጥ ለሳምንታት ቆይተው ፀጉራቸውና ጺማቸው የጎፈረ ወንዶች አገልግሎት ለማግኘት ከጸጉር ቤቶች ደጃፍ ላይ በብዛት ሰልፍ ታይተዋል።

  በርካቶችም ፀጉራቸውን ለመቆረጥ በቀን ብቻ ሳይሆን ሌሊትም በመሰለፍ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚጠብቅ ሲሆን፤ ፀጉር ቤቶቹም ያለማቋረጥ ሌሊቱን በሙሉ ደንበኞቻቸውን እያስተናገዱ ነው።

  በኒውዚላንድ ሱቆች፣ ካፍቴሪያዎችና መናፈሻ ቦታዎች እንዲከፈቱ ተደርገዋል።

  በአገሪቱ ባለፉት ሦስት ቀናት ምንም አይነት በበሽታው የተያዘ ሰው ያልተገኘ ሲሆን፤ ወረርሽኙን በመቆጣጠር በኩል ኒውዚላንድ ተሳክቶላታል እየተባለ ነው።

  ፀጉር ቤት
 11. በሩሲያ የሟቾች ቁጥር ማነስ ላይ ጥያቄ ተነሳ

  ሩሲያ

  በሩሲያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ ሳለ ሪፖርት የሚደረጉት የሟቾች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ጥያቄን እያስነሳ ነው።

  እስካሁን በሩሲያ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ከ252 ሺህ በላይ ሲሆን መንግሥት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 2305 ናቸው ብሏል።

  የሞስኮ ጤና ቢሮ እንዳለው በኮቪድ-19 የሞቱትን አብዛኞቹን ሰዎች በዝርዝሩ ውስጥ ያላከተተ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ሌላ ተያያዥ ህመም ስለነበረባቸው ነው ብሏል።

  ሴይንት ፒትስበርግ ከተማ በበኩሏ ከሳንባ ምች ጋር በተያያዘ የሟቾች ቁጥር ባልተለመደ ሁኔታ መጨመሩን አስታውቃለች።

  ይህ ቁጥር ከዚህ ቀደም በሳንባ ምች ከሚሞቱ ሰዎች ከአምስት እጥፍ በላይ ሲሆን፤ በኮቪድ-19 ሞቱ ከተባለው ደግሞ አስር እጥፍ እንደሚልቅ ተናግረዋል።

  አንድ ገለልተኛ የሆነ የሩሲያ ድረገጽ በበኩሉ በአገሪቱ የሟቾች ቁጥር በመንግሥት ማስተካከያና ማሻሻያ እንደሚደረግበት ጠቅሶ "ሩሲያውያን በኮሮናቫይረስ መሞት አይፈቀድላቸውም" ብሏል።

  በርካቶች የመንግሥትን ይፋዊ ቁጥር ማመን ከባድ ነው በማለት የራሳቸውን መረጃ መመዝገብ ጀምረዋል።

  የሩሲያ ህክምና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ የሞቱ ባልደረቦቻቸውን ቁጥር የሚመዘግቡ ሲሆን የኦሮቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቀሳውስት በበኩላቸው በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን ዝርዝር እየመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው "የመንግሥት ይፋዊ መረጃ የተሟላ አይደለም" ብለዋል።

  ከዚህ ቀደም ፋይናንሻል ታይምስ ሩሲያ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር መንግሥት ከሚገልፀው በ70 በመቶ ይበልጣል ሲል ዘግቦ ነበር። ነገር ግን በሞስኮ የሚገኙ ባለስልጣናት መረጃውን "ሐሰተኛ" በሚል አጣጥለውት ነበር።

 12. Video content

  Video caption: ዶ/ር ሰለሞን ክብረት፡ "ኮሮኖቫይረስን ለመከላከል ኢትዮጵያ ያላት አማራጭ አንድ ብቻ ነው"

  ዶ/ር ሰለሞን ክብረት፡ "ኮሮኖቫይረስን ለመከላከል ኢትዮጵያ ያላት አማራጭ አንድ ብቻ ነው"

 13. ምርምር ሲደረግ

  ከቻይና ጋር ግንኙነት ያላቸው የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች (ሀከርስ)፤ አሜሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ላይ ምርምር እያደረጉ ያሉ ተቋሞች ላይ እንዳነጣጠሩ የአሜሪካ ባላሥልጣኖች ተናገሩ።

  ተጨማሪ ያንብቡ
  next
 14. የዶ/ር ቴድሮስ መሥሪያ ቤት ስለ 'ማስክ' የሚወራው ሃሰት ነው እያለ ነው

  የአፍና አፍንጫ ጭምብል

  ማሕበራዊ ድር-አምባዎች ላይ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለረዥም ጊዜ ማጥለቅ አደጋ አለው ብሏል የሚባለው ሐሰት ኒው ሲል ድርጅቱ አስታውቋል።

  ድርጅቱ ጭምብል ረዘም ላለ ጊዜ አታድርጉ ብሏል የሚለው ሐሰተኛ ዜና መጀመሪያ የተሰራጨው በስፔንኛ ነበር። ከዚያ በኋላ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ እስከ ናይጄሪያ ደርሷል።

  ዘገባው እንደሚለው ከሆነ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለረዥም ጊዜ መጠቀም ሰዎች ካርቦን ዳይኦክሳይ ወደ ውስጥ እንዲስቡና አየር እንዲያጥራቸው ያደርጋል፤ ሊያፈዝም ይችላል።

  አልፎም ሰዎች በየአስር ደቂቃው መሸፈኛውን እያወለቁ ንፁህ አየር መሳብ አለባቸው ይላል።

  የዓለም ጤና ድርጅት ሠራተኛ የሆኑት ዶ/ር ሪቻርድ ሚሂጎ በስፋት እየተሰራጨ ያለው ዜና ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

  ሰዎች መሸፈኛውን መግለጣቸው ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሊያጋልጣቸው ይችላል ይላሉ።

  ዶክተሩ እንደሚሉት የድርጅቱን መርህ ተከትለው የሚሠሩ ጭምብሎች ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ድርብርብ ጨርቅ ያላቸውና ሰዎች መተንፈስ እንዲችሉ የሚፈቅዱ ናቸው።

  ዶክተሩ እንደሚመክሩት ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ሳንባቸው በደንብ ስላልበረታ ማስክም ሆነ ሌላ መሸፈኛ እንዲያደርጉ አይመከርም።

 15. ጫት የሚቅም ወጣት

  ጫት ማሕበራዊ ርቀት አይጠብቅም፣ እጅዎን ወደ አፍዎ አትስደዱ አያውቅም። የሶማሊያ መንግሥት በረራ ሲያግድ ይህንንም ከግምት በማስገባት ነበር። ጫት በእጅ ስለሚለቀም ኮቪድ-19ን ለማስፋፋት ሁነኛ ነው በማለት ነበር ያገደው።

  ተጨማሪ ያንብቡ
  next
 16. የ98 ዓመቷ ግለሰብ ናይጄሪያ ውስጥ ከኮሮናቫይረስ አገገሙ

  የናይጄሪያዋ ንግድ መናኸሪያ ሌጎስ ባለሥልጣናት፤ አንዲት የ98 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ከኮሮናቫይረስ ማገገማቸውን አስታወቁ።

  የዕድሜ ባለፀጋዋ ሌጎስ የሚገኝ አንድ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ከከረሙ በኋላ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል።

  የሌጎስ ግዛት አገረ ገዥ ባባጂዴ ሳንዎ-ኦሉ ትላንት ረቡዕ እንዳስታወቁት የ98 ዓመቷ ግለሰብ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጦ ከሌሎች 25 ሰዎች ጋር ከሆስፒታል ወጥተዋል።

  ግለሰቧ ሌጎስ ውስጥ በዕድሜ ትልቋ የኮቪድ-19 ታማሚ ነበሩ ሲሉ አገረ-ገዥ በባጂዴ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

  ናይጄሪያ እስካሁን ድረስ 5 ሺህ ገደማ ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንደተያዙ ይፋ አድርጋለች። ከእነዚህ መካከል ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት ሌጎስ ውስጥ ነው።

  በሌጎስ ግዛት ኮሮናቫይረስ ከያዛቸው መካከል 33 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ 528 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል።

 17. የናይጄሪያውያን 'ሚስጢራዊ ሞት' ጥርጣሬ እያጫረ ነው

  ሳኒታይዘር

  በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ የምትገኘው ዮቬ ግዛት ውስጥ ባለፉት አምስት ሳምንታት 471 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።

  ሰዎቹ የሞቱት በኮሮናቫይረስ ይሁን አይሁን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

  ናይጄሪያ እስካሁን 5 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙባት እና 164 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን እንዳጡ አስታውቃለች።

  የዮቤ ግዛት ጤና ኮሚሽነር ሙሐመድ ላዋን ጋና ለቢቢሲ እንደተናገሩት አብዛኛዎቹ ሟቾች አረጋውያን ሲሆኑ ስኳር በሽታና ሌሎች ተዛማጅ የጤና እክሎች ያሉባቸው ናቸው።

  አንዳንዶቹ ግን የኮሮናቫይረስ ምልክት አሳይተው ነበር ይላሉ ሚኒስትሩ።

  በሰሜናዊ ናይጄሪያ ባሉ ግዛቶች ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በርካታ ሰዎች የሞታቸው ምስጢር ሳይታወቅ እስከ ወዲያኛው እያሸለቡ ነው። ሕዝብ የሚበዛባት የካኖ ግዛት ከእነዚህ መካከል አንዷ ናት።

  ባለሥልጣናት የሰዎች ሕይወት እየጠፋ ያለው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አማካይነት ነው ለማለት አልደፈሩም። በጥቅሉ ምርመራ እያካሄድን ነው ይላሉ።

  ናይጄሪያ በቀን የምትመረምረው ሰው ቁጥሩ አነስተኛ መሆኑ ቫይረሱ በድብቅ እንዲስፋፋ እንዳያደርገው ተሰግቷል።

 18. በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ ያለባቸው ተጨማሪ ዘጠኝ ሰዎች ተገኙ

  ምርመራ

  ባለፉት 24 ሰዓታት በተካሄደ 3580 የላብራቶሪ ምርመራ ዘጠኝ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡ ተገለጸ።

  የጤና ሚንስትርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባወጡት መግለጫ መሠረት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው።

  ከዘጠኙ አምስቱ ከአዲስ አበባ፣ አራቱ ደግሞ ከሶማሌ ክልል ለይቶ ማቆያ የተገኙ ናቸው።

  ከዘጠኙ አራቱ የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ እንዳላቸው፣ ሦስቱ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ሁለቱ ግን የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው በሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነትም የሌላቸው ናቸው ተብሏል።

  እስካሁን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ባጠቃላይ 272 ደርሰዋል። 108 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፤ አምስት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

 19. ሕንዳዊው ሚኒስትር ቫይረሱ ከቤተ-ሙከራ የወጣ ነው አሉ

  ዉሃን ውስጥ የሚገኝ ቤተ-ሙከራ

  ኮሮናቫይረስ ከቤተ-ሙከራ የወጣ ነው የሚለው ሐሳብ በፖሊተከኞች ዘንድ ሲንፀባረቅ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ምንም እንኳ ሐሳባቸውን የሚደግፍ ማስረጃ ባይገኝም።

  የሕንድ ትራንስፖርት ሚኒስትር የሆኑት ነባሩ የሕዝብ እንደራሴ ኒቲን ሃድካሪ ለአንድ የቴሌቪዥን ጣብያ በሰጡት ቃለ-ምልልስ «ይህ ተፈጥሯዊ ቫይረስ አይደለም፤ ሰው ሠራሽ እንጂ። ይህ የቤተ-ሙከራ ቫይረስ ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።

  የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፓምፔዮ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተመሳሳይ ሐሳብ መሰንዘራቸው አይዘነጋም። ፓምፔዮ ቫይረሱ ዉሃን ከሚገኝ ላቦራቶሪ ነው የወጣው ማለታቸውን ተከትሎ የቻይና ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣብያ ውሃ የማያነሳ ሐሳብ ሲል አጣጥሎት ነበር።

  እስካሁን ድረስ ያሉ ሳይንሳዊ ጥናቶች ቫይረሱ ከእንስሳት እንደመጣ እንጂ ሰው ሠራሽ እንደሆነ አያሳዩም።

  ኮቪድ-19 የተሰኘው በሽታ ምንጭ ውሃን የተሰኘችው የቻይና ከተማ መሆኗን የሚያስረግጥ መረጃ እስካሁን አልተገኘም።

  መጋቢት ወር ላይ የታተመ አንድ አሜሪካ ውስጥ የተሠራ ጥናትም ቫይረሱ ሰው ሠራሽ ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለም ይላል።

 20. ቡሩንዲ የዓለም ጤና ድርጅት ሠራተኞችን አባረረች

  ቡሩንዲ
  Image caption: ምንም እንኳ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባይቀዛቀዝም የፕሬዝደንታዊ ምርጫው ዕጩዎች ሕዝብ በተሰበሰበበት ቅስቀሳ እያደረጉ ነው

  ቡሩንዲ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይና ሌሎች ሶስት የድርጅቱ ሠራተኞች በ48 ሰዓታት አገር ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጠች።

  የቡሩንዲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሰዎቹን ያባረረበትን ምክንያት ይፋ አላደረገም።

  የቡሩንዲ መንግሥት ምንም እንኳ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባይቀዛቀዝም ቀጣይ ሳምንት ረቡዕ ግንቦት 12 አገር አቀፍ ምርጫ ሊያካሂድ ማሰቡን ተከትሎ ትችት እየደረሰበት ነው።

  የፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ሕዝብ በተሰበሰበበት ቅስቀሳ እያደረጉ ነው።

  ቡሩንዲ እስካሁን ድረስ 15 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘውብኛል ስትል ሪፖርት አድርጋለች። አንድ ሰው ደግሞ በቫይረሱ መሞቱ ተዘግቧል።

  ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የተሰኘው ተቋም ግን የመንግሥት አሃዝ የተዛባ ነው ይላል።