ፓስፖርት፡ የሰዎችን እንቅስቃሴ የወሰነ ሰነድ

Image copyright Getty Images

በታሪክ ውስጥ ፓስፖርት ሁሌም የነበረ ነገር አይደለም። ፓስፖርት ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ የሚረዳ በሃላፊዎች ፈቃድ የሚሰጥበት ማስረጃ ነው። ይህን ማስረጃ መጠቀም የተጀመረው ከብዙ ዓመታት በፊት ነው።

በቀደም ሲል በፈረንሳይ ዜጎች ሃገራቸውን ሲለቁ ብቻ ሳይሆን ከከተማ ወደ ከተማ ሲንቀሳቀሱም ማስረጃ ሊኖራቸው ይገባ ነበር። አሁን አሁን የበለጸጉ ሃገራት ሙያ የሌላቸው ሰዎች ወደ አገራቸው እንዳይመጡ የሚከለከሉ ቢሆንም ቀደም ሲል ግን ሙያ ያላቸው ሰዎች አገራቸውን ለቀው እንዳይወጡ ያደርጉ ነበር።

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የመጓጓዣ ዓይነቶች ዕድገት ጉዞን ፈጣንና ርካሽ አድርጓል። በወቅቱ ቁጥጥር የሚበዛባቸው የጉዞ ማስረጃዎች ደግሞ ብዙም አስፈላጊ ተቀባይነት አልነበሩም። በ1890ዎቹ ማንኛውም ነጭ የሆነ ሰው አሜሪካን ያለምንም ፓስፖርት መጎብኘት ይችል ነበር።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በ1890ዎቹ አሜሪካን ለመጎብኘት ፓስፖርት አያስፈልግም ነበር

በወቅቱ አንዳንድ የደቡብ አሜሪካ ሃገራት ያለፓስፖርት የመንቀሳቀስ መብትን በህገመንግስታቸው ውስጥ አስፍረዋል። ጃፓንና ቻይና በበኩላቸው ወደ መሃል ሃገር የሚገቡ የውጭ ዜጎች ፓስፖርት እንዲይዙ ይጠይቁ ነበር።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያም ቢሆን ወደ ሃገራቸው የሚገቡና የሚወጡ ሰዎችን ፓስፖርት የሚጠይቁ መንግሥታት ቁጥር አነስተኛ ነበር። አሁን ግን እንደዚህ ያሉ አገራት መኖራቸው አጠራጣሪ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ፓስፖርትና ስደተኞች

እአአ መስከረም 2015 ጠዋት መዳረሻዋን በግሪክ ደሴቷ ኮስ ያደረገች ጀልባ ከቱርክ ቦድረም ትነሳለች። ጀልባዋ ላይ አብዱላህ ኩርዲ የተባለ ግለሰብ ከሚስቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር ተሳፍሯል። በጉዞው ወቅት ጀልባዋ በመስመጧ ከመላው ቤተሰብ አብዱላህ ብቻ ይተርፋል።

የሦስት ዓመት ልጁ የአይላን ኩርዲ ሬሳ በውሃ ተገፍቶ ወደ ባህር ዳርቻ ከወጣ በኋላ ፎቶው የስደት ምልክት ከመሆን ባለፈ መላው ዓለምን አስደንግጧል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች ከቱርክ ወደ ግሪክ ለመግባት ይጓዛሉ

የእነአብዱላህ ዓላማ በቱርክ መኖር ሳይሆን ቫንኩቨር ካናዳ ወደምትገኘው እህቱ ዘንድ ማቅናት ነበር። ይህን ጉዞ ለማድረግ ብዙ ቀላል አማራጮች ነበሩ። በህገወጥ መንገድ ሰዎችን ለሚያዘዋውሩ የከፈሉት 4460 ዶላር ፓስፖርት ቢኖራቸው ኖሮ ለመላ ቤተሰቡ የአውሮፕላን ትኬት መግዛት የሚያስችል ነበር።

የሶሪያ መንግስት ለኩርዶች የዜግነት መብትን ስለነፈጋቸው ፓስፖርት ሊያገኙ አልቻሉም በዚህም ይህን እድል እንዳይሞክሩ አድርጓል። ቢሆንም ግን ሁሉም ፓስፖርት በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ተቀባይነት ስለሌለው የሶሪያ ፓስፖርት ቢኖራቸው እንኳን ወደ ካናዳ ማቅናት አይችሉም ነበር። ካናዳ ውስጥ የስዊዲን፣ ስሎቫኪያ፣ ሲንጋፖር ወይም የሳሞኣ ፓስፖርት የተሻለ ተቀባይነት አላቸው።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የሶሪያን ፓስፖርት የያዘ ግለሰብ

ፓስፖርት መግዛት

ፓስፖርትን ለመቀየር እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም ፈፅሞ ግን አይቻልም ለማለት ግን አያስደፍርም። 250 ሺህ ዶላር ያለው ሰው ከካሪቢያኗ ሴንት ኪትስ እና ኔቪስ ፓስፖርት መግዛት ይችላል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ሴንት ኪትስ እአአ ከ1984 ጀምሮ 'የዜግነት ኢንቨስትመንትን' ተግባራዊ አድርጋለች

ፓስፖርት በአብዛኛው በወላጆቻችን ማንነትና በተወለድንበት ቦታ ይወሰናል። ይህ ደግሞ በምርጫ የሚወሰን አይደለም። ስለዚህም ሰዎች መመዘን ያለባቸው በባህሪያቸው እንጂ በፓስፖርታቸው መሆን የለበትም ቢባልም ይህ እንዳይሆን አጥብቀው የሚከራከሩ ሰዎች ብዙም አይደሉም።

የበርሊን ግንብ ከፈረሰ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ የስደተኞች ቁጥጥር ፋሽን በሚመስል መልኩ ተጧጡፏል። ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካና ሜክሲኮ መካከል አጥር እንዲገነባ እየጠየቁ ናቸው።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ዶናልድ ትራምፕ ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስናቸው ድንበር ላይ አጥር ለመገንባት አቅደዋል

በአውሮፓ ውስጥ ከሃገር ሃገር በቀላሉ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለው የሸንገን ዞን አካሄድም በስደተኞች ምክንያት በተፅዕኖ ስር ወድቋል። የአውሮፓ አገራት መሪዎች የፖለቲካ ስደተኞችን ብቻ በመቀበል ለተሻለ ኑሮ የሚሰደዱትን ለመተው የሚያደርጉት እንቅስቃሴም ከፋፍሏቸዋል።

ተጠቃሚዎችና ተጎጂዎች

የምጣኔ ሃብት እሳቤ ግን ከፖለቲካው በተቃራኒ ይቆማል። በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ምርት የተጠቃሚን ፍላጎት እንዲከተል መንገዱ ሲመቻችለት የሚገኘው ምርት እየጨመረ ይሄዳል።

በተግባር ስደተኞችን ተከትሎ የሚጠቀሙና የሚጎዱ እንዳሉ ቢታይም፤ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ግን የተጠቃሚዎች ቁጥር ያመዝናል። በበለጸጉት አገራት ከስድስት ዜጎች አምስቱ በስደተኞች መምጣት ህይወታቸው ተሻሽሏል።

ስደተኞች ከአካባቢያቸው ጋር ቶሎ ካልተዋሃዱ ወይም አስፈላጊ የህዝብ አገልግሎት በዚያው መጠን ካልተስፋፋ ችግር ይፈጠራል።

በተጨማሪም ከሚገኘው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱን የማየት ዝንባሌም አለ። ለምሳሌ የተወሰኑ ሜክሲኳዊያን ወደ አሜሪካ ተሰደው በፍራፍሬ ለቀማ ሥራ ላይ በአነስተኛ ክፍያ ተሰማሩ ይባል። በዚህ ምክንያትት በአነስተኛ ዋጋ የቀረበው የፍራፍሬ ዋጋ ሳይስተዋል ከሥራ ስለተፈናቀሉ ጥቂት አሜሪካዊያን በስፋት ይወራል። ተጎጂዎችን መንግሥታት ለህዝብ አገልግሎት በሚመድቡት ገንዘብና ከግብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ መካስ ይቻላል።

የደህንነት ስጋት

አንዳንድ ባለሙያዎች ሰዎች የፈለጉት ቦታ ተንቀሳቅሰው ቢሰሩ የዓለም ምጣኔ ሃብት በእጥፍ ያድጋል ይላሉ። በዚህም መሰረት ፓስፖርት ጥቅም ላይ ባይውል ዓለም የበለጠ የበለጸገች ትሆን ነበር። ይህ ላለለመሆኑ ትንሹ ማሳያ አንደኛው የዓለም ጦርነት ነው። ፓስፖርት ባይኖርም ጦርነት ሃብቱን ስለሚያጠፋው ማለት ነው።

የደህንነት ጉዳይ አሳሳቢ በመሆኑ መንግስታት በጉዞ ላይ የያዙት ጠንካራ አቋም በሰላም ወቅትም የሚላላ አይመስልም።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የተለያዩ አገራት ፓስፖርቶች

እአአ በ1920 የተቋቋመው ሊግ ኦፍ ኔሽን "ዓለም አቀፍ የፓስፖርት፣ ጉምሩክ ህግና ትኬት ኮንፈረንስ" በማዘጋጀት ፓስፖርትን አስተዋውቋል።

በቀጣዩ ዓመት በነበረው ጉባኤው ላይ ፓስፖርቶች ባለ 32 ገጽ፣ ፎቶ ያላቸው፣ ባለጠንካራ ሽፋንና 15.5 ሴንቲ ሜትር በ10.5 ሴንቲ ሜትር እንዲሆኑ በወሰነው መሰረት አስካሁንም ድረስ በጥቂት ማሻሻያ ብቻ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛሉ።